Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊለዓይን ተስፋ

ለዓይን ተስፋ

ቀን:

የ65 ዓመቱ አዛውንት ካጠገባቸው ከተቀመጡት ሦስት ሰዎች በተለየ ከመቀመጫቸው  ተነስተው ከነበሩበት የአውሮፕላን ክፍል ወደ ሌላኛው ይራመዳሉ፡፡ እጃቸውን አጣምረው መለስ ቀለስ እያሉ ተራቸው እስኪደርስ ይጠባበቃሉ፡፡ ሰውየው ከአውሮፕላኑ የተገኙት ወደ አንድ ሥፍራ ለመጓዝ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ዕይታን እንዳያጨልመው ሲያስጨንቃቸው የነበረውን የዓይን ሕመማቸውን ለመታከም ነው፡፡ ተራቸው ደርሶ የዓይን ቀዶ ሕክምና ከሚሰጥበት የአውሮፕላኑ ክፍል እስኪገቡም መቀመጡ አላስችል ቢላቸው ወጣ ገባ ማለቱን ተያይዘውታል፡፡

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የዓይናቸው ጤና መቃወሱን ካተራክት (ሞራ) ቀዶ ሕክምና በዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል ተደርጎላቸው እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ዕይታቸው እየደከመ መጥቷል፡፡ ማክሰኞ መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚደረግላቸው ቀዶ ሕክምናም ለዓይናቸው ሙሉ ብርሃን ተስፋ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ አሁን ላይ የኮርኒያ ቀዶ ሕክምና ለማግኘት ከሆስፒታሉ በተላኩት መሠረት ኦርቢስ ፍላይንግ አይ ሆስፒታል MD 10 አውሮፕላን ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ ሕክምናውን የሚያገኙትም በነፃ ነው፡፡

- Advertisement -

እኝህ ሰው ኦርቢስ ፕሮጀክቱን ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት ከጀመረበት ካለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ ካከናወናቸው 170 ሺሕ ያህል ነፃ ቀዶ ሕክምና ተጠቃሚዎች አንዱ ናቸው፡፡

በኦርቢስ ፍላይንፍ አይ ሆስፒታል የዓይን ሐኪሙ ኦማር ሳላማንካ እንደሚሉት፣ መስከረም 22 ተጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ሳምንታት በሚቆየው የዓይን ቀዶ ሕክምና የካተራክት የኮርኒያ፣ የግላኮማና ሌሎች የዓይን ሕመም ችግር ያለባቸው ሰዎች ቀዶ ሕክምና ያገኛሉ፡፡ ሕፃናትን ጨምሮ በሚከናወነው ቀዶ ሕክምናም እያንዳንዱ ሰው ከ1፡30 እስከ 2 ሰዓት ያህል በቀዶ ሕክምና ክፍል የሚቆይ ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን ሕክምና ደግሞ የላካቸው ሆስፒታል ጋር ክትትል የሚያደርጉ ይሆናል፡፡

የዓይን ሐኪሙ ኦማር ሳላማንካ በአብዛኛው በኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ የዓይን ሕመሞች ቀድሞ መከላከል የሚቻሉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ይህ ባለመሆኑ ሰዎች ለዓይን ቀዶ ሕክምና ይደርሳሉ፡፡ ለኢትዮጵያውያን የዓይን ሕመም ትልቁ ፈተናም ቀድሞ አለመመርመርና ችግሩ ሳይባባስ ሕክምና አለማግኘት ነው፡፡

ኦርቢስ ፍላይንግ አይ ሆስፒታል ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መሥራት ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ከ1998 ወዲህ ብቻ 170 ሺሕ ለሚጠጉ ዜጎች የዓይን ቀዶ ሕክምና ያደረገ ሲሆን፣ የአብዛኞቹም የዓይን ሕመሞች ቀድሞ ባለመከላከል የመጡ ችግሮች ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያ የዓይን ሕመም በተለይም የትራኮማ ጫና ካለባቸው አገሮች ከቀዳሚዎቹ ትመደባለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2006 የተሠራው ብሔራዊ የዓይነ ሥውርነት፣ የማየት እክልና ትራኮማ ዳሰሳ ያሳየውም፤ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ወይም 1.6 በመቶ ያህል ዓይነ ሥውራን መኖራቸውንና 3.8 ሚሊዮን ወይም 3.7 በመቶው ደግሞ ዝቅተኛ ዕይታ እንዳላቸው ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው፣ በኢትዮጵያ ከሚከሰተው ዓይነ ሥውርነት 87 በመቶ ያህሉ እንዲሁም 91 በመቶ ያህሉ ዝቅተኛ የማየት ችሎታ የሚከሰተው ቀድሞ መከላከልና መታከም በሚችሉ በሽታዎች አማካይነት ነው፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም በገጠራማው አካባቢ የዓይን ሕክምናን ማግኘት አንዱ ፈተና ነው፡፡ በመሆኑም በርካቶች ለዓይነ ሥውርነት ምክንያት በሆኑ ካተራከት፣ ኮርኒያና ግላኮማ ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ በተለይም ትራኮማ የአገሪቱ ቀዳሚ የዓይን ጤና እክል ሲሆን፣ በዓለም ከሚከሰቱ የትራኮማ ሕመሞች ውስጥም 37.5 በመቶውን ትጋራለች፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከዓይን ሐኪሞች ማኅበርና ከኦርቢስ ጋር በመተባበር የዓይን ሕክምና ባለሙያዎችን በማብቃቱም ሆነ ለዓይን ሕክምና በመስጠቱ ዙሪያ ትኩረት ከሰጠ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በዓይን ጤናው ዘርፍ ሌሎች ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ድርጅቶች እየሠሩ እንደሚገኙት ሁሉ፣ ኦርቢስ ፍላይንግ አይ ሆስፒታል ፕሮጀክትም በኢትዮጵያ ሥራውን ከጀመረ ሃያ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ከመስከረም 22 ቀን ጀምሮ ለሦስት ሳምንታት ኦርቢስ በሚያከናውነው የአውሮፕላን ውስጥ ቀዶ ሕክምናም ከ200 በላይ ሕሙማን ምርመራና ቀዶ ሕክምና ያገኛሉ ተብሏል፡፡

የዓይን ሐኪሞችንም አቅም ለመገንባትና ሥልጠና ለመስጠት ያለመው ፕሮጀክቱ የሕፃናትና የአዋቂ የዓይን ሐኪሞች ሥልጠና በካተራክት፣ ግላኮማ፣ ኮርኒያ ትራንስፕላንት፣ በሬቲ እና በኦኩሎፕላስቲክ ዘርፍ የሰብስፔሻሊቲ ሥልጠና ይሰጣል፡፡

ፕሮጀክቱ ባለፉት ሃያ ዓመታት በነበረው ቆይታም 2.25 ሚሊዮን ለሚሆኑ አዋቂዎችና ሕፃናት የዓይን ቅድመ ምርመራ፣ ለ25 ሚሊዮን የሕክምና መድኃኒት፣ ለ170 ሺሕ ያህል ደግሞ የዓይን ቀዶ ሕክምና ማድረጉን የኦርቢስ ፍላይንግ አይ ሆስፒታል ፕሮጀክት ኮሙዩኒኬሽንስ ዳይሬክተር ሲሊያ ያንግ ተናግረዋል፡፡

የኦርቢስ ፍላይንግ አይ ሆስፒታል ባለሙያዎች አውሮፕላን በኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ለመስጠት ‹‹በኤምዲ 10›› ለአምስተኛ ጊዜ መምጣታቸውን አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ላይ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ (ዶ/ር) ከበደ ወርቁ እንዳሉት፣ ከኦርቢስ ሕክምና ለመስጠት የመጣው ቡድን ለኢትዮጵያውያን የዓይን ሐኪሞች በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ሥልጠናም የሚሰጡ ይሆናል፡፡

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ከገባበት ከ1998 ዓ.ም. ወዲህም የዘመናዊ ቀዶ ሕክምና ዘዴዎችን በማስተዋወቅ ሰብስፔሻል ሥልጠና በመስጠት ለሕፃናት የዓይን ሕክምና ምቹ የሆኑ ሦስት ማከሚያዎች በመክፈትና ዘመናዊ የሕፃናት የዓይን ሕክምናን በማስተዋወቅ፣ የዓይን ባንክን በመከፍትና ትራኮማን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የተጀመረውን ዘመቻ መምራቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...