በቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ስም፣ በቡታጅራ ከተማ በ129 ሚሊዮን ብር የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ 95 በመቶ ለሚሆኑ ተማሪዎች በነፃ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚችል፣ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የገቢ ማሰባሰቢያውን የሚያስተባብሩት አቶ ብሩክ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡
አቶ ብሩክ በሰጡት መግለጫ መሠረት የትምህርት ቤቱ ግንባታ አገር ውስጥና ውጭ በሚገኙ ባለሀብቶች፣ በዓለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማትና በአገር ወዳዶች አማካይነት ይከናወናል፡፡ የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራሙ ደረጃቸውን ጠብቆ እንደሚካሄድ፣ ግንባታውን ለማስጀመር አቶ አህመድ ሁሴን የተባሉ ባለሀብት አሥር ሚሊዮን ብር መለገሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሚገነባው ትምህርት ቤት የአዛውንቶች መኖሪያና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ስም ከተሰየመ እሳቸው ያውቁት እንደሆነ አቶ ብሩክ ተጠይቀው፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሐሳቡን በፀጋ መቀበላቸውን አስረድተዋል፡፡
ለግንባታው አሥር ሚሊዮን ብር የለገሱት ባለሀብቱ አቶ አህመድ ለጋዜጠኞች፣ ‹‹የትምህርት ቤቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ትምህርት ለሁሉም ተማሪዎች የሚሰጥ መሆኑን፣ የኢትዮጵያን አኩሪ ታሪኮችና ባህሎች በማጉላት የአገሪቱን አንድነትና ሰላም፣ እንዲሁም በዜጎች መሀል እኩልነት ልዩነት ሳይኖር በጥራት ያስተምራል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ብሩክ በበኩላቸው፣ ‹‹የትምህርት ቤቱ ዋና ዓላማ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በትምህርቱ ጥራት ተጠቃሚ እንዲሆን ነው፡፡ አረጋዊያንም የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የራሳችንን ጥረት እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የትምህርት ቤቱ ግንባታ ከየትኛውም የፖለቲካ፣ የዘርና የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት በመፅዳት ለአገራችን ክብር የበሰሉ ተማሪዎችን ለማፍራት ቆርጠን በመረባረብ እንሠራለን፤›› ሲሉ አቶ ብሩክ አስረድተዋል፡፡