Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ጦርነት ሥጋት ያጠላበት የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ሥጋቶች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሰሞኑ የንግድ ጦርነትን ያህል በዓለም ኢኮኖሚ ረገድ ትልቅ መነጋገሪያ ርዕስ ስለመኖሩ ያጠራጥራል፡፡ በቻይናና በአሜሪካ መካከል የከረረው የሸቀጦች ታሪፍ እንኪያ ሰላንቲያ፣ ቀስ በቀስ ሌሎች አገሮችንም እያስከተለ ወደለየለት የንግድ ጦርነት እንዳያመራ አሥግቷል፡፡ በርካታ አገሮች ቢሳተፉበት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገሮች የሚገጥማቸውን የወጪ ንግድ ቀውስ የሚያመላክቱ ትንታኔዎች መውጣት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

በትዊተር ገጾቻቸው ስለዚሁ ጉዳይ ሐሳብ ከተለዋወጡ መካከል፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር)፣ የፕሪሳይስ ኮንሰልት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሔኖክ አሰፋ፣ እንዲሁም ነዋሪነቱ በአሜሪካ የሆነውና በግብርና ጉዳዮች በተለይም ስለቡና ዘርፍ የሚጦምረው (ብሎገር) ወንድወሰን መዝለቂያ፣ ስለንግድ ጦርነት የወደፊት ሥጋቶችና አሁን ስለሚታዩ ምልክቶች የጠቀሷቸው ነጥቦች ነበሩ፡፡ ከሥጋት ባሻገር ለኢትዮጵያ ተስፋ የሚሰጡ ጉዳዮችም በአሜሪካ ጋዜጦች እየተጻፈ ስለመሆኑ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በቢዝነስ ዓምዱ ያሰፈረውንም እነዚሁ ግለሰቦች በገጾቻቸው አጋርተዋል፡፡

ለዓለም የንግድ ጦርነት ሥጋት መንስዔ የሆነው መነሻ ምክንያት በአሜሪካ የተጀመረው የሸቀጦች የቀረጥ ዋጋ ላይ ማሻሻያ መደረጉ ነው፡፡ አሜሪካ ከቻይና በሚገቡ ሸቀጦች ላይ በተለያየ ጊዜ የጣለችው ቀረጥ አሁን ላይ 200 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ቻይናም ለአሜሪካ ምርቶች አጸፋዊ ምላሽ በመስጠት ከፍተኛ ቀረጥ እየጣለች ትገኛለች፡፡ አሜሪካ በቻይና ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ለመጣል የተገደደችው የቻይና ምርቶች በርካሽ ዋጋ ወደ አሜሪካ እየገቡ፣ የአገሬውን የማምረት አቅም አዳክመዋል የሚል መነሻ በመያዝ እንደሆነ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከመመረጣቸውም ቀደም ብሎ የሚያስተጋቡት አጀንዳ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወደ ቻይናም ሆነ ወደ ሌሎች አገሮች ማምረቻዎቻቸውን ነቅለው የሄዱ የአሜሪካ ኩባንያዎች ተመልሰው እንዲመጡ ሲያስጠነቀቁም ቆይተዋል፡፡ ይሁንና በታሪፍ ሰበብ ቻይናና አሜሪካ የተፋጠጡበት መንገድ ለሌሎች አገሮች ሥጋት መሆኑ አልቀረም፡፡ ምንም እንኳ ርካሽ ዋጋ ያላቸውን የቻይና ምርቶች በቀረጥ እንዲወደዱ በማድረግ አሜሪካውያን ሸማቾች በአገራቸው ምርት እንዲጠቀሙ የማድረግ ህልም ያነገበው የፕሬዚዳንት ትራምፕ ዕርምጃ፣ የዓለምን የንግድና የኢንቨስትመንት ሁኔታ ያናጋል፣ ዓለም ከአሥር ዓመታት በፊት በአሜሪካ ባንኮች አማካይነት ወደ ገባችበት ዓይነት የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ዳግም እንድትዘፈቅ ሊያስገድድ የሚችል አቅም ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ ዕውን ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየታዩ በመሆኑ፣ የዓለም ንግድ ጦርነት አይቀሬነት በስፋት እየተተነተነ ይገኛል፡፡

መነሻውን በጥር ወር ያደረገው የአሜሪካና የቻይና ፍጥጫ፣ አሜሪካ የዓለም ንግድ ድርጅት በሚፈቅዳቸው የንግድ ሕግጋት ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቁ መነሻ ምክንያቶችን በማቅረብ የጀመረችው ጥንስስ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከመነሻው ከቻይና ወደ አሜሪካ በሚገቡ የፀሐይ ኃይል ፓኔሎችና የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ላይ በአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ሥጋት የደቀኑ ተብለው የታሪፍ ወይም የቀረጥና የኮታ ገደብ የሚጥለው ዕርምጃ ቀስ ቀስ ወደ አሉሙኒየምና ብረት ምርቶች እየተዛመተ፣ አገሮች በድጎማ የሚያመርቱት ምርት እንደ ሸቀጥ ማራገፊያነት የሚታይበትን ምክንያት የሚያጣቅሱ አንቀጾች እየወጡ የንግድ ፍጥጫውን አክርረውታል፡፡ ሁኔታው እየተስፋፋ በመምጣቱም የአገሮቹን ፍጥጫ ሌሎችም ከተቀላቀሉት ወደ ለየለት የዓለም የንግድ ጦርነት ይወስዳል የሚለው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሥጋት እየበረታ መጥቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ፣ ዓመታዊ ሪፖርትም ይህንኑ ሥጋት አመላክቷል፡፡ በአገሮች መካከል የታየው የቀረጥና የንግድ ከለላ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን ሥጋት ላይ የሚጥልባቸው ምክንያቶችም ተብራርተዋል፡፡ የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ በየዓመቱ የሚያወጣውና ስያሜው ‹‹ንግድና ልማት ሪፖርት›› የዚህ ዓመት ትንታኔ ርዕሱን ‹‹ፓወር፣ ፕላትፎርም ኤንድ ዘ ፍሪትሬድ ዲሉዥን›› በማድረግ በሦስት ዋና ዋና መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ አቅርቧል፡፡ በዲጂታል ኢንዱስትሪና በንግድ ጦርነት ላይ በማድረግ የዓለምን ኢኮኖሚ ወቅታዊ ገጽታዎች አመላክቷል፡፡

ለኢትዮጵያና መሰሎቿ ሥጋት የሆነው የንግድ ጦርነት ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ የኢኮኖሚ ምሁራን ባቀረቡት መላምት መሠረት፣ ዓለም ወደ ለየለት የንግድ ጦርነት ውስጥ ብትገባ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ሸቀጦች ፈላጊ ሊያጡ እንደሚችሉ በተቋሙ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኃላፊዋ ሚስ ራሺሚ ባንጋ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ የሰጡት ትንታኔ፣ ኢትዮጵያ በንግድ ጦርነቱ ሳቢያ ተጎጅ ልትሆን የምትችልባቸው ምክንያቶችን አጣቅሰዋል፡፡

የንግድ ጦርነቱም ሆነ የታሪፍ ፍጥጫው ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ እንደሚያሠጋት ያብራሩት ሚስ ባንጋ፣ በዚህ ሳቢያም ሊደርስባት ስለሚችለው ተፅዕኖ ጠቅሰዋል፡፡ በቀጥታ ሊያጋጥማት ከሚችለው ተፅዕኖ ውስጥ አንደኛውና በሪፖርቱ ከተቀመጡት ይሆናሉ መነሻዎች መካከል የንግድ ጦርነቱ ከቀጠለና ሌሎች አገሮችም በዚህ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ መሆን ከጀመሩ የኢትዮጵያ ተጎጂነት አይቀሬ ስለመሆኑ ያብራሩት ምሁሯ፣ በዚህም ሳቢያ አጠቃላይ የምርትና የሸቀጥ ፍላጎት እንዲቀንስ የሚያስገድድ ሁኔታ እንደሚከሰት፣ አጠቃላይ ፍጆታና ኢንቨስትመንትም እንዲቀንስ የሚያስገድድ ክስተት እንደሚፈጠር አመላክተዋል፡፡

 ‹‹ይህ በሚሆንበት ወቅት እንደ አሜሪካና ቻይና ያሉ አገሮች ውስጥ ከውጭ ለሚገባ ምርትና ሸቀጥ የሚኖረው ፍላጎት ይቀንሳል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ላይ በቀጥታ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ በአጭሩ አገሮች ከውጭ የሚገባ ዕቃ የመግዛት ፍላጎታቸውን መግታት ይጀምራሉ፡፡ ኢትዮጵያም ለሸቀጦቿ ገዥ ታጣለች ማለት ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያው ትልቅ ተፅዕኖ ነው፤›› በማለት ሚስ ባንጋ ማብራራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ‹‹ሁለተኛው ፈተና በኢንቨስተሮች መተማመን ላይ የሚፈጠረው የሥነ ልቦና ተፅዕኖ ነው፡፡ ዓለም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መናጥ ስትጀምር፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች ሀብታቸውን ወደ ሌላ አካባቢ መውሰድ ይጀምራሉ፡፡ ካፒታል መሸሽ የሚጀመረው በዓለም የንግድ ጦርነት ሳቢያ በዶላር ላይ የሚታየው የዋጋ ሁኔታ እየጠነከረ፣ በሚካሄዱ ግብይቶች ላይም የወለድ ተመን እንዲጨምር ስለሚያስገድድ ለውጭ ኢንቨስተሮች ተስማሚ ሁኔታ አይፈጠርም፡፡ ሥጋትን የሚያባብስ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገቡ ዝቅተኛ የሥጋት ደረጃ ወደሚታይባቸው አካባቢዎች መሸሽን ይመርጣሉ፡፡ የነበሩት ብቻም ሳይሆኑ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውም ኢንቨስትመንት ይገታል አለያም ይቀንሳል፡፡ ለአብነት ከቻይና የሚመጣው ኢንቨስትመንት እንደ ቀድሞው ላይሆን ይችላል፡፡ ቻይና የምትሰጣቸው ብድሮችና ኢንቨስትመንቶቿ ላይ በድጋሚ ለማሰብ የሚያስገድዳት ሁኔታ ስለሚኖር፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች አገሮች ከምትሰጠው ገንዘብ ይልቅ በራሷ የኢኮኖሚ ዕድገትና እንቅስቃሴ ላይ መጠመድ ትጀምራለች፡፡ ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ ሥጋት ነው፡፡››

እንደ ሚስ ባንጋ ዕይታ ሦስተኛውና በንግድ ጦርነት ጦስ ኢትዮጵያ ላይ ሊመጣ የሚችለው ችግር የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ ከታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሸቀጦች ዋጋ ለኢኮኖሚ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ በብድር ድጋፍ የሚካሄድ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በአገሮች ውስጥ በስፋት መኖሩ በንግድ ጦርነት ጊዜ ሥጋት እንደሚያስከትል አብራርተው፣ ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ሳቢያ ችግር ውስጥ ልትወድቅ የምትችልባቸው ሁኔታዎች ሰፊ ስለመሆናቸው ተንትነዋል፡፡ የተመድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ባሰፈሩት ትንታኔ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ሸቀጦች በቀረጥ ሽኩቻው ሳቢያ እስከ 50 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ሊታይባቸው እንደሚችል ሥጋታቸውን አሥፍረዋል፡፡ ለወትሮው እያሽቆለቆለ የሚገኘው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚባለው እንዲህ ያለ ዓለም አቀፍ የሥጋት ቀለበት ውስጥ መግባቱ አሳሳቢነቱን ያንረዋል፡፡

ምንም እንኳ የተመድ የኢኮኖሚ ባለሙያዋና ባለደረቦቻቸው ወደፊት ሊመጣ ስለሚችለው ይህን ይበሉ እንጂ፣ ከሰሞኑ የወጣው የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ሪፖርት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ8.5 በመቶ ዕድገት ሊያስመዘግብ እንደሚችል ይፋ አድርጓል፡፡ በዚያም ላይ የቻይና ምርት በአሜሪካ ቀረጥ ሳቢያ ውድ እየሆነ መምጣቱ፣ ከዚህ ቀደም በሠራተኛ የጉልበት ዋጋ መወደድ ሳቢያ ከቻይና የሚሸሹ አነስተኛና መካከለኛ ኩባንያዎችን ቁጥር ሊያበራክት የሚችልበት አዝማሚያ እንደሚኖር በዚህም አጋጣሚም ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ የባንግላዴሽ፣ የቬትናም፣ የካምቦዲያና መሰል አገሮች ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ መስክ ተመራጭ የሚሆኑበት ዕድል እንዳለ የኒውዮርክ ታይምስን ዘገባ ካወሱት መካከል አቶ ሄኖክ አሰፋ፣ ‹‹ዕድሎች እየጠበቡ በመጡበት በዚህ ወቅት ምናልባትም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ይህ የመጨረሻው ዕድላችን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከዚህ በኋላ ሌላ ዕድል ማግኘታችን ያጠራጥራል፤›› በማለት ዘገባውን ተንተርሰው ሐሳባቸውን በትዊተር ገጻቸው አሥፍረዋል፡፡

አቶ ወንድወሰን መዝለቂያ ባሠፈረው ጽሑፉ፣ ካናዳ ከአሜሪካ አስመጪዎች በኩል ለምትገዛው ጥሬ ቡና እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ቀረጥ ሳታስከፍል እንደቆየች አስታውሶ፣ ነገር ግን በቅርቡ ከአሜሪካ በሚቀርብላት ቡና ላይ የአሥር በመቶ ቀረጥ መጣሏን አስታውቀዋል፡፡ ይህም አሜሪካ ከዚህ ቀደም በካናዳ ላይ ለወሰደችው ዕርምጃ አጸፋ እንደሆነና አንዳንዶችም የካናዳ ዕርምጃ ኢትዮጵያን ለመሰሉ ቡና አምራች አገሮች ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል እንደሚገልጹ ጽፈዋል፡፡ ካናዳ በአሁኑ ወቅት በዓመት ከአንድ ቢሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ የሚገመት ቡና በመግዛት የአሜሪካ፣ የአውሮፓና የጃፓን ገበያዎችን እየተፎካከረች እንደምትገኝ አቶ ወንድወሰን አስታውሷል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግ የዚህ ዘገባ አዘጋጅ ጥያቄውን በቲወተር በኩል አቅርቧል፡፡ በኢትዮጵያ የቡና የወጪ ንግድ ላይ የፍላጎት መቀነስ ወይም መጨመር ሊከሰት ይችል እንደሆነ፣ የቀረጥ እሰጣ አገባው በኢትዮጵያ ላይ ሊያስከትል ስለሚችለው ተፅዕኖ ላይ ለቀረበለት ጥያቄ ወንድወሰን መዝለቂያ እንዲህ ብሏል፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ሸቀጦች በተጣለው ቀረጥ ምክንያት በቀጥታ ተፅዕኖ ውስጥ አይወድቁም፡፡ የካናዳ በአሜሪካ የቡና ወጪ ንግድ ላይ ቀረጥ መጣልም እስከታችኛው ገበሬ ድረስ የሚያመጣውን መልካም አጋጣሚ ለመናገር ጊዜው ገና ነው፡፡ ይህ ቢሆን እንኳ ወደ ካናዳ የሚገባው ቡና አሁንም በአውሮፓ ገዢዎች በኩል መሆኑ አይቀሬ ነው፤›› በማለት መልካም ሊባል የሚችል አጋጣሚ ቢኖርም አፍን ሞልቶ ለመናገር ጊዜው አለመሆኑን አመላክቷል፡፡

ከግብርና ሸቀጦች ባሻገር ግን ከዓለም ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ በአወንታዊነት ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል በአገሪቱ እየተገነቡ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአፋጣኝ ተጠናቀውና የሚጠበቅባቸውን ምርት አምርተው ወደ ዓለም ገበያ በስፋት መግባት ካልጀመሩ ወደፊት የሚመጣው አደጋ ቀላል እንደማይሆን ምሁራኑም ሆኑ የቢዝነስ አማካሪዎቹ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች