Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ሚኒስቴር የአለ በጅምላና የምርት ገበያ ኃላፊዎች ላይ ክስ ሊመሠርት ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የንግድ ሚኒስቴር የሕግ ጥሰትና ፀረ ውድድር የሆኑ ተግባራትን ፈጽመዋል ባላቸው በሥሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎችና ፈጻሚዎች ላይ፣ ከሥራ የማገድና በዋና ዋና ኃላፊዎች ላይ ደግሞ ክስ ለመመሥረት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በተለይ ክሱ በዋናነት ይመሠረትባቸዋል ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመው የአለ በጅምላ (የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት) ኃላፊዎች፣ አሥር የሚደርሱ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አመራሮች፣ እንዲሁም የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አመራሮችና ፈጻሚዎች እንደሚገኙበት የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ያዕቆብ ያላ ማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነበር ያስታወቁት፡፡

ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ፀረ ውድድር የሆኑ ተግባራትን ለማክሰምና የሸማቾችን ጤንነትና ደኅንነት ለማስጠበቅ በንግዱ ዘርፍ የሚታዩትን ያልተገባ የንግድ ተግባራትን ለመከላከል፣ የሸማቾችን መብት በመጋፋት የሕግ ጥሰት በፈጸሙ የአመራር አካላትና ነጋዴዎች ላይ የዕርምት ዕርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የአለ በጅምላ የበላይ ኃላፊዎች የሕግ ጥሰት መፈጸማቸው በመረጋገጡ ከኃላፊነታቸው የታገዱ ሲሆን፣ ‹‹በቅርቡ ክስ እንመሠርታለን፤›› ሲሉ አቶ ያዕቆብ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ኃላፊዎችን በስምም ሆነ አጠቃላይ ብዛታቸውን ባይገልጹም፣ ለዕግድ የበቁበት ጉዳይም ከግንባታ ሥራና ከግዢዎች ጋር እንደሚገናኝ አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ግንባታውንም ሆነ ግዢውን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም፡፡

ታግደዋል ከተባሉት አመራሮች ውስጥ ድርጅቱ ሲቋቋም ጀምሮ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩትና በቅርቡ ወደ ሚኒስቴሩ የተመለሱትን አቶ ኑረዲን መሐመድን ይጨምር አይጨምር አቶ ያዕቆብ አልገለጹም፡፡ ሪፖርተርም ይህ ጉዳይ ይመለከታቸው ከሆነ አቶ ኑረዲንን የጠየቃቸው ሲሆን፣ ‹‹እኔ ወደ ቀድሞ መሥሪያ ቤቴ መዘዋወሬን እንጂ ታግደዋል ከተባሉት ውስጥ አለመኖሬን መቶ በመቶ አረጋጋጣለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይም ቁጥራቸው አሥር የሚደርስ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አመራሮች በፀረ ውድድር አሠራር ለውጭ ገበያ ሊቀርብ የሚገባን ቡና ነጋዴዎች ለአገር ውስጥ ገበያ በሕገወጥ እንዲያቀርቡ በመተባበርና በማመቻቸት ዕገዛ ሰጥተዋል የተባሉ አመራሮችን እንዲሁ ማገዱን፣ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ሚኒስቴሩ ዝግጅት ላይ መሆኑንም አቶ ያዕቆብ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚደረገው የግብይት ሒደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማጥራት በተደረገው ጥረት፣ 24 የገበያው አባል የሆኑና ወንበር ያላቸው ነጋዴዎች ከግብይት መድረኩ ኦፊሰሮች ጋር በመመሳጠር አድራሻቸው ለማይታወቅና አንዳንዶቹም የቡና ላኪነት ፈቃድ ለሌላቸው 54 ግለሰቦች የኤክስፖርት ቡና ገዝተው እንዲሰወሩ በማድረጋቸው ከምርት ገበያው ከአባልነት ታግደው ለሕግ እንዲቀርቡ ተደርጓል፤›› ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

እንዲሁም በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመሥርተው የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ተቀብለው ለሕግ በማቅረብ ፋንታ፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ፋይሎችን የመዝጋትና በድርድር የመጨረስ ተግባር ሲፈጽሙ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ባለሥልጣን አመራሮችና ፈጻሚዎችን መገኘታቸውንም ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በእነዚህም አመራሮችና ፈጻሚዎች ላይ በተደረገው ግምገማ በመረጋገጡ ዝርዝር መረጃውን በተጨባጭ የመለየት ዕርምጃ መውሰድ እንዲቻል፣ ኮሚቴ ተቋቁሞ በማጣራት ላይ መሆኑንም ጨምረው አቶ ያዕቆብ አስረድተዋል፡፡

ከተጠሪ ተቋማት በተጨማሪም በራሱ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውስጥ በሚገኙ አመራሮችም በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት በተሳተፉ ላይም ተመሳሳይ ዕርምጃ መወሰዱንም አቶ ያዕቆብ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት የቀረበውን የዋና ኦዲተር ሪፖርት በመጥቀስ በገቢና ወጪ ዕቃዎች ላይ በሚደረጉ የጥራት ቁጥጥር፣ በባለሙያዎች በላብራቶሪ ዝቅተኛና ከስታንዳርድ ያነሰ ጥራት አለባቸው ተብሎ እንዲታገዱ የተወሰነባቸውን ዕቃዎች ከሕግ አግባብ ውጪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በደብዳቤ እንዲያልፉ ማድረጉን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር፡፡

ነገር ግን ሚኒስትሩ የዋና ኦዲተርን ግኝት በተመለከተ በቀጥታ መልስ ከመስጠት ይልቅ፣ በወጪና በገቢ ዕቃዎች ላይ ሚኒስቴሩ እያከናወነ ስላለው የጥራት ፍተሻና የቁጥጥር ተግባራትን በዝርዝር ማስረዳት መርጠዋል፡፡

ምንም እንኳ የጥራት ደረጃ ምዘና፣ ቁጥጥር እንዲሁም የፍተሻ ሥራውን የሚያካሂደው ተቋም ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በቀጥታ ተጠሪ ባይሆንም፣ በንግድ ዕቃዎች ላይ ሊኖር የሚገባውን የጥራት ጉዳይ የማረጋገጥም ሆነ የመቆጣጠር ኃላፊነት ስላለበት፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር ‹‹የተለየ ትኩረት›› ሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አቶ ያዕቆብ ገልጸዋል፡፡

በገቢም ሆነ በወጪ ዕቃዎች ላይ የሚደረገው የጥራት ደረጃን የማስመርመር ተግባር እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን፣ በነጋዴዎችም በኩል አብሮ መሥራቱና መግባባቱ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ማስገባትና ማስወጣት በመፈለግ፣ ወይም ደግሞ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቅሬታ ሊሰማ ይችላል ሲሉ አቶ ያዕቆብ አስረድተዋል፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚደረገው ቁጥጥር እየተሻሻለ ቢመጣም፣ ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ገና አለመቻሉን ከጠቀሱ በኋላ ከደረጃ በታች የወረደ ምርት ወደ ውጭ የመላኩ ዕድል ግን ጠባብ ነው ሲሉ አቶ ያዕቆብ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለዚህም አገሪቱን ከዚህ በፊት ዋጋ አስከፍሏታል፤›› በማለት ክስተቶችን በመጥቀስ ዘርዝረዋል፡፡ ለአብነት ከጥራት ደረጃ መውረድ ጋር ተያይዞ ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ሩሲያ ተልኮ የነበረ ስድስት ኮንቴይነር ቦሎቄ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሞሮኮ ተልኮ የነበረ ሁለት ኮንቴይነር ዝንጅብል፣ እንዲሁም ወደ ጃፓን ተልኮ የነበረ ብዛት ያለው ቡና ወደ አዲስ አበባ መመለሱን አንስተው አስረድተዋል፡፡

ይልቁንም በአሁኑ ጊዜ ችግር የሆነው የገቢና የወጪ ምርትን ሳይሆን፣ አንዳንድ የመንግሥትም ተቋማትም ሆኑ የግል ኩባንያዎችን ምርትን ሳያስመረምሩ ማስገባትም ሆነ ማስወጣት እንዳለባቸው የሚናገሩ መኖራቸውን አቶ ያዕቆብ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በተለይ በመንግሥት ለሚገነቡ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚውሉ ዕቃዎች ሳይመረመሩ እንዲገቡ የሚፈልጉ አስፈጻሚ ድርጅቶች አሉ፡፡ ነገር ግን የግድ መመርመር አለብን ብለን እየመረመርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ለአብነት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከውጭ የሚገቡ የብረት ዓይነቶችን ጨምሮ በእነሱ በኩል ጥራታቸውን የፈለገ አረጋግጠው ቢገቡ በራሳችን መርምረን ካላረጋገጥን፣ ከመጋዘን መውጣት የለባቸውም የሚል አቋም ይዘን እየሠራን ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የወጪ ዕቃዎችንም አስመልክተው ሚኒስቴሩ ባብራሩበት ወቅትም፣ ስሙን ያልጠቀሱትን በአገሪቱ አሉ ከሚባሉ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነውን ጉዳይም በተመለከተ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

