ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከንቲባው የተለያዩበት የወቅት አጠራር
‹‹የክረምቱን ዶፍና ጨለማ ያሸጋገረን አምላክ ይመስገን፤ ኢሬቻ የፀደይ በረከት የምንቋደስበት…›› በማለት ባለፈው ሳምንት ለተከበረው የኢሬቻ የምስጋና በዓል የመልካም ምኞት መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከኢሬቻ በኋላ ክረምት ሲያበቃ የሚመጣው የ‹‹ፀደይ›› ወቅት ነውን? በደራሲነትና በሥነ ጽሑፍም የሚታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ1966 ዓ.ም. ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹እሳት ወይ አበባ›› በተሰኘው የግጥም መድበላቸው ስለመስቀል ደመራ በጻፉት ግጥማቸው ‹‹በራ የመስቀል ደመራ…ፀደይ አረብቦ›› ብለው ከመስቀል በዓል በኋላ የሚመጣው ወቅት ፀደይ እንደሆነ ያስቀመጡትን ተጋርተውታል፡፡ ስለዘመን አቆጣጠር የሚያስተምረን ባሕረ ሐሳባችን ግን ‹‹ፀደይና ደመራ›› ‹‹ፀደይና ኢሬቻ›› እንደማይገናኙ ያሳየናል፡፡ ደመራና ኢሬቻ በመጋቢት ወር ካልተከበሩ በቀር የሚሆን ነገር አይደለም፡፡
የዘንድሮው የመስቀል ደመራ መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ሲከበር የተገኙትና ችቦውን ከመለኮሳቸው በፊት ዲስኩር ያሰሙት የአዲስ አበባ ከንቲባ ታከለ ዑማ የሃይማኖት በአባቶችን ጨምሮ ብዙዎች ‹‹ፀደይ›› ብለው የሚስቱትን ከክረምት በኋላ የሚመጣውን ‹‹መፀው››ን በትክክል ጠርተውታል፡፡
አዲስ ዓመት ከባተ፣ መስከረም ከጠባ ዛሬ 27ኛ ቀን ላይ ይገኛል፡፡ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ የክረምቱ ወቅት አብቅቶ የአበባና የነፋስ ወቅት የሆነው መፀው ከተተካ ሁለተኛ ቀን ሆኗል፡፡
ትናንት መስከረም 26 ቀን የተጀመረው መፀው የአበባ ወቅት፣ እስከ ታኅሣሥ 25 ቀን ድረስ ለ90 ቀን የሚቆይ ሲሆን ሌላው መጠርያ መከር ይሰኛል፡፡
ከታኅሣሥ 26 በኋላ የሚመጣው በጋ ሲሆን፣ ዘመኑን መጋቢት 25 ቀን ከፈጸመ በኋላ በማግስቱ ለፀደይ ያስረክባል፤ ፀደይም እስከ ሰኔ 25 ቆይቶ በማግስቱ ለክረምት ቦታውን ይለቃል፡፡ ቀለልና ለስለስ ያለ ዝናብ የሚኖርበት በልግ በከፊል በጋ ላይና ፀደይ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡
የዘመን አቆጣጠሯ መነሻና መድረሻ የወቅት አከፋፈልና ስያሜ ተጠንቅቆ አለመያዙና በቅጡ አለመተላለፉ ከላይ የተጠቀሰው መንደርደርያ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በሥነ ጽሑፍ ታሪክ ከፍታ ላይ የተቀመጠው የሐዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከመቃብር ልብ ወለድ (ገጽ 91) ስለፊታውራሪ መሸሻ ግቢ መልክዐ መሬት በተገለጸበት ምንባብ ውስጥ ከአራቱ ወቅቶች አንዱ እንዲህ ተገልጿል፡፡
… በወፍራምና በቀጭን አስማምተው እየዘመሩ ካበባ ወዳበባ ይዘዋወሩ የነበሩ ንቦችና አንድ ጊዜ በፍሬ ተክሎች ዙሪያ ሌላ ጊዜ በሜዳው በተነጠፈው ያበባ ምንጣፍ ላይ በየጉዋዳቸው እየዞሩ ይጨፍሩ የነበሩ በጸደይ የሚመጡ፣ ጌጠኛ ብራብሮች ሲታዩ ያ ከልምላሜና ከመአዛ ከውበትና ከለዛ ድርና ማግ የተሰራ ጸደይ ያ የክረምትን ቁርና የበጋን ሀሩር የማያሰማ ጸደይ ባጭር ጊዜ የሚያልፍ መሆኑን በመረዳት ሳያልፍ እናጊጥበት ሳያልፍ እንደሰትበት፣ ሳያልፍ እንስራበት ብለው የሚጣደፉ ይመስሉ ነበር፡፡
አቶ ሐዲስ ከ63 ዓመት በፊት በጻፉት በዚህ ድርሰት በምናባቸው የሣሉት የወርኃ መስከረምን፣ ክረምት መሰስ ብሎ ካለፈ በኋላ የሚታየውን ነፀብራቅ ነው፡፡ ፀደይ በክረምትና በበጋ መካከል የሚመጣ አድርገው ሥለውታል፡፡
አቶ ሐዲስ ፍቅር እስከ መቃብርን በጻፉ በሦስተኛው ዓመት ባለቅኔውና ጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅንም በአንድ ግጥማቸው (በ1966 ዓ.ም. በታተመው ‹‹እሳት ወይ አበባ›› መድበል ውስጥ ይገኛል) ‹‹በራ የመስቀል ደመራ ፀደይ አረብቦ›› የሚል ይገኝበታል፡፡ የመስቀል ደመራ መስከረም 17 ከተለኮሰ በኋላ የነበረውን ክረምት ለመተካት ፀደይ ክንፉን ዘርግቶ እየጠበቀ ለመሆኑ የሚጠቁም ነው፡፡
ሁለቱ ዕውቅ ደራስያን ሐዲስና ጸጋዬ ዐደይ አበባ የሚፈነዳባት፣ ቢራቢሮዎች፣ ንቦች የሚፈነጥዙበት ከክረምት በኋላ የሚመጣው ‹‹ፀደይ›› ነው ብለው መጻፋቸው ነው ስህተቱ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ እንዲመጣ ያደረገው፡፡ ይሁን እንጂ ሎሬት ጸጋዬ በኋላ ላይ ‹‹ኢልማ አባ ገዳ›› በሚለው በሲዲ በተሰራጨው ቅኔያቸው ከክረምት በኋላ የሚመጣው ‹‹መፀው›› መሆኑን በጽሑፋቸው በድምፃቸው ጭምር አስቀምጠውታል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አርትስ ፋኩልቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል በዮናስ አድማሱ፣ ሀብተማርያም ማርቆስ፣ ዮሐንስ አድማሱና ኃይሉ ፉላስ ተዘጋጅቶ ‹‹አማርኛ ለኮሌጅ ደረጃ የተዘጋጀ›› ተብሎ የቀረበው ጥራዝ፣ ‹‹በምንባቡ ውስጥ አቶ ሐዲስ ‘ፀደይ’ ያሉት ‘መፀው’ መሆን አለበት፤›› ብሎ የሰጠው ማስተካከያ ከደራሲውም፣ ከብዙኃኑም የደረሰ አለመሆኑ መጽሐፉ በተደጋጋሚ ሲታተም ማስተካከያ አለመደረጉ፣ የዜማ ግጥም ደራሲዎችም መረጃው ስላልኖራቸው በዘፈኖቻቸው መስከረምና ፀደይን፣ ፀደይና ዐደይን እያያዙ መዝለቁን አልሰነፉበትም፡፡
ዘመን ከሚሞሸርባት፣ ዓመት ከሚቀመርባት ከወርኃ መስከረም የሚነሣው የኢትዮጵያ ዓመት ቁጥር በአራት ወቅቶች የተመደበ ነው፡፡ አራቱ ወቅቶች (ዘመኖች) ክረምትና በጋ፣ መፀውና ፀደይ ናቸው፡፡
ክረምት፡– ዝናም፣ የዝናም ወራት ማለት ነው፡፡ ከሰኔ 26 ጀምሮ የሚገባ ያመት ክፍል ነው፡፡ እስከ መስከረም 25 ቀን ድረስ ይዘልቃል፡፡
መፀው፡– ትርጉሙ አበባ ማለት ነው፡፡ መገኛው ግስ ‹‹መፀወ›› አበበ፣ አበባ ያዘ ዘረዘረ፣ ሊያፈራ ማለት ነው፡፡ ጸገየ (አበበ) ብሎ ጽጌ (አበባ) ይጠቅሳል፡፡ አፈሊቅ አክሊሉ ገብረኪሮስ ‹‹ለኢትዮጵያ ታሪኳ ነው መልኳ›› በሚለው ድርሳናቸው እንዳመሠጠሩት፣ የክረምት ተረካቢው መፀው የተባለው ክፍለ ዘመን እንደ ክረምት የውኃ ባሕርይ ያፈላል፡፡ ይገናል፡፡ እንቡር እንቡር ይላል፤ ይዘላል፤ ይጨፍራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ወንዞች ይመላሉ፡፡ ምንጮች ይመነጫሉ፡፡ አዝርዕትና አትክልት ሐዲሳን ፍጥረታት ሆነው ይነሳሉ፡፡ ይበቅላሉ ይለመልማሉ፡፡
አበባና ነፋስን ቀላቅሎ የያዘው ዘመነ መፀው ምሥጢሩ መዓዛ መስጠት፣ እንቡጥና ፍሬ ማሳየት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
የወቅትን ጥንተ ነገር እንደ ሌሎች ደራስያን ያልሳቱት ዕውቁ ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ የመፀውን መስከረምነት፣ ጥቅምትነት ኅዳርነትና ታኅሣሥነት ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት ተቀኝተውበታል፡፡ ከውበት ጋር በማያያዝ ጭምር፡፡ ርዕሱ ‹‹ይሰለቻል ወይ?›› የሚል ነው፡፡
ይሰለቻል ወይ?
የመፀው ምሽቱ አብራጃው ሲነፍስ
የኅዳር የጥቅምት የትሣሥ አየር
ጨረቃ አጸድላ ተወርዋሪ ኮከብ ሲነጉድ ሲበር
ይሰለቻል ወይ?
በክንድ ላይ ሁና
ብላ ዘንጠፍ ዘና
ሶባ ቀዘባዋ የሚያፈቅሯት ልጅ
ፍቅር ሲፈነድቅ ሲሠራ ሲያበጅ
ይሰለቻል ወይ?
የውበት የፍቅር የሐሴት ሲሳይ፡፡
አደይ አበባንና አበባን፣ እሸትንና ነፋስን አማክሎ የያዘው ዘመነ መፀው ለሠዓልያን፣ ለዘማርያን፣ ለደራስያን፣ ለሙዚቀኞች፣ ለድምፃውያን ሰበበ ድርሰት ለመሆን ታድሏል (አንዳንዶች ከፀደይ ጋር ቢያደባልቁትም)፡፡
በጋ፡- ወቅቱ ሐሩራማ፣ ደረቃማ ነው፡፡ ደረቅነት የሚፀናበት፣ የሚግልበት የሚጋይበት ስለሆነም ሐጋይ ይባላል፡፡ ታኅሣሥ 26 ቀን ገብቶ መጋቢት 25 ይወጣል፡፡ በጋ በመፀውና በፀደይ መካከል የሚገኝ በመሆኑም ሦስቱም በአንድነት በጋ የሚባሉበት አግባብ አለ፡፡ ‹‹ዘጠኝ ወር በጋ ሦስት ወር ክረምት›› እንዲሉ፡፡
ፀደይ
በጋ እንደተፈጸመ የሚከተለው ወቅት ፀደይ ነው፡፡ ከመጋቢት 26 ቀን እስከ ሰኔ 25 ቀን ድረስ ይዘልቃል፡፡ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ፀደይን፣ አጨዳ፣ የአጨዳ ወራት ዘመነ በልግ ይለዋል፡፡ በወዲያ መከር በወዲህ በልግ የሚደርስበት የሚታጨድበት ወዲያውም የሚዘራበት ወርኃ ዘርዕ (የዘር ወር) ሲልም ያክልበታል፡፡ በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት የሚዘንበው ዝናብ የበልግ ዝናብ፣ በመባልም ይጠራል፡፡
‹‹ፀደይ በመስከረም? ወይስ በመጋቢት? በፈረንጅ ወይስ በአበሻ?›› በሚል ርዕስ ሐተታ የጻፉት አፈሊቅ አክሊሉ እንደገለጹት፣ ዛሬ ግን አንዳንድ ሰዎች በአውሮፓ ክፍለ ዘመን እየተመሩ ፀደይ በመስከረም 26 ቀን የሚገባው ክፍለ ዘመን ስም ነው እያሉ ያቀርባሉ፡፡
መምህራን ፀደይ በጥቅምት በኅዳር ነው አይሉም፤ የአቡሻሕርና የመርሐ ዕዉር ቁጥር መምህራን፣ ድጓ ነጋሪዎች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ፀደይ በመስከረም መጨረሻ ይገባል አይሉም፡፡ አይከራከሩበትም አይለያዩበትም፡፡ ፀደይ የሚገባው በመጋቢት 26 ቀን ነው ማለትን አይክዱም አያስተባብሉም፡፡ ክፍለ ዘመናችንም ከፈረንጆች ክፍለ ዘመን መለየቱን ገልጠው ያስረዳሉ፡፡ እኛ መፀው ስንል ፈረንጆች ፀደይ ገባ ይላሉ እያሉ የክፍለ ዘመናችንን ልዩነት ሐተታ ያብራራሉ፡፡ መጻሕፍቱም ይኼንኑ ይመሰክራሉ፡፡
ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ክፍለ ዘመናችንን ለምን ያዘዋውሩታል? ፀደይ ማለት በልግ ማለት እንደሆነ እየታወቀ፣ የበልግ ዝናብ ዘንቦ ገብስ ዘንጋዳ ማሽላ በቆሎ የሚዘራበት ወራት ከፊታችን ቁሞ ነገሩን ቀምሞ እየመሰከረ አደናጋሪ ነገር መምጣት ምን ይጠቅመናል? ይልቅስ ‹‹ወረጎ መሬት›› ማለት መሬት የሚሰባበት የሚወፈርበት የሚዳብርበት ወራት መሆኑን መገንዘብ መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ አስረግጠው ያሳስባሉ፡፡