የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ፣ በ2009 የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ከወላይታ ድቻ ጋር ተጫውቶና በመለያ ምት ተሸንፎ ዋንጫ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌሬሽን ዋንጫ ተካፋይነቱን ጭምር ማጣቱ ይታወሳል፡፡ በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ እየሠለጠነ የሚገኘው መከላከያ ከአንድ ዓመት በኋላም ለተመሳሳይ ውክልና ከአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሐዋሳ ስታዲየም መስከረም 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፍጻሜ ቀርቦ በመለያ ምት ተጋጣሚውን ድል ነስቶ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎውን አረጋግጧል፡፡ ኢትዮጵያ በ2011 የውድድር ዓመት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና በጅማ አባ ጅፋር፣ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ደግሞ በመከላከያ ትወክላለች፡፡