Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የራሳቸውን አጠናቀው ወደ ግንባሩ ጉባዔ አቅንተዋል

  የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የራሳቸውን አጠናቀው ወደ ግንባሩ ጉባዔ አቅንተዋል

  ቀን:

  የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በጉጉት የሚጠብቀውን 11ኛ ጉባዔውን ከመጀመሩ በፊት ለቀናት የግንባሩ አባል ድርጅቶች በየራሳቸው የጉባዔ ስብሰባ ተጠምደው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በጉባዔያቸውም ድርጅቶቹ የሚጠበቁና ግርምትን የፈጠሩ ውሳኔዎችን አሳልፈው፣ ለዋናው የግንባሩ ጉባዔ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡

  ቀደም ሲል ከሁሉም አባል ድርጅቶች ባካሄደው ጉባዔ ስሙን ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የቀየረው የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ)፣ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ ጉባዔውን ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

  ከኦዴፓ ጉባዔ በመቀጠል 13ኛ ጉባዔውን ያደረገውና ከአባል ድርጅቶች በዕድሜ አንጋፋ የሆነው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ ሪፖርት ላይ ግምገማ በማድረግ አጠናቋል፡፡

  በጉባዔውም ሕወሓት ከዚህ ቀደም 65 የነበረውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥር ወደ 55 በመቀነስ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ሕወሓት ከመረጣቸው 55 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ውስጥ 54 በመቶ የሚሆኑት አዳዲስ እንደሆኑ የገለጸ ሲሆን፣ በተቃራኒው ሕወሓት በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይወክሉኛል ብሎ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ዘጠኙን አመራሮች እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡

  ከዚህ በፊት በነበሩት የቅርብ ዓመታት ጉባዔዎችና ከሌሎች አባል ድርጅቶች በተለየ ሕወሓት ከወከላቸው ዘጠኝ የሥራ አስፈጻሚ አባላት በተጨማሪ፣ ሁለት አመራሮችንም ወክሏል፡፡

  በዚህም ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልና (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ ገብረ እግዚብሔርን የድርጅቱ ዋናና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠ ሲሆን፣ በሥራ አስፈጻሚው ውስጥም የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን፣ አቶ ጌታቸው ረዳን፣ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴን (ዓባይ ነፍሶ)፣ አብርሃም ተከስተን (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም አካቶ መጥቷል፡፡ በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑትን ዶ/ር አክሊሉ፣ አትንኩት መዝገቡን (ዶ/ር) የድርጅቱ 10ኛ እና 11ኛ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አድርጓል፣ አሥራ ሁለት ነባር አመራሮችን በክብር መሸኘቱን አስታውቋል፡፡

  ሌላው በቀናት ልዩነት ውስጥ 12ኛ ጉባዔውን የጀመረው የብሔራዊ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ወይም በአዲሱ ስያሜው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በበኩሉ፣ 65 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱን መርጧል፡፡ አዲሱን ስያሜ የለወጠው ቀደም ሲል ኢሕዴን ከዚያም ብአዴን ተብሎ ሲጠራበት የቆየውን የሃያ ዓመታት ስያሜውን በመተው ነው፡፡  

  አዴፓ በምርጫው ከዚህ ቀደም ያልነበሩ የተለያዩ ግለሰቦች በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አካቷል፡፡ ለአብነት ያህልም የቀድሞው ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው ከአምስት ዓመታት በላይ ታስረው በቅርቡ የተፈቱትን አቶ መላኩ ፈንታን፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለመናድ ሲያሴሩ ተገኝተዋል ተብለው 18 ዓመታት ተፈርዶባቸው የነበሩትና በቅርቡም ምሕረት ተደርጎላቸው የተፈቱት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አድርጎ መርጧል፡፡  

  በተጨማሪም አዴፓ ከዚህ ቀደም በመሥራችነት፣ እንዲሁም በአመራርነት ሲያገለግሉ የቆዩ የተለያዩ አራት አመራሮችን በክብር ማሰናበቱን ገልጿል፡፡ በዚህም የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑትን አቶ ከበደ ጫኔን፣ አቶ ጌታቸው አምባዬንና ሁለት ተጨማሪ አመራሮችን በክብር ሸኝቷል፡፡ ከዚህ ቀደም እስከ ጉባዔው ድረስ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ያገዳቸው የአቶ በረከት ስምዖንና የአቶ ታደሰ ካሳ ጉዳይ ታልፏል፡፡

  አዴፓ በጉባዔው የዋና ወይም የምክትል ሊቀመንበር ለውጥ ያደርጋል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ቀድሞ የነበሩት ሊቀመናብርት ቀጥለዋል፡፡ በተለይም የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ከሥልጣናቸው መልቀቅ እንደሚፈልጉ ለጉባዔው አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ጉባዔው ውሳኔያቸውን ስላልተቀበለው በነበሩበት እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክትልነታቸው ፀንተዋል፡፡ 

  ከመስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ‹‹የሕዝቦች አንድነት ለሁለንተናዊ ለውጥ›› በሚል መሪ ቃል አሥረኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን ሲያደርግ የሰነበተው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) በርከት ያሉ ነባር አመራሮችን በመሸኘት፣ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልንና አቶ ሚሊዮን ማቴዎስን ደግሞ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጥ ተጠናቋል፡፡

  ንቅናቄው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ 23 አንጋፋ አባላቱን አሰናብቷል፡፡ በዚህም መሠረት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲመረጡ፣ ሌላኛው ዕጩ የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩትና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ካቢኔ የትራንስፖርት ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሲራጅ ፈጌሳም፣ እንዲሁ ከተሰናባች የንቅናቄው አባላት መሀል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ለበርካታ ዓመታት የብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩትና በቅርቡ በይናገር ደሴ (ዶ/ር) የተተኩት አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ፣ በቅርቡ የኤርትራ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ እንዲሁም የፌዴራል ጉዳዮች፣ የትምህርት፣ እንዲሁም የአካባቢ የደንና የአየር ለውጥ ሚኒስቴር የነበሩትና በአሁን ወቅት በደቡብ አፍሪካ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ሽፈራው ተክለ ማርያም (ዶ/ር) ከተሰናበቱት መሀል ናቸው፡፡

  በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ካቢኔ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር የነበሩትና ከዚያ ቀደም ሲል በተለያዩ አገሮች በአምባሳደርነት፣ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩት ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፣ አስፋው ዲንጋሞ (አምባሳደር)፣ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ እንዲሁም አቶ ያዕቆብ ያላ ከተሰናባች የንቅናቄው አባላት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

  በተመሳሳይ ንቅናቄው 65 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ አድርጓል፡፡ በቅርቡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ሆነው የተሾሙት አቶ ዘይኑ ጀማል፣ እንዲሁም የቀድሞው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አሰፋ ዓብዩ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሆኑ ተመርጠዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ደመቀ አጪሶ (ዶ/ር) የንቅናቄውን ማዕከላዊ ኮሚቴ ተቀላቅለዋል፡፡ አቶ ፍፁም አረጋ፣ አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ እንዲሁም አቶ ደሴ ዳልኬ ንቅናቄው ቀጣይ ጉባዔውን እስከሚያካሂድ ድረስ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንደሚያገለግሉ ታውቋል፡፡

  በሐዋሳ ሲካሄድ የሰነበተው አሥረኛው የደኢሕዴን ድርጅታዊ ጉባዔ ሰባት አባላት ያሉት የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትንም ምርጫ አከናውኗል፡፡

  ከዚህ በመቀጠልም አራቱም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮቻቸው ከረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚጀመረው 11ኛ የኢሕአዴግ ጉባዔ ይሳተፋሉ፡፡

  ለሦስት ቀናት ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የኢሕአዴግ ጉባዔ በመጀመርያ ‹‹በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ የለውጥ እንቅስቃሴያችንን በማስቀጠል የኢትዮጵያን ህዳሴ እናረጋግጥ፤›› በሚል መሪ ቃል ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ በቀናት ልዩነት ውስጥ መፈክሩ፣ ‹‹አገራዊ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና›› በሚል መሪ ቃል መቀየሩ ይታወሳል፡፡

  በነአምን አሸናፊና በዳዊት እንደሻው

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img