ቡድኑ በበጎ ተግባር ላይ ለመሳተፍ የቀይ መስቀል አባልም ሆኗል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሮን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅቱን በባህር ዳር ጀመረ፡፡ ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. የኬንያ አቻውን የሚገጥመው ብሔራዊ ቡድኑ በቀሪዎቹ ሰባት ቀናት ውስጥ አስፈላጊውን ዝግጅት እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ ቡድኑን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ፣ ሐዋሳ ከነበረው ጨዋታ በኋላ ተጫዋቾቹ ወደ ክለባቸው በማምራታቸው ከቡድኑ ጋር ዝግጅት ያላደረጉ ቢሆንም፣ በየክለባቸው ሲዘጋጁ መቆየታቸውንና ከክለቦቻቸው ጋርም በቅርበት ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
በሐዋሳ ሰታዲየም የሴራሊዮን አቻውን 1 ለ 0 የረታው የዋልያዎቹ ስብስብ ከኬንያ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ቀላል እንደማይሆን የተገመተ ሲሆን፣ የአማካይ ክፍተት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ «ባለን ጊዜ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ ጨዋታ ላይ ከነበሩት ተጫዋቾች ባሻገር ዕረፍት ላይ የነበሩትን በግላቸውም ቢሆን ማድረግ የሚገባቸውን እንቅስቃሴ ነግረናቸዋል፤» በማለት የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አብራርቷል፡፡
ዝግጅቱንና ጨዋታውን በባህር ዳር ስለመደረጉ ጥያቄ የቀረበላቸው አሠልጣኙ የሦስት ወር ዕቅድ ሲወጣ የአየር ጠባይና የሜዳ ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነና ብዙ ተመልካች ይታደምበታል ተብሎ እንደተመረጠ አስረድተዋል፡፡ መስከረም 30 ጨዋታውን የሚያደርገው ብሔራዊ ቡድኑ፣ ከአራት ቀናት በኋላ ደግሞ ጥቅምት 4 የመልስ ጨዋውን በኬንያ ያደርጋል፡፡
ሰኞ መስከረም 22 በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ዝግጅት ባሻገር ብሔራዊ ቡድኑ ከቀይ መስቀል ጋር ለዕድሜ ልክ የሚዘልቅ የአባልነት ፊርማውን በይፋ አከናውኗል፡፡ በፊርማውም ብሔራዊ ቡድኑ በበጎ ፈቃደኝነት ዙሪያ በመሳተፍ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በማሰብ ነው ተብሏል፡፡
በመጨረሻም በለንደን ከተማ ፊፋ ባዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ የግምገማ ኮንፍረንስ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ መሳተፍ የቻለው የዋልያዎቹ አሠልጣኝ በኮንፍረንሱ ላይ ኢትዮጵያም ትልቅ ልምድ ማፍራት እንደቻለች ገልጸው፣ በአገር ውስጥ ለሚገኙት አሠልጣኞች ጭምር ለማጋራት መታቀዱንም አክለዋል፡፡