Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ታዋቂ በዝቶ አዋቂ ሲጠፋስ?

እነሆ መንገድ ከመገናኛ ወደ ቦሌ። ጎዳናው በአዳዲስ ነገሮች ያበደ ይመስላል። አዲስ እንደ መፀየፍ፣ አዲስ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፍ፣ አዲስ እንደ ደንታ ቢስነት፣ አዲስ እንደ መጨካከን። ‘የነበረው ሁሉ አልፏል፣ እነሆ ሁሉ እንደ አዲስ ሆኗል’ የሚባለውን እያሰብን፣ የታክሲያችን የውስጥ አካል ላይ ስናፈጥ ሚዳቋ እየሮጠች አንበሳ እያባረራት ‘ላታመልጭኝ አታሩጭኝ’ ያላትን እናነባለን። የእኛና የኑሮአችን አሯሯጥም እንዲያ ይመስላል። እኛ ማለት ሚዳቋ፤ አንበሳው ደግሞ ኑሮ። የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ሆኖብን እንደ አማራጭ ያልተዘራብን በቅሎብናል። ያልሸመነውን ተከናንበናል። ይህ ጭንቅ የወለደው የባህሪ መክፋት፣ ለዘመን መለወጫ እንደገዛነው አዲስ ልብስ፣ ጃኖና ቡልኮ ማታ ማታ የደስ ደስ ሲያራጨን እያደረ ቀን ቀን እርስ በእርስ ሲያናጨን ይውላል። የማይደክመው ተቺ ‘የዕድገቱ ውጤት…’ እያለ ጋዜጣ ላይ ይቸከችካል።

ምናልባት ያልተለወጠ፣ ጥንትም ዛሬም አብሮን ያለ አመል ቢባል ከትችትና ከጽንፈኝነት ሌላ ያለ አይመስልም። ይኼው እዚህ ጎዳና ላይ በጠራራ ፀሐይ ራቁቱን በአፍጢሙ ተደፍቶ ተኝቶ፣ ምናልባት በደጉ ቀን እህቱ ወይ እናቱ በጉሎና ኦሞ ዘፍዝፈው አጥበው፣ አድርቀው፣ ለብሰዋት ደጀ ሰላም ስመው የተመለሱባትን ነጠላ፣ ዛሬ ጊዜ እሱን ሲጥለው ነጠላዋም አብራው ወድቃ ረብጣ እየሰበሰበች እያየን፣ አንዳንዶቻችን . . .  ‘ኑሮ ባይወደድ ሃምሳ ሳንቲም ለአንተ አላጣም ነበር’፤ እንላለን፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ . . .  ‘እንዲህ ያለ አፀያፊ ነገር እያየን ለመጓዝ ነው ለመንገድ ሥራ የብድር መዓት ስንቆልል የኖርነው?’ ስንል፣ ሌሎቻችን ደግሞ ‘መንግሥት ጋዜጠኛ ከሚያስር ለምን ለማኞችን አያስርም?’ እያልን እንጓዛለን። ይህን ያህል ርህራሔ ላይ ቆፍጠን ብለን፣ ይህን ያህል በኑሮ ውጣ ውረድ እጃችን አጥሮ በአንድም በሌላም ስንመዘን አብዛኞቻችንን ያፈራነው አመል ያልነበረብንና ያልተፈጠረብንን መስሏል። መንገድና መመሳሰል!

ከሾፌሩ ጀርባ ከሁለት ልጆቿ ጋር እየተጓተተች የገባች እመጫት ከወያላው ጋር ትነታረካለች። ወያላው ለሁለቱ የአንድ ሰው ሒሳብ ትከፍይላቸዋለሽ ይላታል። አጠገቧ ለተቀመጠ ወጣት አንደኛውን አስታቅፋ፣ “ለምን ሲባል? እኮ ለምን ሲባል? ይኼው አንዱን እሱ ታቅፎልኛል ሌላው ጭኔ ላይ ይቀመጣል፤” አለችው። ድምጿ ውስጥ ሲቃና እልህ እየተንቀለቀሉ ነጎድጓድ እንዳዘለ ከባድ ደመና ከአሁን አሁን ዶፍ ልሁን ይላሉ። “እነሱም እኮ ሰዎች ናቸው፤” አላት ወያላው። “ምናለበት ቢተዋት?” መሀል ረድፍ ላይ የተሰየመ ባለመነጽር ጎልማሳ የእዝን ያስተባብራል። “እውነት ሰው መሆናቸው ታይቶህ ነው? ወይስ ገንዘብህ ነው የታየህ?” እርግማን ታጉተመትማለች። ሰማይና ምድሩ፣ ወያላው፣ እኛ፣ ሰይጣንም፣ እግዜርም አይቀሯትም። “በቃ ተዋት አንተ” ይላል መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ፂማም ወጣቶች አንዱ። “ለምንድነው የምተዋት?” ወያላው ይደርቃል።

