ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ባደረጉት ጥሪ መሠረት፣ በርካቶች ወደ አገር ቤት እንደመጡ መታዘብ ተችሏል፡፡ ከፖለቲከኞችና ከመብት ተሟጋቾች ባሻገር በርካታ የዳያስፖራው አባላት አዲሱን ዓመት በኢትዮጵያ ለማክበር ከያሉበት መጥተዋል፡፡
ከ2011 ዓ.ም. አዲስ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ ወደ አገር ቤት የገቡት ዳያስፖራዎች፣ በአገር ቤት ቆይታቸው ወቅት ስለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና በኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት ስለሚችሉባቸው መንገዶች ግንዛቤ የሚሰጡ የምክክር መድረኮች ተዘጋጅተው፣ በዳያስፖራው አባላት ጥያቄዎችና ሐሳቦችን ቀርበዋል፡፡
ማክሰኞ መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካይነት ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሰናዳ የውይይት መድረክ ነበር፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የቤት ባለቤት ለመሆን የሚችሉበት የብድር አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ይፋ ለማድረግ ባንኩ በጠራው በዚህ መድረክ፣ ስለአገልግሎት አሰጣጡ ንግግር ያደረጉት የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና ‹‹በየኖራችሁበት ክፍለ ዓለም በትምህርትና በሥራ ያዳበራችሁትን ልምድ የአገራችንን ትንሳዔ ለማረጋገጥ የምትጠቀሙበት ጊዜው አሁን ነው፤›› በማለት፣ ንግድ ባንክ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በውጭ ምንዛሪ የሚከፈቱ የባንክ ሒሳቦች እንዲኖሯቸው ሁኔታዎችን ስለማመቻቸቱ አስታውቀዋል፡፡ አገልግሎቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገር ቤት የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ንብረቶች ለማፍራት እንዲችሉና በኢንቨስትመንት ሥራዎች ውስጥም መሳተፍ በሚፈልጉበት ወቅት መሠረት እንዲሆናቸው ታስቦ የተጀመረ አገልግሎት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
እነዚህን የመሳሰሉ አገልግሎቶች በስፋት ለማቅረብ የሚያስችሉ አማራጮችን ባንኩ በጥናት እየለየ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ የቤት መሥሪያና መግዣ የብድር አገልግሎት ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እገዛ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡
የዳያስፖራ የቤት መግዣና ቤት መሥሪያ የብድር አገልግሎትን በተመለከተ ሌሎችም የባንኩ ኃላፊዎች በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ ንግድ ባንክ ያቀረበው የብድር አገልግሎት በውጭ የሚኖሩና ዕድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውንን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ዳያስፖራው ቤት መሥራት ወይም መግዛት በሚፈልግበት ወቅት፣ የቤቱን ዋጋ 20 በመቶ በውጭ ምንዛሪ ሲቆጥብ፣ 80 በመቶን ባንኩ በብድር የሚከፈልበትን አሠራር ያመቻቻል፡፡
በባንኩ አዲሱ የዳያስፖራ ብድር አሠራር መሠረት፣ ዳያስፖራው በዝግ አካውንት የሚያስቀምጠው በባንኩ ተቀባይነት ባላቸው በዶላር፣ በፓውንድና በዩሮ ገንዘቦች እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡ ይህም ሆኖ የብድር አገልግሎቱ በተለያዩ መሥፈርቶች ለተጠቃሚው እንደሚቀርብ የተገለጸ ሲሆን፣ እንደየቁጠባው መጠን ከ8.5 እስከ 11.5 ወለድ የሚከፈልበት አገልግሎት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
በሌሎች አገሮች የሞርጌጅ ወይም የቤት መሥሪያ ብድር የተለመደ ነው፡፡ በኢትዮጵያም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዚህ ዓይነት አገልግሎት በቀድሞው ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ አማካይነት ለዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ መንግሥት ይህንን ሥርዓት በማፍረስና ባንኩንም በንግድ ባንክ እንዲጠቀለል በማድረግ የወሰደው ዕርምጃ እያስደሰታቸው ይገኛል፡፡ ይሁንና ንግድ ባንክ ለቁጠባ ቤቶች ወይም ለ40/60፣ ለ20/80 እና ለ10/90 የጋራ ቤቶች ግንባታ የሚሰጠው የብድርና የቁጠባ አገልግሎት ታሳቢ ቢደረግም ካለው ፍላጎት አኳያ ሥራው አብዛኛውን ቤት ፈላጊ አላረካም፡፡ ይህ ባለበት ወቅት ግን በውጭ ለሚኖሩ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሆን የሞርጌጅ ብድር በሥራ ላይ ካለው በተለየ አኳኋን እንዲጀመር ለማድረግ የተቀረፀ አሠራር መዘርጋቱን ንግድ ባንክ አስታውቋል፡፡
አዲሱ የብድር አገልግሎት ከዚህ ቀደም ከተዘረጉና ዳያስፖራውን ከሚመለከቱ የባንክ አገልግሎቶች በተለየ መንገድ የሚተገበር ነው፡፡ የሞርጌጅ የቁጠባ አካውንትን በመጠቀም ዳያስፖራው በቂ የሚባለውን ያህል የግሉን ገንዘብ ካጠራቀመ በኋላ፣ የብድር ጥያቄውን ለባንኩ በማቅረብ ይስተናገዳል፡፡
ዳያስፖራው በውጭ ምንዛሪ ሲቆጥብ፣ በኢትዮጵያ ለሚኖረው እንቅስቃሴ ብድር እንደሚመቻችለትና በውጭ ምንዛሪ ለሚያደርገው ቁጠባም በብር ተተምኖ የሚሰጠውን ብድር በመያዝ እንደየምርጫው ከሪል ስቴቶችና ከግል ባለይዞታዎች መኖሪያ ቤት መግዛት የሚችልበት አሠራር እንደሆነ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም የአገሪቱን ሕግ በመከተል ጅምር ቤቶችንም መግዛት የሚያስችል ዕድል እንደሆነ በዳያስፖራ ሞርጌጅ ብድር ዙሪያ የተሰጠው መግለጫ ያስረዳል፡፡ እያንዳንዱ የቤት ግዥና ተያያዥ ሒደቶቹ ሁሉ በባንኩ በኩል የሚፈጸሙ ሲሆን፣ ብድሩ ተከፍሎ እስኪያልቅ ድረስ ባንኩ የተገዛውን ቤት ለዕዳ ማስከፈያ በዋስተናነት ይይዘዋል፡፡
ዕድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ዳያስፖራ የብድር ጥያቄ ሲያቀርብ ማሟላት ከሚጠበቁበት ጉዳዮች መካከል የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ፣ አመልካቹ ኢትዮጵያዊ ከሆነ የታደሰ ፓስፖርት፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከሆነም የውጭ ዜግነቱን የሚገልጽ የታደሰ መታወቂያና የትውልደ ኢትዮጵያውያን መታወቂያ (ቢጫ ካርድ) የቁጠባ ሒሳብ ለመክፈት እንደሚያስፈልጉ ከተጠቀሱ መረጃዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የጋብቻ የምስክር ወረቀት፣ ያላገባ ከሆነም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሰነድ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ብድሩ የተጠየቀው በወኪል አማካይነት ከሆነም የወኪሉ የታደሰ መታወቂያ፣ የውክልና ማስረጃና እንደአስፈላጊነቱ ጠቅላላ ዓመታዊ የደመወዝ መጠንና የተጣራ ገቢን የሚገልጽ ከቀጣሪው የተጻፈ የቅጥር ደብዳቤና ሌሎችም ሰነዶችን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ እንደ አግባብነቱ የቅጥር ውል ኮፒ፣ ከውጭ አገር ባንክ ቢያንስ የአንድ ዓመት የሒሳብ መግለጫ፣ አመልካቹ በንግድ ሥራ የሚተዳደር ከሆነም፣ ቢያንስ የሦስት ተከታታይ ዓመታት የሒሳብ ዝርዝር መግለጫ፣ የታደሰ የንግድ ፈቃድ፣ የንግድ ምዝገባ የምስክር ወረቀትና የግብር ከፋይነት የምስክር ወረቀት ለብድር ጥያቄው ከሚቀርቡ ሰነዶች መካከል ናቸው፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ በዚህ የብድር አገልግሎት መጠቀም የሚችሉ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ወይም በሚኖርበት አገር በሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ቀርበው የቁጠባ ሒሳብ በመክፈት መቆጠብ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡
ለመኖሪያ ቤት መሥሪያና መግዣ የሚውለው ብድር የመክፈያ ጊዜ እስከ 20 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፣ ተበዳሪው በብድር መዋጮው የሚሠራውን ወይም የሚገዛውን ቤት የመሐንዲስ ግምት ቢያንስ 20 በመቶ ይቆጥባል ማለት ነው፡፡ ዳያስፖራው የሚኖርበትን ዕዳ ያለተጨማሪ ክፍያ በፈለገበት ጊዜ አጠናቆ ለመክፈል የሚችልበት ዕድልም ስለመመቻቸቱ ተጠቅሷል፡፡
የሞርጌጅ ብድር አካውንት የከፈቱ ዳያስፖራዎች፣ በአንድ ወር ውስጥ ካሉበት ቦታ ሆነው በከፈቱት አካውንት ገንዘብ ማስገባት እንደሚችሉ በባንኩ የተገለጸላቸው ሲሆን፣ ይህም የተደረገው በአሁኑ ወቅት አገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች በእጃቸው የውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ላይኖራቸው ይችላል ከሚል መነሻ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ በአንድ ወር ውስጥ ማስገባት ካልቻሉ ግን የከፈቱት አካውንት እንደሚዘጋ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የሞርጌጅ ብድር አካውንት ለመክፈት ለዳያስፖራዎች ሌላም ዕድል ስለመመቻቸቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይኸውም ከዚህ ቀደም በባንኩ የዳያስፖራ የግዥ አካውንት ያላቸው ዳያስፖራዎች፣ ወደ ሞርጌጅ ብድር አካውንት ሒሳብ በማስተላለፍ አዲስ የሞርጌጅ ሒሳብ መክፈት ይችላሉ፡፡ ዳያስፖራው ከሞርጌጅ አካውንቱ ገንዘቡን ሲያንቀሳቅስ ግን በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ እንደሚሆን ከተሰጠው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የብድር ዕዳ ክፍያውን በውጭ ምንዛሪ ማድረግ ለሚፈልጉ የተሻለ የወለድ ተጠቃሚነት ዕድል ማመቻቸቱንም ባንኩ አስታውቋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ቆጣቢ ለቤት ግዥው የሚሆውን መዋጮ 20 በመቶ ሰጥቶ 80 በመቶውን መበደር የሚችል ሲሆን፣ ለተበደረው ገንዘብ የሚከፈለው የወለድ መጠን 10.5 በመቶ ተደርጓል፡፡ ይህ የፋይናንስ ሥርዓት ያልተመቸውና ቅድሚያ 30 በመቶ አስቀምጦ ቀሪውን በተበደረ ለ20 ዓመታት ውስጥ ለሚከፍል ተበዳሪም የወለድ መጠኑ 9.5 በመቶ ተደርጎለታል፡፡ 40 በመቶ ላጠራቀመ 60 በመቶውን በ20 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል ብድር ከወሰደ፣ ወለዱ 8.5 በመቶ ይሆናል፡፡
የሚፈለግባቸውን መረጃዎች በተወሰነ ደረጃ ማሟላት ያልቻሉ ዳያስፖራዎች ግን ብድሩን መክፈላቸው ስለመቻላቸው የሚያረጋግጥ መረጃ ማቅረብ በሚችሉበት ወቅት 50 በመቶውን በውጭ ምንዛሪ ቆጥበው፣ 50 በመቶውን መበደር የሚችሉበት የብድር ዓይነት ስለመኖሩም ተጠቅሷል፡፡ በአጠቃላይ ይህ የብድር አገልግሎት ከ15 እስከ 20 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል ብድር የሚቀርብበት ሲሆን፣ ቅድሚያ በተበዳሪዎቹ በሚቀርበው መዋጮ መጠን የሚጠየቁት ወለድም ከ8.5 እስከ 11.5 በመቶ ልዩነት ይኖረዋል፡፡