Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የካናዳ ባለሙያዎች በአወዛጋቢው የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ላይ ጥናት ሊያካሂዱ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በማዕድን ማውጫው መዘጋት የውጭ ምንዛሪ እየታጣ ነው

በሻኪሶ ከተማ አካባቢ ነዋሪዎች በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት ሥራውን እንዲያቋርጥ በተደረገው የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ንብረት በሆነው የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ላይ፣ የካናዳ ከፍተኛ ባለሙያዎች ጥናት ሊያካሂዱ እንደሆነ ታወቀ፡፡

ከለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ የሚወጣ ኬሚካል በኅብረተሰቡ ጤናና በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ በመግለጽ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ በማሰማታቸው የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የሚድሮክ ወርቅን የማዕድን ምርት ፈቃድ በግንቦት 2010 ዓ.ም. ማገዱ ይታወሳል፡፡ ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን እስኪጣራ ድረስ ኩባንያው የወርቅ ምርት ሥራውን እንዲያቋርጥ ተደርጓል፡፡

ሚድሮክ ወርቅ በአካባቢው ኅብረተሰብ ጤና ላይ የፈጠረው ችግር እንደሌለ፣ የወርቅ ምርት ሒደቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነ በመግለጽ የሚኒስቴሩን ውሳኔ ተቀብሎ ጥናቱ በገለልተኛ ወገን በአፋጣኝ እንዲከናወን ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በማዕድን ማውጫው መዘጋት አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማጣቷና የበርካታ ዜጎች የሥራ ዋስትና አደጋ ውስጥ መግባቱ እየተገለጸ ነው፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በለገደንቢ የወርቅ ማውጫ ጉዳይ ላይ በቅርቡ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡ በስብሰባው ላይ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚድሮክ ጎልድ ኃላፊዎችና የሻኪሶ አካባቢ ነዋሪዎች ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተካፍለዋል፡፡

ቀደም ሲል ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያስጠና ቢሆንም ውጤቱ ይፋ አልተደረገም፡፡ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል መንገሻ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደው ውይይት በወርቅ ማምረቻው ላይ ጥልቀት ያለው ጥናት እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ቀደም ሲል የተሠራው ጥናት በቂ ባለመሆኑ ጥልቀት ያለው ጥናት በገለልተኛ ወገን እንዲሠራ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አቶ ሚካኤል አስረድተዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የካናዳ ኤምባሲ በማዕድን ማውጫ ላይ የሚካሄደውን የአካባቢ ተፅዕኖ ጥናት ለመደገፍ ቃል መግባቱን ጠቁመው፣ ኤምባሲው ከሚኒስቴሩ ጋር ባለው የትብብር ስምምነት መሠረት ጥናቱን በቴክኒክና ገንዘብ ለመደገፍ መስማማቱን ገልጸዋል፡፡

ሁለት ከፍተኛ ባለሙያዎች ከካናዳ በመምጣት መረጃ ማሰባሰብ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ባለሙያዎቹ በነበረው የፀጥታ ሥጋት ወደ አካባቢው ያልተጓዙ ቢሆንም ከሚኒስቴሩና ከሚድሮክ ወርቅ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ከአካባቢው ነዋሪዎች ተወካዮች ጋር ውይይት ማካሄዳቸውንና መረጃዎች እንዳሰባሰቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባለሙያዎቹ ባለፈው ሳምንት ወደ ካናዳ መመለሳቸውን የገለጹት አቶ ሚካኤል፣ በቅርቡ ተመልሰው ጥናቱን እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡ ባለሙያዎቹ የመስክ ጉብኝት በማድረግ የተለያዩ መረጃዎችና ናሙናዎችን እንደሚሰበሰቡ ይጠበቃል፡፡

ጥናቱ ተካሂዶ ሲጠናቀቅ ሪፖርቱ ለሚኒስቴሩ፣ ለሚድሮክ ወርቅና ለሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ በውጤቱና በምክረ ሐሳቡ ላይ ተመርኩዞ የመፍትሔ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል፡፡ ‹‹ኢንቨስትመንቱ የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ አለበት፡፡ የበፊት ስህተቶች መታረም አለባቸው፡፡ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ዕርቅ መውረድ አለበት፡፡ የማዕድን ማምረት ሥራው መከናወን ያለበት በመንግሥት ፈቃድ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡን ይሁንታ ሲያገኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ሥራ በማቆሙ ምክንያት አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያጣች እንደሆነ የመስኩ ባለሙያዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ሚድሮክ ወርቅ በየዓመቱ አራት ቶን ወርቅ በማምረት ከ60 ሚሊዮን ዶላር ላይ ያስገባ እንደነበር የገለጹት ምንጮች፣ ይህ በመቋረጡ ምክንያት ከማዕድን ወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ እንደመጣ ያስረዳሉ፡፡

አገሪቱ ከማዕድን ወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ከዓመት ወደ ዓመት እያሽቆለቆለ መጥቶ፣ ባለፈው ዓመት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 130 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ ሚኒስቴሩ በቅርቡ አስታውቋል፡፡ ቀድም ሲል ከማዕድን ወጪ ንግድ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይገኝ እንደነበር ያስታወሱት አንድ የመስኩ ባለሙያ የወርቅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ መቀነስ፣ በአገር ውስጥ የወርቅ ኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት፣ የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻና የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ መዘጋት ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሽቆልቆል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹በምርት ሒደቱ ላይ ችግር ካለ የዕርምት ዕርምጃ መውሰድ እንጂ፣ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የማዕድን ማውጫዎች ዘግቶ ስለውጭ ምንዛሪ እጥረት ማውራት ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ሥራ ማቋረጥ በውጭ ምንዛሪ ግጭት ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ሚኒስቴሩ እንደሚገነዘብ አቶ ሚካኤል ገልጸው፣ ሚኒስቴሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ለኅብረተሰብና አካባቢ ደኅንነት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የኢኮኖሚ ተፅዕኖ እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጠቀሜታን እያየን የኅብረተሰቡ ጤና ጉዳይን በዝምታ ልናልፍ ግን አንችልም፡፡ በስብሰባው ላይ ጊዜ እንደሌለና ጥናቱ በአፋጣኝ ተሠርቶ፣ የመፍትሔ ዕርምጃ ተወስዶ ወደ ሥራ እንዲገባ ከጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፤›› ብለዋል፡፡

የሚድሮክ ወርቅና የካናዳ ኤምባሲን አስተያየት ለማካተት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ነገር ግን ለኩባንያው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ባለፉት አምስት ወራት ኩባንያው ከሽያጭ አሥር ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን፣ በተጨማሪም ለ1,700 ያህል ሠራተኞቹ በወር ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ደመወዝ ወጪ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በላይ አሳሳቢ የሆነው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገዙ የወርቅ ማምረቻ ማሽኖች ያለ ሥራ ለረዥም ጊዜ መቆማቸው አሳሳቢ መሆኑን ምንጮች አክለዋል፡፡ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ከሚተዳደሩት በርካታ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ሚድሮክ ወርቅ በ1989 ዓ.ም. የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻን ከቀድሞ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ በጨረታ በ172 ሚሊዮን ዶላር መግዛቱ ይታወሳል፡፡ ኩባንያው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የከርሰ ምድር ማዕድን ማውጫ በመገንባት፣ ሰፊ የማዕድን ፍለጋ ሥራዎች በማካሄድ ተጨማሪ የወርቅና የብር ክምችት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች