Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግዙፉ የኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና በውጭ ተፅዕኖ ሥር የሚገኘው የግንባታ ኢንዱስትሪ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት እየታየበት መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በመላ አገሪቱ ከአነስተኛ እስከ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ባለው ደረጃ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ከአገሪቱ በጀት ብልጫ ያለውን የሚወስዱ ግንባታዎችም ይከናወናሉ፡፡ ይሁን እንጂ እየተካሄደ ያለውን የመሠረተ ልማት ግንባታ የሚሸከም አቅም ያለው አገር በቀል የኮንስትራክሽን ኩባንያ ማፍራት አልተቻለም፡፡ ከአምስት ሺሕ በላይ  ተቋራጮች ቢኖሩም አቅማቸው ገና እየተገነባ ይገኛል፡፡

በእርግጥ በፌዴራል ደረጃ በመንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍ አንድ መቶ የሚደርሱ አገር በቀል ተቋራጮችን ማፍራት ወይም ማብቃት እንደተቻለ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ይገልጻል፡፡ አዳዲስ አገር በቀል ኮንትራክተሮች በመንገድ ሥራ  ተሳታፊ እንዲሆኑም ዕድሉ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንደሚገልጹት፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በጠጠር መንገድ ሥራ ላይ ብቻ ይሳተፉ ነበር፡፡ አሁን ግን አቅማቸው እንዲጎለብት ተደርጎ በአስፓልት ኮንክሪት ሥራዎች ላይ ተሳታፊ እየሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ትላልቅ በሚባሉ የመንገድ ሥራዎች ላይ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑ ግን አልቀረም፡፡ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እየወሰዱ ያሉት የውጭ ኮንትራክተሮች ስለመሆናቸውም ተገልጿል፡፡  

እንደ አቶ ሳምሶን ማብራሪያ በመንገድ ዘርፍ ከጠቅላላ ፕሮጀክቶች ውስጥ 75 በመቶው ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የተሰጠ ነው፡፡ በገንዘብ ደረጃ ሲታይ ግን የውጭዎቹ ኩባንያዎች የወሰዷቸው ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ደረጃ ብልጫ አላቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ትልልቆቹ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ወጪ ስለሚወጣባቸው እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡  

በመንገድ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የግንባታ ዘርፎችም የውጭ ኩባንያዎች ጡንቻ ፈርጣማ እየሆነ ከመጣ ውሉ አድሯል፡፡ በውኃ፣ በትላልቅ የኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ በትላልቅ ሕንፃዎችና የባቡር መስመር ግንባታዎች ሳይቀር ግንባታውን እያከናወኑ ያሉት የውጭ ኮንትራክተሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ከፍተኛ በጀት ተይዞላቸው የምታካሂዳቸው ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ያሉት በውጭ ኩባንያዎች በተለይም በቻይና  ተቋራጮች እንዲሆን ዕድል ሰጥቷል፡፡

በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ መስቀል ተፈራ እንደሚገልጹት፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ በተለይ የአገር ውስጥ አቅም ላይ ክፍተት አለ፡፡  

በአሁኑ ወቅት ከአምስት ሺሕ በላይ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ቢኖሩም፣ በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ያልተደፈሩ እንዲያውም ያልተሞከሩ ፕሮጀክቶች እጅግ በርካታ ስለመሆናቸውም ያስታውሳሉ፡፡ እንደ አዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ያሉ ፕሮጀክቶችን በአገር ውስጥ ተቋራጭ ለመገንባት የሚያስችል አቅም አልጐለበተም፡፡ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ የፈጀው ይህ መንገድ፣ በቻይና ተቋራጮች የተገነባ ነው፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ የፍጥነት መንገዶች ግንባታም ለውጭ ኮንትራክተሮች የተሰጠ ሲሆን፣ ወደፊትም እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ሁለቱ የፍጥነት መንገዶች ብቻ (የተጠናቀቀውና በሒደት ላይ ያለው) ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ትላልቅ የሚባሉት የግድብ ሥራዎች በጣልያንና በቻይና ኩባንያዎች የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሥራ ላይ ለዋሉት አራት ግድቦች ከ40 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ወጪ አውጥታለች፡፡ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ብቻውን 80 ቢሊዮን ብር ያህል ወጪ ይጠይቃል፡፡ እንደ የግልገል ግቤ አንድ፣ ግልገል ግቤ ሁለትና የተከዜ ግድቦች በዋናነት በቻይናና በጣልያን ኩባንያዎች የተገነቡ ናቸው፡፡ የህዳሴው ግድብም ሆነ ግልገል ግቤ ሦስትም ግንባታቸው እየተካሄደ ያለው በእነዚሁ የውጭ ኩባንያዎች መሆኑ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

የአገር ውስጥ ተቋራጮች አነስተኛ ሥራዎችን በሰብ ኮንትራት ከመውሰዳቸው በቀር የሁሉንም ፕሮጀክቶች ዋና ዋና ሥራ የወሰዱት የውጭ ኮንትራክተሮች መሆናቸው፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ሀብት ተጠቃሚዎቹ የውጭ ኮንትራክተሮች እንዲሆኑ አስገድዷል፡፡  

