Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአዲሱ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሊሾም ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድወሰን ኢተፋ፣ በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲሠሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይሁንታ መስጠቱ ተሰማ፡፡

አቶ ወንድወሰን በኢትዮጵያ የጠለፋ ዋስትና ለመስጠት የመጀመርያው የሆነውን የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበርን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ ብሔራዊ ባንክ ይሁንታ የሰጠው፣ የሪኢንሹራንስ ኩባንያው ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ ለመጀመር መሟላት ከሚገባቸው መሥፈርቶች መካከል አንዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሰየም በመሆኑ፣ በዚህ መሠረት የአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ አቶ ወንድወሰንን በዕጩነት በማቅረብ የብሔራዊ ባንክን ምላሽ ሲጠባበቅ ነበር፡፡

በፋይናንስ ተቋማት የቦርድ አመራሮች ተመርጠው በዕጩነት የቀረቡ አመራሮችን የማፅደቅና የመሻር መብት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ አቶ ወንድወሰን የሪኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲሠሩ ውሳኔ ያሳለፈው ባለፈው ሳምንት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ለኢንሹራንስ ኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለመሰየም ኩባንያው በምሥረታ ወቅት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቢቆይም፣ ሳይሳካለት እንደቀረ አደራጅ ኮሚቴው አስታውቆ ነበር፡፡

በኩባንያው መሥራች ጉባዔ ላይም ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን መሥፈርት ሊያሟላ የሚችል ተሿሚ ባለመገኘቱ ለኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለመቅጠር አለመቻሉን ጥቅምት 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የኩባንያው ምሥረታ ጉባዔ ላይ መገለጹ ይታወሳል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ ወንድወሰን እስካሁን ድረስ ስለአዲሱ ሥራ የደረሳቸው ደብዳቤ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በዛሬው ዕለት (ረቡዕ ግንቦት 16 ቀን 2008 ዓ.ም.) የሪኢንሹራንስ ቦርዱ የሚሰበሰብ በመሆኑ፣ ‹‹ሹመቱ ፀድቆ ከሆነ መረጃውን ላገኝ እችላለሁ፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ምንጮች ግን ብሔራዊ ባንክ ሹመቱን ማፅደቁንና ይህንንም የሚገልጽ ደብዳቤ ለኩባንያው የሚደርስ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

አቶ ወንድወሰን የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ከአምስት ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ ወደ አዲሱ ሥራ የሚዛወሩ ከሆኑ ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ይሰየማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ ባለፈው ጥቅምት 2008 ዓ.ም. በይፋ የተመሠረተ ሲሆን፣ በዋናነት የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለአክሲዮን በማድረግ እስከ ሰኔ 2007 ዓ.ም. ድረስ 669 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ የተቋቋመ ነው፡፡ የተፈቀደ ካፒታሉ ደግሞ አንድ ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ጥቂት ባንኮችም በኩባንያው ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 200 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን በመግዛት ከፍተኛ ባለአክሲዮን ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ አንድ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያ ወደ ሥራ ለመግባት የተከፈለ ካፒታሉ 500 ሚሊዮን ብር መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እስካሁን ከውጭ የጠለፋ ሰጪ ኩባንያዎች ሲያገኙ የነበረውን አገልግሎት በአገር ውስጥ በተቋቋመው የኢንሹራንስ ኩባንያ እንዲጠቀሙ የሚያስችለው የሪኢንሹራንስ ኩባንያ፣ ወደ ሥራ ለመግባት የብሔራዊ ባንክን ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ አገልግሎት ከተጀመረ ከ100 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ የቆየው ይህ ኢንዱስትሪ እስካሁን ድረስ የጠለፋ ዋስትና ሽፋን ሲያገኝ የቆየው ከውጭ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያዎች ነው፡፡ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጠለፋ ዋስትና ሽፋን ለማግኘት ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያዎች በየዓመቱ ከፍተኛ የሆነ ክፍያ ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓመት ከሚሰበስቡት ዓረቦን (ፕሪሚየም) እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ለጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሪ ይከፍላሉ፡፡ አዲሱ የሪኢንሹራንስ ኩባንያ መመሥረት ግን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይወጣበት የነበረውን አገልግሎት በአገር ውስጥ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

በአገሪቱ አንድ መንግሥታዊና 16 የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ገበያው ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ባለፈው ዓመት የሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዓመታዊ ዓረቦን መጠን 5.6 ቢሊዮን ብር መድረሱ ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች