በደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ በመካሄድ ላይ ያለውና ሁለተኛ ቀኑን የያዘው 11ኛው የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ፣ ዛሬ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ትናንት በቀረበለት የጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ ሪፖርት ላይና በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ አፈጻጸም ላይ ተሳታፊዎችን በቡድን ከፋፍሎ ሲያወያይ ዋለ፡፡
በቡድን የተደረገው ውይይት ትናንት የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ በ10ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች አፈጻጸም በተመለከተ ያቀረበው ሪፖርት ላይ ተንተርሶ የተደረገ ሲሆን፣ የተፈጸሙና ያልተፈጸሙ መመርያዎችን በመለየት ያልተፈጸሙት ለምን እንዳልተፈጸሙ ሲገመግም ውሏል፡፡ በዚህ በቡድን የተደረገው ውይይት ላይ የግንባሩ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዳልተሳተፉ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