በመንገድ ዘርፍ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የአገር ቤቶቹ ለምን አይሳተፉም? የሚለው ጥያቄ አጭር ምላሽ በዋናነት ያለባቸው የአቅም ችግር ነው፡፡ በተለይ በውጭ ፋይናንስ በሚደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ የሚወጣው የጨረታ መሥፈርት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አቅሙም ቢኖራቸው እንዳያሸንፉ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ተቋራጮች አቅርቡ የሚባሉት የገንዘብ ፍሰታቸው ማሳያ (ተርን ኦቨር) ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የመንገድ ሥራ ጨረታ ላይ አንዱ የጨረታ መሥፈርት ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰታቸው ይህንን ያህል መሆን አለበት መባሉ ነው፡፡ ብዙዎቹ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ግን የሚጠየቀውን ያህል የገንዘብ እንቅስቃሴ ስለማያከናውኑ ከጨረታ ውጭ ይሆናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂት አገር በቀል ኮንትራክተሮች የውጭ ኮንትራክተሮች በተሰጡ ትላልቅ ጨረታዎች ላይ ሳይሳተፉ ቀርተው እንዳልሆነ የአቶ ሳምሶን ገለጻ ያስረዳል፡፡

ለምሳሌ ለአንድ የመንገድ ሥራ ጨረታ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ተርን ኦቨር ሊቀርብ ይገባል ቢባል ይህንን የሚያሟላ የአገር ውስጥ ተጫራች ባለመኖሩ ከጨረታ ውጭ ይሆናሉ፡፡

እንዲህ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ግን በመንግሥት ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች ለአገር ውስጥ ተጫራቾች እየተመቻቸ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ አሠራር በመንግሥት ፋይናንስ በሚደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ የአገር ውስጥ ተቋራጮች ቁጥር እየጨመረ እንዲመጣ አስችሏል፡፡ እንዲህ በማድረግም የፋይናንስ አቅማቸውን እንዲያዳብሩና የሚጠየቀውን መሥፈርት እንዲያሟሉ ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡

በሕንፃ ግንባታው ዘርፍም በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ በቅርቡ ወደ ግንባታ እየገቡ ያሉትን የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች እንዲገነቡ ዕድሉን ያገኙት የቻይና ኩባንያዎች መሆን የአገሪቱ የግንባታ ሥራ ለውጭ ኩባንያዎች የተመቸ ሆኗል፡፡ ከዚያው አንፃር አገር በቀል ኮንትራክተሮች ተወዳዳሪ ያለመሆናቸውን እያመላከተ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ የወጋገን ባንክና የኅብረት ባንክ፣ ከ30 እስከ 42 ወለሎች ያላቸውን ሕንፃዎች ግንባታ ለቻይና ተቋራጮች የተሰጠ ሲሆን፣ እነዚህ ሦስት ሕንፃዎች ብቻ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መጠየቃቸው ሲታይ፣ የአገር ውስጥ የውጭ ኮንትራክተሮች በግንባታ ዘርፉ ያላቸው ቦታ ውሱን መሆኑን አሳይቷል፡፡

የግል ተቋራጮች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥታዊ ተቋማትም በገበያ ውስጥ ቢኖሩም፣ አቅማቸው ልክ እንደ ግል ተቋራጮቹ ውሱን በመሆኑ የውጭ ኮንትራክተሮች ግዙፍ የሚባሉ ፕሮጀክቶችን በቀላሉ ለመረከብ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡

እንደ አቶ ኃይለ መስቀል ገለጻ ግን መንግሥት ይህንን ክፍተት ለመሙላት በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን በማሰባሰብ እንዲቋቋም የተደረገው ኮርፖሬሽን የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ በውጭ ኮንትራክተሮች ብቻ ተይዘው የቆዩ ሥራዎች ውስጥ እንገባለን ይላሉ፡፡ በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሳይደፈሩ የቆዩትና እንደ ግድብ ሥራዎች ላይ ሁሉ እንገባለን በማለት ይናገራሉ፡፡  

መንግሥታዊ የኮንስትራክሽን ተቋማትን ለማብቃት የተደረጉ ለውጦችም ገና በእንፉቅቅ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ዓለም አቀፉን ተቋራጮች የሚወዳደር አቅም አላጐለበቱም፡፡ ትላልቅ ግንባታዎች ላይም ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡ አነስተኛ የግድብ ሥራዎችን እንኳ የመገንባት አቅም ሳይፈጥሩ የቆዩ በመሆናቸው ወደፊትስ በሚፈለገው ፍጠነት ሊገነቧቸው ይችላሉ ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ አቶ ኃይለ መስቀል ግን ይቻላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

መንግሥት በአገሪቱ በግዙፍነቱ ተጠቃሽ የሆነውን ኮርፖሬሽን ሲያቋቁም ታሳቢ ተደርገው ዋናው ነገር ያልተሞከሩ ሥራዎች ውስጥ ለመግባት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሥራ ላይ ያሉ ተቋማትን በአንድ አሰባስቦ መሥራቱ ውጤት ያመጣል ተብሎ ያስረዳሉ፡፡

በግንባታ ሥራዎች ላይ የነበሩ መንግሥታዊ ተቋማት በአንድ ጥላ ሥር መሆናቸው ጥንካሬ ያወጣል ባይ ናቸው፡፡ የኮርፖሬሽኑ መቋቋም ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አገር በቀል ኩባንያዎችን አቅም ማጐልበት ያስችላልም ተብሏል፡፡

መንግሥት እያቋቋማቸው ያሉ ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች ውጤት የታሰበውን ያህል ላይሆን እንደሚችል ሥጋት ያላቸው መሆኑን የሚጠቅሱ አስተያየት ሰጪዎች ግን የስኳር ኮርፖሬሽን አፈጻጸምን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ አንድ ላይ መጣመራቸው ውጤት ካመጣ መልካም ቢሆንም እያንዳንዱ ተቋም ለብቻው የሚሠራው ሥራ ውጤታማ ከሆነ በጥምረቱ ሊዳከሙ ይችላሉ የሚለውን አስተያየት አቶ ኃይለ መስቀል አይቀበሉትም፡፡

አቶ ኃይለ መስቀል በበኩላቸው የቀድሞዎቹ የመንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅቶች በአንድ ላይ መዋሃዳቸው አገሪቱ ትልቅ የኮንስትራክሽን ኩባንያ እንድትፈጥር ያስችላታል፤ ለውጥ ይመጣል ይላሉ፡፡

ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪው ውስጥ ችግሮችን እያረመ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ በመቀጠል በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሁለት ዓመት በኋላ ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኩባንያ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት የሚሠራ ተቋም ይሆናል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ግን ኮርፖሬሽኑ በጨረታ፣ በድርድርና በትዕዛዝ ትልልቅ የመስኖና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ጨምሮ የተለያዩ ግንባታዎችን ለማካሄድ ተዘጋጅቻለሁ ቢልም፣ ይህንን ሁሉ ለመከወን አቅም ከየት ይመጣል? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡

አቶ ኃይለ መስቀል ግን ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት ከተመደበለት ካፒታል በተጨማሪ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት በመበደር ጭምር የኮርፖሬሽኑን ውጥን ዳር ማድረስ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በውህደት ከጠቀለላቸው የመንገድና የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽኖች በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ትላልቅ ኩባንያዎች በመመሥረት ወደ ሥራ የሚገባና እነዚህም አዳዲስ ኩባንያዎች ለኮርፖሬሽኑ የገቢ ምንጭ ይሆናሉ ተብሎ ታቅዷል፡፡

እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው ደግሞ የሕንፃ መገጣጠሚያ ማምረቻውና አሁን ያሉትን ግድቦች በማስተዳደር ለመስኖ ልማት እንዲውሉ ማድረግ ነው፡፡ ግድብ የማስተዳደር ሥራው ለመስኖ ተጠቃሚዎች ውኃ መሸጥን ያጠቃልላል፡፡

አገር በቀል ኮንትራክተሮች በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ አሁንም ብዙ መሠራት እንዳለበት ይስማማሉ፡፡

አቶ ሳምሶን በተለይ በመንገድ ዘርፍ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ግድ መሆናቸውንም ያሰምሩበታል፡፡ በተለይ የባለሙያዎችን እጥረት ለመቅረፍ የምሕንድስና ባለሙያዎች ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመንግሥት ወጪ እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ከፍተኛ ክፍተት አለበት የሚባለውን የማሽን ኦፕሬተሮችን ለመቅረፍ በባለሥልጣኑ ማሠልጠኛዎች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በሽርክና መሥራት ልምድም አገር በቀሎቹን ለማሳደግ የተመቸ እንደሚሆን ያምናሉ፤ ይህ ከተሠራና ትላልቅ ፕሮጀክቶች በአገር በቀል ተቋራጮች ይሠራሉ፡፡  

ከዚህም ተጨማሪ ከኮርፖሬሽኑ የሥራ ዕቅዱ አንፃር ሲቋቋም የተመደበለትን 20.3 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚያሳድግ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም የኮርፖሬሽኑን ካፒታል ወደ 52 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ለመንግሥት ጥያቄ ቀርቧል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግን ኮርፖሬሽኑ ሥር የተጠቃለሉ ኩባንያዎች ድምር የካፒታል መጠን በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ሲተመን ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የዘለለ አይደለም፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሥር የተጠቀለሉት የመንገድ ሥራ ኮርፖሬሽንና የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት አሁን በእጃቸው ያለው ሥራም ቢሆን ከፍተኛ የሚባል ባይሆንም፣ አዳዲስ ሥራዎችን በማከል በኢንዱስትሪው ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አቶ ኃይለ መስቀል ገልጸዋል፡፡

አቶ ሳምሶን በበኩላቸው በመንገድ ግንባታው ዘርፍ አገር በቀል ተቋራጮች የበለጠ እንዲሠሩ ከተፈለገ ተቋራጮችም የውስጥ የቤት ሥራቸውን መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ በሚሰጣቸው ዕቅድ አቅጣጫቸውን ካጐለበቱ በትላልቅ ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ዕድል ይኖራቸዋል ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች