Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየትራፊክ አደጋ መብዛቱ ምን ያህል አሳስቦናል?

የትራፊክ አደጋ መብዛቱ ምን ያህል አሳስቦናል?

ቀን:

ጳጉሜን 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በዋልታ ቴሊቪዥን የተላለፈው ዜና፣ በአዲስ አበባ ሲኤምሲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ወረድ ብሎ የሚገኘውን መንገድ ተሽከርካሪዎች የባቡር ሐዲዱን አቋርጠው ወደ ቀኝና ወደ ግራ መታጠፍ እንዲችሉ ታስቦ የተከፈተው ማቋረጫ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ቢሆንም በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ችግር በመፍጠሩ ይመስላል፣ በኮንክሪት ተዘግቷል፡፡ በዚህም ኅብረተሰቡ ለከፋ እንግልት መዳረጉን የሕንፃ መሣሪያ ነጋዴዎችና የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች እንዲሁም ሾፌሮች በስሜት ሲገልጹ ሰምቼ ተገረምኩ፡፡

የተጠቀሰው መታጠፊያ መንገድ ቀድሞውኑ መከፈት ያልነበረበት ሲሆን፣ መዘጋቱም ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የመታጠፊያዎች መብዛት አዲስ አበባ ውስጥ ለሚደርሱት የትራፊክ አደጋዎች አስተዋፅኦ ማድረጉን አሌ ማለት አይቻልም፡፡ በሠለጠኑት አገሮች መታጠፍ የሚቻለው በአደባባዮች ብቻ መሆኑን እነዚህን አገሮች የማየት ዕድል የገጠማቸው ሰዎች ሲያወሩ እንሰማለን፡፡ ይህ ባህል እዚህም ቢዳብር መልካም ነው፡፡

ነጋዴዎቹና የጭነት ተሽከርካሪዎቹ ባለንብረቶች ‹‹ኅብረተሰቡ›› የሚሉት ደንበኞቻቸውን ከሆነ በቁጥር የሚልቀው የእነሱ ደንበኛ ያልሆነው የኅብረተሰብ ክፍል እንደሚሆን መገመት ስለማያዳግት፣ መከበር ያለበት የዚህኛው ክፍል ጥቅምና ፍላጎት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለነገሩ ነጋዴዎቹ ለጋዜጠኛው በሰጡት አስተያየት መሠረት፣ ሰሚት አደባባይ ሰማይ ጥግ ያለ አስመሰሉት እንጂ ከመታጠፊያው ሰሚት አደባባይን ዞሮ ወደ እነሱ መደብር ለመድረስ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ እንደማያስኬድ አካባቢውን የሚያውቁ ሁሉ ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ደንበኞቻቸው ይኼንን ርቀት መጓዝ ይከብዳቸዋል ብዬ አልገምትም፡፡ አደባባዩ አካባቢ የትራፊክ መጨናነቅ መኖሩ እርግጥ ነው፡፡ ለዚህ ችግር ተጠያቂዎቹ ወደ ሰሚት የሚወስደውን መንገድ ሙሉ በሙሉ ዘግተው ተሳፋሪ የሚጭኑ ታክሲዎችና ባለ ሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) ናቸው፡፡

ለትራፊኩ መጨናነቅ ሌላው ሰበብ የባቡሩን ሀዲድ የሚያቋርጡ ተሽከርካሪዎች ለባቡሩ ቅድሚያ ለመስጠት ሲሉ በመቆማቸው ምክንያት የሚፈጠር ሠልፍ ነው፡፡ ነዳጅ ለመቅዳት የመንገዱን ጠርዝ ይዘው የቆሙ ተሽከርካሪዎችን ደርበው ተሳፋሪዎችን የሚጭኑና የሚያወርዱ ታክሲዎችና መካከለኛ አቶቡሶች ለመጨናነቁ መባባስ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ነዳጅ ከቀዱ በኋላ ወደ ዋናው መንገድ ለመግባት የሚሽቀዳደሙ ተሽከርካሪዎች ለትራፊኩ ፍሰት መታወክ ድርሻ አላቸው፡፡ የትራፊክ ፖሊሶች ወደዚህ አካባቢ ዝር አይሉም፡፡ አልፎ አልፎ ወረራ በሚመስል አካሄድ አካባቢን ያተራምሳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ለወራት አይታዩም፡፡ እንደሚመስለኝ ይኼ ብቅ ጥልቅ የሚለው አሠራራቸው ነው አሽከርካሪዎች ከሕጉ ይልቅ ፖሊሶችን እንዲጠነቀቁ ያደረጋቸው፡፡

‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› እንዲሉ አበው፣ ሃይ የሚል በሌለበት እንዳሻቸው የሚክለፈለፉ ሞተር ብስክሌቶች የሚፈጥሩት ችግር ሳያንስ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችም ወትሮውንም ቅጥ ያጣውን የትራፊክ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲያወሳስቡት ስለተፈቀደላቸው፣ የእንቅፋትነት ሚናቸውን ተያይዘውታል፡፡ ተሽከርካሪ አስመጪዎችስ የሚሸጧቸውን ተሽከርካሪዎች በየመንገዱ ዳር የሚያቆሙት ተፈቅዶላቸው ነው ወይስ በማን አለብኝነት? እንደውም ይኼንን ድርጊት ከሚፈጽሙት አንዱ አስመጪ የሚገኘው ከትራፊክ መቆጣጠሪያው ዋና መሥሪያ ቤት አፍንጫ ሥር መሆኑ አስገራሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡

አሁን ያለው የመንገዶች ዲዛይን እስከሚሻሻልና ለሕግ ተገዥ የሆኑ አሽከርካሪዎች እስኪፈጠሩ ድረስ፣ ከመሐል ከተማ ራቅ ባሉ አካባቢዎች የትራፊክ ፖሊሶችን በቋሚነት መመደብ በየዕለቱ ከሚደርሱት አሰቃቂ አደጋዎች አንፃር ሲታይ ይዋል ይደር የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ የትራፊክ ፖሊሶቹም በሥነ ምግባር የታነጹ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚመለከተው አካል የተጣለበት አደራና ኃላፊነት ነው፡፡ ሽንጠ ረዣዥም ተሽከርካሪዎች ባለፉና ባገደሙ ቁጥር ወታደራዊ ሰላምታ የሚሰጡ ፖሊሶች፣ ከአሽከርካሪዎቹ ጋር የሥጋ ዝምድና ከሌላቸው በቀር መቆጣጠር ይቸግራቸዋል ብለን ለመደምደም እንቸገራለን፡፡ ይባስ ብለው አሽከርካሪዎቹን መሐል መንገድ ወይም አደባባይ ውስጥ አስቁመው የደራ ጨዋታ የሚያጧጡፉ ፖሊሶችም አልፎ አልፎ ያጋጥሙናል፡፡

በነገራችን ላይ አንዱን አሽከርካሪ የትራፊክ ፖሊስ በደንብ መተላለፍ ሲያስቆመው፣ አሽከርካሪው ፖሊሱ የሚገልጽለትን ጉዳይ መከታተል ያለበት ከተሽከርካሪው ሳይወርድ ነው፡፡ በከተማችን ውስጥ በየጊዜው እንደምንታዘበው ግን ፖሊስ በደንብ መተላለፍ የሚያስቆማቸው አሽከርካሪዎች ፖሊሱን የሚያነጋግሩት ከተሽከርካሪው ወርደው ነው፡፡ በተለይ በዚህ ረገድ የታክሲ አሽከርካሪዎች ቅልጥፍና አጃኢብ ያሰኛል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ወዴት እንደሚያመሩ መገመት ብዙ ምርምር አይጠይቅም፡፡

የአዲስ አበባን የትራፊክ ችግር በጥልቀት ማጥናታቸውን እንድጠራጠር ያደረገኝ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ኃላፊው በመታጠፊያው ጉዳይ ላይ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት፣ የሲኤምሲ ነጋዴዎች የጠቀሱት የተዘጋው መታጠፊያ እንደገና ሊከፈት እንደሚችል ዳር ዳር ማለታቸው ነው፡፡ ኃላፊው ጊዜ አግኝተው ወደዚያ አካባቢ ብቅ ቢሉ፣ መታጠፊያው ተዘግቶም የትራፊክ ፍሰቱ እንዳልተሻሻለ ሊገነዘቡ ይችሉ ነበር፡፡ እግረ መንገዳቸውንም መሥሪያ ቤታቸው ለተሽከርካሪዎች ማቆሚያ በየመንገዶቹ ጠርዝ በነጭ ቀለም ያሰመራቸው ሳጥኖች ሙዝና ብርቱካን በሚቸረችሩ ነጋዴዎች በመያዛቸው፣ ወደ ሱፐርማርኬትም ሆነ ወደሌሎች አገልግሎት ወደሚሰጡ ቦታዎች መሄድ የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች ጋሪዎቹን ደርበው ለማቆም ስለሚገደዱ፣ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ እያስከተሉ ያሉትን ጫና ለመታዘብ መልካም አጋጣሚ ይሆንላቸዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡

በአጠቃላይ ከመገናኛ እስከ አያት አደባባይ ድረስ ባለው መስመር በየዕለቱ የሚስተዋለው የትራፊክ እንቅስቃሴ ችግር፣ ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል ቢባል ከቶውንም ማጋነን አይሆንም፡፡ ይልቁንም በከተማችን ውስጥ በሚታየው የትራፊክ ሥርዓተ አልበኝነት ዙሪያ ጥናት ለሚያደርግ ተመራማሪ ወይም በዚሁ ጉዳይ ላይ የመመረቂያ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ለሚፈልግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ፣ ያለብዙ ውጣውረድ  መረጃ እንደልብ ያገኛል፡፡ ለምሳሌ ከተባበሩት ነዳጀ ማደያ እስከ አያት አደባባይ ባለው መንገደ ሞተር ብስክሌቶች፣ ባጃጆች፣ በፈረስ የሚጎተቱ ጋሪዎች፣ በሰዎች የሚገፉ ቆሻሻ የጫኑ ጋሪዎች፣ በተለይ ጠዋት ደግሞ ሌሎችም ተሽከርካሪዎች በመምጫው መሄድ፣ በመሄጃው መምጣት የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ያለ ምንም መሸማቀቅ በልበ ሙሉነት ሲያሽከረክሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከባለ ሞተር ተሽከርካሪዎቹ የሚፈለገው ‹‹ሐዛርድ›› ወይም አደጋ የሚለውን የማስጠንቀቂያ ምልክት ማብራት ብቻ ይመስላል፡፡ እነዚህ የሚፈጥሩት ችግር ያነሰ ይመስል፣ በእርጅና ወይም በበሽታ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያልቻሉ ፈረሶች መሀል አስፋልቱ ላይ ቆመው እያንቀላፉ የትራፊኩን ፍሰት ሲያውኩ ማየት እግረኞችን ዘና የሚያደርግ ትርዒት ነው፡፡ የወቅቱን ቅዝቃዜ መቋቋም ያልቻሉ የቀንድ ከብቶች ደግሞ መሀል አስፋልቱ ላይ ተኝተው ሲያመሰኩ ማየት በአፍሪካ መዲናነቷ ለምትሞካሸው አዲስ አበባ የሚመጥን ዕይታ አይደለም፡፡ ይኼ ሁሉ አልበቃ ብሎ በእርጅና ወይም በመለዋወጫ ዕጦት ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ተሽከርካሪዎች የመጨረሻ ማረፊያቸው የከተማችን መንገዶች ሆነዋል፡፡

ይህን ማለት ግን በከተማችን ሌሎች አካባቢዎች ሥርዓት ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ አለ ማለት አይደለም፡፡ እኔ እያወራሁ ያለሁት በቅርብ ስለማውቀው አካባቢ ነው፡፡ ችግሩ ዘርፈ ብዙ መሆኑ ተነግሯል፣ ተጽፏልም፡፡ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ትራፊክ ፖሊሶች ሥነ ምግባር፣ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ ይነገራል፡፡ የእነዚህን ጥርጣሬዎች እውነተኛነት የማረጋገጥ አቅም ያላቸው ኩነቶች በየዕለቱ ሲፈጸሙ እንታዘባለን፡፡ ለምሳሌ አደባባይ ለሚዞር ተሽከርካሪ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆነ አሽከርካሪዎች የሚያውቁ አይመስልም፡፡ በድፍን መስመር ላይ ማሽከርከር ሌላው በስፋት የሚጣስ የትራፊክ ሕግ ነው፡፡ መንገዶች በነጭ ቀለማት የመከፋፈላቸውን ፋይዳ የሚረዱ አሽከርካሪዎች በከተማችን ውስጥ መኖራቸውን በበኩሌ በእጅጉ እጠራጠራለሁ፡፡

መነሻችን የሲኤምሲ ሚካኤል አካባቢ መታጠፊያ ነውና ወደዚያው ስንመለስ፣ ለመሆኑ በከተማችን ውስጥ በርካታ የተዘጉ መታጠፊያዎች እያሉ ዋልታ ቴሌቪዥን ዘገባውን በዚህኛው ላይ ለመሥራት የፈለገው በራሱ ተነሳሽነት ነው ወይም በነጋዴዎቹ ጥያቄ ያም ሆነ ይህ አስተያየት ሲሰጡ የነበሩት ነጋዴዎች ለሕዝብ ያላቸው ተቆርቋሪነት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡ ጄሶ ከእህል ጋር፣ ሸክላ ከበርበሬ ጋር ሙዝና ድንች ከቅቤ ጋር ተደባልቀው በሚሸጡበት አገር ውስጥ ደንበኛ ‹‹ንጉሥ›› ነው ማለት የሚዳዳቸው ነጋዴዎች መኖቸውን ላበሰረን ዋልታ ቴሌቪዥን ምሥጋና ይገባዋል፡፡

(ከአሥራት አበበ፣ አዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...