በሰለሞን መለሰ ታምራት
የሰው ልጅ ለአቅመ አዳም ደረሰ የሚባለው ዕድሜው ሰላሳ ዓመት ሲሞላው እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ይኼ ጊዜ አፍላ የጉርምስና ወቅት ተጠናቆ ሰው በአስተሳሰቡ መብሰልና መጎልመስ የሚጀምርበት ዕድሜም ነው፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት አዳም ሲፈጠር የሰላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነበር፡፡ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ የማዳን ሥራውን የጀመረውም ልክ በ30 ዓመቱ ነው፡፡ በዘመናቸው በርካታ ቁምነገር ለእዚህች ምድር ትተው ያለፉ የዓለማችን ታላላቅ ሰዎችን ታሪክ (እንዲሁም የራሳችንንም ሕይወት) ብንመረምር፣ ትልቁን አሻራቸውን ያሳረፉበት (Life’s Turning Point) ጊዜ በዚህኛው የዕድሜያችን ክፍል እንደሆነ ልንረዳ እንችላለን፡፡ የቁጥሩን ጨዋታ እንደ ተራ ነገር እንዳንቆጥረውና ይኼን የዕድሜያችንን አጋማሽ ወቅት የብቃትና የጉልምስና መጀመሪያነት እንድናየው ያህል ያመጣሁት መነሻ እንጂ፣ ከዚህ ዕድሜ ቀደም ብሎም ሆነ ዘግይቶ አንዳንዴም እጅግ በጣም ዘግይተው ታሪክን ለውጠው ያለፉ ሰዎች እንደነበሩና ዛሬም እንደሚኖሩ ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ጉዳዩን ከሰው ልጆች ታሪክ ባለፈ ወደ ተቋማትና ክስተቶች (Events and Institutions) አስፍተን ቁጥሩን ከተመለከትነው፣ ከሰዎችም በላይ በዓለማችን ላይ ለተከናወኑት ሁነቶችም ሊሠራ የሚችል የጊዜ ክልል ሆኖ ስለታየኝ፣ ‘ለዛሬ ለምን ከአገራችን ቁልፍ ተቋማት አንዱን ኢሕአዴግን አንፈትሽበትም?’ በማለት ይኼንን ጽሑፍ ለመከተብ ተነሳሁ፡፡
ኢሕአዴግ የሚባል ድርጅት የዛሬ ሰላሳ ዓመት እንዲመሠረት ትልቁን ግፊት ያደረገው (ጠፍጥፎ የሠራው ማለትም ይቻላል) ትግራይን ከኢትዮጵያ በመገንጠል ሪፐብሊክ እመሠርታለሁ በማለት ጥራኝ ዱሩ ያለው ሕወሓት፣ በዕድሜ ልክ ጦርነት ከተሰላቸው የደርግ መንግሥት ሙሉ የትግራይን ክፍለ አገር ከተረከበ በኋላ በመጣ ሐሳብ መሆኑን ማንም ያጣዋል ብዬ አላስብም፡፡ ለትግራይ ሕዝብ ልዕልና ሕወሓትን የተቀላቀሉት ታጋዮች ‘ሥራችንን ጨርሰናል፣ ወደየቤታችን ተመልሰን አገራችንን ትግራይን እናስተዳድር’ የሚል ጥያቄ ባነሱ ማግሥት፣ ዋነኛ ዓላማው ቢሳካም ቀሪ ፍላጎቱ (ማለትም ኤርትራን ነፃ በማውጣት ቢቻል የትግራይ ትግሪኝ ሪፐብሊክን መፍጠር) ባለመሳካቱ፣ የኢትዮጵያዊነትን ካባ ደርቦ ወደቀሪው የአገራችን ክፍል የሚስፋፋበት ምክንያት አስፈልጎታል፡፡ እናም ለክፉ ቀን ይሆኑኛል በማለት ያደራጃቸውን አማርኛ ተናጋሪ የቀድሞ የኢሕአፓ አባላትን እንደ አንድ ድርጅት በመቁጠር ትግሉን ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ግዛቶች አስፋፋው፡፡ ኢሕአዴግንም እንደ ሰው ብናስበው በግንቦት ወር 1980 ዓ.ም. ይህችን ምድር ተቀላቀለ፡፡ ታጋይ መለስ ዜናዊም በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ሕይወታቸው እስከሚያልፍ ድረስ የድርጅቱ ፈላጭ ቆራጭ (ወላጅ አባት) በመሆን ለ24 ዓመታት ያህል በቀደዱለት ቦይ ሲፈስ ቆይቷል፡፡
ዛሬ ኢሕአዴግ የጉልምስና ዕድሜውን ሲጀምር መንታ መንገድ ላይ ቆሟል፡፡ አንድ ነፍስ ያወቀ ሰው የወላጆቹን አቋም እንደሚሞግተው ሁሉ፣ ድርጅቱ አሁን በሁለት እግሬ ቆሜ መራመድ አለብኝ ብቻ ሳይሆን፣ ‘እንደ ስያሜዬ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ የማገለግልበት ወቅት ነው፣ ከዚህ በኋላ ወላጆቼ የምበላውንና የምለብሰውን ሊመርጡልኝ አይገባም’ በማለት ጠበቅ ያለ እሰጥ አገባውን ተያይዞታል፡፡ ወልደን አሳድገን ለዚህ ያደረስንህ እኛ በመሆናችን ዛሬም ቢሆን እንደምንልህ መሆን አለብህ የሚሉት ወላጆቹም ቢቻል በምክር፣ ካልተቻለም በበትር ሕልምና ፍላጎታቸውን ሊግቱት ግብ ግቡን ተያይዘውታል፣ የጥንቱ የጠዋቱ የወላጆች ወግ ነውና፡፡ ምንም እንኳን ኢሕአዴግ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን አጥብቀው ከሚጠሉ ወላጆች የተገኘ፣ በክፋት ተፀንሶ ለተንኮል የተወለደ፣ ስግብግብነት፣ ዘረፋን እንዲሁም ብዙ ደም ማፍሰስን በማየት ለአቅመ አዳም የደረሰ ቢሆንም፣ ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? ከየት መጣሁ? መድረሻዬስ ወዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች የሚጠይቅበት የጉልምስና ዕድሜው ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ለራሱ የአብርሆትን ፍሬ ማየት የሚጀምርበት፣ ለወላጆቹ ደግሞ ከፍቃዳቸው በመውጣት ቅስማቸውን የሚሰብርበት ጊዜ በመሆኑ ሕመሙ ዕረፍት የሚነሳቸው ወቅት ላይ ይገኛሉ፡፡
አሁንም ጉዳዩን ሰውኛ መልክ እየሰጠ ነው ትርክታችንን እንቀጥል፡፡ የትኛውም ቤተሰብ ውስጥ ሊፈጠር እንደሚችለው መከፋፈል በኢሕአዴጎችም መካከል ከተራ የጥቅም ግጭት አንስቶ፣ መሠረታዊ የሆነና የአቋም/መስመር ልዩነትን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መከፋፈል መፈጠሩን መንገር ለቀባሪው የማርዳትን ያህል ይሆንብኛል፡፡ ይልቁንስ ጥያቄው መሆን ያለበት ይኼንን ልዩነት ቢቻል ለማጥፋት፣ ካልተቻለም አጥብቦ ቤተሰቡን እንዳይበተን ማድረግ ይቻል ይሆናል ወይ? የሚል ነው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ድርጅቱ ወለም ዘለም የማያውቅ፣ አይደለም የመስመር ልዩነትና የጥቅም ግጭትን የሚያህል ትልቅ ጉዳይ፣ የዓይኑ ቀለም ያላማረውን ሁሉ በፅኑ የሚቀጣ ሰብሳቢ ስለነበረው፣ መጣላትንም ሆነ ከተጣሉም በኋላ መታረቅን የሚያስበው አልነበረም፡፡ እንኳንስ ሰብሳቢው እርሱን የተጠጉት እንደነ አቶ በረከት ስምዖንን የመሳሰሉት የቤተሰቡ አባላት ያሻቸውን እንዳሻቸው የሚያደርጉበት ዘመን አልፎ ዛሬ ሁሉም ትከሻውን የሚለካካበት ዘመን ላይ በመደረሱ፣ ልዩነትን ማጥበብ እንዲህ በቀላሉ የሚታሰብ አልሆነም፡፡ ድርጅቱ ከራሱም አልፎ ጥላው መላ ኢትዮጵያን የሸፈነበት አጓጉል ጊዜ ላይ በመሆናችን፣ የተፈጠረው እሰጥ አገባ ሞልቶ ከፈሰሰ አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ለማዳረስ መቻሉን ለማወቅ ማንንም መጠየቅ አያስፈልግም፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትየጵያውያን (እኔንም ጨምሮ) ዛሬ በኢሕአዴግ ላይ የምናየውን ለውጥ የምንመለከተው፣ ጊዜውን ጠብቆ የተከሰተና ከማንም በላይም ራሱን ኢሕአዴግን ከመጣበት ጥፋት ሊታደገው የሚችል በጎ ክስተት እንደሆነ አድርገን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፉት በርካታ ዓመታት እጃቸውን ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ወንጀሎች ሲያጨማልቁ ለነበሩት ከተራ እስከ ከፍተኛ አመራሮች ድረስ ለሚገኙት አባላቱ፣ አጋጣሚው ወደ ልቦናቸው የሚመለሱበትና ቆሻሻቸውንም በይቅርታ የሚያፀዱበትን ዕድል ይዞ የመጣ ነው፡፡ መቼም የፈርኦንን ልብ ከሰጠው ሰው ከጥፋቱ ለመማር እንዲሁ ቀላል ባይሆንለትም፣ ዞሮ ዞሮ ሊመጣ ያለው ለውጥ መምጣቱ የግድ ነውና እያንዳንዱ የድርጅቱ አባል በግሉም ይሁን ለአገሪቷ በአጠቃላይ ለውጡ የመልካም ዘመን ጅማሬ እንዲሆን አጥብቆ ሊሠራ ይገባል የሚል ምክሬን በዚህ አጋጣሚ እለግሳለሁ፡፡
ከሺሕ አንድ በሚያጋጥም መልካም ዕድል ዛሬ ኢሕአዴግን ለመምራት አጋጣሚውን ያገኙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በየትኛውም ዘመን ከተፈጠሩት መሪዎች በተሻለ ሕዝቦቿን አንድ ያደረጉ ሰው በመሆናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ግንባሩ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ (ምናልባትም ከዚህ በኋላ እስከ መጨረሻው የማያገኘው) ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ነገ ጠዋት ምርጫ ቢደረግና አገሪቷን የሚመራ አካል ይሰየም ቢባል፣ ኮሮጆ ግልበጣ ሳያስፈልግ ሁላችንንም ሊያስማማ የሚችል አንድ ፓርቲ ከነችግሮቹም ቢሆን፣ ኢሕአዴግና ኢሕአዴግ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ምንም እንኳን የቆሸሸ ስሙና ረጅም ጥቁር ጥላው ዛሬም ድረስ አብሮት ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ አሉኝ ከሚላቸው ስድስት ሚሊዮን አባላት (በትክክል ካሉ) መካከል ሩቡን ያህል እንኳን አሁን እየተከናወነ ባለው ለውጥ እንዲያምኑ ካደረገ፣ ዛሬም ቢሆን በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሻለ ተንቀሳቅሶ ሕዝቡን ከጎኑ ለማሠለፍ የሚበቃ ኃይል ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት እንደሆነው ኢትዮጵያን ያለምንም ይሉኝታ ለመዝረፍና በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል ሕዝቦቿን አዳክሞ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስብ ከሆነ፣ የቱንም ያህል አባላቶቹን ቢያደራጅ በለውጥ ፈላጊው ኃይል ቢያንስ በአሥር እጥፍ ተበልጦ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ መሬቱን እንደምናየው አልጠራጠርም፡፡
ረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ ሊካሄድ የታሰበው የኢሕአዴግ ጉባዔ፣ ከመቼውም በላይ በድርጅቱና በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚያርፍ ዘላቂ አሻራ የሚተው መሆኑ ከወዲሁ ይታየኛል፡፡ አራቱም አባል ፓርቲዎች የየግል ጉባዔያቸውን ሲያከናውኑ የመረጡት መሪ ቃልና የያዙትንም አጀንዳ ስንመረምረው፣ በሐዋሳው ጉባዔያቸው ላይ ሊለኮሱ የታሰቡትን ጉዳዮች ከሩቁ ማሽተት ይቻላል፡፡ በቅርብ ጊዜያቱ የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ ሲፈጠር ያየነው መሻኮትና አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነትን ለማግኘት ሲደረጉ የነበሩ ግብግቦች፣ አሁን በሚካሄደው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አይኖርም ብሎ መገመት ጅልነት ይሆናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ባለፈው የአንድ ዓመት የለውጥና የውጣ ውረድ ፈታኝ ጊዜያት ራሱን እንደ ተሸናፊ የቆጠረ ኃይል በመኖሩና ይኼንን አደገኛ ኃይል በመተማመንም፣ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩት ረብሻዎችና መፈናቀሎች ከፍተኛ የልብ ስብራትን ፈጥረው በማለፋቸው፣ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የአገሪቷ ዜጎች ‘በእርግጥ ይኼ ለውጥ/ነውጥ ያስፈልገናል?’ የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ እያስገደዳቸው ይገኛል፡፡ ለእነዚህ በተሸናፊነት ሥነ ልቦና ውስጥ ለሚገኙት አደገኛ የጥፋት ኃይሎች መጪው የኢሕአዴግ ጉባዔ በድርጅታቸው ውስጥ ያላቸውን ዕጣ ፈንታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወስኑበት አጋጣሚን ስለሚሰጣቸው፣ አለኝ የሚሉትን አቅማቸውን አሰባስበው እንደሚገቡ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
ዛሬም በሙሉ ልቤ እንደማምንበት አሁን በአገራችን የተፈጠረውን ለውጥ በትክክል ካስተዋልነው፣ እንደ ኢሕአዴግ ሊጠቀምበት የሚችል ኃይል መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡ ፓርቲው እንደ ንስር አሮጌ ላባውን አራግፎና ጉልበቱን አድሶ ለመውጣት፣ አለበለዚያም እንደ እባብ የልቡን በልቡ ይዞ ቆዳውን ብቻ ገልብጦ ለመምጣት ያለው የመጨረሻ ዕድሉ የሚወሰነው፣ ሐዋሳ በሚከናወነው ጉባዔ ይሆናል፡፡ እግረ መንገዳችንንም የአገራችንን ቀጣይ የጉዞ አቅጣጫ የምንመለከትበት ዕድል ይሰጠናል፡፡ በዚህ አጋጣሚም መላው የኢሕአዴግ ጉባዔተኛ በሙሉ ታሪክ የጣለበትን ትልቅ ኃላፊነት በጥልቀት ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ይህች አገር አንድ ሆና መቀጠል ካልቻለች መሪ ድርጅታቸው ኢሕአዴግም ሆነ በተናጠል አባል ድርጅቶቻቸው ሊኖሩ አይችሉም፡፡ የወረዳም ሆነ የዞን፣ እንዲሁም የክልል ሹመቶች ሊኖሩ የሚችሉት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ካለች ብቻ ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ እስከ ዛሬ የዘረፉትም ሀብት ካለ፣ አጣጥሞ ለመብላትም ይሁን ለልጆች ለማውረስ ይህችው መከረኛ አገር ታስፈልጋለች፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት በተጓዝንበት መንገድ ከዚህ በኋላ ልንቀጥል አንችልም ብሎ ቁልጭ ያለ ሐሳቡን አስታውቋል፡፡ የሚኖረው አማራጭ አንድም ከሊቀመንበራቸው ከዶ/ር ዓብይ አህመድ ጎን ተሠልፈው በአዲሱ የለውጥ ጎዳና መራመድ፣ አለበለዚያም ደግሞ ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ ካለው የተሸናፊና የጥፋት ኃይል ጋር በማበር አገሪቷን ማፈራረስና የሚሆነውን ነገር መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ሦስተኛ አማራጭ መንገድ የለም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