Thursday, June 13, 2024

ከተመዘገቡ ስኬቶች እኩል ጉድለቶችም ይታዩ!

ኢሕአዴግ ደርግን ያስወገደበትን 25ኛውን የብር ኢዮቤልዮ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ ይገኛል፡፡ ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣን ይዞ የቆየባቸውን እነዚህን ዓመታት ሲዘክር፣ በኢኮኖሚው መስክ የተገኙት ስኬቶች ከምንም ነገር በላይ እየተስተጋቡ ነው፡፡ በማኅበራዊው መስክ የተገኙ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን በፖለቲካው መስክ በጣም በብዙ፣ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ መስክ እዚህም እዚያም የሚታዩ ጉድለቶች መፈተሽ አለባቸው፡፡ የግንቦት 20 ድል ያስገኛቸው ትሩፋቶች ተዘርዝረው እንደማያልቁ ሲገለጽ፣ ጉድለቶችም የዚያኑ ያህል መሆናቸው መተማመን ሊኖር ይገባል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በአገሪቱ መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦች መታየታቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡ እነዚህ ለውጦች ግን ስኬትንም ጉድለትንም አጣምረው የያዙ ናቸው፡፡ ዋና ዋናዎቹን እንያቸው፡፡

አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመመሥረት በተደረገው ጉዞ የብሔርና ብሔረሰቦችን መብት በማስከበር፣ በአገር ልማት በጋራ ለማሳተፍ የተደረገው ጥረት መልካም ነው፡፡ ብዝኃነትን አክብሮ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ ተሳትፎን ለማጠናከር ጅምሮች ታይተዋል፡፡ ነገር ግን የተኬደበት ርቀት ግን ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ በተለይ ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር፣ የመዳኘትና የመሳሰሉት ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ሥራ ላይ ቢውሉም፣ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት በሕገ መንግሥቱ መሠረት መስተናገድ አልቻለም፡፡ ገዥ ከሆነው አንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውጪ ያለው አመለካከት ባለመፈለጉ ምክንያት የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቧል፡፡ በየጊዜው አቤቱታ የሚቀርብበት የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ መሻሻል አላሳየም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ ሲቪክ ተቋማት ተዳክመዋል፡፡ ዴሞክራሲ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በተግባር ማየት አልተቻለም፡፡ ብዙዎቹ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት ተፈረካክሰዋል፡፡ ይኼ ትልቁ የአገር ችግር ነው፡፡ ተቃራኒ ሐሳቦች መስተናገድ ያልቻሉበት ወቅት ላይ ነው ያለነው፡፡

አገሪቱ በኢኮኖሚው መስክ እያስገኘችው ያለው የዕድገት ግስጋሴ የሚደነቀውን ያህል፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ረገድ ትልቅ ነቀፌታ በዓለም ዙሪያ ይሰማል፡፡ ለዘመናት የነበረው የአገር ችግር እየተጠቀሰ ዴሞክራሲው እንደሚያድግ ቃል ቢገባም፣ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አይታይም፡፡ ዋናው ጉዳይ የአገሪቱ ሰላም አስተማማኝ ሆኖ የሚቀጥለው ዴሞክራሲ ሲሰፍን፣ ሰብዓዊ መብት ሲከበር፣ የአመለካከት ብዝኃነት ሲረጋገጥና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታው መሠረት እንዲይዝ ሲደረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕዝብ ተሳትፎ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ በአገር ልማት የባለቤትነት ስሜት የሚዳብረው ዜጎች በአገራቸው በነፃነት የመሰላቸውን አመለካከት የማንፀባረቅ ባህል ሲዳብር ነው፡፡ ዋናው ትግል መሆን ያለበትም በሰላም፣ በዴሞክራሲና በብልፅግና ውስጥ የምትገኝ አገር እየተፈጠረች መሆኑን ማሳየት እንጂ፣ በየጊዜው ተስፋ የሚያስቆርጡ ድርጊቶች ውስጥ መሰማራት አይደለም፡፡

በዚህ ዘመን በስኬት ከሚወሱ ተግባራት መካከል ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ትግል እየተመዘገበ ያለው ውጤት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር ትኩረት የሳበው ይህ ስኬት ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን ቢያሳይም፣ አሁንም ለዘመናት አገሪቱን ከሚታገለው ድርቅ ለመላቀቅ አልተቻለም፡፡ የተፈጥሮ ሚዛን ባስነጠሰው ቁጥር ድርቅ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን የሚላስ የሚቀመስ እያሳጣቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለዕለት ዕርዳታ ፈላጊነት ተጋልጠዋል፡፡ በዓለም ፊት ለበርካታ ዓመታት መሳቂያና መሳለቂያ ያደረገን ድርቅ በአየር ንብረት መዛባት እየተሳበበ መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ብዙዎቹ ተፈጥሮ የበደላቸው አገሮች ተፈጥሮን ገርተው በብልፅግና ማማ ላይ ሆነው ቁልቁል እያዩን፣ እኛ የአየር መዛባትን መቆጣጠር አለመቻላችን ሊያሳፍረን ይገባል፡፡ ተፈጥሮን ተቆጣጥሮ መልማት ፈጣሪን እንደ መካድ ተቆጥሮ የሚተውት ሳይሆን፣ ከኃፍረት የመገላገል ዕርምጃ መሆን አለበት፡፡ ተስማሚ የአየር ንብረት፣ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የውኃ ሀብት፣ ከ70 በመቶ በላይ ወጣት ኃይል ይዞ መራብና ለልመና አደባባይ መውጣት የአገር ጉድለት ነው፡፡ ይኼ በራሱ አንገት የሚያስደፋ ውርደት ነው፡፡

በሌላ በኩል ከኢኮኖሚ ዕድገቱ የሚጠቀመው ሕዝብ ነው? ወይስ ሌላ? በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ የተለያዩ ልማቶች ይካሄዳሉ፡፡ የልማቱ ውጤት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው የሚከፋፈለው? ወይስ ብዙኃን እየተገለሉ ጥቂቶች ናቸው የሚጠቀሙት? ለዚህ ቀላል ማሳያ የሚሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሀብት ወደ ሀብት ከፍተኛ የሆነ ሽግግር የሚያደርጉ ወገኖች አሉ፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ ግን በኑሮ ውድነት ይጠበሳል፡፡ ከሚያገኘው እዚህ ግባ የማይባል የወር ገቢ ለቤት ኪራይም ለምግብም የማይበቃው ብዙኃኑ ሠርቶ አደር ሕዝብ ከልማቱ እንደ አስተዋጽኦው ተጠቃሚ ካልሆነ፣ ለልማቱ እንዴት የባለቤትነት መንፈስ ይኖረዋል? በሙስና የሚበለፅጉ አልጠግብ ባዮች በሚፈለፈሉበት በዚህ ዘመን፣ ብዙኃኑ ሕዝብ ከኑሮ ጋር ሲታገል እንዴት ስለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል መነጋገር ይቻላል? ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ይህንን ያህል ደርሷል ተብሎ በአኃዝ ሲጠቀስ፣ ቢያንስ አመዛኙ ሕዝብ በተነፃፃሪ ከኢኮኖሚው ተጠቃሚነቱ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ አገሪቱ መካከለኛ ደረጃ ካላቸው አገሮች ተርታ ትሠለፋለች ሲባል ምልክቶቹ በደንብ መታየት መጀመር አለባቸው፡፡ አለበለዚያ በዕቅድ ተይዘው እንዳልተሳኩ ፕሮጀክቶች አንገት ያስደፋል፡፡

ኢሕአዴግ ያለፉትን 25 ዓመታት ሲዘክር ራሱን ጥሎት ከመጣው ደርግና ተገንጥላ ከሄደችው ኤርትራ ጋር ያወዳድራል፡፡ ደርግ በ17 ዓመታት ቆይታው ወቅት ያለፈበትን ጎዳና ከአሁኑ ጋር በማነፃፀር የሚደረገው ውድድር ለዚህ ዘመን አስተሳሰብ የሚመጥን አይደለም፡፡ አንዳንዴ ወደኋላ እየተሄደም ከአፄዎቹ ሥርዓቶች ጋር ንፅፅር ውስጥ ሲገባ ያሳቅቃል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ሌላው ቀርቶ የይስሙላ ምርጫ፣ ፓርላማ፣ ተቃዋሚ ፓርቲና የግል ፕሬስ ከሌላት የአፍሪካ አኅጉር እስር ቤት ከሆነችው ኤርትራ ጋር የሚደረገውም ውድድር አገሪቱን ፈጽሞ አይመጥናትም፡፡ ይልቁንም በዴሞክራሲ ከዳበሩና በኢኮኖሚ ዕድገት አርዓያ ከሆኑ የአፍሪካም ሆነ ሌሎች አገሮች ጋር መወዳደርና እኩያ መሆን ይጠቅማል፡፡ አዲሱ ትውልድ በዚህ እጅግ በጣም በቴክኖሎጂ እያደገ ያለ ዘመን ውስጥ ሆኖ የጨለማ ተምሳሌት ከሆኑ ነገሮች ጋር መነፃፀርም አይፈልግም፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ እየሆነ ካለው አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ ድርሻ ያላቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና ተምሳሌት የሆነች አገር እንድትኖራቸው ነው የሚፈልጉት፡፡ ለአምባገነንነትማ በአፍሪካም ሆነ በእስያ፣ በአውሮፓም ሆነ በላቲን አሜሪካ ወደር የሌላቸውን ከታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ያገኛቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት ጥቀርሻ ሆነው ያስቸገሯትን ችግሮች ለመገላገል ብሔራዊ መግባባት ሊኖራት ይገባል፡፡ በአገር ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ተሳትፎአቸው ሳይገደብ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መበረታታት አለባቸው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዜጎች በአገራቸው ጉዳዮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ሲደረግ የፈለጉትን አመለካከት ይዘው መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ ዕውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ገንዘባቸውንና የመሳሰሉትን ይዘው በአገር ልማት እንዲሳተፉ ይረዳቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕግ መከበር አለበት፡፡ ከድሮ ጀምሮ የአስፈጻሚው አካል ከሕግ በላይ የመሆን አባዜ ሊገታ ይገባል፡፡ ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው አንዱ ሌላውን እየተቆጣጠረና እየተናበበ መሄድ አለበት፡፡ የአስፈጻሚው ጡንቻ በበረታ ቁጥር እንኳን ብሔራዊ መግባባት ሊኖር በዓይን መተያየትም አይቻልም፡፡ አገር የምታድገውና የምትበለፅገው ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ የባለቤትነት ስሜት ሲኖራቸው ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋስትናው የሕግ የበላይነት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን ያስወገደበት 25ኛ ዓመት ሲያከብር ከስኬቶቹ እኩል ጉድለቶቹንም ይመልከት!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...