Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ሁሌም የማይረሱኝ ሁለት ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች አሉ፡፡ በአንድ ወቅት ዓለም ሁለት ታዋቂ ሰዎችን አጥታ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማክተም በኋላ ተጠቃሽ ከሆኑ ታዋቂ ሰዎች መካከል ጉልህ ሥፍራ የያዙት፣ የቼክ ዝነኛ ፖለቲከኛ ቫክላቭ ሐቬልና ኮሪያዊው ኪም ጆንግ ኢል ናቸው፡፡ ሁለቱም በተለያዩ ምህዋሮች ውስጥ የሚመዘኑ ቢሆንም፣ የያኔው አጋጣሚ ግን መነሻ ሆኖኛል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ ደግሞ ሌሎች ቢጋሩት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

የቼኩ ሐቬል የቀድሞው የቼኮዝሎቫኪያ የኮሙዩኒስት መንግሥት ላይ አመፅ በማስነሳት አገሪቱን ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የሚያመራውን የነፃነት ጉዞ ሲያስጀምሩ፣ በዓለም ዙሪያ ዝናቸው ከዳር እስከ ዳር ናኝቶ ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ መሞት አይቀርምና ቼኮች እኚህን የቁርጥ ቀን ልጅ እጅግ በሚያስደስት ሥነ ሥርዓት ትግላቸውን እያወደሱ ሥርዓተ ቀብራቸውን ሲፈጽሙ ታይተዋል፡፡ በወቅቱ አንዲት የ19 ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ “ቫክላቭ ሐቬል ያንን ጨካኝና አረመኔ የኮሙዩኒስት አምባገነን በድፍረት በተጋፈጡበት ዘመን ባለመፈጠሬ እጅግ በጣም አዝን ነበር፡፡ ነገር ግን እኚህን የአገራችንን ጀግና በክብር ለመሸኘት በመታደሌ ግን እጅግ በጣም ተደስቻለሁ፤” ማለቷ ይታወሳል፡፡

የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኢል ሕልፈተ ሕይወት እንደተሰማ ሰሜን ኮሪያውያን እንደዚያ እየወደቁ፣ እየተነሱ ሲያለቅሱና ደረታቸውን እየመቱ ሲጮኹ ላያቸው ግርም ያሰኝ ነበር፡፡ የሰውየው አባት የዛሬ 25 ዓመት አካባቢ በሞት ሲለዩ የቴሌቪዥን ዜና አንባቢውን ጨምሮ አገሬው በሙሉ ሲላቀስ ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡ ኮሪያውያን ለመሪያቸው እንዲያ በማልቀሳቸው ሊገባኝና ሊዋጥልኝ የማይችል ነገር ሆኖብኝ ነበር፡፡ ከዓለም ተገልላ ዜጎቿ በድህነት የሚኖሩባትና ኑክሌር የጦር መሣሪያ የሠራች አገር ለመሪዎቿ እንዴት እንዲህ ይንገበገባሉ አሰኝቶኛል፡፡ ጃፓን ውስጥ ነዋሪ የሆነው ሰሜን ኮሪያው ዋንግ ሐን፣ “እኛ ኮሪያውያን ቅርበታችን የቤተሰብ ያህል ስለሆነ መሪም ሆነ ሌላ ሰው ሲሞት እናዝናለን፡፡ በበኩሌ አገሬ ያለችበት ሁኔታ ባያስደስተኝም፣ የአገራችን መሪ ሞተ ሲባል አዝኛለሁ፤” ነበር ያለው፡፡

ልብ በሉ ኮሪያዊው በአገሩ ደስተኛ ባይሆንም መሪው ሲሞት ሐዘን እንደሆነበት ነው የተናገረው፡፡ የእኔም ገጠመኝ የጀመረው ከዚህ ነው፡፡ በአገራችን ለመሪዎቻችን ፍቅርና ክብር የሚኖረን መቼ ነው? በየትኛውም ደረጃ ያሉ የሚመሩን ሰዎችስ ከእኛ ጋር ግንኙነታቸው ምን ያህል ነው? እርስ በርሳችን ከመሸነጋገልና ከአንገት በላይ ከሆነው ግንኙነታችን ውጪ መቼ ይሆን የምንተሳሰበው? የምንፈቃቀረው? የምንወቃቀሰው? የምንተጋገዘው? እንኳን በአገር ደረጃ አይደለም በአንድ አነስተኛ መሥሪያ ቤት ውስጥ ሳይቀር አንዱ ላንዱ አይተኛም፡፡ የራሱን ሳይሆን የሰውን ጥፋትና ጉድለት እየተከታተለ ለማሳጣት ወይም ለማስጠላት የሚያደርገው ትንቅንቅ ጎልቶ ይታያል፡፡ እሱ ስለተሰጠው ሳይሆን ሌላው ስላገኘው እንቅልፍ አጥቶ ያድራል፡፡ ውስጣችን በክፋትና በምቀኝነት የተሞላ ስለሆነ ሰላም የለንም፡፡

ትናንት በችግር ጊዜ፣ በመከራ ጊዜ፣ ሕይወት አደጋ ውስጥ በነበረችበት ወሳኝ ወቅት፣ ከመከራው ፅናት የተነሳ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ይባባሉ የነበሩ የት አሉ? የትናንቱ የአብሮነት መንፈስ ዛሬ በግላዊ ፍላጎት ተውጦ ክፋት ሲነግሥ ቅኖች ያዝናሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መንፈስ ጥላቻና ክፋትን እያገነነ የመተሳሰብና የመደጋገፍን ስሜት ያበላሻል፡፡ እንዲህ ዓይነት ክስተት ደግሞ ወንድማማቾችን፣ ጓደኛማቾችን፣ ባለትዳሮችን፣ የትግል ጓደኞችንና የመሳሰሉትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አለያይቷል፡፡ በእዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ጎረቤት ከሆነኝ ሰው ጋር ስንነጋገር እንዲህ አለኝ፡፡

በወጣትነቱ ከኮሌጅ ተመርቆ እንደወጣ ያገባት ባለቤቱ አንድ ልጃቸውን ከወለደች በኋላ ድንገት ፀባይዋ ይቀየርበታል፡፡ ቢያባብላት፣ ቢመክራት፣ ቢያስመክራት እየባሰባት ይሄዳል፡፡ ይውጣልህ ብላው ጭራሽ እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ድረስ እሱ የማያውቀው ቦታ እያመሸች መምጣት ትጀምራለች፡፡ ለሕፃኑ ልጅ ሲል ቢታገሳትም ይባስ ብላ ደጅ ማደር ትጀምራለች፡፡ ሕፃን ልጅ ማሳደግ፣ ሥራና የማታ ትምህርት ፋታ ያሳጡት ጎረቤቴ ምርር ሲለው ባለቤቱን መሰለል ይጀምራል፡፡ ከእሷ ቢጤ አለሌዎች ጋር መቅበጥ መጀመሯን ይደርስበታል፡፡ ወዲያውኑ ለቤተሰቦቿ ነግሮ በፍርድ ቤት ፍቺ ይፈጽማል፣ ይለያያሉ፡፡ እሱም አድካሚውን ተግባሩን ይቀጥላል፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የልጁ እናት ታማ መሞቷን ይሰማል፡፡ ጦሱ ደግሞ የገባችበት አደገኛ ተግባር ነው፡፡ የራሱንና የልጁን ጤናማነት በወቅቱ ያረጋገጠው ጎረቤቴ ምንም እንኳ የአሁኗን ፀባየ ሸጋ ባለቤቱን ቢያገባም፣ ሟችን እንባውን አዝርቶ በክብር ይቀብራታል፡፡ መቼም ቢሆን ወልዳለታለች፡፡

“አየህ እኔና ልጄን ለአደጋ አጋልጣ እንደዚያ ስትሆን በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ልጄን ያለ እናት አሳድጋለሁ ብዬም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ በእሷ የተነሳ ሕይወቴ ተመሰቃቅሏል፡፡ ትምህርቴንም ለረዥም ጊዜ አቋርጬ ልጄ ሲጠነክር የአሁኗን ባለቤቴን ካገባሁ በኋላ ነው የቀጠልኩት፡፡ የእኔንም ሆነ የልጄን ሕይወት አደጋ ውስጥ ከትታ የክህደት ሥራ ብትሠራም፣ በወቅቱ ከጠብ ይልቅ የመረጥኩት ፍቺን ነበር፡፡ ዓመታት ነጉደው በፈጠረችው ችግር ምክንያት ሞተች ሲባል ግን በጣም አዘንኩ፣ ውስጤ ተላወሰ፤” አለኝ፡፡ ቂምና ብቀላ በበዛበት በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነቱ ቅን ሰው መገኘቱ ገርሞኝ፣ “ውስጥህ እንዴት እሺ አለው?” በማለት ጠየቅኩት፡፡ “ልብህን ለክፋት ካዘጋጀኸው ሰይጣን ይገባበታል፣ ለደግነት ከከፈትከው ደግሞ የፍቅር አምላክ ይጎበኘዋል፤” ሲለኝ ጎረቤቴን ከመቼውም ጊዜ በላይ አከበርኩት፣ ወደድኩት፡፡

አገራችን የምትፈልገው እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ነው፡፡ ከክፋት ይልቅ ደግነት፣ ከበቀል ይልቅ ይቅርታ፣ ከአሉባልታ ይልቅ እውነት፣ ከሌብነት ይልቅ ንፅህና፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ወዘተ የሚያስተምር መሪ አግኝተን እንኳን ልባችን እየሸፈተ በርካታ በደሎች በወገኖቻችን ላይ ተፈጽመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ከበቀለኛ አስተሳሰብ ወጥተን አገር እንገንባ ሲሉን፣ እኛ በምላሹ እርስ በርስ የምንበላላ ከሆነ ውስጣችን የማይታወቅ የተደበቀ ነገር አለ ብለን መፈተሽ ይኖርብናል፡፡ አንዱ ይነሳና ከክልሌ ውጣ በማለት የገዛ ወገኑን ባዕድ ሲያደርግ፣ ሌላው ደግሞ እንትን የሚባለው ሥፍራ ወይም ከተማ የእኔ ብቻ ነው ብሎ አካኪ ዘራፍ እያለ ሲደነፋ የኢትዮጵያዊነትን ትልቅ ምሥል ሲያደበዝዝ ይውላል፡፡ ለአገር ማለት ቀርቶ ወንዜን ብቻ እያሉ ማላዘን የጤነኝነት ሳይሆን የዕብደት ምልክት ነው፡፡ “የዶ/ር ዓብይን መርህ ተከትለን ቅድሚያ ለኢትዮጵያዊነት ማለት ካልጀመርን፣ በጎጠኝነት ተውጠን እርስ በርስ ተበላልተን አገር እናፈርሳለን፤” ያለኝ ከላይ ያነሳሁት ጎረቤቴ ነበር፡፡ አገር ወዳድ ለመሆን ሰብዓዊነትን መላበስ የግድ ይላል፡፡ አገሩን የማይወድ የወገኑን ደም ለማፍሰስ ወደኋላ አይልም፡፡ ልባችንን ለደግነትና ለሰብዓዊነት ከፍተን አገራችንን ከቀውስ በመታደግ ወደ ዴሞክራሲና ብልፅግና እናምራ፡፡ አይሆንም ብለን በተቃራኒው ብንጓዝ ግን የማንወጣው አዘቅት ውስጥ ነው የምንገባው፡፡   

(ነገደ ታምራት፣ ከዮሐንስ)   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...