‹‹አንድ የውጭ ባለሀብት ትልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካ ገንብቶ ሳይፈተሽ ወደ ውጭ ምርቱን እንዳይላክ ከልክለናል፡፡ ይህ ፋብሪካ በምርቱ ጥራት በዓለም ታዋቂ ቢሆን እንኳ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረተ ዕቃ ወደ ውጭ ተልኮ ጥራቱ ችግር ቢኖርበት አገሪቷ ላይ የሚያመጣው ጦስ ቀላል እንደማይሆን ስለምናውቅ፣ ምንም ዓይነት ነገር ሳንፈትሽ እንዲወጣ አናደርግም፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

የወጪ ንግድ ዘርፍን በተመለከተ በሪፖርታቸው ከወጪ ንግድ ዘርፍ ከዕቅዱ በታች የሆነ አፈጻጸም መመዝገቡን፣ ለዚህም ምክንያት ያሏቸውን ዋና ዋና ችግሮች አቅርበዋል፡፡

በኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ምርታቸውን በብዛትና በጥራት በማምረት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ፣ በዘጠኝ ወራት በአጠቃላይ ከሁሉም ዘርፎች 2.91 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 2.053 ቢሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 70.46 በመቶ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ከግብርና ምርቶች 1.95 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 1.54 ቢሊዮን ዶላር (79 በመቶ)፣ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 508.06 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 258.58 ሚሊዮን ዶላር (51 በመቶ) እና ከማዕድን ዘርፍ 458.38 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 223.43 ሚሊዮን ዶላር ወይም 48.5 በመቶ ተገኝቷል፡፡ ይህ አጠቃላይ የኤክስፖርት አፈጻጸም ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 2.18 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ129.21 ሚሊዮን ዶላር (5.92 በመቶ) ቅናሽ ማሳየቱንም አቶ ያዕቆብ ተናግረዋል፡፡ የቅናሹ ምክንያቶችም በዓለም ገበያ ላይ ያለው የግብርና ምርቶች ዋጋ መቀነስና የፍላጎት ማነስ፣ የግብርና ምርቶችን አቅርቦትን በጥራትና በመጠን ያለማሳደግ፣ ለአምራች ኢንዱስትሪው የግብዓት አቅርቦትና የጥራት ችግር መኖር፣ የአገር ውስጥ ዋጋው ሳቢ በመሆኑ ፋብሪካዎቹ ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መምረጣቸው፣ በኢንቨስትመንት ሒደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ወደ ማምረት አለመሸጋገር የሚሉት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በማዕድን ዘርፍም የዓለም የወርቅ ዋጋ መቀነስ፣ በአንዳንድ ክልሎች የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋትና በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶች የሚባሉትንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከግብርና ምርቶች ትኩረት ከተሰጣቸው ውስጥ የሰሊጥ ምርት አንዱ ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ገበያ በታየው ዝቅተኛ ፍላጎት በታቀደው ያህል ገቢ አለመገኘቱንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ያዕቆብ በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ የቀረበው የሰሊጥ ምርት በመጠን ረገድ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት የ38 በመቶ ብልጫ ያለው ቢሆንም፣ ያስገኘው ገቢ ግን ካለፈው ዓመት በ12 በመቶ ያነሰ ነው፡፡

ምንም እንኳ እንደ ሌሎቹም የግብርና ምርቶች ሁሉ ወደ ውጭ የተላከው የጫት ምርትም መጠነኛ ቅናሽ የታየበት ቢሆንም፣ በአንፃራዊ የተሻለ ገቢ ያስገኘ የኤክስፖርት ንዑስ ዘርፍ መሆኑን አቶ ያዕቆብ አመልክተዋል፡፡

‹‹ለዚያውም ለሌሎቹ የግብርና ምርቶች የምንሰጠውን ዓይነት ልዩ የቴክኖሎጂም ሆነ የኤክስቴንሽን ዕገዛም ሆነ ልዩ ድጋፍ ሳንሰጠው፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከጫት ኤክስፖርት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ አግኝተናል፡፡ የጫት ምርት በወር እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ለአገራችን እያስገኘ ነው፡፡ እንዲያውም የዝናብ ዕጥረት በሌለበት ወቅት ወርኃዊ ገቢው እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል፤›› በማለት የጫትን የገቢ ድርሻ አስረድተዋል፡፡ በዓመቱም በተለይ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረው የዝናብ ዕጥረት፣ እንዲሁም አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ጫት እንዳይገባ ማገዳቸው ጫናዎችን ቢያስከትልም በጫት ገቢ መገረማቸውን ጨምረው አቶ ያዕቆብ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች