የቀድሞ የፓርላማ አባል ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ውስጥ በኢንቨስትመንት ሆስፒታል ለመገንባት ለዓመታት ሲያደርጉት የነበረው ጥረት የገጠመውን እክል ለመፍታት ላቀረቡት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተመልክቶ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስነሳል ሲል ወሰነ፡፡ ይሁን እንጂ ውሳኔው ዶ/ር አሸብርን አላስደሰተም፡፡
ዶ/ር አሸብር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት ይግባኝ እንደሚያስረዳው፣ ለረዥም ዓመታት ከአገር ውጭ ያፈሩትን ሀብት ወደ አገር ይዘው በመግባት ለተወለዱበት አካባቢ ማኅበረሰብ እንዲሁም ለመንግሥት እገዛ ያደርጋል ያሉትን የሆስፒታል ግንባታ ኢንቨስትመንት በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ውስጥ ጀምረው፣ ግንባታው 70 በመቶ ከደረሰ በኋላ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ችግር ፈጥሮባቸዋል፡፡
የከተማው ማዘጋጃ ቤት የሆስፒታሉ የግንባታ ቦታ ላይ የኮንቴይነር ሱቆችን በመደርደሩ ምክንያት የግንባታ ዕቃዎችን ለማስገባት ባለመቻሉ ግንባታው እንዲቆም ማድረጋቸውን፣ በዚህ የተነሳ ማዘጋጃ ቤቱ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ክስ እንዳቀረበባቸው በይግባኛቸው አብራርተዋል፡፡
የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቦንጋ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ቀሪው ግንባታ መጠናቀቅ ያለበትን ጊዜ ወስኖ እንዲያሳውቅና ለግንባታ ሥራው እንቅፋት የሆኑትን የደረደራቸውን የኮንቴይነር ሱቆች በየደረጃቸው በመለየት እንዲያፈርስ፣ በዚህ ሁኔታ ግለሰቡ በሚሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ግንባታ ካላጠናቀቁ ማዘጋጃ ቤቱ ግንባታውን ባለበት ሁኔታ የመረከብ መብት እንዳለው መጥቀሱን በይግባኛቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህም የተነሳ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ በአጠቃላይ እንዲሁም ያለምንም ካሳ ክፍያ ማዘጋጃ ቤቱ ንብረቱን እንዲረከብ ብሎ የሰጠው ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 (7)፣ እንዲሁም ከኢንቨስትመንት ሕጉ ጋር የሚቃረን መሆኑን በማመልከት አቤቱታውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቢያቀርቡም፣ ጉባዔው የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደማያስፈልገው በመግለጽ አመልካቹ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 (7) መሠረት ተመጣጣኝ የካሳ ክፍያ እንዲሰጣቸው በማለት ወስኗል፡፡
ይህንን ውሳኔ በመቃወም ይግባኛቸውን ለፌዴሬሽን ምርክ ቤት ቢያቀርቡም፣ የምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጥያቄ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል፤›› ቢልም፣ ይዘቱ ግን ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ጋር ተመሳሳይ የሆነ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
ኮሚቴው ጉዳዩን የተመለከተው ከግንባታ ውሉ አንፃር አለመሆኑን ይገልጻል፡፡ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያትም ውሉ የተሰጠው በአግባቡ ነው አይደለም? ለውሉ መሰረዝ ጥፋቱ የማነው? የሚሉት ክርክሮች በፍርድ ቤት እንጂ በሕገ መንግሥት ትርጉም ሊታይ አይችልም የሚል ነው፡፡
በመሆኑም በቋሚ ኮሚቴው በኩል በዋናነት የታየው ውሉ ተሰርዞ ማዘጋጃ ቤቱ ቦታውን መረከቡ ሳይሆን፣ ከነግንባታው እንዲረከብ ሲደረግ በመሬቱ ላይ አመልካች የገነቡት ግንባታና ሁብት ጉዳይ በአግባቡ መታየት እንደነበረበት ነው፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 (7) ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ ማሻሻል ሙሉ መብት እንዳለው ይህ መብት የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማውረስ፣ የመሬት ተጠቃሚነቱ ሲቋረጥ የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ መብትን ያካትታል ብሎ እንደሚደነግግ ቋሚ ኮሚቴው በውሳኔ ሐሳቡ ገልጿል፡፡
ይህ ድንጋጌም በኢንቨስትመንት አዋጁ ከመሬት ይዞታ እንዲለቅ የሚደረግ ባለይዞታ፣ በመሬቱ ላይ ለሚገኘው ንብረት እንዲሁም በመሬቱ ላይ ላደረገው ቋሚ መሻሻል ካሳ እንደሚከፈለው በመደንገግ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን እንደሚያጠናክር ገልጿል፡፡
በመሆኑም በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የአቤቱታ አቅራቢውን ካሳ የማግኘት መብት የሚፃረር በመሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት የውሳኔ ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ውሳኔውን በአብላጫ ድምፅ ተቀበሎታል፡፡
ውሳኔውን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው ዶ/ር አሸብር፣ ‹‹ይግባኝ የጠየቅኩት ለካሳ ሳይሆን የጀመርኩትን ግንባታ ተረክቤ ለማጠናቀቅ ነው፤›› በማለት ቅሬታቸውን በስልክ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የቦንጋ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የዶ/ር አሸብር የነበረውን ይዞታ በማልማት ላይ እንደሚገኝ ከምክር ቤቱ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