Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክመስኩን ያቃተው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ በሕገ መንግሥታዊነት መነጽር

መስኩን ያቃተው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ በሕገ መንግሥታዊነት መነጽር

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በውብሸት ሙላት

ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሕዝባዊ አጀንዳ ሆነው ከቆዩት ጉዳዮች መካከል አንዱ ኢሕአዴግና ብሔራዊ አባል ድርጅቶችን የሚያያይዝ ነው፡፡ አባል ድርጅቶቹ ያደረጓቸው ለውጦችና ሕዝባዊ አጀንዳ የሆኑ፣ ነገር ግን ለውጥ ያልተደረገባቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው ግን ባለፈው ሳምንት በወጣው ጽሑፍ ላይ እንደገለጽነው የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ሕገ መንግሥታዊነት፣ እንዲሁም የግንባሩና የአባል ድርጅቶችን የሚኖራቸው ግንኙነትና ከፓርቲ ሕጉ አንፃርና ከመተዳደሪያ ደንባቸው አኳያ ፍተሻ እናደርጋለን፡፡

ከዚያ በፊት ግን ስለፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት እንመልከት፡፡ አንዳንዶቹ ንቅናቄ፣ ሌሎቹ ፓርቲ ወይም ድርጅት አለበለዚያ ግንባር የሚል ስያሜ ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህ ስያሜዎች ጽንሰ ሐሳቦቹንና ሕግ ትርጓሜ ያላቸውንም እንዲሁ ሕጉንም እንቃኛለን፡፡

እንደሚታወቀው የኦሮሞ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ወደ የኦሮሞ ዴሞክራሲ ፓርቲ ስያሜውን ቀይሯል፡፡ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲ ንቅናቄም (ብአዴን) ስሙን ወደ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለውጧል፡፡ እነዚህን ለውጦች መነሻ በማድረግ ስለንቅናቄ፣ ፓርቲ/ድርጅት፣ ግንባርና ቅንጅት ምንነት አስቀድመን እናያለን፡፡

የተቃዋሚ (የተፎካካሪ) ፓርቲዎችን ትተን አገሪቱን በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ እያስተዳደሩ ያሉትን ፓርቲዎች አደረጃጀት ስናጤን አንድ ግር የሚል ነገር ማስተዋላችን አይቀርም፡፡ እሱም የተወሰኑት ግንባር (ሕወሓት/TPLF፣ ኢሕአዴግ)፣ ሌሎቹ ንቅናቄ (ብአዴን፣ ደሕዴን፣ ጋሕዴን)፣ የተወሰኑት ፓርቲ (አብዴፓ፣ ሶሕዴፓ፣ ቤጉዴፓ)፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ድርጅት (ኦሕዴድ) የሚል ገላጭ ወይም አመላካች መጠቀማቸው ነው፡፡ ሕወሓት (TPLF) አንድ ድርጅት ብቻ ሆኖ ሳለ በግንባርነት መጠራቱ ወይም መመዝገቡ፣ ብአዴን፣ ደኢሕዴን፣ ጋሕዴን ደግሞ ገዥ ፓርቲዎች ሆነው ሳለ፣ ንቅናቄ የሚል ቅፅል ይዘው መጓዘቸው ብዥታን ሳይፈጥር አይቀርም፡፡ ንቅናቄ፣ ግንባርና ፓርቲ ወይም ድርጅት ሲባል ምን ማለት ነው? ልዩነታቸው ምንድን ነው?

‘ንቅናቄ’ (Movement) በሚል ዘውግ የሚሰባሰቡትና የሚደረጁት በአብዛኛው ማኅበራዊ ድርጅቶች ናቸው፡፡ አንድ ግብ አስቀምጠው እሱን ለማሳካት የሚጥሩ ናቸው፡፡ ስለጉዳዩ የተጻፉ ድርሳናትን በምንቃኝበት ጊዜ ንቅናቃዎች በግልጽ የተቃዋሚ ፓርቲነት ሚና ባይኖራቸውም ከፖለቲካ ግን ገለልተኛ ላይሆኑ ይችላሉ፣ አይደሉምም፡፡ የተቋቋሙበትን ዓላማና ግብ ለማሳካት ሲሉ የሚንቀሳቀሱ ስለሚሆኑ፡፡ ወደ ፓርቲነትም ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ንቅናቄዎች ሊመደቡ የሚችሉት ከብዙኃን ማኅበራት (Civil Societies/Organizations) ጎራ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የትጥቅ ትግል የመረጡ ድርጅቶችም በንቅናቄ መልክ ይደራጃሉ፡፡ ማስወገድ የሚፈልጉትን የአገዛዝ ሥርዓት እስከሚያስወግዱ ድረስ በዚሁ አኳኋን ይጠራሉ፡፡ ሥልጣን ሲይዙ ግን ወደ ፓርቲ ይቀየራሉ፡፡ ከአደረጃጀት አንፃር ሲታዩም ንቅናቄዎች ላላ ያለ ሞዴል ይከተላሉ፡፡ በእርግጥ የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ድርጅቶች በሰላማዊ ትግል ከሚታገል ፓርቲም የበለጠ ጥብቅ ተዋረዳዊ ዲሲፕሊን እንደሚከተል ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ንቅናቄዎች የሆነ ግብ ለማሳካት ሲባል የሚቋቋሙ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በሌላ ክፍለ ዓለም ከቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት የተቋቋሙ በርካታ ንቅናቄዎች ነበሩ፡፡ ስማቸው ግን በዚያው አልቀጠለም፡፡

በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጁ ቁጥር 573/2000 ላይ ስለንቅናቄ ምንነት አልተገለጸም፡፡ በኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲም ሆነው ንቅናቄ የሚለውን ስያሜ የያዙ አሉ፡፡ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በቅርቡ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ብሎ ስያሜውን እስከቀየረበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ኢሕዴን) ሲወርስ ንቅናቄ የሚለውን ግን አልተወም፡፡ ደኢሕዴንም እንደ ብአዴን ሁሉ ንቅናቄ ነው፡፡ ብአዴን በቅርቡ ስሙን መለወጡን በመርሳት አይደለም፡፡

 እዚህ ላይ አዲሱን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብንን) በምሳሌነት ብናነሳ የአማራ ሕዝብን ብሔራዊ ንቃት በመጨመር እንዲደራጅ፣ ለመብትና ጥቅሙ ዘብ እንዲቆም ማንቃትና የመሳሰሉትን ተግባራት የሚያከናውን እስከሆነ ድረስ ንቅናቄ የሚለው ገላጭ ነው፣ አብሮ ይሄዳል፡፡ ለምርጫ ሲወዳደር ግን ከንቅናቄ ይልቅ ወደ ፓርቲ ቢቀየር ከላይ ከቀረበው ጋር ይስማማል፡፡

 ግንባር የሚለውን እንይ፡፡ ‘ግንባር’ (Front) ማለት ጠቅለል ብሎ ሲገለጽ የሚያመለክተው ለጋራ ዓላማ በአንድ አመራር ሥር ተሰባስበው ወይም ተጠቃልለው የሚታገሉ ወይም የሚሠሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚመሠርቱት ወይም የሚሰባሰቡበት መድረክ ነው፡፡ አባል ድርጅቶች በአንድ ዘላቂ ፕሮግራም የመተሳሰር ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ‘ግንባር’ የሆነ ግን አንድን ግብ ለማሳካት ሲባል ነው የሚፈጠረው፡፡ የግንባር አባል ድርጅቶች በተወሰነ ፕሮግራም ላይ የዓላማ አንድነት ይፈጥሩና በአንድ አመራር ሥር ሆነው ይታገላሉ፡፡ ‘ግንባር’ በመፍጠር የሚታገሉለት ዓላማ ሲሳካ ይፈርሳሉ፡፡ ካልሆነም ወደ ሌላ ቅርፅ ይለወጣሉ፡፡

ስለሆነም ‘ግንባር’ ጊዜያዊ ነው ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ አገሮች እንደተስተዋለው ሕዝባዊ ግንባር በመሆን የተወሰነ ዓላማን ከማሳካትም አልፈው ቀጣይነት እንዲኖረው በማሰብ የተመሠረቱ ድርጅቶች አሉ፡፡ አሁንም በበርካታ አገሮች ይሠራባቸዋል፡፡ አንድ የጋራ ዓላማን እስከሚያሳኩበት ጊዜ ድረስ ብቻም ይሁን ቀጣይነት ባለው መልኩ ይቋቋሙ፣ ዞሮ ዞሮ ግን ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ፓርቲዎችን ወይም ድርጅቶች በሌሉበት ግንባር መሆን አይቻልም፡፡

የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጁ ቁጥር 573/2000ም ስለግንባር ከዚሁ ጋር የተቀራረበና የሚስማማ ትርጓሜ ሰጥቶታል፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ራሱን የቻለ ፖለቲካ ፓርቲ ወይም ደግሞ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅንጅት ወይም በግንባር መልክ ሊመሠርቱ ይችላሉ፡፡ ‘ቅንጅት’ እና ‘ግንባር’ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ፓርቲዎችን ይፈልጋል፡፡ በግንባር መልክ ሲደራጁ የእያንዳንዱ ፓርቲ የተናጠል ህልውናው እንደተጠበቀ ይቀጥላል፡፡ ይሁን እንጂ የጋራ ፕሮግራምና አመራርም ይኖራቸዋል፡፡ ‘ቅንጅት’ ሲሆን ለአንድ ጊዜያዊ ዓላማ ስኬት ሲባል የሚቋቋም ነው፡፡ ከዚያም በቅንጅት መልክ የተፈጠረው ድርጅት ይፈርሳል፡፡ ስለግንባርና ቅንጅት፣ የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጁ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 2 (9) እና (10) መመልከት ነው፡፡

እዚህ ላይ ከላይ ከቀረበው አንፃር ኢሕአዴግንና የአባል ድርጅቶቹን ሁኔታ የተወሰኑ ነጥቦችን መጀመርያ ላይ እንመልከትና በመቀጠል ደግሞ ስለ ‘ቅንጅት’ እንመለከታለን፡፡ ሁለትና ከእዚያ በላይ የሆኑ ፓርቲዎች ግንባር ሲፈጥሩ የየራሳቸው ሕጋዊ ሰውነት እንደተጠበቀ ሆኖ በግንባርነት ደግሞ ሌላ ድርጅት ይሆናሉ፡፡ አባላቱም ግንባሩም ለየብቻቸው መብትም ግዴታም ማለት ነው፡፡ ውል መዋዋልም ሀብት ማፍራትም ይችላሉ፡፡

ኢሕአዴግ በግንባርነት የራሱ ህልውና ስላለው ለምርጫ ይወዳደራልም ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ እንደ ድርጅት ይወዳደራል፡፡ ከኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ መረዳት እንደሚቻለው አባላቱ እኩል መብት ስላላቸው በእኩል ቁጥር ወይም ግንባሩ በሚወስነው መሠረት አዲስ አበባ ላይ ለምርጫ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ ድሬዳዋ ላይ ሲሆን ደግሞ ከኢሕአዴግ በተጨማሪ የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትም ጉዳይ አለ፡፡ የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የኢሕአዴግ አጋር በመሆን ይወዳደራል፡፡ ከዚህ ባለፈ አራቱ ክልሎች ላይ ግን አባል ድርጅቶች እንዳሉ ይወዳደራሉ፡፡ አባል ድርጅቶችም ግንባሩ ሕግና ደንብ የመገዛትና የማክበር ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡

ስለአጋር ፓርቲ ምንነት በፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጁ ላይ የተገለጸ ነገር አናገኝም፡፡ ከምርጫ በኋላ የሚደረግ ጥምረትም ነው እንዳይባልም በተግባር የሚታየው ሌላ ነው፡፡ የድሬዳዋን በምሳሌነት ብንወስድ እንኳን ኢሕአዴግ ወይም የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከሁለት አንደኛቸው ከተማውን ለማስተዳደር የሚያስችል መቀመጫ ሳያገኙ ስለቀሩ የሚፈጠር አጋርነት ሳይሆን እንደ አንድ ፓርቲ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህንን የበለጠ መረዳት የሚቻለው ከኢሕአዴግ ፕሮግራም ነው፡፡  በመሆኑም ከምርጫ በፊት የሚደረግ አብሮ የመሥራት ስምምነት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ እንመለስበታለን፡፡

በቅንጅት ወደሚመለከተው ጉዳይ ስናልፍ ለመቀናጀት የሚፈልጉ የክልል ወይም አገር ዓቀፍ ፓርቲዎች በምን በምን ጉዳይ ላይ ተቀናጅተው መሥራት እንደሚፈልጉና የወሰኗቸውን ጉዳዮች ለምርጫ ቦርድ በማስፅደቅ የራሳቸውን ሕጋዊ ሰውነት ሳይተው አዲስ ድርጅት ፈጥረው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ቅንጅት ለመፍጠር የሆነ ጊዜያዊ ግብ መለየት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ግብ ለማሳካት ይሠራል፡፡

እዚህ ላይ ምርጫ በሚደረግበት ጊዜ በጋራ ለመወዳደር ከሆነ ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ወይም ምርጫው ካለቀ በኋላም በምክር ቤት መቀመጫ ካገኙም እንደ አንድ ፓርቲ ሆኖ ለመሥራትም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ለምን ጉዳይና እስከ ምን ድረስ ተቀናጅተው እንደሚቀጥሉ ራሳቸው የሚቀናጁት ፓርቲዎች በሚወስኑት ላይ የሚመሠረት ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት

የፖለቲካ ፓርቲና የፖለቲካ ድርጅት ትርጉማቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ፓርቲ ወይም ድርጅት የሚል ቅፅል ወይም ገላጭ ቢጠቀሙም ትርጓሜው ግን አንድ ነው፡፡  የተወሰኑ አባላት እስካለው፣ የፖለቲካ እምነቱንና ፍላጎቱን ሕግ በሚፈቅደው ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ለመራመድ የተመዘገበ ማኅበራዊ ተቋም ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡

ወደ ሁለተኛው ዓቢይ ጉዳይ እንመለስ፡፡ አብዮታዊ ዴምክራሲን ወደሚመለከተው ነጥብ፡፡ የኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ማኅበራዊ መሠረቱም ገበሬው ነው፡፡ በፕሮግራሙ ላይ እንዳሠፈረውም ኢሕአዴግ የገበሬ ድርጅት ነው፡፡ ከእዚህ ውጪ ያሉ ለምሳሌ የከተማ ነዋሪ፣ ሠራተኛውና የተማረው/ልሒቁ አጋርና ደጋፊ ነው፡፡ ይህ አካሄድና መከፋፈል በተለይም የሆነ የማኅበረሰብ ክፍልን ብቻ በዋናነት ለመጥቀም ሲባል አገርን መምራት ሕገ መንግሥቱን ያከበረ ነውን? የሚለውንም መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል፣ መደቡ ምንም ይሁን ምን፣ የተማረ ይሁን ገበሬ፣ ነጋዴ ይሁና ሌላ በፈለገው የኢኮኖሚ ዘርፍ የመሠማራት፣ ንብረት የማፍራት፣ ከአድልኦ የፀዳ አገልግሎት ማግኘት መብት እንዳለው ሕገ መንግሥቱ አረጋግጦ እያለ ገበሬን ብቻ መሠረቴ፣ ሦስት የሚደርሱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አጋርና ደጋፊዬ ብሎ መሥራት ሌላውን ማግለል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሊሆን አይችልም፡፡

ይህ ዓይነቱ ርዕዮተ ዓለም በተለይ በቻይና የተተገበረ ነው፡፡ ማኦ የቻይናን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ሶሺያሊስታዊ አብዮት ለማካሄድ የሚያስችል መካከለኛ ገቢ ያለው የከተማ ነዋሪ፣ ሠራተኛና ልሒቅ ስላልነበር በገበሬው ላይ የባህል አብዮት በማከናወን ከላይ ወደታች የሚደረግን ውሳኔ ሰጥ ለጥ ብሎ በማስፈጸም የባህል አብዮት አካሄደ፡፡ የኢሕአዴግ ፍላጎትም (ቢያንስ በፕሮግራሙ ላይ እንደተቀመጠው) ይኼንኑ አካሄድ መርጧል፡፡ ለአፈጻጸሙም የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የተሳትፎና የውሳኔ ሥርዓትን ተቀብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ ይህን ዓይነቱን አካሄድ አይቀበልም፡፡ እንደ ፓርቲ ውስጣዊ ዴሞክራሲ መከበር አለበት፡፡ ይህን ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 መረዳት ይቻላል፡፡ የውሳኔ ሥርዓትም በተለይ ልማትን የሚመለከቱ፣ ከታች ወደ ላይ መሄድ እንዳለባቸው አንቀጽ 43 ላይ ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ ከታች ከሚገኘው ማኅበረሰብ በመጀመር በማሳተፍ ወደ ላይ የሚሄደውን ነው ሕገ መንግሥቱ የመረጠው፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ ይህ እንዳለ ሆኖ ከላይ የሚወሰኑትነም ሳያቅማሙ ማስፈጽምን ፕሮግራሙ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ከሕገ መንግሥቱ ጋር ያለው ተቃርኖው ግልጽ ነው፡፡ እንደ ፕሮግራሙ ብቻ ማስፈጸም የሚችልበት ዓለም አቀፋዊም ሕገ መንግሥታዊ ሁኔታም የለም፡፡

ኢሕአዴግ አብዮታዊ በሆነ አካሄድ በአገሪቱ ሰፍኗል በማለት የገለጸውን ኋላቀር የአስተዳደርና የዴሞክራሲ ባህል መዋጋት አንዱ ዓላማው ነው፡፡ እዚህ ላይ ወደ ማንም ሰው ህሊና የሚመጣ አንድ ጥያቄ ይኖራል፡፡ ኢሕአዴግ ኋላቀር ያላቸውን ባህሎች ማጥፋት ግቡ ከሆነ እንደምን አድርጎ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል ማክበር፣ የራስን ዕድል በራስ መወሰን፣ መብት ጋር እንዴት ማጣጣም ይቻላል?

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢሕአዴግ እንደ አንድ ሕጋዊ ሰውነት እንዳለው ድርጅት ደግሞ አባል ድርጅቶቹ የሚመሩት ሕግና ደንብ አለው፡፡ አባላቱ ውልፍት ሳይሉ አብዮታዊ ዴሞክራሲን መከተልም በእሱ መሠረትም መመራት አለባቸው፡፡ ካልሆነ በአባልነት ላይቀጥሉ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም በተናጠል ይህንን ርዕዮተ ዓለም እንዲቀይሩ የሚፈቅድ የፓርቲው ሕግ አይፈቅድም፡፡ የርዕዮተ ዓለሙ ሕገ መንግሥታዊነት ከላይ እንዳየነው አጠያያቂ ቢሆንም፣ በተናጠል መቀየር ካልቻሉ ወይ ከግንባሩ መልቀቅ አለበለዚያም ሕገ መንግሥታዊ አለመሆኑን በመገዳደር መተዳደሪያ ደንቡንም ርዕዮተ ዓለሙንም እንዲቀይር ማድረግ ነው፡፡

እንግዲህ ኢሕአዴግ በፕሮግራሙ እንደገለጸው ኢትዮጵያን ማስተዳደር የሚቻለው በግንባር መልክ በመደራጀት ብቻ ነው፡፡ በግንባር የመደራጀት ፋይዳም ያስቀምጣል፡፡ በአንድ በኩል ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር እንዲታገሉ ለማድረግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ በመመራት በብሔሮች መካከል ወንድማማችነትን (Fraternity) ለማጎልበትና አንድነት ለማምጣት ስለሚጠቅም እንደሆነ ይገልጻል፡፡

እነዚህ ሁለት ግቦችንና ነባራዊ ሁኔታው ምን እንደሚመስል ለአንባቢው ትተናል፡፡ በተለይ ወንድማማቻዊነትን ለማምጣት ብሔርን መሠረት ያደረገ ፓርቲያዊ አደረጃጀት እንደምን ሊመረጥ ይችላል በእርግጥስ ይህ ሁሉ ማንነትን መሠረት ያደረገ መፈናቀልን ስንመለከት ያው ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይቺ በብሔሮች መካከል የወንድማማችነት (እህትማማችነት) መርህ ለመፍጠር መንግሥት መሥራት እንዳለበት ማንነትን፣ ማክበርና እኩልነት ጋር በተደራቢነት ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 88 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ ሠፍሮ እንገኘዋለን፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ፖለቲካ ነክ ዓላማዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ብሔራዊ ማንነትን የማክበር፣ እኩልነትና ወንድማማችነትን በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ከማጠናከር ረገድ በአገራችን የሠፈነው የፓርቲ አደረጃጀት ሥርዓት (የኢሕአዴግንም ጨምሮ) ሊጤን ይገበዋል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...