Wednesday, February 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገራችን የትምህርት ጥራት ውድቀት በቀላሉ የሚታይ አይደለም

ከበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

ክፍል ፪

ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጥራት መውደቅ ውጫዊና ውስጣዊ ነገሮች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ውጫዊው አስቀድሜ የጠቀስኩት የመንግሥት አላስፈላጊ ውሳኔዎች፣ የተማሪው ቅድመ ዝግጅትና አስተሳሰቡ፣ የተማሪዎች መብዛት፣ በዚያው ልክ ብቃት ያላቸው መምህራን አለመኖር፣ ቤተ ሙከራዎች አለማዳረስ ወዘተ. ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ውጫዊ ተፅኖዎች ቢኖሩም፣ የውስጡን ተፅዕኖ ብንፈታው የትምህርት ጥራትን ቁልቁል ከመውደቅ ልንከላከል በቻልን ነበር፡፡ ይኼንንም የምለው በደርግ ጊዜ ለዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው በጀት ከመምህራንና ከሠራተኞች ደመወዝ በስተቀር ብዙም አይመደብም ነበር፡፡ ለተለያዩ ምርምሮችም ሆነ ሥራ ማስኬጃ ዩኒቨርሲቲው በጀቱን የሚደጉመው፣ ከውጭ አገሮች እንደ ጀርመን፣ ስዊድን፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ወዘተ. ከመሳሰሉት በዕርዳታ ከሚያገኘው ነበር፡፡ በዚህ ኢምንት በሆነ ሀብት ላይ ግን ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት መስጠት ተችሎ ነበር፡፡ ለዚህም ዋናው በኅብረተሰብና በአመራሩ የነበረው ውስጣዊው ጥንካሬ ነበር፡፡ ይኼ እንዴት ተሸርሽሮ ለውድቀት ተደረሰ ቢባል በዋናነት የትምህርት አመራሩ በነፃ አለመሥራት፣ ተፅዕኖ ውስጥ ሆኖ አላስፈላጊ ድርጊቶችን እንደ የትምህርት ክፍሎች የሚፈልጓቸውን መምህራን ከመቅጠር ይልቅ፣ ከላይ ያለው የትምህርት አመራሩ የብሔር አስተዋጽኦ በሚል በነጭ ወረቀት ለማስተማር ብቁ ያልሆኑ መምህራንን መክተት፣ ልምድ ያለው (Senior) መምህር ካለሥራ ተቀምጦ ኮርስ ለማዳረስ በሚል መልክ ልምድ የሌለው (Junior) መምህር እንዲያስተምር ማድረግ፣ መምህራንን በብሔር መከፋፈል፣ አቅምና ፍላጎት ሳይዳሰስ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን መክፈት፣ መሪ ዩኒቨርሲቲዎችን መርጦ፣ ሌሎቹን እንዲያሳድጉ አለመደረግ፣ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ሳይጤን ከውጭ የተገለበጡ መመሪያዎች እንዲተገበሩ ማድረግ፣ አቅምን ያላገናዘቡ መመሪያዎች በቅድመ ምረቃ ትምህርት ላይ ማውጣት፣ ተገቢው መምህር ለተገቢው የትምህርት ዓይነት ትምህርቱን እንዲያስተምር አለመመደብ፣ የመሳሰሉትን መፈጸሙ ነው፡፡

 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ለመከፈት አቅምና ፍላጎት ሳይዳሰስ “ተማሪዎች እንዲመረቁ ብቻ እንጂ፣ ዕውቀት ለማስጨበጥ ያለው ብቃት ሳይታወቅ” ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲከፈቱ ሆነ፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በኢትዮጵያ  ሕዝብ አኳያ አሁን የተከፈቱት ዩኒቨርሲቲዎች ይበዙበታል ማለት አይደለም፣ እንዲያውም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት አኳያ ከዚህ እጥፍ መከፈት አለበት፡፡ ካለ በቂ ዝግጅትና አቅም መከፈታቸው ግን የትምህርትን ጥራት በከፍተኛ ደረጃ እንዲወድቅ ዋናው ምክንያት ሆኗል፡፡   

 እነዚህ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የተከፈቱት ለፖለቲካ ጥቅም እንጂ፣ ለአካባቢው ሕዝብ ብሎም ለአገሪቱ ዕድገት የሚያስፈልግ መሆኑ ተጠንቶ አይደለም፡፡ ለምሳሌም በአንዳንድ ቦታ ዩኒቨርሲቲዎች የተከፈቱት የእገሌ ክልል /ዞን/ ነዋሪ ዩኒቨርሲቲ ክፈቱልን ስላለ መንግሥት ጥያቄያቸውን ለመመለስ ነው ተብሎ ሲነገር ሰምተናል፡፡ የእገሌ ክልል /ዞን/ ነዋሪ ዩኒቨርሲቲ ክፈቱልን ስላለ ከፈትንለት ሲባል፣ ጥራቱን ማሳጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሌላ መዘዝም ይዞ መጣ፡፡ የክልል /ዞን/ ነዋሪ ፍላጎትን ለማርካት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት የሚሆነውን  ካለ ልሂቃን (Merit) ምንም ልምድ በዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ላይ የሌለውን ከሚቋቋምበት አካባቢ በመሾም ተሿሚውም የሌሎችን አገር ዩኒቨርሲቲዎች ታሪክ በማንበብ፣ የአዲስ አበባን ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ትምህርት እንዳለ በመገልበጥ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን ለመምህርነት በማሰባሰብ ወዘተ. ዩኒቨርሲቲ ከፈትኩ ይላል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የሚከፈቱት አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ይዘው የመጡት መዘዝ “የወንዜ ልጆች መፈንጫ” እንዲሆኑ፡ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ዩኒቨርሲቲዎች የፌዴራል መንግሥት አስተዳደር አካል ናቸው የሚለውን የትምህርት ፖሊስ በመሻር በክልል ዓይን አስተዳደራቸው፡፡ ይኼም “የወንዜ ልጆች” ዩኒቨርሲቲን እንዲመሩ ማድረጉ በኋላም የትምህርት ጥራቱን ከማጥፋቱም በላይ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የጎሳ ፖለቲካ እንዲለመልም በር ከፈተ፡፡ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች የመጡ ተማሪዎች በአንድ ቦታ በመሰብሰባቸው ኅብረ ብሔር የሆነችውን ኢትዮጵያ ከማሳየት “የወንዜ ልጆች አመራር” የብሔርን ፖለቲካ  በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመዝራት፣ አዲስ ተማሪዎች ሲመጡ ለመኝታ ቤት፣ ለፕሮጀክት ሥራ ወዘተ. በብሔረሰብ በመለየትና በመመደብ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች መሞቻ ቦታዎች ሆኑ፡፡  

ለዚህም ይመስላል የትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርሲቲ የሚመደቡትን አመራሮች ለመመልመልና ለመሾም፣ በአሁኑ ጊዜ መመሪያ አውጥቷል፡፡ የዚህ መመሪያ ችግር የሚጀምረው በሁለት ዓመት ውስጥ የተቋቋመውና ከ75 ዓመት በላይ የኖረውን ዩኒቨርሲቲ በአንድ ላይ ይመራ ማለቱ ነው፡፡ ለምሳሌም በአዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ አይገኙም ብሎ በመፍራት አመልካቾች ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሊወዳደሩ ይችላሉ አለ፡፡ በዚሁ መመሪያም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲገዛ አደረገ፡፡ እንግዲህ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ በውስጡ ምርምር ማካሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ታዲያ እንዴት ምርምር በበቂ ያልሠራውን ሁለተኛ ዲግሪ ብቻ የያዘ ፕሬዚዳንት ሊመራ ይችላል፡፡ ሌላው በዚሁ መመሪያ ውስጥ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን በዕድሜ መሥፈርት እንዳይወዳደሩ በማድረግ ልምድ ያላቸውን አገለለ፡፡ መንግሥት እንደ ለመደው የራሱን ሰው በማስቀመጥ አካዴሚውን ለመምራት እንዲያስችለው መንግሥትን በመወከል የሚሠራውን ቦርድ ምርጫውን እንዲያስፈጽም አደረገው፡፡ ትክክለኛ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ማስመረጥ ያለበት የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ነው፡፡ ባጠቃላይ የመመሪያው ዓላማ ያደረገው ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን አመራር እንዲመርጡ አመቻቸሁላቸው በሚል የአዞ እንባ የመንግሥትን እጅ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለማጠናከር ሲሆን፣ በዚህ ዓይነቱ ምርጫ የትምህርትና ምርምር ጥራት መውደቅን ሊቀንስ አይችልም፡፡

