Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ የወሰነውን ፌዴሬሽን ምክር...

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ የወሰነውን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ውድቅ አደረገው

ቀን:

የሕገ መንግሥት ትርጉም የማያስነሳና በአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ መታየት የሚችል ነው ብሏል

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በሐምሌ ወር 2007 ዓ.ም. በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ለተነሳው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የሰጠውን ውሳኔ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውድቅ በማድረግ፣ ቀድሞውንም ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የማያስነሳ ነው ሲል ውሳኔ ሰጠ፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ (10 ሰዎች) የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም የይግባኝ ጥያቄ መርምሮ፣ ውሳኔውን ለምክር ቤቱ ሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የተመለከተው ይግባኝ መነሻ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት እነ አቶ መላኩ ፈንታ በተጠረጠሩባቸው የሙስና ወንጀል ሁለት የክስ መዝገቦች የተዘረዘሩ ክሶች፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ጉዳዩን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. በመጠየቁ እንደሆነ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ፍርድ ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም የጠየቀበት መሠረታዊ ጭብጥም የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 60/89፣ 368/95፣ 622/2001 እና የወንጀል ሕጉን በመጥቀስ፣ እነ አቶ መላኩ ፈንታ (10 ሰዎች) ሥልጣንን ያላግባብ በመገልገል ዕቃዎች እንዳይመረመሩ ማድረግ፣ ገደብና ቁጥጥር የሚደረግባቸውን ዕቃዎች (መድኃኒቶች) በማስገባት ክስ አቅርቦባቸው ጉዳያቸው በመታየት ላይ እንዳለ አዲስ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 በመውጣቱ ነው፡፡

አዲሱ የጉምሩክ አዋጅ ነባር የጉምሩክ አዋጆችን ሙሉ በሙሉ ከመሻሩ ባለፈም፣ ከላይ በተከሳሾቹ ላይ የተመሠረቱት ክሶች በአዲሱ ሕግ መሠረት ወንጀልነታቸው እንዲቀር አድርጓል፡፡

በዚሁ አዲስ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 የመሸጋገሪያ ድንጋጌ ላይ ደግሞ ‹‹በሌሎች ሕጐች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ አዲሱ አዋጅ ከመፅናቱ በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች በነባሩ ሕግ መሠረት ፍፃሜ ያገኛሉ፤›› የሚል ድንጋጌ ማስቀመጡ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 2 እና የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 5(3) ላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች ጋር እንደሚቃረን ይገልጻል፡፡

የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 22(2) እና የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 5(3) የሚደነግጉት የወንጀል ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው የሚጠቅም ሆኖ ከተገኘ፣ ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ አንቀጽ 182 (የተጀመሩ ጉዳዮች በነበረው ሕግ መሠረት ፍፃሜ ያገኛሉ) ድንጋጌ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) እና ከወንጀል ሕጉና (3) ጋር የሚቃረን በመሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል የሚል ጥያቄውን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አቅርቦ ነበር፡፡

በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰብሳቢነትና በሌሎች የሕግ ባለሙያዎች የተዋቀረው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ግን አዲሱ የጉምሩክ አዋጅ በመሸጋገሪያ ድንጋጌው አንቀጽ 182 ላይ፣ ‹‹በሌሎች ሕጐች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ አዋጅ ከፀናበት ቀን በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች በነበረው ሕግ መሠረት ፍፃሜ ያገኛሉ፤›› በማለት በግልጽ ተከሳሾችን በዚህ አዋጅ እንዳይጠቀሙ ያደገ በመሆኑ፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 (2) ጋር አይቃረንም የሚል ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡

‹‹የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 (2) ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚነት ይኖረዋል በማለት የተደነገገው፣ የሚሠራው አዲሱ አዋጅ ተከሳሾችን እንዲጠቅም ያደረገ ከሆነ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ አዲሱ አዋጅ ተከሳሾች እንዲጠቀሙ ያላደረገ በመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 (2) ጋር አይቃረንም፤›› በማለት የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስነሳም ሲል ወስኗል፡፡

ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቋሚ ኮሚቴው በኩል እንዲታይ ያደረገ ሲሆን፣ ቋሚ ኮሚቴውም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሁራንን በመጋበዝ ሙያዊ አስተያየታቸውን በማዳመጥ የደረሰበትን የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ለደረሰበት ውሳኔ ሁለት ትንታኔዎችን የሰጠ ሲሆን፣ አንደኛው አዲሱ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 የተደነገገው ከሕገ መንግሥቱ ተቃርኖ ተከሳሾችን ተጠቃሚ ያለማድረግ ዓላማ ይዞ አለመሆኑን፣ ለዚህም ሕጉ በግልጽ ተከሳሽን የሚጠቅም ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም ወይም በማናቸውም ሁኔታ ነባሩ ሕግ ተግባራዊ ይሆናል እንደማይል ሁለተኛው ትንታኔ ደግሞ በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 182 በሌሎች ሕጐች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የሚለው ሐረግ የሚጠቁመው፣ የወንጀል ሕጉ መርህ ብሎ ያስቀመጠውን አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 3 እንደሆነ ገልጿል፡፡

‹‹የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 5 (3) የያዘው ሐሳብ ተከሳሽን የሚጠቅሙ ድንጋጌዎች በኋለኛው ሕግ ካሉ ተፈጻሚ ይሆናሉ ወይም ተከሳሽን የማይጠቅሙ ከሆነ ግን፣ በነበረው ሕግ መሠረት ይቀጥላል የሚለውን እንደሆነ መረዳት እንደሚቻል፣ ይህ የወንጀል ሕግ ድንጋጌ ለወንጀል ጉዳዮች እንደ መነሻና መርህ የሚያገለግል እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም እንኳ ሕገ መንግሥቱ ራሱን ችሎ የሚቆም የበላይ ሕግ በመሆኑ መጠቀስ ባያስፈልገውም፣ በሌሎች ሕጐች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የሚለው ድንጋጌ ሐሳብ ሰፋ ባለ ትርጉም ሲታይ የሕገ መንግሥቱንም ድንጋጌ ሊያሳይ ይችላል፤›› የሚል ትንታኔ ሰጥቷል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች በአዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 የተደነገገው የመሸጋገሪያ ድንጋጌ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 (2) ጋር የሚቃረን ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን የሚጠቅሙ ወይም ወንጀልነታቸው በአዲሱ ሕግ ቀሪ የሆኑ ደርጊቶችን በመለየት የሕግ ትርጉም ሊሰጥባቸው እንደሚችል በመግለጽ፣ በይግባኝ የቀረበው ጥያቄ የሕገ መንግሥት ትርጉም የማያስነሳ መሆኑን የሚገልጽ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተቸገረበትና የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበበት ምክንያት፣ ተከሳሾቹ እነ አቶ መላኩ በመዝገብ ቁጥር 141352 እና 141356 የቀረቡባቸው ክሶች በአዲሱ አዋጅ ወንጀልነታቸው የቀረ በመሆኑ ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ በሁለቱ መዝገቦች የቀረቡባቸውን ክሶች በአዲሱ አዋጅ የሚመለከት ከሆነና ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ከተባሉ የሚጣልባቸው ቅጣት በገንዘብ ብቻ ይሆናል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...