Tuesday, May 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሐሳብና የተግባር አንድነት የሚረጋገጠው የሕግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው!

ኢሕአዴግ በሐዋሳ ከተማ ያካሄደው 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የሐሳብና የተግባር አንድነት ተረጋግጦ በነፃነት፣ በግልጽነትና በአሳታፊነት በተደረገ ውይይት ውሳኔ ላይ ተደርሶ እንዲጠናቀቅ የብዙዎች ጉጉት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ በሕዝብ ከፍተኛ ግፊት ተደርጎበት ከውስጥ ባሉ የለውጥ ኃይሎች የበላይነት ቢጀመርም፣ በተለያዩ መንገዶች ይደረጉ የነበሩ ችግር ፈጣሪ እንቅስቃሴዎች ለሰላምና ለመረጋጋት  ጠንቅ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ለውጡ ተደናቅፎ ቀውስ እንዲፈጠር በተደረጉ ያላሰለሱ ጥረቶች፣ በርካታ ግጭቶች ተከስተው በርካቶች ለሕልፈት ተዳርገዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ ከፍተኛ የአገር አንጡራ ሀብት ወድሟል፡፡ አለመረጋጋቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት በሄደበት ወቅት ነው፣ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሐዋሳ ከትመው ጉባዔያቸውን ያካሄዱት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንን ታሪካዊ ጉባዔ በከፍተኛ ጭንቀትና ውጥረት ተከታትሎታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሕግ የበላይነት እየጠፋና ሥርዓተ አልበኝነት እየነገሠ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ በመፈጠሩ ነው፡፡ ሕዝብ የአገሪቱ ሰላም ወደ ነበረበት ተመልሶ ደኅንነቱ አስተማማኝ እንዲሆንና ኢሕአዴግ የሐሳብና የተግባር አንድነት ይዞ ጉባዔውን እንዲያጠናቅቅ የተመኘው፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሕግ የበላይነት እየተመራች ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምታመራ ሰላማዊ አገር እንድትኖረው ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሕግ የበላይነት ጀርባ መስጠት አገር ያጠፋል፡፡

ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ በአገሪቱ ሕዝብ ከፍተኛ ቅቡልነት ያገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊት አገር ለመፍጠር ሲያደርግ የነበረው ጥረት በፈተናዎች የተከበበ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለንፁኃን ሞት፣ እንግልትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ግጭቶች በየቦታው እየፈነዱ የአገሪቱ ሰላም ተቃውሷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው በፈለጉት ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት በሕግ የተረጋገጠ መብታቸው እየተጣሰ እንደ ባዕድ ተሳደዋል፡፡ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ የዘለቀው ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እየተሸረሸረ በጎጠኝነት በተለከፉ ኃይሎች ምክንያት ከባድ ችግር ተፈጥሯል፡፡ በተጀመረው ለውጥ አማካይነት ኢትዮጵያውያን በፍቅር፣ በሰላም፣ በይቅር ባይነት፣ በመተሳሰብና በእኩልነት የሚኖሩባት አገር ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ በተቃራኒው አገር የማፈራረስ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በየቦታው የሕግ የበላይነት እየተጣሰ ሥርዓተ አልበኝነት በመስፈኑ የሕዝብ ደኅንነት ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ አሁን ኢሕአዴግ የሐሳብና የተግባር አንድነት ይዞ አገሪቱን ከቀውስ ውስጥ የማውጣት ታላቅ ታሪካዊ አደራ አለበት፡፡ በአባል ድርጅቶች መካከል የሚታየው አላስፈላጊ ትንቅንቅ አብቅቶ፣ አዘቅት ውስጥ ያለች አገርን መታደግ የሕዝቡ ዋነኛ ጥያቄ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ በትዕቢትና በአላዋቂነት ስሜት የተሞሉ አጥፊ ድርጊቶች በፍጥነት ታርመው፣ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር መስማማት የግድ ይላል፡፡ እዚህ ላይ ቀይ መስመሩን ደመቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ እጅግ በጣም በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት፡፡ እነዚህ ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፈታት የሚችሉት የፖለቲካ አጉል እንካ ሰላንቲያ በማቆም በዴሞክራሲያዊ መንገድ መነጋገር ሲቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት ሲከበር እየተከፈተ ባለው የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በእኩልነት መንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሐሳባቸውን በነፃነት ይገልጻሉ፡፡ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ይከበራሉ፡፡ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት በሕግ አደብ ይገዛሉ፡፡ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎች ሥራቸውን በገለልተኝነት ያከናውናሉ፡፡ በፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ የሚሳተፉ ኃይሎች በሙሉ ሕግ አክብረው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ሕግ አውጪው፣ ተርጓሚውና አስፈጻሚው የእርስ በርስ ቁጥጥር እያደረጉ በመናበብ ይሠራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በሕግ ፊት እኩል እንደሚሆኑ ሁሉ እኩል ተጠያቂነት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በጉልበት ለመንቀሳቀስ የሚፈልግ ካለ በሕግ ቋንቋ አደብ እንዲገዛ ይደረጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሒደት በአግባቡ ሲከናወን በኢትዮጵያ ምድር ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ ተካሂዶ በሕዝብ ይሁንታ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ አገር የማስተዳደር ሥልጣኑን ይረከባል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የሚያስፈልጋት ለዚህ ነው፡፡ ሕዝብም ኢሕአዴግ ከውስጣዊ አጉል ልፊያ ወጥቶ ይህንን ጥርጊያ እንዲያመቻች አጥብቆ እየጠየቀ ነው፡፡ ሌላ ምንም አማራጭ የለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ከስምንት ሚሊዮን በላይ ወገኖች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ወገኖች መካከል ሦስት ሚሊዮን ያህሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባጋጠሙ ግጭቶች ምክንያት ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ናቸው፡፡ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አጥቢ እናቶች፣ አዛውንቶችና አቅመ ደካሞች ትልቁን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ ከእነዚህ ወገኖች በተጨማሪ በሴፍቲኔት የምግብ ለሥራ ፕሮግራም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች የለጋሾችን ድጋፍ ይጠባበቃሉ፡፡ ከአጠቃላዩ ሕዝብ ውስጥ ሃያ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖች ከድህነት ወለል በታች በፍፁም ድህነት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥቅሉ በዓለም የድህነት መለኪያ መሠረት በጉስቁልና የሚኖር ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ በየዓመቱ ከ600 ሺሕ በላይ ወጣቶች ሥራ ይፈልጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት የተወሳሰበ ችግር ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰላምና ለመረጋጋት ትልቅ ትኩረት ካልተሰጠ፣ ለመገመት አዳጋች የሆነ ማኅበራዊ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ኢሕአዴግ ለ27 ዓመታት የመራት ኢትዮጵያ ይህንን ስለምትመስል ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ይህንን እውነታ ዘንግቶ አጉል እሰጥ አገባ ውስጥ መዘፈቅ በዋዛ የሚገላገሉት አይሆንም፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለም በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገሮች ተርታ ስሟ ቢነሳም፣ ከዓለም ደሃ አገሮች ረድፍ ደግሞ ግንባር ቀደሟ ናት፡፡ ይህንንም ለቁጥር የሚታክቱ መረጃዎች ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ልዩ ትኩረት፣ ክትትልና የማያቋርጥ ድጋፍ ካልተደረገ ለማኅበራዊ ቀውስ ይዳርጋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት፣ ኤክስፖርት ተደርገው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ማዕድናት ወደ ገበያ መውጣት አልቻሉም፡፡ ሥራ እንዲያቆሙ የተደረጉም አሉ፡፡ የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርቡ ማምረቻዎችም በውጭ ምንዛሪ ዕጦትና ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት፣ ከአቅማቸው በታች ከማምረት አልፈው ሥራ ያቆሙም አሉ፡፡ በተለያዩ ጫናዎች ሳቢያ መረጋጋት ተስኗቸው ግራ የገባቸው ሞልተዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በግል እርሻዎች፣ ማሽኖችና መጋዘኖች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው፡፡ እነሱ ሥራ ሲያቆሙ የሚበትኗቸው ሠራተኞችና ቤተሰቦች ዕጣ ፈንታ ሲያስቡት ያስደነግጣል፡፡ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ሲጠፋ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ ኢንቨስተሮች ከምንም ነገር በላይ አስተማማኝ ሰላም ይፈልጋሉ፡፡ በስንት ማባበል የመጡ የውጭ ኢንቨስተሮች ከማበረታቻ በተጨማሪ፣ የሰላምና የመረጋጋት ጉዳይ ያሳስባቸዋል፡፡ ኢንቨስተሮች በመንግሥት ላይ እምነት ኖሯቸው በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉት፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስከበር አገር የመምራት ብቃቱን ሲያሳይ ነው፡፡ በየቦታው እንደ አሮጌ ስልቻ የሚቦተረፈው የአገሪቱ ሰላም ሲቃወስና ትርምስ ሲፈጠር፣ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተሮች እጅና እግራቸውን ይሰበስባሉ፡፡ ኢኮኖሚው የደቀቀ አገር ደግሞ ተፈረካክሶ፣ የነውጠኞችና የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ ይሆናል፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ ምልክቶችን እያሳየ ስለሆነ ጥብቅ የሆነ ዕርምጃ ይፈለጋል፡፡

የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ከጉባዔ መልስ አንድ ልብ አንድ ሐሳብ ሆነው መሥራት ከቻሉ ድርጅታቸውንም አገራቸውንም ያድናሉ፡፡ በተለይ የአገር ህልውና መተኪያ የሌለው ስለሆነ፣ ከተለመደው አባዜ በመውጣት አገር አድነው ታሪክ ይሥሩ፡፡ ለዓመታት ለተበላሹ በርካታ ነገሮች ተጠያቂ የሆነ ድርጅት ሕዝብ ዕድል ሰጥቶት ለውጡን ማቀላጠፍ ሲጠበቅበት፣ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ ከሄደ ችግር ይፈጠራል፡፡ ኢሕአዴግ አገር እመራለሁ ብሎ በቁርጠኝነት ከተነሳ የሕዝብ ድጋፍ ያገኛል፡፡ ይህ ድጋፍ ግን የሚቀጥለው ሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጀቶች እኩል መራመድ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ አንዱ ለውጥ እየመራ ሌላው አደናቃፊ ሆኖ መቀጠል አይቻልም፡፡ ስለዚህ የማይታለፉ ቀይ መስመሮች ተሰምረዋል ከተባለ የሐሳብና የተግባር አንድነቱ ይረጋገጥ፡፡ ከአሁን በኋላ በሕዝብ ላይ መቆመር እንደማይቻል ከበቂ በላይ ተረጋግጧል፡፡ አዳራሽ ውስጥ አጨብጭቦ ደጅ ደግሞ ሌላ ሴራ መጎንጎን ፋሽኑ ያለፈበት አጉል ትርዒት ነው፡፡ ለአገር አይበጅም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ዓይነቱን መሰሪነት የሚሸከምበት ትከሻ የለውም፡፡ ይህንን በቅጡ ተገንዝቦ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዕውቀት ያላቸውና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለአገር ሰላምና ደኅንነት በአንድነት ይቁሙ፡፡ የሐሳብና የተግባር አንድነት መረጋገጥ የሚችለው የሕግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው ይበሉ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...

የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሁሴን አህመድ (1930-2015)

ኢትዮጵያ የሁለተኛውን የፋሺስት ጣሊያን ወረራ (1928-1933) በድል ከተወጣች በኋላ...

ከወለድ ነፃ ባንክ የተሰበሰበውን በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለምን ሥራ ላይ ማዋል አልተቻለም?

  ባንኮች ከወለድ ነፃ የሚሰበስቡት ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገት እያሳየ...

መንግሥት ባለፈው ዓመት ለማዳበሪያ የደጎመው 15 ቢሊዮን ብር ለአርሶ አደሮች አለመድረሱ ጥያቄ አስነሳ

መንግሥት ለ2014/15 በጀት ዓመት እርሻ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ያለውን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...

ለመጪው ዓመት የሚያስፈልገው 4.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል

ለመጪው 2016 ዓ.ም. ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ለታቀደው 4.3...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...

ጠንካራና አስተማማኝ ተቋማት በሌሉበት ውጤት መጠበቅ አይቻልም!

በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ መዛነፎችና አለመግባባቶች ዋነኛ ምክንያታቸው፣ ከበፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ጠንካራና አስተማማኝ ተቋማትን ለመገንባት አለመቻል ነው፡፡ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በፀጥታ፣...