ሌላው በከፍተኛ ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዳይሰጥ ምክንያት የሆነው፣ መሪ ዩኒቨርሲቲዎችን መርጦ ሌሎቹን እንዲያሳድጉ አለመደረጉ ነው፡፡ በየአገሩ ያለው ልምድ ለምሳሌ በአንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በኮሪያ፣ በፈረንሣይ፣ ወዘተ. ውስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማርና በምርምር ደረጃ እኩል እንዳልሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ከ1000 በላይ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ቢኖሩም አገሪቱ ብቃት ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ብላ የምትመካባቸው ከ50 አይበልጡም፡፡ እንግሊዝም እንደዚሁ ነው፡፡ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ የሚመደብ ነው፡፡ እነዚህ በየአገሩ ያሉ ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች በቅንጅት ከመደበኛ ሥራዎቻቸው በተጨማሪ በማስተማርና በምርምር ደረጃ ውጤት አነስ ያሉትን ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በማጠናከር የአናሳ ዩኒቨርሲቲዎች አቅም ያሳድጋሉ፡፡ በአገራችን የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ተብሎ በጠንካራ መሠረት ላይ በመመሥረቱ ጠንካራ አቅም ፈጥሯል፡፡ ይኼም አቅም በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ እንዲቀመጥ አስችለውታል፡፡ ለዚህ ዩኒቨርሲቲ ትንሽ አቅም ጨምሮ የአገሪቱን ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገነባ ማስቻል ሲቻል፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ሊጠቀምበት አልፈለገም፡፡ እንዲያውም ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በመመደብ የተሻለ ዩኒቨርሲቲዎች እንገነባለን በሚል ከፍተኛ ሀብት መንግሥት ሲያባክን ነበር፡፡ በዓለም ላይ ያለው ልምድ በሀብት ብዛት አዲስ ከፍተኛ ብቃት ያለው ዩኒቨርሲቲ መገንባት እንደማይቻል ነው፡፡ ለዚህም ነው ኳታር በዓለም ላይ የሌለ ስታዲየም፣ ትልቅ ሕንፃ ወዘተ. ስትገነባ ዩኒቨርሲቲን ግን አልሞከረችውም፡፡ እዚህም በአገራችን ደርግ በአርባ ምንጭ አዲስ የትምህርት ተቋም ለመገንባት ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ ደርግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዚያኔው የቴክኖሎጂ ፋኩሊቲን ከአቅም በላይ የውኃ ተቋም እንዲያቋቁም ይጠይቃል፡፡ ፋኩሊቲውም  ‹‹ብቃቴ ገና ስለሆነ፣ ብቃቴን ለማሳደግ በጀት ይመደብልኝ?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ሊቀመንበሩ ኮሪያ ሄደው የውኃ ኢንስቲትዩቱን ተመልክተው ከመጡ በኋላ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይኼንን የማይሠራ ከሆነ በአርባ ምንጭ ላይ ከፍተኛ የውኃ ተቋም እንከፍታለን፤›› ብለው በመነሳት በዚያኔ አቅም ያለ የሌለውን የአገሪቱን ሀብት ቅድሚያ በመስጠት የውኃ ኢንስቲትዩት ተቋቋመ፡፡ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ መንግሥት ሲይዝ፣ ኢንስቲትዩት የያዘው ዕቃ ብቻ እንጂ፣ ኢንስቲትዩትን የሚያንቀሳቅሰው የሰው ኃይሉ ከሁለተኛ ዲግሪ በላይ ፈቀቅ አላለም፡፡ አሁንም መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን ማሳደግ ቀላል እንዳልሆነ ተረድቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሀብት አሟጦ ለመጠቀም ሰትራቴጂ በመቀየስ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እገዛ የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን አቅም ለማሳደግ ካልሠራ ዩኒቨርሲቲዎቹ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት አላስፈላጊ ብዙ ዓመታት መንቀሳቀስ ሊኖርባቸው ይችላል፡፡

ሌላው የከፍተኛ ትምህርት ጥራት መውደቅ ምክንያት አንዳንዶቹ የመጡት የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ሳይጤን በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ከውጭ ተገልብጠው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲተገበሩ የተላኩት መመሪያዎች ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ለትምህርቱ ጥራት ውድቀት ካስከተሉት አንዱ ተማሪን ያለማውደቅ ዘይቤ (Zero Attrition Rate) የሚለው የተሳሳተ ሐሳብ ‹‹መምህራኑ ተማሪዎችን እንዳይጥሉ ይኼ መመሪያ ይከለክላቸዋል፤›› የሚሉ ተማሪዎቹ ቄጥር በመብዛቱና “ባናጠናም እናልፋለን” በሚል ሰበብ ሳይዘጋጁ ለፈተና መቅረብ የተለመደ እየሆነ በዩኒቨርሲቲዎች መጥቷል፡፡ ከዚህም ጋራ ተመሳሳይ የሆነው የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ አነስተኛ ውጤት (የወደቀ ተማሪ) ያመጣውን ተማሪ፣ “መምህሩን ተማሪውን እንደገና አስተምረህ እንዲያልፍ አመቻች (Fix)” የሚለው ለትምህርት ጥራት በዩኒቨርሲቲ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገኙ ተማሪዎች ከሚያወጣቸው መመሪያዎች አንዳንዶቹ በተማሪዎቹ አላግባብ ከመተርጎማቸው የመጣ ነው፡፡ ከነዚህም የተሳሳተ ትርጓሜ ከሚሰጣቸው “ተማሪ ተኮር የትምህርት አመራር፣ መምህራንን መገምገም፣ የመመረቂያ ጽሑፍ አሠሪ መምህራን በተማሪዎቹ ይመረጥ፣ ወዘተ.” ሲሆኑ፣ እነዚህ ፖሊሲዎች ተማሪዎቹ ከአንዳንድ መምህራን ጋራ በነጥብ እንዲደራደሩ አስችለዋል፡፡ እዚህ ላይ መታየት ያለበት ሌላው “ተማሪን ያለማውደቅ ዘይቤ (Zero Attrition Rate)” የሚለው ፖሊሲ ነው፡፡ ተማሪዎቹ በዚህ ላይ የተሳሳተ ሐሳብ በመውሰዳቸው ማለትም መምህራኑ ተማሪዎችን እንዳይጥሉ ይኼ መመሪያ ይከለክላቸዋል በሚል አብዛኛው ተማሪዎች “ባናጠናም እናልፋለን” በሚል ሰበብ ሳይዘጋጁ ለፈተና መቅረብ የተለመደ እየሆነ በዩኒቨርሲቲ መጥቷል፡፡ ከዚህም ጋራ ተመሳሳይ የሆነ ፖሊሲ፣ አነስተኛ ውጤት (የወደቀ ተማሪ) ያመጣውን ተማሪ፣ “መምህሩን ተማሪውን እንደገና አስተምረህ፣ እንዲያልፍ አመቻች (Fx)” የሚለው ዋና የትምህርት ጥራት ጉዳይ ሆኖ በዩኒቨርሲቲዎች እየተካሄደ ያለ ነው፡፡ ሌሎች ፖሊሲዎች በዩኒቨርሲቲው ግርምት ያስከተሉት “አንድ ለአምስት መቧደን፣ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አንድ ዓይነት መርሐ ግብር፣ የመምህራን ቅጥር አስተዳደር፣ አንድ ዓይነት የዩኒቨርሲቲ ሹማምንት ምልመላ ወዘተ.” ከሚሰጡት ጥቅም ይልቅ፣ ጭቅጭቁ ስለሚበዛ መተው አለባቸው፡፡

አቅምን ያላገናዘበ በትምህርት ሚኒስቴር ከወጡት መመሪያዎች ውስጥ ከሚጠቀሱት በቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ እንዲካተት የተደረገው በኢንዱስትሪ ውስጥ ቢያንስ ለአንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተማሪዎች የተግባር ትምህርት እንዲያገኙ ማድረጉ ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ተማሪዎች የተግባር ትምህርት ለሥራቸው ቅርብ በሆኑ ሙያዎች ላይ እንዲያገኙ ማድረግ በአብዛኛው አገሮች የተለመደ ስለሆነ እኛም አገር መተግበሩ የሚቃወም የለም፡፡ ችግሩ ያለው መመሪያው ወጣ እንጂ፣ እንዴት እንደሚፈጸም በሚመለከታቸው አካላት የተሠራ ሥራ የለም፡፡ በዚህም  በተማሪዎቹ፣ በዩኒቨርሲቲው፣ በኢንዱስትሪው፣ ቅንጅት አለመኖርና ከግንዛቤ ዕጦት የተነሳ ብዙም ውጤት አላመጣም፡፡ ተማሪዎች ይላካሉ፣ ፋብሪካው ውስጥ የሚያስችለው ከዩኒቨርሲቲም ሆነ ከኢንዱስትሪ የተወከለ አጠገባቸው ስለ ሌለ ግቢው ውስጥ ሲዞሩ ከርመው ሠርተዋል ተብሎ ማረጋገጫ ይዘው ይመጣሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተመደበው መምህር አንድም ቀን ከፋብሪካው ሳይሄድ ማረጋገጫ ይቀበላል፡፡ የኢንዱስትሪው ችግር ከዚህ የላቀ ነው፡፡ በመሠረቱ በሳይንስና በኢንጂነሪንግ የተማሩ ምሩቃን፣ የሚያገለግሉት በኢንዱስትሪው ውስጥ በመሥራት ነው፡፡ በዚህም ኢንዱስትሪው የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል አገኘ ማለት ነው፡፡ ይኼ የሰው ኃይል ብቃት ይዞ እንዲወጣ ኢንዱስትሪው የሚፈልገው ነው፡፡ ስለዚህ ኢንዱስትሪው ዩኒቨርሲቲውን በመማር ማስተማር እንዲደግፍ የውዴታ ግዴታ አለበት፡፡ ይኼ በዚህ እንዳለ የትምህርት ሚኒስቴር በኢንዱስትሪ ውስጥ የሙያ ማጎልበቻ ሥልጠና መሰጠት አለበት ብሎ ፖሊሲ ሲያወጣ፣ በመንግሥትና በኢንዱስትሪ ሊኖር የሚገባውን ሰጥቶ መቀበል አላየሁም፡፡ ኢንዱስትሪው ተማሪ ሲላክበት፣ የሥራ ሒደቴን ያደናቅፍብኛል አልቀበልም ነው መልሱ፡፡ የኢንዱስትሪው ዓላማ ጥራቱን ጠብቆ በማምረት ተወዳዳሪ መሆን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በተማሪ ሥራ አይመጣም፡፡ ይኼንን ማካካሻ ተማሪዎች ሲላኩለት ከመንግሥት ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ለሚቀበለው ተማሪ፣ “የሆነ የታክስ ቅናሽ” በዚህና በሌሎች ምክንያት የዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ትስስር የተማሪ የተግባር ሥልጠና እንደገና ተፈትሾ በሕግ በማውጣት የትምህርቱን ጥራት በሚያስጠብቅ ሁኔታ መዘጋጀት አለበት፡፡ በዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት መውደቅ ምክንያት ከሆነው አንዱ የትምህርት ክፍሎች ተገቢው መምህር ለተገቢው የትምህርት ዓይነት ትምህርቱን እንዲያስተምር አለመመደባቸው ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድን ትምህርት ለማስተማር መምህሩ በሦስተኛ ዲግሪ የተመረቀ መሆን አለበት፡፡ ይኼንን በአገራችን ለማግኘት ስለሚያስቸግረን መምህሩ ቢያንስ ከሚያስተምረው ትምህርት በአንድ ዲግሪ ከፍ ብሎ ልምድ የያዘ መሆን አለበት፡፡ ይኼም ማለት የቅድመ ምረቃን ትምህርት የሚያስተምር መምህር ልምድ ያለው በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቀ መሆን አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው መምህር የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪን ሊያስተምር አይችልም፡፡ ሁለተኛ ዲግሪ ያለው መምህር የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪን ሊያስተምር አይችልም፡፡ ወዘተ. ”በአገራችን ያሉት አብዛኛዎቹ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች“ መጀመሪያ ዲግሪ ያለው መምህር የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪን” ነው የሚያስተምረው፡፡ ይኼም በነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች አጠራር  “እየተማርን እናስተምራለን”  ነው የሚባለው፡፡ በዚህም ምክንያት እዚህ አካባቢ የትምህርት ጥራት ይመጣል ተብሎ ሳይሆን፣ የሚጠበቀው ለትምህርቱ አስተማሪ መገኘቱና ተማሪዎቹ የተመደበላቸውን ጊዜ አጠናቅቀው ዲግሪ ሰጥተናቸዋል የሚለው ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጥራት መውደቅ የመምህሩ ሚና ከሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የተለየ የሚያደርገው ያሉትን መምህራን የትምህርት ጥራት እንዲያስጠብቁ ሆነው አለመመደብ ነው፡፡ ሁለተኛ ዲግሪ ያለው መምህር በግዴታ “ማስተማር (Course መያዝ)” አለበት፡፡ ይኼ አካሄድ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪም በብዛት የሚታይ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ አንድ የዩኒቨርሲቲ ሙያ ለምሳሌ በባዮሎጂ መሠረታዊ ትምህርት የሚገኘው በመጀመሪያ ዲግሪ ላይ ነው፡፡ በባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ አለኝ የሚል ሰው፣ የባዮሎጂን ትምህርት ያውቃል፣ በዚህም በተወሰነ የሥራ ሥልጠና ለመሥራት ብቁ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዩኒቨርሲቲዎች ይኼንን መሠረታዊ ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ተባባሪና ሙሉ ፕሮፌሰሮች መሆን አለባቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግን በአብዛኛው በአሁኑ ጊዜ ተባባሪና ሙሉ ፕሮፌሰሮቹ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች አስተማሪዎች ሆነዋል፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ለማስተማር ተባባሪና ሙሉ ፕሮፌሰርነት እንደሚጠይቅ ዕሙን ቢሆንም፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ላይ የሚሰጠው ትምህርት፣ ዕውቀትን ለማሳደግ “Advanced Courses” ነው እንጂ መሠረታዊ ትምህርት የሚማርበት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛው የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎቹ በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው፤ ፕሮፌሰሩ አጭር መግቢያ ይሰጣል፡፡ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎቹ ማጣቀሻን ዋቢ በማድረግ ግብረ መልስ ይሰጣሉ፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች በተለይ አድገዋል ከሚባሉ አገሮች የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት የምርምር ሥራ ውጤት እንጂ ክፍል ተገብቶ መማር “Course Work” የሌለው፡፡ ታዲያ ለምን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “Course Work” አካተተ ለሚለው መልሱ በአገራችን የሚሰጠው የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ጥራቱ የወደቀ ስለሆነ እሱን ለማካካስ Course Work” እንዲኖር ተደረገ፡፡ ለመሆኑ ፕሮፌሰሮቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስተማር ሲገባቸው እንዴት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስተማር ትተው ወደ  ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተሸጋገሩ የሚለው መልስ ማግኘት ተገቢ ነው፡፡ መልሱ የተያያዘው ከትምህርት ክፍሎች ኃላፊዎች /ዲኖች/ እና ከራሳቸው ከፕሮፌሰሮቹ ነው፡፡ የትምህርት ክፍሎች ኃላፊዎች ብዛት ያላቸው ጀማሪ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች መምህራን ስላሏቸው /እነሱም የዚሁ አካል ስለሆኑ/ “Course” ማዳረስ አለብን በሚል ለትምህርት ጥራት ባለማሰብ የሚያደርጉት ነው፡፡ አንዳንድ ፕሮፌሰሮቹ ደግሞ የሚያዛቸው የሚመድባቸው ስለሌለ “ስንፍናና ግዴለሽነት ተጨምሮ” ሳያውቁት በትምህርቱ የማይተማመን ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡  

ማጠቃለያ

 ከላይ የቀረበው ጽሑፍ ለ38 ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት በትምህርት ክፍል ኃላፊነት፣ በዲንነትና በሴኔት አባልነት በቆየ መምህር የተዘጋጀ ነው፡፡ ጸሐፊው በአገር ውስጥ ካካበተው በተጨማሪ በውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ካካበተው ልምድ ተነስቶ ያቀረበው የትምህርት ጥራት መውደቅ የግል አመለካከት እንጂ፣ በትምህርት ሙያ ተምሮ ዲግሪ ይዞ በሳይንሳዊ ሙያ ተንተርሶ አይደለም፡፡ በሳይንሳዊ ሙያ ብቻ ተንተርሰን የአገራችንን ትምህርት ችግር እንፈታለን ካልን አቅም ስለማይኖረን ብዙም ፈቀቅ ልንል አንችልም፡፡ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የሳይንሳዊ ሙያን እንደ ግብ አስቀምጠን፣ ከዕለት ዕለት አሠራራችን ላይ ማስተካከያ በማድረግ የትምህርቱን ጥራት መውደቅ ለመቀነስ መንቀሳቀስ አለብን፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ፍፁም የሆነ የትምህርት ጥራት ማምጣት እንደማይቻልና አባባሉ አንፃራዊ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ኮሪያ ወዘተ. ሁል ጊዜ የሚሉት በዘገባቸው ላይ የአገራቸው ትምህርት ጥራት ይጎድለዋል ነው››፡፡

የትምህርትን ጥራት ለማምጣት የችግሩን ምንጭ ነቅሰን ማውጣት አለብን፡፡ መታወቅ ያለበትም ለተለዩት ችግሮች አንዴና ለሁሌም መፍተሔ እንሰጣለን ብለን ከተነሳን፣ ከችግሩ ብዛት የተነሳ ብዙም ላንራመድ እንችላለን፡፡ ችግሩ በአገሪቱ እያደገ ያለው የሕዝብ ብዛትና ከዚሁ ጋራ ተያይዞ የሚመጣው ድህነት ብሎም የአገሪቷ አቅም ውስንነት የትምህርት ጥራት ጥያቄ ሁሌም አብሮን የሚሄድ ነው፡፡ በተቻለ መጠን የባለድርሻ አካላት የሚባሉት የተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የትምህርት አመራር፣ የወላጆች፣ የቀጣሪዎች፣ የመንግሥት፣ ባጠቃላይ የኅብረተሰቡ ወዘተ. ትብብር በመጠቀምና የአገሪቱን ውስን ሀብት ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ በመጠቀም ሊከተሉ የሚችሉ የትምህርት ጥራት ጉድለትን ልንከላከል እንችላለን፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የትምህርት ጥራት መውደቅ ለመቀነስ፣ በተቋማት አካባቢ ያሉትን ችግሮች መፍታት ይጠበቅብናል፡፡ ያገባኛል ባዮች የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት ለሟሟላት መተግበር ከሚጠበቁት ዓብይ ጉዳዮች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

 • መንግሥት የአገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ መርምሮ አሳሪና ለትምህርት ጥራት መውደቅ ምክንያት የሆነውን ማውጣትና የትምህርት አመራሩ ከመንግሥት ጣልቃ ውጪ እንዲሠራ ማረጋገጥ፡፡
 • በሁሉም የትምህርት ተቋማት መምህርነት በኅብረተሰቡ ዘንድ የተከበረ ሆኖ አመኔታ እንዲያገኝ ከቃላት በዘለለ ተጨባጭ ሥራ በመምህራን ምልመላ፣ አሠለጣጠን ብቁ ደመወዝ፣ ጥቅማ ጥቅም ወዘተ. ላይ መንግሥት መሥራት፡፡
 • የትምህርት ፖሊሲ የሚያወጡና የሚመሩ የመንግሥት ተሿሚዎች የሚመደቡት ከፍተኛ ልምድ በማስተማር ሙያ ያካበቱና በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ክብር ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ፡፡
 • በማንኛውም  የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚመደቡ ኃላፊዎች ብቃት ብቻ ዋነኛ መሥፈርት ሆኖ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ ወዘተ. ላይ ያልተመሠረተ ማድረግ፡፡
