Sunday, April 14, 2024

እስራኤል ወደ አፍሪካ ቀንድ ፊቷን እያዞረች ይሆን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እንግዶቹ የአምባሰደሯን ንግግር በጥሞና እያደመጡ ነው፡፡ በንግግራቸው መካከል አንዳች ጣል ያደረጓት ዓረፍተ ነገር ግን በተለየ ቀልብ ሳትስብ አልቀረችም፡፡ ‹‹የእስራኤልና የኢትዮጵያ ግንኙነት በታሪክና በባህል ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ በንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰለሞን ጉብኝት ይጀምራል፤›› ብለው፣ በአንደኛው እጃቸው  የያዙት የወይን ዋንጫ ሳይገድባቸው በጭብጨባ አቀለጡት፡፡

እስራኤል በድጋሚ እንደ አገር የተቆረቆረችበት 68ኛው ብሔራዊ ቀን በመከበር ላይ ነው፡፡ የውጭ አገር ሰዎች የበዙበት ክብረ በዓል በኢትዮጵያም በሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ የተከበረ ሲሆን፣ በአፍሪካ  ዋነኛዋ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ በሆነችው አዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ እንዲሁም የመንግሥት ባለሥልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታዳሚ ሆነውበት ነበር፡፡

የበዓሉ ድምቀት ከሦስት ዓመት በፊት በሸራተን አዲስ በዚሁ ላሊበላ አዳራሽ ቻይና ብሔራዊ ቀኗን ያከበረችበትን አጋጣሚ የሚያስታውስ ነው፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተገኝተው ነበረ፡፡ በዚሁ የእስራኤል ብሔራዊ ቀን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት በላይነሽ ዘቫድያ ያደረጉት ንግግር፣ በአብዛኛው በሁለቱ አገሮች ግንኙነት መጠናከር አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ይፋዊ ግንኙነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተፈረሙትን ስምምነቶች፣ በተግባር በመከናወን ላይ ያሉትንና የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነቶች አብራርተዋል፡፡

በቀዳሚነት ያነሱት የማሸቭ (የእስራኤል ዓለም አቀፍ ትብብር) በኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በተለይ ደግሞ፣ በጤናና በትምህርት የተሰማራባቸው የቴክኒክ ዕርዳታዎች በተመለከተ ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 በኢትዮጵያ በእስራኤል መካከል የትምህርትና የባህል የመግባቢያ ስምምነት የተፈረመ ሲሆን፣ አምባሳደሯ እንደሚሉት በፊልምና በሌሎች የሥነ ጥበብ ዘርፎች ከፍተኛ የልምድና የዕውቀት ልውውጥ ተደርጓል፡፡

በቅርቡም ሁለቱም አገሮች በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ሌላ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ በዓለም ታላላቅ የሚባሉት የእስራኤል ኩባንያዎች በማዕድንና በስኳር ዘርፎች ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ እነዚህም በአፋር ክልል በፖታሽ ፍለጋ የተሰማራው እስራኤል ኬሚካልስ ሊሚትድ (ICL) እና ኔታፊም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ረጂም ዓመታት በኋለ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቪግደር ላይቨርማን እ.ኤ.አ. በ2014 ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በሽብርተኝነትና በደኅንነት ላይ በጋራ ለመሥራት ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መክረው መሄዳቸው ይታወሳል፡፡

አምባሳደሯ በንግግራቸው ማጠቃለያ፣ ‹‹በዚህች ታላቅ አገር ላይ ሆነን የእስራኤልን የነፃነት ቀን በጋራ ስናከብር፣ ምንም ያህል ፈተና ቢገጥመንም የኢትዮጵያና የእስራኤል ታላላቅ ቀናት ገና መፃኢ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በበኩላቸው፣ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ታሪካዊ ዳራ ያለውና ወደ ላቀ ደረጃ ሊሸጋገር የሚችል መሆኑን ገልጸው በተለይ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ግንኙነቱ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የተጫወቱትን ከፍተኛ ሚና አድንቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ

ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑት አምባሳደር በላይነሽ የሁለቱም አገሮች ታላላቅ ቀናት መፃኢ መሆናቸውን ሲናገሩ በአንድ ዓብይ ዜና አጅበው ነበር፡፡ በመጪው ሐምሌ ወር በአፍሪካ ጉብኝት የሚያደርጉት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የጉብኝታቸው ቀዳሚ ምዕራፍ ኢትዮጵያን ያደርጋሉ፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርግ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን፣ በተለይ ለኢትዮጵያውያን የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች ከፍተኛ ደስታ የሰጠ ነበር፡፡ ተጋባዥ እንግዶችም ደስታቸውን በከፍተኛ ጭብጨባ ነበር የገለጹት፡፡

በአምባሳደሯ እንደተገለጸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ዓላማ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ከፍ ለማድረግ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ታዛቢዎች ግን ጉብኝቱ ከደኅንነት ጉዳይ ጋር ሳይገናኝ አይቀርም ይላሉ፡፡

እስራኤል የዛሬ 68 ዓመት እንደገና ከተቆረቆረች ጊዜ ጀምሮ ጠላት በምትላቸው የዓረብ አገሮች የተከበበች በመሆኗ ህልውናዋን የሚፈታተን የደኅንነት አደጋ ሁሌም እንደተጋረጠባት ትናገራለች፡፡ በተለይ ከጎረቤት ፍልስጤም ጋር ያላት የተበላሸ ግንኙነት ዕልባት ያላገኘ በመሆኑ በጦርነትና በግጭት የሚገለጽ ነው፡፡ የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮችም የጧትና የማታ የመነጋገርያ አጀንዳቸው የሁለቱ ባላንጣዎች የዘመናት ጠላትነት ነው፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በየመን የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የተፈጠረው የዓረብ አገሮች ቅንጅት፣ በአጭር ጊዜ የሁቲ አማፂ ቡድንን ለማጥፋትና የቀድሞውን የየመን ፕሬዚዳንት ወደ ቦታቸው ለመመለስ ያለመ ቢሆንም፣ እየተዋጣ ያለው ከፍ ያለ ገንዘብና የጦር መሣሪያ ለእስራኤል የደኅንነት ሥጋት መፍጠሩ ይነገራል፡፡ በተለይ ደግሞ የእስራኤል ባላጋራ የሆነችው ግብፅ ያለችበት ይኼው ቅንጅት፣ ለመካከለኛው ምሥራቅና ለአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ የደኅንነት ትርጉም ያለውን ቀይ ባህር ነፃ የበረራ ዞን እንዲሆን በኤርትራ መፈቀዱ፣ አደጋው ከፍ ያለ እንዲሆን ያደርገዋል ተብሎም ይሠጋል፡፡

በሶማሊያ ከአልሸባብ የሽብርተኝነት አደጋ ጀርባ እንዳሉ የሚታመንባቸው በርከት ያሉት የዓረብ አገሮች፣ በዚሁ ቅንጅት ውስጥ መሰባሰባቸው ለኢትዮጵያም ሌላ የደኅንነት ሥጋት ሊያስከትል እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

ይኼም ብቻ አይደለም፡፡ ሁለት አሥርት ሊደፍን ሁለት ዓመት ብቻ የቀረው የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ግጭት እስካሁን ዕልባት ያልተገኘለት ሲሆን፣ የድንበር ኮሚሽኑም ያላንዳች መፍትሔ መበተኑ ይታወሳል፡፡

የሁለቱም አገሮች ሰላምም ጦርነትም አልባ ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ ብቅ ጥልቅ የሚሉ ሰርጎ ገቦች የሚሞክሩዋቸው የሽብር ድርጊቶች፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ከመጠን ያለፈ ትዕግሥት ምክንያት መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ አስመራ ላይ የከተመው በፕሬዚዳንት ኢስያስ አፈወርቂ የሚመራው መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ማዕቀብ የተጣለበትና ፀረ ዴሞክራሲና ፀረ ሰብዓዊ መብት ቢሆንም፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚገባ ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው እንደሆነ ሲተች ነበር፡፡

ታዲያ የአስመራ መንግሥት በአሁኑ ወቅት በየመን እያበጠ ያለው ፈርጣማ ቅንጅታዊ ኃይል አባል ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለዚሁ ቅንጅት ላደረገው ትብብር ውለታ የተከፈለው ይመስላል፡፡ የተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ የአሰብ ወደብ እስካሁን ይፋ ባልሆነ ነገር ግን ከፍተኛ ዋጋ ለ30 ዓመታት መከራየቷ፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአካባቢው እንቅልፍ የሚነሳ መሆኑም ይነገራል፡፡

በአብዛኛው የዓረቡ ዓለም የክርስቲያን ደሴት ተደርጋ ትታይ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መፍጠር ያቃተው የአስመራ መንግሥት የጥቃት ዒላማ እንዳትሆን ሥጋት ያላቸው አሉ፡፡

የእስራኤል ዋነኛ ጠላት የሆነችው ኢራን በቀይ ባህር ለመገንባት የሞከረችው ወታደራዊ ቤዝ መክሸፉ መልካም ዜና ቢመስልም፣ ስትራቴጂካዊው ሥፍራ በሌሎች ጠላቶች እጅ ውስጥ እየገባ እንዳይሆን በእስራኤልም ተሠግቷል፡፡ ምናልባት ከጥንት ጀምሮ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው እስራኤልና ኢትዮጵያ፣ ግንኙነታቸውን የበለጠ ያሳድጋል ተብሎ የሚታመንበት የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጉብኝት ከዚሁ የጋራ ሥጋት የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

ሞቅና ቀዝቀዝ ያለው ግንኙነት

በተለይ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ኢትዮጵያውያን ዘንድ እስራኤል እንደ ሁለተኛና እንደ ተስፋይቱ ምድር ተደርጋ የምትታይ ሲሆን፣ በዘመናዊው ታሪክ ግን የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ሞቅና ቀዝቀዝ እያለ ቆይቷል፡፡

በአንድ ወቅት አፄ ኃይለ ሥላሴ ይፋዊ ላልሆነ ጉብኝት ወደ እስራኤል መሄዳቸው የሚነገር ሲሆን፣ እ.አ.አ. በ1960 ንጉሡ በብራዚል ለጉብኝት በሄዱበት ወቅት የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት በማክሸፍ እስራኤልና የስለላ ድርጅቷ ሞሳድ ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸው ይነገራል፡፡

‹‹ሲክስ ደይስ ወር›› (የስድስት ቀናት ጦርነት) በመባል የሚታወቀው የእስራኤልና የግብፅ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ በኤርትራ የመገንጠል ጥያቄ ያነሳው ጀበሃ (የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር) መጀመርያ የተቋቋመው በካይሮ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ድርጅቱ ከፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ድርጅት (PLO) ጋር ትስስር እንዳለው በመረጋገጡ፣ በኤርትራ ውስጥ የተደረገው ጦርነት የዓረብና የእስራኤል የውክልና ጦርነት ተደርጎ ነበር የተቆጠረው፡፡

የንጉሡ የኮማንዶ ኃይል በአንድ ወቅት ወታደራዊ ሥልጠና ያገኘው በእስራኤል እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያ በንጉሡ ጊዜ በኤርትራ ደሴቶች ወታደራዊ ቤዝ ሰጥታለች የሚሉ ውንጀላዎች የቀረቡባት ሲሆን፣ በወቅቱ በምሥረታ ወቅት ግንባር ቀደም በሆነችበት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል አገሮች (በተለይ ደግሞ በሊቢያ) ተቃውሞውን መቋቋም ባለመቻሉ (ንጉሡ ባይፈልጉም)፣ በጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ ግፊት ከእስራኤል ጋር የነበራትን ግንኙነት እንድታቆም ተገዳለች፡፡

ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን ላይ ሲወጣም የሁለቱም አገሮች ግንኙነት አንዳንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ እየቀዘቀዘ የቀጠለ ሲሆን፣ እስራኤል በተለይ የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ለመምታት (ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተቋረጠ ወቅት ጭምር) ወታደራዊ ድጋፍ ታደርግ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1984 ቤተ እስራኤላውያንን ወደ እስራኤል ለመውሰድ ‹‹የሙሴ ዘመቻ›› እየተባለ በሚጠራው ዘመቻ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ላደረጉት ትብብር በውለታ 83 ሚሊዮን ዶላር በዕርዳታ መገኘቱን፣ ከ300 በላይ የእስራኤል ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ሥልጣን ይሰጡ እንደነበር የመረጃ ምንጮች ያመለክታሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -