ከመስከረም 23 ቀን እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)፣ ላለፉት 27 ዓመታት ሲመራበት የቆየውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የሚተካ ርዕዮተ ዓለም ተጠንቶ በመጪው ጉባዔ እንዲቀርብ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
ኢሕአዴግ የሦስቱ ቀናት ጉባዔው ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሮ የወጣበት፣ የሐሳብና የተግባር አንድነት የፈጠረበትና ልብ ለልብ ተገናኝቶ የመከረበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ቀጣዩ የግንባሩ ርዕዮተ ዓለም ከወዲሁ እንዲጠና ስምምነት መደረሱ ተጠቁሟል፡፡
ለሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት ተጠናክረውና ከወገንተኝነት ፀድተው ሕዝባዊ ተዓማኒነታቸው እንዲጎለብት፣ መወሰድ ያለባቸው ቁልፍ ዕርምጃዎች በጥናት ላይ ተመሥርተው እንዲከናወንም ጉባዔው ወስኗል፡፡
በተጨማሪም የሕግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ ሥርዓተ አልበኝነትን መታገስ እንደማይገባም ኢሕአዴግ በጉባዔው ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የሚዲያ ተቋማት ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ድርሻ እንዲኖራቸው መደገፍ እንደሚገባና የግል ሚዲያዎች እንዲስፋፉና ተበረታተው በነፃነት እንዲሠሩ በመፍቀድ፣ በጥራትና በትጋት ካልሠሩ በስተቀር ተጎጂዎቹ ራሳቸው መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ማድረግ እንደሚገባና በዚህ መንገድ እንዲሠራም ወስኗል፡፡
የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ዓርብ መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ፣ አገሪቱ ወደ ታሪካዊ የለውጥ ምዕራፍ በመግባቷ የጉባዔው አባላት ለውጡ እንዳይቀለበስና የበለጠ እንዲቀጥል ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱ በአቋም መግለጫው ተገልጿል፡፡
ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ድርጊቶች ስለሚታዩ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የማንነት ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲፈቱ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በማድረግ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ጠንክሮ መሥራትና የመሳሰሉት በአቋም መግለጫው ተካተዋል፡፡ የተጀመረውን ለውጥ ሕዝባዊ፣ ሕገ መንግሥታዊና ድርጅታዊ ማድረግ የጉባዔተኞቹ ኃላፊነት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ዓርብ መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባካሄደው ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ድምፅ ከሰጡ 177 አባላት 176 ድምፅ በማግኘት ዳግም በሊቀመንበርነት ተመርጠዋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን 149 ድምፅ በማግኘት ምክትል ሊቀመንበርነታቸውን ዳግም አረጋግጠዋል፡፡ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም (ኢንጂነር) የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ እስከሚቀጥለው ጉባዔ ድረስ ተመራጮቹ ድርጅቱን ያገለግላሉ፡፡
የኢሕአዴግ ምክር ቤት መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትላቸውን በዋናና በምክትል ሊቀመንበርነት መምረጡ አይዘነጋም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ መሰየማቸው ይታወሳል፡፡
የኢሕአዴግ ጉባዔ አጋር ድርጅቶች እስከሚቀጥለው ጉባዔ ድረስ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ያለ ድምፅ እንዲሳተፉ የወሰነ ሲሆን፣ ግንባሩ ወደፊት አጋር ድርጅቶችን በማካተት ወደ ውህደት የሚያመራበት አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውቋል፡፡ ውህደቱ የዛሬ ሁለት ዓመት በሚካሄደው ቀጣዩ ጉባዔ ዕውን የሚሆን ከሆነ የአጋር ድርጅቶች ጥያቄ ምላሽ ያገኛል ተብሏል፡፡