Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹‹ሕዝብ›› ወይስ ‹‹ሕዝቦች››?

‹‹ሕዝብ›› ወይስ ‹‹ሕዝቦች››?

ቀን:

በመርሐ ጽድቅ መኰንን ዓባይነህ

በየትኛውም ሉዓላዊ አገር ውስጥ የሚኖርና ራሱን በቻለ አንድ ብሔራዊ መንግሥት ጥላ ሥር የታቀፈ የሰዎች ስብስብ ‹‹ሕዝብ›› እንጂ፣ ኢሕአዴግ እንደሚለው ‹‹ሕዝቦች›› በመባል አይታወቅም፡፡ በምድራችን እንዲያ እየተባለ የሚጠራበት ከኢሕአዴጓ ኢትዮጵያ በስተቀር ሌላ አገር ካለች ከምላሴ ፀጉር ይነቀል፡፡

‹‹ሕዝብ›› የሚለው ቃል ራሱ ብዙ ሆኖ ሳለ ‹‹ሕዝቦች›› ብሎ ያላግባብ ማባዛቱ የአንድና ብዙን ሰዋሰዋዊ ሕግ በዘፈቀደ ከማፍረሱም በላይ፣ የጋራ በሆኑ እሴቶች የተሳሰረን አንድና የተዋሀደ ሕዝብ አፍራሽ በሆነ መንገድ በመከፋፈልና በመለያየት ረገድ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ እየዋለም ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ወሰኑ በታወቀና ድንበሩ በዓለም አቀፍ ሕግ ሳይቀር በተረጋገጠ አንድ አገር ውስጥ ሊኖር የሚችለው አንድ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ የቻይና ሕዝብ፣ የአውስትራሊያ ሕዝብ፣ የናይጀሪያ ሕዝብ፣ ወዘተ… እንዲሉ፡፡

እዚህ ላይ ታዲያ ሊስተባበል የማይችለው ዓብይ ቁም ነገር በዚህ ወይም በዚያ ሕዝብ ውስጥ በትውልድ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና እነዚህን በመሳሰሉት ጉዳዮች ረገድ የተለያዩ ነገዶችና ማኅበረሰቦች ሊኖሩ የመቻላቸው እውነታ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያችንም ከዚህ የተለየች አይደለችም፣ ልትለይም ከቶ አይቻላትም፡፡ ይሁን እንጂ በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው ባለ ብዙ ማንነት ማኅበረሰቦች ቢኖሩም፣ ከአገሪቱ ጋር ካላቸው ጥብቅ የዜግነት ቁርኝትና ትስስር አንፃር ድምር ወይም የጋራ መጠሪያቸው ‹‹ሕዝብ›› እንጂ ‹‹ሕዝቦች›› ሊሆን አይችልም፡፡

በእርግጥ ብሔራዊ ማንነቱን፣ የሚናገረውን የአፍ መፍቻ ቋንቋ ወይም በተለይ የሰፈረበትን መልክዓ ምድራዊ አካባቢ ተንተርሰን አንድን የሕዝብ ክፋይ በተለምዶ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የጉራጌ… ሕዝብ እያልን እንዳንጠራ ፈጽሞ የተከለከለ ነገር አይደለም፡፡ ሆኖም ይህ የቡድን መጠሪያ የዚያ ማኅበረሰብ የራሱ ዘውጋዊ መለያ እንጂ፣ የአገራዊ ማንነቱ መገለጫ እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ያንኑ ማኅበረሰብ ከሌሎች መሰል ስብስቦችና ከአገሩ ጋር ስናቆራኘው የጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ክፍልና አካል እንጂ፣ ራሱን የቻለና የተነጠለ ሕዝብ ሊሆን አይችልም፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የታወቀና የተጠበቀ የግዛት ወሰን ያላት የምድራችን አንድ ክፍል ናት፡፡ ቁጥሩ እስካሁን ድረስ በውል ተለይቶ ባይታወቅም፣ አብዝተን በለመድነው አነጋገር ከሰማኒያ በላይ የሚሆኑ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ይኖሩባታል፡፡ በዚህ ረገድ እስከ 250 የሚደርሱ ብሔር ብሔረሰቦችን በመያዝ ሁለት ጊዜ ያህል ከሚያጥፏት ከእነ ናይጀሪያ ባትበልጥ እንኳ የብሔረሰቦች ሙዚየም ናት እያልን እንውረገረግባታለን፡፡

እኛ ሐበሾች በሁሉም ነገር አንደኞች ነን ማለቱ ስለሚቀና፣ ይህ በእርግጥ እንደ ቁም ነገር ተቆጥሮ እምብዛም ላያስገርም ይችል ይሆናል፡፡ ከቅርብ አሠርተ ዓመታት ወዲህ ከእምነት፣ ከቋንቋም ሆነ ከጂኒኦሎጂ አንፃር የተለያየ ማንነት ቢኖራቸውም፣ በረዥሙ የአገር ምሥረታ ታሪካዊ ሒደት እርስ በርስ ከመደባለቃቸውና ከመጋመዳቸው የተነሳ እንደ አንድ ሕዝብ የተጠቃለሉትን አያሌ ማኅበረሰቦች፣ ከቡድናዊ መጠሪያቸው ባሻገር በደምሳሳው ሕዝቦች እያሉ ጠዋትና ማታ ማንቆለጳጰሱ ግን ሰሚውን ግር ከማሰኘት አልፎ ለዘመናት በመካከላቸው የተገነባውን ፅኑ አንድነት ክፉኛ ያላላዋል፡፡

መሬቱ ይቅለላቸውና ይህን ፈሊጣዊ አነጋገር በአገራችን ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀሙበት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ ይታወስ እንደሆነ ንግግራቸውን በጀመሩ ቁጥር ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ›› ከማለት ይልቅ ‹‹መላ የአገራችን ሕዝቦች›› እያሉ ቢጠሩን ነበር አብዝቶ የሚቀናቸው፡፡ እኛ ደግሞ መሪዎቻችንን ለምን ብሎ መጠየቅ እምብዛም አለመደብንም፡፡ እነሆ ያንን ያልተገራ የአነጋገር ዘዬ እስካሁን የሙጥኝ በማለት ይዘነው የቀጠልነው ለዚያ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እ.ኤ.አ. በ1966 በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ አማካይነት መክሮ ያፀደቀው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ሰነድ፣ የተለያየ ማንነት ያላቸውና በአንድ አገር ውስጥ የታቀፉ ቡድኖች እዚያው ሳሉ ስለሚኖሯቸው ልዩ መብቶች አንድ ራሱን የቻለ አንቀጽ አስገብቶ እናገኘዋለን፡፡ የዚህ ቃል ኪዳን ሰነድ አንቀጽ 27 በግልጽ እንደሚደነግገው ከሆነ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት አባል በሆኑ ሉዓላዊ አገሮች ውስጥ የሚኖሩና የተለያየ ማንነት ባላቸው ቡድኖች ሊካተቱ የሚችሉ ግለሰቦች ስለህልውናቸው ተገቢውን ሕጋዊ ዕውቅናና ከለላ ከማግኘት ባለፈ በጎሳ ወይም በደም ጥልቀት፣ በቋንቋም ሆነ በሃይማኖት ወይም በባህል ረገድ ከሚዛመዷቸው ማኅበረሰቦች ጋር በመሆን ባልና ወጎቻቸውን በአደባባይ እንዳይገልጹ ወይም እንዳይለማመዱ፣ በቋንቋቸው እንዳይጠቀሙና የየራሳቸውን የአምልኮ ሥርዓት በይፋ እንዳይፈጽሙ አይከለከሉም፡፡

ይህ ማለት ታዲያ አቶ መለስ በተሳሳተ መንገድ ይሥሉልን እንደነበረው ዓለም አቀፋዊ ድንበር የተበጀላቸውና ራሳቸውን የቻሉ ሕዝቦች ነበሩ ወይም ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ (1) እንደሚደነግገው፣ ባሻቸው ጊዜ አገር አፍርሰው ሊገነጠሉና የየራሳቸውን ትናንሽ መንግሥታት ሊመሠርቱ የሚችሉም አይደሉም፡፡ ቀድሞ ነገር የዓለም አቀፍ ሕግ ሥርዓት የሉዓላዊ መንግሥታትን የግዛት አንድነትና አይከፋፈሌነት እንጂ፣ እንዲህ ያለውን የተባበረና ጠንካራ ምልዓተ ሕዝብ በደካማ መንግሥትነት የመደራጀት ፍላጎት ፈጽሞ አያበረታታም፡፡

ማንኛውም ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው ያለ ጥርጥር ይጋራዋል ተብሎ በሚታመነው በዚህ ጸሐፊ አስተያየት በአንድ አገር ውስጥ የግለሰብ ዜጎች በዘር ሐረግ፣ በትውልድ፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በእምነት ወዘተ… ተለያይተው መገኘታቸው ቡራኬ እንጂ እርግማን አይደለም፡፡ እንዲያውም አገር ማለት ይህ ዓይነቱ ልዩነት ያላግባብ እየተቀነቀነ አንድነት የሚጣጣልበት ወይም የሚንኳሰስበት ሳይሆን፣ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ከቡድናዊ ማንነታቸው ይልቅ በአብሮነታቸው ደምቀው የሚታዩበት አደባባይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ከቁጥራቸው ማነስና ከማንነታቸው መሳሳት የተነሳ በዚህ ትዕይንት ጎልቶ የመውጣት ዕድል የሌላቸው ህዳጣን ወገኖች ቢኖሩ እንኳ፣ ልዩ ጥበቃና ድጋፍ ተደርጎላቸው የጋራ መጫወቻ ሜዳውን እንደተቀላቀሉ ይዘልቃሉ እንጂ፣ በማንነታቸው ምክንያት የመገለል ስሜት እንዲያድርባቸውና ይኸው ሰበብ ሆኖ ከማዕቀፉ ጨርሶ እንዲወጡ የሚፈቀድበትና ቅቡልነት ያለው አሠራር የለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...