ነጋዴዎችና የመንግሥት ሹማምንት በሕገወጥ ተግባሩ ተሳትፈዋል ተብሏል
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ወረገኑ አካባቢ የተጀመረው ሕገወጥ የተባሉ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ፣ በዚህ ሳምንት ቀጥሎ በርካታ ቤቶች እየፈረሱ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‹‹የከፋ የመሬት ወረራ›› ባለው የወረገኑ መንደር፣ ሕገወጥ የተባሉ ግንባታዎችን ለማፍረስ በርካታ የፀጥታ ኃይሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በዕለቱ ወደ ሥፍራው ሲያመራ፣ ግንባታዎች ሊፈርሱ አይገባም የሚል አቋም ካላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር የከረረ ግጭት ተከስቷል፡፡
በዚህ ግጭት እስካሁን ሪፖርት የተደረገው አራት ፖሊሶችና 12 የአካባቢው ነዋሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውና 200 ሰዎች ደግሞ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ነው፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት አስናቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአካል ጉዳት በስተቀር ምንም ዓይነት ሞት አላጋጠመም፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥም ማጣራት ተደርጎ 38 ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመሥረት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ወረገኑ እየተባለ የሚጠራው መንደር በወረዳ 12 ከገርጂ በታች ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጀርባ፣ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ የሚወስደው የፍጥነት መንገድ ቀጣይ ክፍል ከሆነው የጎሮ መንገድ ወዲህ ከቦሌ ቡልቡላ ጎን የሚገኝ መንደር ነው፡፡
ይህ መንደር በአጠቃላይ 52 ሔክታር ስፋት ያለው ሲሆን፣ በአቅራቢያው ከሚገኘው ሰፋፊ ቦታዎች ጋር ለሦስት ፕሮጀክቶች ዕጩ የተደረገ ነው፡፡ ፕሮጀክቶቹ የሕዝብ መናፈሻ፣ የጎልፍ መጫወቻ ቦታና የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ናቸው፡፡ የሕዝብ መናፈሻ በአጠቃላይ 450 ሔክታር መሬት ይፈልጋል፡፡ የመናፈሻው አንዱ ክፍል እስከ ወረገኑ መንደር የሚዘልቅ መሆኑ ታውቋል፡፡
ለጎልፍ መጫወቻ የተመደበው 450 ሔክታር መሬት ነው፡፡ ባለቤትነቱ የመከላከያ ሚኒስቴር የሆነውና በአዲስ አበባ አሮጌ አውሮፕላን ማረፊያ የሚገኘው ጎልፍ ክለብ፣ በዚህ ቦታ ላይ ዘመናዊ የጎልፍ መጫወቻ ለመገንባት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት ማግኘቱ ታውቋል፡፡ ለጎልፍ ክለብ ከተመደበው ቦታ የተወሰነው መሬት በወረገኑ መንደር የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ 318 ሔክታር ለማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ተፈቅዶለታል፡፡ ከዚህ መሬት ውስጥ የተወሰነው በወረገኑ መንደር የሚገኝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የፀጥታ ክልል ነው ተብሎ በአካባቢው የመሬት ምሪት ባይካሄድም፣ ኅብረተሰቡ ባለው የመኖርያ ቤት ችግር ምክንያት መኖርያ ቤት መገንባቱ አልቀረም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሦስት ሺሕ ያህል ቤቶች በመንደሩ መገንባታቸውን ይናገራል፡፡
አቶ ታምራት ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የወረገኑ መንደር መፍረስ ከመጀመሩ በፊት ጥናት ተካሂዷል፡፡ በዚህ ጥናት በአብዛኛው በሕገወጥ መንገድ መኖርያ ቤት እየገነቡ የሚኙት ነጋዴዎች፣ የፋብሪካ ባለቤቶች፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ ያልሆኑ ከተለያዩ ሥፍራዎች የመጡ ሰዎች፣ የመንግሥት ሹማምንትና የፀጥታ ኃይሎች ናቸው፡፡
‹‹ይህ ሁኔታ ለሕገወጥ ቤተ ሠሪዎች የልብ ልብ ሰጥቷል፤›› በማለት አቶ ታምራት ገልጸው፣ ‹‹የወረገኑን ሕገወጥ ግንባታም ልዩ የሚያደርገው ይኼው ነው፤›› በማለት ቤቶቹን የማፍረስ ሒደቱ ፈታኝ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በመጀመርያ ያደረግነው ሰው ያልገባባቸውን 950 ቤቶች ማፍረስ ነበር፡፡ ይህንንም አድርገናል፤›› ያሉት አቶ ታምራት፣ ‹‹ከዚያም ቀጣዮቹን ሕገወጥ ቤቶች ማፍረስ ቀጥለናል፤›› ብለዋል፡፡
መንግሥት ከወዲሁ መኖሪያ ቤቶቹ በሚፈርሱበት ጊዜ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች አራሶች ሊኖሩ ስለሚችሉ መጠለያ፣ ሕክምናና ምግብ አዘጋጅቶ ወደ ማፍረስ መግባቱን አቶ ታምራት ገልጸው፣ በአካባቢው ዳግመኛ ሕገወጥ ግንባታዎች እንዳይካሄዱ ለማድረግ ፈቃድ የሌላቸውን የአጠና መሸጫና የንግድ ቤቶችን ማፍረሱን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በወረገኑ በርካታ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀላቸው ለከፍተኛ ሐዘን መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ በርካቶች ላስቲክ ወጥረው ከወቅቱ ዝናብና ቁር ለመጠለል ሲሞክሩ፣ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ዕቃቸውን ጠቅልለው ከመንደር በመውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡
አቶ ሲሳይ መኮንን የወረገኑ የወቅቱ ችግር ገፈት ቀማሽ ናቸው፡፡ አምስት ቤተሰብ ያላቸው አቶ ሲሳይ፣ በ2003 ዓ.ም. ከአካባቢው አርሶ አደር 80 ካሬ ሜትር ቦታ በ15 ሺሕ ብር ግዢ ፈጽመው መኖርያ ቤት ቀልሰው ኑሮአቸውን ጀምረው ነበር፡፡
በቀን ሥራ እንደሚተዳደሩ የሚናገሩት አቶ ሲሳይ በ2005 ዓ.ም. አስተዳደሩ ቤታቸውን በግብረ ኃይል ቢያፈርሰውም፣ በስህተት የፈረሰ መሆኑ ተረጋግጦ በድጋሚ መኖርያቸውን ሠርተው ኑሮአቸውን ቀጥለው እንደነበር አስረድተዋል፡፡
አሁን ግን መኖርያ ቤታቸው ተመልሶ ላይሠራ በመፍረሱ ተስፋ መቁረጣቸውን ገልጸው፣ ዕቃዎቹን በላስቲክ ቤት አድርገው ቤተሰባቸውን ደግሞ ወዳጅ ዘመድ ቤት ይዘው መጠለላቸውን ተስፋ በቆረጠ ስሜት ተናግረዋል፡፡
አቶ ታምራት ይህ ወቅት የተመረጠበትን ምክንያት ሲገልጹ ትንሽ ከቆየ ክረምት እንደሚገባ፣ በክረምት ቤት ማፍረስ ደግሞ አይቻልም ይላሉ፡፡ በጋ ይውጣ ከተባለ ደግሞ ልጆች ትምህርት ጀመሩ ስለሚባል ያለው ጊዜ ይህ ብቻ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 12 በተጨማሪ በወረዳ ዘጠኝ፣ በወረዳ አሥርና በወረዳ 11 የሚገኙና ሕገወጥ ያላቸውን ግንባታዎች በቀጣይ እንደሚያፈርስ አቶ ታምራት አስታውቀዋል፡፡