አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ለተጨማሪ ምርመራ ተቀጠሩ
በኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማና አካባቢው ከመስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተፈጸመ ግድያ፣ አካል ማጉደልና ንብረት ማውድም ወንጀል ገንዘብ በማከፋፈልና በማስተባበር ተሳትፈዋል ተብለው የታሰሩ ግለሰቦች በሽብርተኝነት ተጠረጠሩ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ስድስት ተጠርጣሪዎች፣ ሐሙስ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት አቅርቦ ለተጨማሪ ምርመራ 28 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው፣ ቀደም ባለው የችሎት ጊዜ በተፈቀደለት 14 ቀናት የሠራውን ካስረዳ በኋላ ነው፡፡
መርማሪ ፖሊስ እንዳስረዳው ተጠርጣሪዎቹ አቶ ሳምሶን ጥላሁን፣ አቶ ዓለሙ ዋቅቶላ፣ አቶ ቡልቻ ታደሰ፣ አቶ ሐሺም አሚር፣ አቶ ሽፈራው ኢራና፣ እንዲሁም አቶ ዓሊ ዳንኤል ናቸው፡፡ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሐሰተኛ መታወቂያ፣ የመንግሥት ተቋማት ማኅተም፣ ቲተርና 74 የሥለት መሣሪያዎችን በቤታቸው ውስጥ አስቀምጠው መያዙን ፖሊስ ገልጿል፡፡ በተለይ አቶ ሳምሶን ጥላሁን የተባለው ተጠርጣሪ የአካባቢውን ነዋሪዎች መሬት በሐሰተኛ ሰነድ በመቀማትና ለሌሎች በመስጠት ግጭት እንዲነሳ ማድረጉን ፖሊስ አስረድቷል፡፡
የበርካታ ወጣቶች ፎቶግራፍ፣ መታወቂያ፣ የመንግሥት ተቋማት ማኅተሞችና ቲተሮች በእጁ ይዞ መገኘቱን አክሏል፡፡ ተጠርጣሪው የኦነግ መራሮችን ለመቀበል ድጋፍ ለማድረግ በወጡ የኦሮሚያ ወጣቶችና የአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ግጭት እንዲነሳ፣ ፓስተር አካባቢ ሲደርሱ በመሀላቸው በመሆን ሽጉጥ መተኮሱንም ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በተለይ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በመንግሥት ተሽከርካሪዎች የወንጀል ድርጊት የፈጸሙትን ማመላለሳቸውንና ገንዘብ ማከፋፈላቸውን መርማሪ ፖሊስ ተናግሯል፡፡ በግጭቱ የተገደሉ ሰዎች የአስከሬን ምርመራ ውጤት ለመቀበል ሌሎች ግብረ አበሮችን ለመያዝ፣ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግና የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ የ28 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በጠበቃቸው አማካይነት እንደተናገሩት፣ መርማሪ ፖሊስ በጅምላ እንጂ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ምን እንደሠራ በተናጠል የገለጸው የለም፡፡ ድርጊቱ የሽብር ወንጀል መሆኑን ፖሊስ የገለጸው ተጠርጣሪዎቹን በእስር ለማቆየት በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸው ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት ወንጀሉን አልፈጸሙም፡፡ የታሰሩት ከአዕምሮ ሕሙማን ጋር በመሆኑ ሲሯሯጡ እንደሚያድሩ፣ በጨለማ ውስጥ መታሰራቸውን፣ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበርላቸውና የዋስትና መብትም እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
መርማሪ ፖሊስ ግን የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሞ፣ የወንጀል ድርጊቱ ውስብስብና የምስክሮችን ቃል መቀበል የሚቀረው በመሆኑ የጠየቀው ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ በእስር ቤት ይደርስብናል ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲከበርላቸው ገልጾ፣ የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ የተጠየቀውን 28 ቀናት ፈቅዶ ለጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን የጣሰ ነው የሚል በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው ሥልጣን ሳይኖረው መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተዘጋጀው ድጋፍ ሠልፍ በመስቀል አደባባይ በተገኘው ሕዝብ ላይ ከተወረወረው ቦምብና ካደረሰው ጉዳት ጋር በተገናኘ ተጠርጥረው በታሰሩት፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል መምርያ ኃላፊ በነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ተጨማሪ ስምንት ቀናት የምርመራ ጊዜ ተፈቅዷል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በአቶ ተስፋዬ ቤት በብርበራ ያገኘውን ቦምብ በመስቀል አደባባይ ከፈነዳው ቦምብ ቅሬት አካል ጋር ያለውን ልዩነትና አንድነት ለማመሳከር፣ ቅሪተ አካሉን ለፌዴራል ፖሊስ ፈንጂ አምካኝ ኦፕሬሽን ዲቪዚዮን መላኩን ጠቁሞ ምላሹን ለመጠባበቅ አሥር ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ አቶ ተስፋዬ ግን የመርማሪውን ጥያቄ ተቃውመዋል፡፡ ፖሊስ ጊዜውን ሆነ ብሎ እያራዘመ መሆኑን ተናግረው ፍርድ ቤቱ ለመጨረሻ ጊዜ ብሎ አጭር ቀናት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ስምንት ቀናት ብቻ በመፍቀድ ለጥቅምት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