ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ ከስምንት ወራት በፊት ማቅረብ የጀመረውን የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ቦታ ጥያቄ በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ መዘግየት ምክንያት ወደ ሥራ ሊገባ እንዳልቻለ ገለጸ፡፡
ቅዳሜ ግንቦት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በ80 ሚሊዮን ብር በአዲስ አበባ ያስገነባውን የሀዩንዳይ ተሽከርካሪዎች የጥገና ማዕከል ያስመረቀው ማራቶን ኩባንያ፣ አዲሱን መገጣጠሚያ ለመጀመር አስተዳደሩ ቆራጥ የሆነ መልስ እንዲሰጠው በመጠየቅና ‹‹ተፈቅዷል ወይም አልተፈቀደም›› የሚል ምሻል ስጡን በማለት የድርጅቱ ሊቀመንበር አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ተናግሯል፡፡
ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ የሀዩንዳይ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ለመገንባት ቀደም ብሎ የ70 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠው ጠይቆ 50 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ የተፈቀደለት ሲሆን፣ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነገ ዛሬ እያለ ቀጠሮ እያበዛ ወደ ሥራ እንዳልገባ አድርጎኛል፤›› በማለት አትሌት ኃይሌ በምርቃቱ ወቅት ተናግሯል፡፡
የተሽከርካሪ መገጣጠሚያውን ለማስገንባት የግማሽ ቢሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ ፈቃድ ከተወሰደ ሦስት ወር እንዳለፈው ተገልጾ፣ ከዓለም አቀፍ የሀዩንዳይ እህት ኩባንያ ጋር ያለውን ስምምነት መጨረሱን የድርጀቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መልካሙ አሰፋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ቅዳሜ በተደረገው የምርቃት ሥነ ሥርዓት ለተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁም፣ መንግሥት ኩባንያው በጠየቀው የመሬት ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ መልስ ይሰጣል ብለዋል፡፡
የሀዩንዳይ ተሽከርካሪዎችን ለመገጣጠም የተነሳው ማራቶን ሞተርስ ወደ ሥራው ለመግባትና ፈቃድ ለማግኘት ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደበት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ አስተዳደር የፕሮጀክቱ አዋጪነት ጥናት ተጠናቆ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ማግኘት ብቻ እንደቀረው አቶ መልካሙ ተናግረዋል፡፡
የመሬት ጉዳይ ካላዘገየን በስተቀር ከዘንድሮ የበጀት ዓመት መጠናቀቂያ በፊት ወይም በጣም በዛ ከተባለም በመጪው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተሽከርካሪዎቹ ተገጣጥመው ለገበያ መቅረብ እንደሚችሉ አቶ መልካሙ ገልጸዋል፡፡
የመገጣጠሚያው ግንባታ ወጪ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሲሆን፣ ሥራ እንደጀመረ 1,500 ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ለማቅረብ እንደታቀደ አቶ መልካሙ አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም ማራቶን ኢንጂነሪንግ የገበያ ዋጋ ዓይነቱን የማይለወጥ ከሆነ ከውጭ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች 30 በመቶ ቅናሽ እንደሚኖረውና የአሮጌ መኪና ሽያጭ የሚቀንስበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
መገናኛ ከሚገኘው የመለዋወጫ፣ መሸጫና ማሳያ (Show Room) እንዲሁም በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ባስገነባው ሕንፃ በተጨማሪ በተመሳሳይ ሁኔታ በ40 ሚሊዮን ብር በሐዋሳ ያስገነባውን የሀዩንዳይ ማሳያ፣ መለዋወጫ፣ መሸጫና መገጣጠሚያ ማዕከልን ማስመረቅ ችሏል፡፡
በምርቃቱ ወቅት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርበት አገር ውስጥ ከ600 እስከ 650 ሺሕ የሚገመት መኪና መኖሩን ገልጸው፣ ዘርፉ ባለሀብቶች ከተሰማሩበት አዋጭ መስክ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የተጀመሩት ሥራዎች በአግባቡ እንዲጠናቀቁ መንግሥት ዘርፉ ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል በማለት አክለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2008 ሥራውን የጀመረው ማራቶን ሞተርስ፣ በሦስት ሠራተኞችና በአሥር ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደ ሥራ ሲገባ፣ በአሁኑ ወቅት 100 ሚሊዮን ብር ካፒታልና ከ200 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ተጠቅሷል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀዩንዳይ ኩባንያ ኪሳራ ውስጥ ገብቶ የነበረ ሲሆን፣ ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ ያንን ወቅት ተቋቁሞ እዚህ ደረጃ መድረሱ ዓለም አቀፉ የሁዩንዳይ ኩባንያ በማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ ላይ እምነት እንዲኖረው አስተዋጽኦ አስችሎታል በማለት አትሌት ኃይሌ ተናግሯል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የሀዩንዳይ ተሽከርካሪ ገበያ በተቀዛቀዘበት ወቅት ሱዳንን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች መሸጫዎቻቸውን ለመዝጋት ተገደው የነበረ ሲሆን፣ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ባላት የሰው ኃይል አቅምና ለትምህርት ወደ ኩባንያው የተላኩት ተማሪዎች ቀልጣፋ መሆን፣ ኢትዮጵያ ከገበያው እንዳትወጣ አድርጓታል ተብሏል፡፡
የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ለመጀመር በቂ የካፒታል አቅምና የሰው ኃይል ዋነኛ ሲሆኑ፣ የካርቦን ጋዝ ልቀት ለመቀነስም ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ መኪናዎችን ማምረት ቀዳሚ ሥራዎች ናቸው፡፡ ከማሽነሪዎች ጋር በተያያዘ የሀዩንዳይ ኩባንያ በራሱ ቦታ በማስመጣት እንደሚተክላቸው ታውቋል፡፡
እንደ አቶ መልካሙ ገለጻ ለተሽከርካሪ መገጣጠሚያው የሚያስፈልጉ ነገሮች ማለትም ባትሪና ጎማ የመሳሰሉ ተዛማች ግብዓቶችን 30 በመቶ ከአገር ውስጥ መጠቀም ይቻላል ብለዋል፡፡ መገጣሚያምው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከ500 እስከ 2,000 ለሚደርሱ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