“ስማ እንኳን ለአንተ ስምንት ወራት ሲማሩም አምስት ሳንቲም ከፍዬ አላውቅም። ወልደህ እየው፤” እያለች የታቀፈችው ልጅ እንባ እንባ ሲለው ስታባብል አጠገቧ የተሰየመው ደግሞ፣ “የት ነው የሚማሩት?” ብሎ ጠየቃት። “እዚህ መገናኛ አካባቢ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚረዳ ትምህርት ቤት አለ። ነጮች ናቸው። እንደኔ ያለአባት እያሳደጉ በቁም የሞቱትን እናቶች አጥንቶ በነፃ ያስተምርልናል። እዚህ የአገሬ ልጅ ወንድሜ ደግሞ እንደምታየው ሲሶ መቀመጫ የማይዙ ሕፃናት ይዤም እያየኝ ክፈይ ይለኛል። ወገን ብሎ ዝም። አገር ብሎ ስም። ድንቄም…” እያለች ተብላላች። “ተዋት በቃ አቦ ደህና ውለን አታስነጅሰን፤” ባዩ ሾፈሩ ነው። “ገንዘብ እንዲህ ያጨካክነን?” ይላሉ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ከጎኔ የተሰየሙ አዛውንት። “ኧረ እኛ በተጨካከነው ገንዘብ ምን በወጣው? በቅጡ ሠርቶ በአቅሙ ለኖረ የዋለው ውለታስ?” ሲላቸው ከኋላ፣ “እንደ አፍህ ያድርገው። ሌባና ቀማኛ ሥራና አሠሪውን በተቆጣጠረበት አገር በታማኝነት ሠርቶ አግኝቶ በአቅም መኖር ካዛለቀንማ እሰየው፤” አሉት። ማደሪያ እንጂ ማምሻ አልቸገረንማ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ኢምፔሪያል አደባባይን እያለፍን ነው። ሾፌራችን የተሳፋሪዎች ነገር ማተግተግ የተመቸው አይመስልም። ስለዚህ የቴፑን ድምፅ ጨመር አደረገው። “ወይ ሸገር ወይ ሸገር ስንቱ በእሷ አዘነ፣ ታሪካዊ ፍቅሯ ሒሳባዊ ሆነ፤” ይላል ዘፋኙ። “አፈር ልብላልህ። እንዲህ በዘፈን ብሶታችንን ንገርልን እንጂ። የብሶታችን አስተጋቢዎች እኮ ዘፋኞቻችን ብቻ ሆኑ እናንተ?” አለች መጨረሻ ወንበር ሻሽ የጠመጠመች ወይዘሮ። ‘በነበር ቢሆን በነበረማ፣ የሐበሻ ጆሮ ችግር ባልሰማ’ ሲል ደግሞ አዛውንቱ ቀበል አድርገው፣ “እውነት ነው! ነበርን በነበር ከመስማት ደግሞ የኖረው ብዙ ያውቀዋል። እናንተ ዘንድሮ አንድም ያሰለቸን ነገር ያልኖረውና ያልሆነውን እየቀባጠረ በአደባባይ በኒሻን የተንቆጠቆጠው ነው፤” አሉ።

“ምን ይደረግ ሸላሚውም ከተሸላሚው አልለይ ብሏል፤” ብላ አጠገባቸው የተሰየመች ባለፍንጭት አገዘቻቸው። “ተባረኪ!” አሉዋት። “ምን አደረግኩና?” ስትላቸው ግራ ተጋብታ፣ “ያልሽውን በማለትሽ ነዋ። ዘንድሮ ብዬ የዘንድሮኛን አኗኗር የነቀፍኩበት ምክንያት እኮ አንዱም ወጣቱን ለመንካት ነው። ወጣቱ ለማድነቅና ለመደነቅ ችኩል ሆኗል። አንቺ ግን ወጣት ሆነሽ ልብሽ ብሩህ ነው። ማስተዋል ያብዛልሽ፤” ሲሏት አሜኑዋን ቀጠለች። ‘እኔ አላማረኝም ዘንድሮ ሌላ ነው፣ ሕይወት ላለው እንጂ አይሆን ለነበረው’ የምትለዋ የአቀንቃኙ ግጥም ስትከተል ጎልማሳው እመጫቷን እየጠቆመ፣ “በእናት ፍቅር ማን እንደኛ የምንል እኛ፣ ይኼው ማሳያ፤” ብሎ ወያላውን ገላመጠው። ‘የአራዳ ልጅ በርታ ዘንድሮ የድንጋይ ኳስ ቀረ ድሮ’ ከማለቱ አብዱ ኪያር መጨረሻ ወንበር የተቀመጠው ፂማም ቀበል አድርጎ፣ “ኧረ እንኳን በርቱ ተብለን እንዲሁም አልተቻልንም፤” አለ። ያለመቻቻል ቀውስ አዙሮ አዙሮ አራዳ ያደርገን ይሆን? ወይስ እንደ አራዳ መሬት ወጣ ገባችን ያጠፋፋን ይሆን? ወይ እርድናና አራዳ!

ወያላው መልስ እየሰጠን ሳለ ድንገት ቀልቡ ወደ መንገዱ ተሳበና ለወሬ አሰሰገገ። አብረን አሰገግን። በመለኛው የቀለበት መንገዱ ክፍል የተጓዙ መኪኖች እያዞሩ ይመለሳሉ። “ግጭት ነው?” ይላል ጋቢና ያለው። ሾፌሩ፣ “ምን ግጭት ነው? ‘ክራውድድ’ ነው ብለው እኮ ነው፤›› ይላል። ‹‹አሁን ነበር ትራፊክ ፖሊስ መሆን። ይኼን ሁሉ አሽከርካሪ ታስቆምና መንጃ ፈቃድ ነጥቀህ እስከ ዕድሜ ልኩ እንዳይነዳ ማስከልከል ነበር፤” አለ አሁን ጋቢና የተቀመጠው። “አንተ ብትከለክላቸው እነሱ የሚፈቅድላቸው ያጣሉ ታዲያ? መንገዱ እኮ በ‘ኮኔክሽን’ የተጣበበም ነው በመኪና ብቻ አይደለም፤” አለ ከእመጫቷ ጎን ልጇን ታቅፎ እያጫወተ ይጓዝ የነበረው ወጣት።

“እኛ እኮ የመኪና ፍቅር እንጂ ሕግ የማክበር ፍቅር የለንም፤” ስትል መጨረሻ ወንበር ባለሻሿ ከጎኗ የተሰየመ ባለፈር ጃኬት፣ “መጀመሪያ የሰው ፍቅር ሲኖር እኮ ነው። ራሱን የሚወድ ሰው ሌላውን ይወዳል። ሌላውን የሚወድ ሰው ደግሞ ሌሎችንም፣ ራሱንም ሲያፍርና ሲያከብር ሕግ ያከብራል፤” ሲላት የሆነ ስልክ ጮኸ። ጋቢና በሾፌሩና በጥግ በኩል በተቀመጠው ተሳፋሪ መሀል ያለ ተሳፋሪ ‘ሃሎ’ አለ። “ማን ነሽ? ማ?” ከመጠን በላይ ይጮሃል። “አላወቅኩሽም!” ብሎ አሁንም የጆሯችንን ታንቡር ሲደልቀው፣ “እንዲህ የመጮህ የመጮህ ለምን ሲም ካርድ አወጣ? ለምንስ ሞባይል ቀፎ ገዛ?” ብሎ ጎልማሳው ማያያዝ። “ማን አልሽኝ?” ሲል አሁንም ከዚህ አንታርቲካ በሚሰማ ድምፅ “ዋ! ዘንድሮ ሲም ካርድና መንጃ ፈቃድ እንደባከነው ምን ነገር ባከነ እናንተ?” ብላ ወይዘሮዋ አሳቀችን። በጩኸት ካልተደማመጥን ተኮራኩረን እንሳሳቅ እንጂ እንግዲያ!

ወደ መዳረሻችን ቦሌ ተቃርበናል። “ቦሌ ስሟ ብቻ ቀርቷል እኮ። ዘመናዊነትና ሥልጣኔ ያቺ በስስት የሚረግጧት ቦሌ እኮ ድሮ ቀረች፤” ይላል ከመጨረሻ ወንበር ፂማሙ። “ደግሞ በቦሌ ቀዳዳ ምን ታየህ?” ስትለው ባለሻሿ “አይታይሽም? አይታይሽም?’’ እያለ በሰልባጅ ልብስና በጉልት ንግድ ያበደውን ጎዳና ጠቆማት። “ምን ሠርተው ይብሉ? እንዲህ በፀሐይ ሲቀቀሉ ውለው ቋጥረው በገቡ?” ስትል ወይዘሮዋ፣ “ገና ለገና ለቦሌ ውበት ብላችሁ ደግሞ በግብረ ኃይል አስመቷቸው፤” አለ አንዱ። “ኧረ እናንተ እያልክ አትጠቁመን ስለፈጠረህ። ያወራነው እኮ ለጨዋታ ነው፤” ሲል ነገሩን የጀመረው፣ “ለጨዋታ ተብሎ የሚኖር ኑሮ እስከሌለ ድረስ ለጨዋታ ድምቀት ተብሎ የሚነሳ ሂስ ነዋ አልገባን ያለው፤” ብሎ ዞሮ ሲያፈጥ ጋቢና የተሰየመው ተሳፋሪ መሆኑን አየን። “ተረጋጋ! ተረጋጋ!” ወያላው እያሾፈ ነው።  

“እባካችሁ እናንተ ልጆች ተዉ። በሠርቶ አዳሪው ተበሳጭታችሁ፣ በሙሰኛው ተበሳጭታችሁ፣ በመንግሥትና የኢኮኖሚ አተናተኑ ተብከንክናችሁ፣ በሚዲያ ሆድ ብሷችሁ፣ እንዴት ትችሉታላችሁ?” አዛውንቱ ገላጋይ ሆኑ። ቀልደኛው ጎልማሳ ቀበል አድርጎ፣ “አንድ አፍና አንድ ሰው እስኪቀር ድረስ እንታገላለን፤” ብሎ አስፈገጋቸው። “ቀልዱስ ቀልድ ነው። ግን እንዲያው ለማለት የፈለግኩት፣ እስኪ ጉልበት ቆጥቡና ነገን አልሙ። አንድም እንዲህ በየመንገዱ፣ በሰበብ አስባቡ እሪ እያላችሁ ኃይላችሁ እያለቀ፣ ሐሞታችሁ እየፈሰሰ እኮ ነው የበይ ተመልካች የሆናችሁት? እኔን ስሙኝ! የድሮን ለድሮ ተውት። ቅድም ዘፋኙ አላለም? ‘በነበር’ ምንም የሚሆን ነገር የለም። ፍቅርም ሒሳባዊ ሆኗል። አበቃ። ራሳችሁን አውጡ፤” ብለው ወያላው “መጨረሻ” ከማለቱ እንደ ጎረምሳ ዱብ ብለው ወረዱ። እኛ ወጣቶቹ ወገባችንን ይዘን እየታሸን ወረድን። ‘ልብ እየጠበበ ሳንባ እየሰፋ፣ ታዋቂ ሰው በዝቶ አዋቂ ሰው ጠፋ’ የሚለውን የታክሲ ውስጥ ጥቅስ የሚያስታውስ የሚመስል ጎረምሳ በአዛውንቱ አኳኋን ተገርሞ፣ ‹‹አሁን እኛ እንረባለን? ዝናና ታዋቂነት ስናባርር እኮ ነው ከዕውቀቱ የጎደለን፤›› ሲል በእርግጥም ታዋቂው በዝቶ አዋቂ ቢጠፋ ምን ያስገርማል ያስብል ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት