Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቲቢ ያመሳቀላቸው ነፍሶች

ቲቢ ያመሳቀላቸው ነፍሶች

ቀን:

ከታክሲ ለመውረድ ወደ አንድ ግድም አነባብረው ያስቀመጧቸውን ድጋፎች አነሱ፡፡ ሁለቱን ክራንቾች በወጉ መጠቀም የለመዱ አይመስሉም፡፡ ለነገሩ በክራንች ታግዘው መሄድ ከጀመሩም ገና ዓመት አልሞላቸውም፡፡ ከትንሿ ታክሲ ለመውረድ ክራንቹ ብቻ በቂ ስላልነበር በጓደኛቸው መደገፍ ነበረባቸው፡፡ እንደ ምንም ብለው በድጋሚ ከቆሙ በኋላ መራመዱ ምጥ ሆነባቸው፡፡ ሰውነታቸው ብርክ እንደያዘው ሁሉ ተንዘፈዘፈ፣ እግራቸውም መሬት አልይዝ አለ፡፡ ሁለት ሜትር ያህል ርቀት ለመራመድ ደቂቃዎች ፈጁ፡፡ ጭንቀታቸውን ያዩ እንደግፍዎ ብለዋል፡፡ እሳቸው ግን በጄ አላሉም፡፡

እንደምንም ብለው ወደ ካፌው ገብተው አረፍ አሉ፡፡ ወዲያው አስተናጋጁ ብቅ ብሎ ምን ልታዘዝ ከማለቱ ‹‹ሻይ ይምጣልኝ›› አሉ፡፡ ትዕዛዙን ለማድረስ ዞር ከማለቱ ደግመው ጠሩትና ‹‹በሻይ ፋንታ ወተት አምጣልኝ፤›› ሲሉ አዘዙት፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ወተት ቢጠጡ ደስታቸው ነው፡፡ ይህ የሆነው ግን ለወተት ልዩ ፍቅር ስላላቸው ሳይሆን በሽታ ያደከመው ገላቸውን ወተት እንዲያጠነክረው ነው፡፡

 ‹‹50 ዓመቴ ነው›› የሚሉት አቶ ሲሳይ ደሴ፣ ከወራት በፊት ጠንካራ ክንድ የነበራቸው የግንባታ ባለሙያ ነበሩ፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ከሚኖሩበት ባሌ በሥራ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ እንደቆዩ ይናገራሉ፡፡ ከሃያ ዓመታት በላይ በግንባታ ሙያ ቆይተዋል፡፡ የሚያገኙትን እየቆጠቡ ባሌ ለሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ወርወር ያደርጉ ነበር፡፡ አሁን ግን ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ቀርቶ ቆሞ መሄድ የማይታሰብ ሆኖባቸዋል፡፡ የአልጋ ቁራኛ ያደረጋቸውን አጋጣሚ ከመነሻው ጀምሮ ሲተርኩ እንባ እየተናነቃቸው ነው፡፡

በጉልበት ሥራ የጠነከረ አካላቸው ሲወጡ ሲወርዱ፣ ብረት ሲያቀኑ ሲያጎብጡ፣ ሲሚንቶ ሲያቦኩ፣ ድንጋይ ሲፈልጡ ቢውሉ ይህንን ያህል ድካም የማይሰማቸው ዓይነት ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግን ያልተለመደ ነገር ማስተዋል ጀመሩ፡፡ ያ ጠንካራ ክንዳቸው ይዝል፣ አንድ ፎቅ ከመውጣታቸው እግራቸው ይደክም፣ መላ ሰውነታቸው በላብ ይጠመቅና ትንፋሽ ያጥራቸው ጀመር፡፡ ይህ ሁኔታ  እየቆየባቸው ከመሄዱ ባሻገር ሳልም ያጣድፋቸው ገባ፡፡

ሕመማቸው ቲቢ መሆኑን እስኪያውቁ የተለያዩ የሕክምና መስጫዎችን መጎብኘት ግድ ብሏቸዋል፡፡ በሽታቸው ለዚያውም የተላመደ ቲቢ ነበርና ነገሮች ውስብስብ ሆኑ፡፡ እንዴትና በምን አጋጣሚ ሊያዙ እንደቻሉ የሚጠረጥሩት ነገር የለም፡፡ ጭንቀታቸው አድካሚ ከሆነው የበሽታው ተፅዕኖ መላለቅ ነበር፡፡ ሕክምና የጀመሩትም ወዲያው ነበር፡፡

በመርፌ መድኃኒት ይሰጣቸው ጀመር፡፡ መድኃኒትን መውሰድ በጀመሩ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ፡፡ ‹‹ያለፈው ዓመት መስከረም 10 ቀን 2010 ዓ.ም. መድኃኒቱን መውሰድ ጀመርኩ፡፡ መስከረም 13 ቀን ከአልጋ መውረድ አቃተኝ፤›› የሚሉት አቶ ሲሳይ፣ ሐኪሞቻቸው ቆይቶ እንደሚሻላቸውና የመድኃኒቱ ባህሪ ስለሆነ አይደናገጡ ብለዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ይሁንና አቶ ሲሳይ፣ አሁንም ድረስ ወደ ቀድሞው አካላዊ ደኅንነታቸው መመለስ ተስኗቸዋል፡፡ የሚወስዱት የቲቢ መድኃኒት በጤናቸው ላይ መሻሻል ቢያመጣም፣ በበሽታው ምክንያት እጅግ ቀንሶ የነበረ የሰውነት ክብደታቸው ወደ ቀድሞው እንዲመለስ ቢያደርግም የጎንዮሽ ጉዳቱ ግን ያለ ድጋፍ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል፡፡ ‹‹በቀን ውስጥ 20 ዓይነት መድኃኒቶችን እወስዳለሁ፡፡ ጠዋት ላይ ከቫይታሚን ጋር 16 መድኃኒቶች እወስዳለሁ፡፡ ማታ ደግሞ ተጨማሪ አራት እወስዳለሁ፤›› ይላሉ፡፡

መድኃኒቶቹን የሚያገኙት ተኝተው ከሚታከሙበት ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ቢበዛ ስድስት ወር ቢያንስ ደግሞ አራት ወር ያለማቋረጥ መድኃኒቱን መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ከደረሰባቸው የጎንዮሽ ጉዳት በጊዜ ሒደት እንደሚለቃቸው ቢነገራቸውም እስካሁን ድረስ ግን ብዙም መሻሻል አላሳዩም፡፡ ይበልጥ የሚያሳስባቸው ነገር ሕክምናቸውን ጨርሰው ከሆስፒታል ሲወጡ የሚወድቁበት ቦታ ነው፡፡ እንደ ቀድሞው ተንቀሳቅሰው መሥራት እንደማይችሉ ግልጽ ነው፡፡ በጊዜ ሒደት ይሻልዎታል ቢባሉም አሁንም ድረስ በድጋፍ መንቀሳቀስ እንኳ ይከብዳቸዋል፡፡ መድኃኒቱ ከቲቢ ቢፈውሳቸውም ተንቀሳቅሰው ለመሥራት እንዲቸገሩና ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

የከባድ ተሽከርካሪ ሾፌሩ ቡሽራም (በደረሰበት አጣዳፊ ሕመም ከሪፖርተር ጋር የነበረውን ቃለ መጠይቅ ሳያጠናቅቅ ወደ ፀበል ተወስዷል፡፡ ሪፖርተር የቡሽራን የአባት ስም እንኳን ማግኘት አልቻለም) እንደ አቶ ሲሳይ ሁሉ በመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ አቅቶታል፡፡ ሕክምናውን ጨርሶ ከሆስፒታል እንዲወጣ ቢደረግም የመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት እንደ ልቡ እንዳይንቀሳቀስ አግዶታል፡፡ ስለዚህም ወደ ቀድሞ ሥራው ተመልሶ ራሱን መቻል ተስኖታል፡፡

የሚጠጋው ቤተሰብ፣ የኔ የሚለው ገቢ የሌለው ቡሽራ ሕክምናውን ጨርሶ ከሆስፒታል ሲወጣ የወደቀው ጎዳና ላይ ነበር፡፡ ሪፖርተር በስልክ ሲያነጋግረው ከዚህ ቀደም የሚያውቁት ሰዎች ጎዳና ላይ አግኝተውት ምሳ ሊጋብዙት ወደ ቤታቸው እንደወሰዱት ገልጾ ነበር፡፡ ስላለበት ሁኔታ የበለጠ ለመነጋገርም ለረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም. የተቀጣጠርን ቢሆንም ቡሽራን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በስልኩ ደውለንለት ጥሪውን የተቀበለው አብሮ አደግ ጓደኛው ስንታየሁ ዳኜ ነበር፡፡ ‹‹እኛ ጋ ነበር ያደረው፡፡ ጠዋት ከአልጋ መነሳት አቃተው፡፡ እግሩን ሸምቅቆ ይዞት ነበር፡፡ ከዚያም ለማንኛውም ብለን ወደ ፀበል ቦታ ላክነው፤›› የሚለው ስንታየሁ፣ የቀድሞ ጓደኛውን ባልተጠበቀ ሁኔታ ስላገኘው መደናገጡን አልሸሸገም፡፡

አሁንም ድረስ የዓለም ሁሉ ሥጋት ሆኖ የቆየው ቲቢ በየዓመቱ አሥር ሚሊዮን የሚሆኑ የዓለም ሕዝቦችን ሲያጠቃ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑትን ደግሞ ለሞት ይዳርጋል፡፡ ይህ አኃዝ በርካቶችን ከሚገድሉ ተላላፊ በሽታዎች ቀዳሚ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ 100 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች መኖሪያ የሆነችው ኢትዮጵያም ከፍተኛ የቲቢ ጫና ካለባቸው ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች ተርታ ነች፡፡ በየዓመቱ 125 ሺሕ ሰዎች በቲቢ ይያዛሉ፡፡ ይህም በዓለም ላይ ከሚገኙ ከፍተኛ የቲቢ ጫና ካለባቸው 22 አገሮች መካከል ኢትዮጵያን የመጀመርያዋ አድርጓታል፡፡

ኢትዮጵያ ቲቢን ለመቆጣጠር ከ1960ዎቹ ጀምሮ ጥረት እያደረገች ብትገኝም አሁንም ድረስ ጫናውን በተገቢ መጠን መቀነስ ከባድ ሆኗል፡፡ ተመላልሰው ለሚታከሙ ታካሚዎች ሞት ምክንያት በመሆን ቲቢ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቲቢ ከኤችአይቪ ጋር መቆራኘት ሌላ ጣጣ ሆኗል፡፡ መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ሲደረብበትም ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ዓይነት ከብዷል፡፡ በደማቸው ውስጥ ኤችአይቪ የሚገኝባቸው ሰዎች ሞታቸውን በማፋጠን ረገድ ቲቢ ቀዳሚው ነው፡፡

ቲቢን ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት በሽታው የሚያስከትለውን ጥፋት ያህል ጠንካራ አለመሆን፣ መድኃኒት የተላመደ ቲቢ መከሰት የበሽታውን ሥርጭት መቆጣጠር ከባድ እንዲሆን ካደረጉ አጋጣሚዎች መካከል ነው፡፡ በሽታው የሚተላለፍባቸው መንገዶችም ሥርጭቱን ለመቆጣጠር ከባድ እንዲሆኑ ካደረጉ አጋጣሚዎች መካከል ነው፡፡ በትንፋሽ የሚተላለፍ መሆኑ በአንዴ በወረርሽኝ መልክ እንዲከሰት ይረዳዋል፡፡ ንቁ የሆነ የሳንባ ቲቢ ያለባቸው ሰዎች በትንፋሽ፣ በአክታና በምራቅ በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡

 በአክታ ውስጥ የበሽታው አምጭ የሆኑ ባክቴሪያዎች በብዛት ስለሚገኙ የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ሲያስነጥስ በአማካይ እስክ 40,000 የምራቅ ቅንጣቶችን ወደ አየር ይለቃል፡፡ በዙሪያው የሚገኙ ሰዎች የተበከለውን አየር ወደ ውስጥ በሚስቡበት ጊዜም የበሽታው ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ተገቢውን ሕክምና ያላገኘ አንድ የቲቢ ታማሚም በዓመት ውስጥ እስከ 20 የሚሆኑ ሰዎችን ሊበክል ይችላል፡፡ በቲቢ የተጠቃ ቤተሰብ ያላቸው በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም በበሽታው የመጠቃት ዕድላቸው ከሌላው ሰው አንፃር በ22 በመቶ ይጨምራል፡፡

የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው ቲቢ አሁንም ድረስ የዓለም ትልቅ ሥጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ አሁንም ድረስ ሚሊዮኖችን እንደ ቅጠል እያረገፈ ይገኛል፡፡ በሕክምና መዳን የሚችል በሽታ ሆኖ ሳለ እስካሁን ድረስ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉ ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ምስክር ነው፡፡ ለሕክምናው የሚሰጡ መድኃኒቶች እንኳ እንደ ሌሎቹ መድኃኒቶች ያልዘመኑ፣ የጎንዮሽ ጉዳታቸው ከበሽታው የማይተናነስ ጉዳት የሚያስከትል ነው፡፡ በስፋት በሦስተኛው ዓለም ላይ የሚከሰተው ይህ በሽታ ከአኗኗር ዘይቤና ከድህነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአንድ መኪና ውስጥ ብዙ ሰዎች ተጭነው የሚሄዱበት፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ተሰብስበው የሚኖሩበት ሁኔታ በተለመደበት አገር ውስጥ ቲቢን በመድኃኒት አክሞ ማጥፋት የማይፈታ ህልም ሆኗል፡፡

መድኃኒቱን በአግባቡ መውሰድ ባለመቻሉም የተከሰተው የተላመደ ቲቢ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ድርብ ችግር ሆኗል፡፡ ‹‹ለቲቢ የሚሰጡ መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላሉ፡፡ በተለይም ለተላመደ ቲቢ የሚሰጠው መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቱ ጠንካራ ነው፤›› የሚሉት በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ውብሸት ጆቴ ናቸው፡፡ ለቲቢ ታካሚዎች መርፌና የሚዋጡ መድኃኒቶች የሚሰጥ ሲሆን፣ መድኃኒቱን እንዲወስዱ የሚደረግበት የጊዜ መጠንም የተለያየ ይሆናል፡፡ መደበኛው የቲቢ ሕክምና ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት የሚወሰድ መድኃኒት፣ ለተላመደው ደግሞ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ የሚቆይ መድኃኒት እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡

‹‹መድኃኒቶቹ እንደየዓይነታቸው በታማሚው ላይ የሚያሳድሩት የጎንዮሽ ጉዳት የተለያየ ነው፤›› የሚሉት ዶክተሩ፣ በመርፌ የሚሰጡ መድኃኒቶች የጆሮን የመስማት አቅም እንደሚቀንሱ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ ታማሚዎች የሰውነት ሚዛን ለመጠበቅ እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡ በሰውነት ውስጥ ያለውን የፖታሲየም ንጥረ ነገር መዛባትም ያስከትላል፡፡ የሚዋጡ መድኃቶች እንዲሁ ጉበት የማስቆጣትና ሌሎችም ተጓዳኝ ጉዳቶች ያስከትላሉ፡፡

አንዳንድ መድኃኒቶች የሥነ ልቦና ቀውስ ሊያስከትሉ ሁሉ ይችላሉ፡፡ ‹‹በሚያጋጥማቸው የሥነ ልቦና ቀውስ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ አሉ፡፡ ከፎቅ ላይ ራሱን ወርውሮ ለመሞት የሞከረ ሰው አጋጥሞኛል፤›› ሲሉ መድኃኒቱ የሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ምን ድረስ እንደሆነ ዶክተሩ ያስረዳሉ፡፡ በነርቫቸው ላይ በሚደርስ ጉዳት እንደ አቶ ሲሳይ ለአካል ጉዳት የሚዳረጉና ዓይናቸውን የሚጋርዳቸውም ያጋጥማሉ፡፡

‹‹እኔ ራሴ ዓይኔ በደንብ አያይልኝም፤›› የሚሉት አቶ ሲሳይ መድኃኒቱ ድርብርብ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳስከተለባቸው ተናግረዋል፡፡ በግምት 90 በመቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ላይ የሚያጋጥመው የጎንዮሽ ጉዳት ቀላል የሚባል እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ውብሸት ቀላል የሚባለው የጎንዮሽ ጉዳት የጨጓራ ሕመም፣ የማቅለሽለሽ፣ የማስመለስና የመሳሰሉትን እንደሆኑ ያብራራሉ፡፡ ከባድና ውስብስብ የጤና ችግር የሚያጋጥማቸው ግን አሥር በመቶ የሚሆኑት ሲሆኑ፣ የሚያጋጥማቸው የጎንዮሽ ጉዳት ጊዜያዊ ወይም ዘለቄታዊ እንደሚሆን ዶ/ር ውብሸት ገልጸዋል፡፡

‹‹ከስድስት ዓመታት በፊት የሕክምና ተማሪ ሳለሁ መድኃኒቱን ወስጃለሁ እኔ ከበሽታው ስፈወስ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት ሳይደርስብኝ ነው፡፡ አብራኝ መድኃኒቱን ስትወስድ የነበረች ነርስ ጓደኛዬ ግን የመስማትና ሚዛን የመጠበቅ ችግር አጋጥሟት ነበር፤›› ሲሉ የሚያጋጥመው የጎንዮሽ ጉዳት በሁሉም ታካሚዎች ላይ ተመሳሳይ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው፣ በበሽታው ከፍተኛ የሰውነት ክብደት መቀነስ ያጋጠማቸው ከሌላው በተለየ የጎንዮሽ ጉዳቱ ይጠነክርባቸዋል፡፡ የጎንዮሽ ጉዳቱ ሳይቆይና ሥር ሳይሰድ ክትትል ከተደረገበት ግን በሕክምና የሚድን ይሆናል፡፡ አለዚያ በሕክምና የማይድን ዘለቄታዊ ችግር ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ‹‹በመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት የመስማት ችግር ያጋጠማት ጓደኛዬ ለጆሮዋ ሕክምና ስትከታተል ቆይታ ነበር፡፡ ነገር ግን ወዲያው ባለመታከሟ ድንገት አንድ ቀን ጆሮዋ መስማት አቆመ፡፡ የሰው ከንፈር ሲንቀሳቀስ ታያለች እንጂ አይሰማትም ነበር፤›› በማለት በዘላቂነት ሊደርስ ስለሚችለው ጉዳት ተናግረዋል፡፡ አብራቸው መድኃኒቱን ትወስድ የነበረችው ሌላ ጓደኛቸውም በጆሮዋ ከደረሰው ጉዳት ባሻገር ባጋጠማት የጉበት መቆጣት ብዙም ሳትቆይ ሕይወቷ ማለፉን አስታውሰዋል፡፡

‹‹መድኃኒቱ ጽንስ ያሰወረደባቸውና ዳግመኛ መውለድ እንዳይችሉ ያደረጋቸው አሉ፡፡ ከዚህም ሌላ የተለያዩ ችግሮች ያጋጠማቸው ሕክምና ጨርሰው ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ያገኘኋቸው ብዙ ያጫውቱኛል፤›› የሚሉት አቶ ሲሳይ ጉዳዩ አሁንም ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል፡፡ መድኃኒቱ በሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት የተማረሩ ሕክምና እንደሚያቋርጡ ይህም አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት የከፋ ቢሆንም ‹‹በቲቢ በሽታ ሁሉም ሰው ይሞታል፡፡ በሕክምና ግን አብዛኛውን ማትረፍ ስለሚቻል የጎንዮሽ ጉዳቱን ፈርቶ አለመታከም አይመከርም፤›› የሚሉት ዶ/ር ውብሸት የተሻለ ሕክምና እንዲኖር ተግቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገሮች በጣም ውድ የሚባሉ አዳዲስ መድኃኒቶችን ወደ አገራቸው እያስገቡ እንደሚገኙ በተቻለ መጠን ወደ ኢትዮጵያም እንዲገቡ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በቲቢ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጋ በመሥራቷ እንዲሁም አዳዲስና በጣም ውድ የሚባሉ መድኃኒቶችን ከወር በፊት ማስገባት የጀመረችው ደቡብ አፍሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ አካል በነበረው በቲቢ ላይ ባተኮረው ዓውደ ጥናት ኮከብ ሆናለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ ያስገባችው አንደኛው መድኃኒት ሁለት ዓመት ገደማ የሚወስደውን መድኃኒት ወደ አንድ ዓመት ያሳጠረ ነው፡፡

በኒውዮርክ ከተማ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው በዚህ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የተገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻዎች በወቅቱ የችግሩን ጥልቀት ከመፍትሔ ሐሳቦች ጋር አያይዘው አቅርበዋል፡፡ ቲቢን ለመቆጣጠር ከገንዘብ አኳያ ለተነሳው ጉዳይ አገሮች በትምባሆ ላይ የሚጥሉትን ቀረጥ በማሳደግ ቲቢን ፋይናንስ ማድረግ አለባቸው የሚለውን ሐሳብ የሰነዘሩት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የተገኙ ባለሙያ ናቸው፡፡

የሚመለከታቸው አካላትም የቲቢን ጉዳይ የማኅበረሰቡ እንዲሆን መሥራት አለባቸው፣ ቲቢን በተመለከተ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በለጋሽ ድርጅቶች ድጋድፍ ብቻ ሳይሆን በአገሮች የውስጥ በጀት መደገፍ አለባቸው የሚሉና ሌሎችም የመፍትሔ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡ የተነሱት ሐሳቦች ከምክረ ሐሳብነት በዘለለ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ሒደቱን እየተከታተሉ ሪፖርት የሚያደርጉ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት በየአገሩ እንዲቋቋሙም ተጠይቋል፡፡ የዚህ ዕውን መሆን እ.ኤ.አ. ቲቢን በ2030 ለማጥፋት የተያዘውን ግብ ለመምታት ወሳኝ እንደሆነ፣ አሁን ባለው አካሄድ ግን ለሚመጡት አሠርታትም ሥርጭቱን መቆጣጠር ከባድ እንደሚሆን በመድረኩ ተነስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...