 • ተማሪዎች ዋና ተግባራቸው መማር ነው፡፡ ሰብአዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው መንግሥት በፖሊሲው ውስጥ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በትምህርትና  በነጥብ አሰጣጥ ውሳኔ ላይ የተማሪዎች ሚና እንዳይኖር ማድረግ፡፡
 • በአገሪቱ ባሉት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አንድ ዓይነት ሙያዎች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ሙያዎች ከአገሪቱ ልማት ጋር ተመጣጣኝ ለማድረግ ያሉትን የትምህርት ሙያዎችን በየዩኒቨርሲቲዎች ለይቶ የበዙትን ወደ ሌሎች ሙያዎች መለወጥ፡፡
 • በአነስተኛ ግብዓት ጭማሪ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ሊሰጡ የሚችሉ ዩኒቨርሲቲዎችን በማሳደግ እነሱ አካባቢያቸው ያሉትን ዩኒቨርሲቲዎች እንዲያሳድጉ ማቆራኘት፡፡
 • አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አቅም እንዳለው ዕውቅና ተሰጥቶና በራሱ እንዲተዳደር ቻርተር ተሰጥቶትና በውስጡ የሚገኙትን ትምህርት ክፍሎች እንዲያጠናክር ተደርጎ፣ ለጊዜው እሱ ብቻ በአገሪቱ ውስጥ የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር እንዲሰጥ ማድረግ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከአንድ ክፍል በላይ የቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር እንዳይኖር መከልከል፡፡
 • ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውጪ ያሉት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር (የመጀመሪያ ዲግሪ) ብቻ እንዲሰጡ ማድረግ፡፡
 • የትምህርት አመራሩ የብሔር አስተዋጽኦ በሚል፣ በነጭ ወረቀት ለማስተማር ብቁ ያልሆኑ መምህራንን መክተት፣  ልምድ ያለው (Senior) መምህር ካለ ሥራ ተቀምጦ ኮርስ ለማዳረስ በሚል መልክ ልምድ የሌለው (Junior) መምህር እንዲያስተምር ማድረግ፣ መምህራንን በብሔር መከፋፈል ወዘተ. መተው፡፡
 • የመንግሥት የትምህርት አመራሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላይ ሲያንፀባርቅ የነበረውን ጥላቻ፣ ማናናቅ፣ ወዘተ. ትቶ መምህራኑ እየፈለሱ እንዳይሄዱ ማበረታቻ በማድረግና ለዩኒቨርሲቲው በቂ ሀብት በመመደብ ዩኒቨርሲቲው ለአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ማደግ ዋናው አውታር መሆኑን መንግሥት አምኖ በመቀበል ተልዕኮውን እንዲያስፈጽም ማስቻል፡፡
 • የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዴት ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን ማሳደግ እንዳለበት ዝርዝር መርሐ ግብር ማውጣትና ለተፈጻሚነቱም መሥራት፡፡
 • የከፍተኛ ትምህርት ተቋም     ኃላፊዎች ዲኖች፣ ፕሬዚዳንቶች ወዘተ. የሚመደቡት በወገናዊነት ሳይሆን፣ በሙያው የሠሩና በቂ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ በተመሳሳይ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የሚመሩ ኃላፊዎች የሚመደቡት በመንግሥት ሳይሆን፣ በትምህርት ቤቶች ለብዙ ዓመት ልምድ በማስተማርና በመምራት ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ፡፡
 • የዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ትስስር የተማሪ የተግባር ሥልጠና እንደገና ተፈትሾ ሕግ በማውጣት የትምህርቱን ጥራት በሚያስጠብቅ ሁኔታ መሰጠትን ማረጋገጥ፡፡ ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ (ዶ/ር- ኢንጂነር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ   የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles