Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‘አያ ጅቦ ሳታማሃኝ ብላኝ’

‘አያ ጅቦ ሳታማሃኝ ብላኝ’

ቀን:

በመርሐ ጽድቅ መኮንን ዓባይነህ

አገርና የፖለቲካ ድርጅት አንድ እንዳልሆኑና በአንድ ዓይነት መስፈሪያ እንደማይመዘኑ መናገር፣ መአልትና ሌሊት እየቅል መሆናቸውን የማስረዳት ያህል ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሚስጥረ ሥላሴ እንዳልሆነ እየታወቀ ከሰፊው አገራዊ ጥቅም ይልቅ፣ ለአንድ የተወሰነ ቡድን ፖለቲካዊ ትርፍ ወይም ለግለሰብ መሪዎቹ ስምና ዝና የበለጠውን ትኩረት በመስጠት ሁለቱን ሆን ብሎ ለምን ማምታታት ይኖርብናል?

በሌሎች አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ተወጥረን እያለ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ውስጥ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና የፖለቲካ ድርጅቶች መለያ ዓርማ፣ አንደኛው ከሌላው ጋር ክፉኛ እየተምታቱ ጥብቅና በቆሙላቸው ኃይሎች ሲቀነቀንላቸው መታዘብ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ከዚህ አልፎ ዜጎቻችን በጽንፈኛ ኃይሎች አነሳሽነት በዘውግ እየተከፋፈሉና ወዳላስፈላጊ አመፅ እየተገፋፉ፣ በሰንደቅ ዓላማና በዓርማ ምክንያት ሳይቀር እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በመባባል እርስ በርስ እስከ መጋጨትና ጎራ ለይተው እስከ መደባደብ መድረሳቸው ግር የሚያሰኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ከሁሉም በላይ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ነፍጥ አንግቦና መቀመጫውን በውጭ አድርጎ ለዘመናት ሲታገል የነበረውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች (አንጋፋውን አቶ ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ) ለመቀበል መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተካሄደውን ስሜት የተቀላቀለበት ሠልፍ ተከትሎ፣ በቡራዩና በሌሎች የመዲናይቱ አካባቢዎች በአፈንጋጭ ወጣቶች አማካይነት በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ብሔር ወለድ ጥቃትና የደረሰው ዕልቂት፣ የሕዝብ መፈናቀልም ሆነ የተደራጀ የንብረት ዝርፊያና ውድመት አንድን የፖለቲካ ቡድን በአሉታዊ መንገድ ከመደገፍና ሌላውን ያላግባብ ከማጥላላት ጋር ተያይዞ ስለመከናወኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ታሪክ በማይዘነጋው በዚህ ወደር የለሽ የጭካኔ ተግባር ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ምንም ይበል ምን፣ በሰውና በንብረት ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን በትክክል ማወቅ የተቻለ አይመስልም፡፡ አስቀድሞ ያንን እኩይ ሥምሪት የሰጣቸውን ክፍል ከመገመት ባለፈ በሚገባ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርመራ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የድጋፍ ሠልፉ እንደተበተነ በአስፈሪ ሁኔታ ተደራጅተው ሰለባዎቹን በጅምላ ለማጥቃት ወደ ሥፍራው የተንቀሳቀሱት እነዚህ ጽንፈኛ ወገኖች በጊዜው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሉትና ይህንኑ አንዳንድ ሚዲያዎች ያለ ይሉኝታ ተቀባብለው እንዳስተጋቡት፣ በእርግጥ ማንንም የማይወክሉ ተራ ዘራፊዎች ነበሩ ለማለት አይቻልም፡፡ እንዲህ ያለውን ወሬ ገና ጡጦ ለሚጠቡ ሕፃናት እንኳ መናገር በእጅጉ ሊያሳፍርና ሊያሸማቅቅ ይገባል፡፡

በመሠረቱ የአንድ አገር ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የዚያች አገርና የዜጎቿ የጋራ መታወቂያ በመሆኑ፣ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት የተናጠል መለያ ዓርማ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ አገራችን ኢትዮጵያ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (1) ሥር በተደነገገው መሠረት፣ የራሷ የሆነ ባለሦስት ቀለማት ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ አላት፡፡ ማንም እንደሚያውቀው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት ሰንደቅ ዓላማ ከላይ ወደ ታች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት አግድም የተሰመሩበት ሲሆን፣ መሀሉ ላይ በሰማያዊ ቀለም የተከበበ ቢጫ ኮከብ ታክሎበታል፡፡ በእርግጥ ይኼ ቢጫ ኮከብ የቅርብ ጊዜ ጭማሪ በመሆኑ በብዙ ወገኖች ዘንድ ጠንካራ ተቃውሞ እንዳስከተለና የሁሉንም ዜጎች ስምምነት እንዳላገኘ በሚገባ ይታወቃል፡፡ ብዛት ያለው የኅብረተሰባችን ክፍል የቀድሞውንና ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ የሙጥኝ ብሎ በአደባባይ ሲያጌጥበት የምንመለከትበት አጋጣሚ የዚህ አለመግባባት ማሳያ ይመስላል፡፡

ሕገ መንግሥቱም ቢሆን እኩል ሆነው አግድም በተሰመሩት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት መሀል በሰማያዊ መደብ ታጥሮ በብሔራዊ ዓርማ ስም ስለተጨመረው ኮከብ በጥቅሉ ከመናገር በዘለለ አስቀድሞ የሰጠው ፍንጭ የለም፡፡ ያደረገው ተጨማሪ ነገር ቢኖር ይኼው ዓርማ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስከ ወዲያኛው ተፈቃቅደውና ተከባብረው በእኩልነትና በአንድነት አብሮ ለመኖር ያላቸውን ብሩህ ተስፋ የሚያንፀባርቅ መሆኑን በአንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ ፺ (2) ድንጋጌ ሥር ከርቀት ማመላከቱ ብቻ ነው፡፡

ከዚህ የተረፈው ዝርዝር በሥራ ላይ ባለውና ስለሰንደቅ ዓላማ በወጣው አዋጅ ቁጥር 654/2001 ዓ.ም. ተወስኗል፡፡ ይህ እናት ሕግ አከራካሪ ጉዳዮች ቢኖሩበት እንኳ፣ በአዋጅ ቁጥር 863/2007 ዓ.ም. ብቻ መጠነኛ ማሻሻያ የተደረገበት ከመሆኑ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ተሽሮ በአዲስ እስኪተካ ድረስ በሁሉም ወገኖች ዘንድ መከበር ይኖርበታል፡፡ ከፍ ብሎ ከተገለጸው የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ በታች የሚውለበለብ ሰንደቅ ዓላማ ሊኖራቸው እንደሚችል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (3) ሥር በግልጽ የተደነገገላቸው አካላት ቢኖሩ የፌደሬሽኑ አባል ክልሎች ብቻ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን ከመለያ ወይም ከመታወቂያ ዓርማ በስተቀር እንደ አገሪቱም ሆነ እንደ ተለያዩ ክልሎቿ ሁሉ እንዲህ ያለው ሰንደቅ ዓላማ የላቸውም፡፡ በአገራችን ይህ ጉዳይ ተሻሽሎ በወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ዓ.ም. አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ (2) ፊደል ተራ ቁጥር ለ. ሥር በማያሻማ ቋንቋ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

ከዚህ ውጪ ነገሩን አስፍቶ ከመመልከት የተነሳ በግልጽ እስካልተከለከለ ድረስ በተዘዋዋሪ ሳይፈቀድ አልቀረም የሚባል ቢሆን እንኳ፣ በግል የፖለቲካ እምነት ማራመጃነት የተቀረፀን አንድን ባንዲራ ወይም ዓርማ በግድግዳዎች ወይም በምሰሶዎች ላይ መስቀል፣ ወይም ከእነዚሁ ላይ ማውረድ በቅርቡ እንደታዘብነው ወንድማማች ማኅበረሰቦችን በቡድን ከፋፍሎ የሚያነታርክ፣ ድንጋይ የሚያወራውርና እርስ በርስ የሚያበጣብጥ ጉዳይ አይደለም፡፡ በእርግጥ ይኼንን ተንተርሶ በሕግ ጥበቃ የተደረገለትን የአገሪቱን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ መተናኮል ወይም በማናቸውም ሁኔታ ማዋረድ አይቻልም፡፡ እንዲያውም በወንጀል ኃላፊነት ሳይቀር የሚያስጠይቅ ይሆናል፡፡ አገር ሌላ ድርጅት ሌላ፣ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ይሉ ነበር እትዬ እናኑ በልማድ ከሚያውቁት ያፈነገጠ የነገሮች ኢ ተዛምዶ ሲያጋጥማቸው፡፡

ለዶ/ር ዓብይ አስተዳደር ምሥጋና ይግባውና በባህር ማዶ ሆነው ስለኢትዮጵያ ወይም በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ሲንቀሳቀሱ የቆዩ አያሌ የፖለቲካ ስብስቦችና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ የከራረሙ ግለሰብ አክቲቪስቶች፣ እንዳመቺነቱ የየብስም ሆነ የአየር ትራንስፖርት አውታሮችን እየተጠቀሙ ባልተገመተ ፍጥነት ወደ አገር በመመለስ ላይ ናቸው፡፡ በመዲናችን በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች ደጋፊዎቻቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና የፀጥታ ሠራተኞች ጭምር እነርሱን በመቀበል፣ በማጀብና በመንከባከብ ዕለታዊ ተግባር አብዝተው እንደ ተጠመዱም በአንክሮ እናስተውላለን፡፡

ይህ መቸም በቁሙ ሲወሰድ ጤናማ አዕምሮ ባለው ሰው አስተያየት ይበል የሚያሰኝ ዕርምጃ ስለመሆኑ ማንም ሊስተው አይችልም፡፡ እኛም ቢሆን ታዲያ ከዚህ ሁሉ ተከታታይ ሆታና ፈንጠዝያ መልስ የናፈቅናቸው ወገኖቻችን ምን በጎ ነገር ይዘውልን እንደመጡ መጠየቃችን አይቀርም፡፡ ከአንጀት ጠብ ሊል የሚችል አንዳች ትሩፋት ካጣንባቸው ግን ምናልባትም በቀላሉ ልንጣላቸው እንችል ይሆናል፡፡ ሌላው ቢቀር የመጡበትን ዓላማ ሕጋዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ብቻ ያራምዱ ዘንድ ለገቡት ቃል ታምነው እንዲገኙ እንጠብቃለን፡፡ እንደ ብዙዎቹ ነባርና አዳዲስ የፖለቲካ ቡድኖች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን ለመቀጠል ወስኖ ከተራዘመ የስደት ቆይታ በኋላ፣ በቅርቡ ወደ አገር ቤት የተመለሰው ኦነግ አገሩ መላዋ ኢትዮጵያ እንጂ ኦሮሚያ ብቻ ልትሆን አትችልም፡፡ ዓይነተኛ የመታገያ አካባቢው ያለ ጥርጥር ኦሮሚያና የኦሮሞ ሕዝብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ስለሆነም ታክቲካዊ በሆነ አመክንዮም ይሁን በአርቆ አስተዋይነት በሰላማዊ ትግሉ ለመቀጠል ከወሰነ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ሕግ መሠረት ተፈላጊ መሥፈርቶችን አሟልቶ የመመዝገብና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ዕውቅና የማግኘት ግዴታ ይኖርበታል፡፡ በአዋጁ መሠረት ደግሞ ኦነግ እንደ ፖለቲካ ድርጅት መጠን መለያ ዓርማ እንጂ፣ ሰንደቅ ዓላማ ወይም በቆየው አነጋገር ባንዲራ እንዲኖረው አልተፈቀደለትም፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ወርቃማ መርህ ለኦነግ ብቻ ሳይሆን፣ የአመሠራረታቸው ታሪካዊ ዳራ፣ የመልክአ ምድራዊ ሥምሪታቸው ወሰንና የተቀባይነታቸው ደረጃ ግምት ውስጥ ሳይገባ ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እኩልና ያለ አድልዎ የሚሠራበት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች በበኩላቸው ይህንኑ ሕጋዊ ሁኔታ በቅድሚያ ራሳቸው በሚገባ አውቀው ለደጋፊዎቻቸው ማስተዋወቅና በቅጡ ማስረዳት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ብዙ አልመሸምና ያን ያህል ውኃ በማይቋጥረው ያልተገባ እሰጣ ገባ ምክንያት ተጨማሪ ጥፋት ከመድረሱ አስቀድሞ፣ በዚህ ላይ ተግተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ‘የጭቅጭቅ በራፍ ሳይዘጋ ያድራል’ እንዲሉ፡፡

ከሁሉ በፊት ሰንደቅ ዓላማ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ዋና ገንዘብነቱ የማን እንደሆነና ለምን አገልግሎት እንደሚውል ረጋና ሰከን ብሎ ማስተዋል ይገባል፡፡ ይህንኑ በቅድሚያ ሳይጠይቁ፣ ሳይጠነቀቁና በውል ሳያጤኑ ብሔራዊውን ሰንደቅ ከታለመለት ዓላማ ውጭ በግድ የለሽነት መጠቀም ብቻ ሳይሆን፣ ያንኑ ሰንደቅ ዓላማን ንቀት በተሞላበት ሁኔታ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዓርማ መተካት ቢያንስ ነውር እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ጭራሹን ይኼው ሰበብ ሆኖ ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን ደም እስከማፋሰስ ለዘለቀ አምባ ጓሮ ማቀጣጠያ እንዲሆን መደረጉ ግን ‘አያ ጅቦ ሳታመሃኝ ብላኝ’ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...