Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ማንኛውም ተቋም የፋይናንስ ሪፖርቱን በግልጽ የማሳወቅ ግዴታ አለበት›› አቶ ጋሼ የማነ፣ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር

በኢትዮጵያ ውስጥ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብና አጠቃላይ የኦዲት ሥራ ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ እስካሁን ሲሠራበት የነበረውም አሠራር ዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው እንዳልሆነም ይታወቃል፡፡ የፋይናንስ ሪፖርት ግልጽነትና ተጠያቂነት አገርን እንደሚያድን ይቆጠራል፡፡ የሕዝብ ሀብት ተጠቅሞ የሚሠራ ተቋምም ሆነ ማንኛውም የንግድ ድርጅት የፋይናንስ ሪፖርቱ ግልጽ መሆን እንዳለበት፣ ሪፖርቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው አሠራር መደገፍ እንደሚኖርበት በግልጽ የተደነገገ አዋጅ አለ፡፡ ከአካውንቲንግና ከኦዲት ሥራ ጋር በተገናኘ ግልጽ የሆነ አሠራር እንዲሰፍን፣ ከሙያው ጋር የተገናኘ ሥራ ላይ ያሉ ተቋማትን ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እየሠራ ያለው፣ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ነው፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ጋሼ የማነ ናቸው፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ ሪፖርትና የኦዲት ሥራዎችን በተመለከተ አቶ ጋሼ ለሪፖርተር ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አሁን ያለውን አጠቃላይ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ በዓለም አቀፍ ስተንዳርድ መሠረት ሊሠራበት ካልቻለ አደጋው የከፋ ስለመሆኑም ይጠቁማሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ወስደዋል፡፡ እንግሊዝ ከሚገኘው ኤሲሲኤ በቻርተርድ አካውንታትነት ተመርቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከጀማሪ ኦዲተር አንስቶ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች እስከ ዳይሬክተርነት ሠርተዋል፡፡ በተለይ የኦዲት ሥራዎች ላይም ተሳትፈዋል፡፡ ከዚያም በግል በናሽናል ኦይል ኩባንያና በኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከተቋቋመ ጀምሮ ዋና ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡ ከዳዊት ታዬ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ እንዴት ተቋቋመ?

አቶ ጋሼ፡- ቦርዱ የተቋቋመበት ታሪካዊ ዳራ ሲታይ በ2002 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ የፋይናንስ ቀውስ ሲፈጠር ትልልቅ ኩባንያዎች ወደቁ፡፡ ከነዚህ ጋር ተያይዞ ኦዲተራቸው የነበረውና ቢግ ፋይቭ ከሚባሉት ኦዲተሮች አንደርሰን ኩፐር ነበር፡፡ ይህ ኩባንያ ኦዲት ያከናወን የነበረው ፋይናንሻል ስቴትመንቱ ትክክለኛ መሆኑን ያሳያል እያለ ነበር፡፡ ከዚያ አንፃር ሲታይ ሁሉም ነገር ባዶ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የፋይናንስ ቀውሱ ተነሳ፡፡ በአሜሪካ ብዙ ባንኮች ከሰሩ፡፡ የቡድን ሃያ አገሮች አንድ ቦታ የሚነሳ የፋይናንስ ቀውስ ሌላ ቦታ ይገባል፡፡ በዓለም ላይ ያለው የፋይናንስ ሁኔታ ምን ይመስላል? በተለይ በሚቀርቡ የፋይናንስ ሪፖርቶችና በኦዲት ሪፖርቶች ላይ ተዓማኒነት ጠፋ፡፡ እኛ አገር የደረሰው 2007 ዓ.ም. ላይ ነው፡፡ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ጥናት አደረጉ፡፡ እንዲህ ያለው ጥናት በሁሉም አገር ተደርጓል፡፡ በሁሉም ዘርፎች ላይ ተደረገ፡፡ ዓላማው አካውንቲንግ በአገሮች እንዴት ነው ተግባራዊ የሚደረገው? የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገው ግምገማ የሚያስነደግጥ ነበር፡፡ ጥናቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአካውንቲንግ አሠራር ክፍተት ያለው መሆኑን አሳየ፡፡

ሪፖርተር፡- የጥናቱ ገምጋሚዎች ምዘናቸው እንዴት ነበር?

አቶ ጋሼ፡- ባለሙያዎቹንና ተቋማቱን ወስደው ባንኮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የመሳሰሉት በኦዲት የተደገፈ ነው ያሉትን የሒሳብ ሪፖርታቸውን ዓይተው ነው የሠሩት፡፡ አንድ ፋይናንሻል ሪፖርት ሲዘጋጅ በዚህ ማዕቀፍ ነው የተዘጋጀው ይባላል፡፡ ኦዲተሩም ቼክ የሚያደርገው ይህንን ነው፡፡ ግን ጥናቱ ኩባንያዎች ተዘጋጅተንበታል ያሉት ማዕቀፍና የቀረበው ፋይናንሻል ስቴትመንት በፍፁም አይገናኝም፡፡ መሥፈርቱ በሙሉ አልተጣጣመም፡፡ በምሳሌ ለመግለጽ ኢትዮጵያ ውስጥ አለን የሚሉት የሜዳ አህያ፣ የሜዳ አህያ አይደለም፡፡ አህያውን ቀለም ቀብተውት ነው እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የንግድ ሕጉ ትክክል አይደለም፡፡ የሙያ ማኅበራት የሉም፡፡ የባለሙያ ቁጥር በጣም ያነሰ ነው ተባለ፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከእነ ጋናና ኡጋንዳ ይበልጣል፡፡ የእኛ ብቁ የሆኑ አካውንቶች ቁጥር 200 ነበር፡፡ በእነዚህ አገሮች ግን አንድ ሺሕ ነበሩ፡፡ ኬንያ ሦስት ሺሕ አካውንታቶች ነበሩ፡፡  የፋይናንስ ሪፖርት ሥርዓትን የሚቆጣጠር ተቆጣጣሪ አካል የለንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በትምህርት ቤት የምንማረው የአካውንቲንግ ትምህርትና በተግባር ላይ ያለው ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ሲታይ ይህ ጉዳይ የተበላሸ ነው ተባለ፡፡ መንግሥት አስተያየት እንደተሰጠ ወዲያው አጣሪ ኮሚቴ አቋቋመ፡፡ ለፋይናንሻል ሪፖርት ግን የሚያስገድድ ሕግ የለም፡፡ ስለዚህ ለፋይናንሻል ሪፖርቲንግ ሕግ መቀረፅ አለበት ተብሎ ሐሳብ ቀረበ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፋይናንስ ሪፖርቶች ምን መምሰል አለባቸው? የሚለውም ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቅርብ ይህንን ጉዳይ ሲከታተሉት ነበር፡፡ ከብዙ ድካም በኋላ የቦርዱ ረቂቅ በ2004 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀረበ፡፡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታመሙና አረፉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሳይፀድቅ ቆይቶ በ2007 ዓ.ም. ፀደቀ፡፡ ይህም ከውጭ በመጣ ግፊት ነው የፀደቀው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ቦርድ በዋናነት መሥራት አለበት  ተብሎ የተሰጠው ሥልጣንና የተቋቋመበት ዓላማ በጥቅል ምን ዓይነት አሠራር ለመፍጠር ነው?

አቶ ጋሼ፡- ማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ የሚሠራ ተቋም፣ የመንግሥት ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሙሉ ፋይናንስ ሪፖርት የሚዘጋጅበትን የሪፖርቲንግ ማዕቀፍ የሚያመላክት፣ የፋይናንስ ሪፖርቶች ኦዲት መደረግ እንዳለባቸውና ኦዲቱ በምን ደረጃ መሠራት እንዳለበት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሙያ ማኅበራት የሚመሠረቱበትና የመሳሰሉትን የሚያከናውን ነው፡፡ በአዋጁ ቦርድ እንደሚመሠረት ይገልጻል፡፡ ቦርዱ በ2007 ዓ.ም. ተቋቋመ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተዘመገበ ያለውን ዕድገት ለማስቀጠል፣ ማንኛውንም ውሳኔ አስተማማኝ በሆነ መረጃ ላይ መመሥረት አለበት፡፡ ለዚህም አስተማማኝና በቀላሉ ሊረዱት የሚችል የፋይናንስ ሪፖርት እንዲዘጋጅ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ከተማ ውስጥ ስትዞር የምታየው ሕንፃ አለ፡፡ ይህ ሕንፃ የእገሌ ነው ይባላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ በባንክ ብድር የተሠራ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የእኔ፣ የአንተና የሌላው ነው፡፡ ሌላውንም ቢዝነስ ስታይ እንደዚያው ነው፡፡ ፋይናንሻል ስቴትመንቱን ስታይ ግን በሙሉ በባንክ የተያዘ መሆኑን ትረዳለህ፡፡ ትምህርት ቤትን ውሰድ ንብረትነቱ የባለሀብቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን የማኅበረሰቡ ነው፡፡ አንተ ልጆችህን ለማስተማር ከፈለግክ ትምህርት ቤቱ   

በፋይናንስ የተረጋጋና አስጀምሮ የሚያስጨርስ መሆኑን ማወቅ ይኖርብሃል፡፡ ይህ ድርጅት እኮ የግል ድርጅት ነው፡፡ መዝናኛና ፋብሪካ የግል ድርጅት ነው፡፡ አዎ የግል ድርጅት ነው፡፡ ግን የድርጅት ጤናማነትና ቀጣይነት ላይ ባለቤት ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡ ኃላፊነት አለበት፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ሪፖርት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንንም  ለቦርዱ ሪፖርት ማድረግ አለበት፡፡ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ቦርዱ ለማንም ፍላጎት ላለው አካል እንዲደርስ ጭምር የመስጠት ሥልጣን አለው፡፡ እኔ የግል ሴክተር ናሽናል ኦይል ስሠራ ኩባንያችን በዚህ ዘርፍ ምን ያህል ተወዳዳሪ ነው? ቼክ ለማድረግ በተመሳሳይ ቢዝነስ ላይ ያሉን የፋይናንስ ስቴትመንት ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ የእኛ አገር ነጋዴ ካፒታሉን ሚስጥር አድርጎ ነው የሚያስበው፡፡ የተመዘገበ ካፒታሉን እንኳን አይነግርህም፡፡ ግን እኮ ይመለከተኛል፡፡ የፋይናንስ ግልጽነት ያስፈልጋል፡፡ ይህ አዋጅ የሚያመጣው በፋይናንስ ግልጽነት ነው፡፡ እንዲውም እኔ እንደ ባለሙያ ስናገር ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ መንግሥት ለዚህ አዋጅ ራሱን የሰጠበት ነው፡፡ ትክክለኛና ዘመናዊ ኅብረተሰብ ከፈለግን አንድ ተቋም በአግባቡ እየሠራ ነው አይደለም? መንግሥት በአግባቡ ሠርቷል አልሠራም? የሚለውን ማወቅ ከተፈለገ መረጃ ያለው ማኅበረሰብ ሊኖር ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ ዘመናዊ የፋይናንስ አሠራር ይከተላሉ የሚባሉ እንደ ባንክና ኢንሹራንስ ያሉ ተቋማት ሳይቀሩ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን ለማወቅ ጥያቄ ሲቀርብ አይገኝም፡፡ ብዙ ኩባንያዎች መረጃ ሊሰጡ አይፈልጉም፡፡ ግን ደግሞ ይህ አዋጅ ይሰጥ ይላል፡፡

አቶ ጋሼ፡- መብትህ የሆነውን ነገር ነው የሚከለክሉህ ማለት ነው፡፡ ለማንም ፈላጊና ምርምር ለሚያደርግ ሁሉ ሊሰጥ ይገባል፡፡ እኔ ኦዲተር ስለነበርኩ የአንድ ኩባንያ መረጃ ከአገር ውስጥ ገቢ የፋይናንሻል ስቴትመንት አገኘሁና ትንተና ለመሥራት ተነሳሁ፡፡ ምጣኔውን፣ አትራፊነቱን የመክፈል አቅሙ ምን ያህል ነው? የሚለውና የመሳሰለውን ሳይ ያስደነግጣል፡፡ ምንም ነገር የለውም፡፡ እኔ የማስታውሰው በዚያን ወቅት ድርጅቱ አንድ ወር ገንዘብ ቢዘገይ የሠራተኛ ደመወዝ መክፈል አይችልም፡፡ አብዛኛው የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች እንዲህ ናቸው፡፡ ግን አትራፊ ናቸው ይባላል፡፡ ያን ድርጅት እንኳን ብድር ልትሰጠው አይደለም እስካሁን የሰጠሁህን ብድር አምጣ ነው ልትለው የሚገባው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ጋሼ፡- ምክንያቱም በጣም የገንዘብ እጥረት አለባት፡፡ ግን ባንክ ብድር ሰጠው፡፡ ባንክ ብድር እንዴት እንደሚሰጥ እናውቃለን፡፡ ባንክ እንዴት የውጭ ምንዛሪ እንደሚሰጥ እናውቃለን፡፡ ሰው ካወቅክና የተወሰነ ነገር ለቀቅ ካደረግህ ይሰጥሃል፡፡ የባንክ ቢዝነስ ሞዴል የሚታወቅ ነው፡፡ ባንክ ሌላ ገንዘብ የለውም፡፡ እኛ ዲፖዚት የምናደርገውን ወስዶ ለሌላ ያበድራል፡፡ በልዩነቱ ላይ ወለድ ያስከፍላል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውን ሒደት ስታይ እኔ ደመወዝ አለኝ እንዲህ አገኛለሁ ብለህ ዝም ብለህ የምትቀመጥበት አይደለም፡፡ ቀውስ ከመጣ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ግሪክን አይተሃል፡፡ ተያይዘህ ነው ገደል የምትገባው፡፡ አንዱ እየበላ ሌላው ሳይበላ መኖር አይችልም፡፡ አሁን በየዜናው ይህንን ያህል ሚሊዮን ብር ተያዘ ይባላል፡፡ የፋይናንስ ኢንተለጀንስ አዋጅ ግን አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተ ችግርና ቀውስ ስለአካውንቱ ወይ ተስማምቶ ወይ ተበልጦ ዝም ብሎ ካልሆነ በቀር ሊያውቀው ይገባ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት ሊያውቅ ይገባል? እሱ የሚሠራበት ኩባንያ ገንዘብ ስላንቀሳቀሰ በአካውንታንትነቱ ማወቅ አለበት ማለት ነው?

አቶ ጋሼ፡- አዎ፡፡ ይህንን ያህል ሚሊዮን ብር ከባንክ ሲወጣ ሰነድ መኖር አለበት፡፡  ዕቃው ሲሸጥ ወይም አገልግሎት ሲሰጥ ገንዘቡ ባንክ መግባት ሲገባው አልገባም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የሚታየው ቀውስ ምንጭ ይኼ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ማጣት አንዱ መገለጫም ይኼ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚገለጸው በሀብት ላይ ነው፡፡ ስለዚህ በጥቅል ስታየው አስተማማኝ መረጃ የለም፡፡ ይህ ደረጃ ማስጠበቅ ኦዲት ማስደረግ ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፋይናንስ ጤናማነትን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ አሁን ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን እየተቆጣጠረ ነው ይባላል፡፡ ግን ቁጥጥር እያደረገ ነው ማለት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- የሚባለው ግን ቁጥጥር እያደረገ ነው?

አቶ ጋሼ፡- ከተለያየ አቅጣጫ እንደሚሰማው እናንተም እንደምትጽፉት ቁጥጥር እያደረገ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በ2009 ዓ.ም. የተጻፈውን ሪፖርት ስንመለከት የትኛውም ቦርድ ውስጥ አደጋን የመቆጣጠር ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ቦርዱ ስለአደጋው አያውቅም፡፡ ባንክ ውስጥ ይህን አደጋ ካላወቅክ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ምክንያቱም ፋይናንሻል መረጃ የለም፡፡ ጋፕ ነው ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋፕ (የአሜሪካ ስታንዳርድ) ነው፡፡ ጋፕ ምንድነው ብትል ማንም አይነግርህም፡፡ በሥነ ሥርዓት አናውቀውም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አያውቁትም፡፡ ማኅበረሰቡ እነዚህን ድርጅቶች የሚጠይቅበት፣ የተሰጣቸውን ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ የሚያውሉበት፣ ሲናገሩዋቸው ደስ የሚሉት ተጠያቂነትና ግልጽነት ሲተገብሯቸው ግን ይጎተታሉ፡፡ እኛ አገር ስለተጠያቂነትና ግልጽነት ይወራል፣ ግን ይተግበር ሲባል ወገቤን ይባላል፡፡ የሙስና አዋጅ ከወጣ በኋላ ሀብት ማስመዝገብና ግልጽ ማድረግ ለ30 ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ ተወራለት እንጂ አልተተገበረም፡፡ ምክንያቱ ይኼ ነው፡፡ መረጃ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ዋና አስፈጻሚው ራሱ መንግሥት ሆኖ እንዲህ ከሆነ ችግር አለ፡፡ ሙያው አላደገም፡፡ የሙያ ማኅበራት የሉንም፡፡ እነ ጌታቸው ካሳዬ (ቻርተርድ አካውንታትነት) ሰርቲፋይድ የሆኑት ኬንያ ነፃ ከመውጣቷ በፊት ነው፡፡ አሁን ኬንያ ከ60 ሺሕ በላይ ባለሙያ አላት፡፡ እኛ ግን እስካሁን የሙያ ማኅበር የለንም፡፡ ዝም ብሎ ክለብ ናቸው፡፡ ባለሙያው ላይ ቁጥጥር አያደርጉም፡፡ ትምህርት እንኳን የምንማረው እንግሊዝ ነው፡፡ ሌላ አደጋ ደግሞ አለ፡፡ የቻይናን ብድር ውሰድ፡፡ አሁን አራጣ ሲባል ብድር የሚመስለኝ ከባንክ የበለጠ ወለድ አስቦ የሚያበድር ነው፡፡ ከባንክ አሥር በመቶ የምትበደረውን ብድር እሱ በ15 በመቶ ወለድ ብድር የሚሰጥ ይመስለኝ ነበር፣ ግን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍ ያለ ወለድ ከመጠየቅ የበለጠ ዓላማ አለው?

አቶ ጋሼ፡- አዎ፡፡ ከፍ ካለ ወለድ መጠየቅ በላይ ዓላማ ያለው ነው፡፡ ይህንን ነገር በደንብ የተረዳሁት ዳና የሚሉት ድራማ ሳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እዚያ ላይ ምን አለ?

አቶ ጋሼ፡- እነዚህ አራጣ አበዳሪዎች ደላሎች አሉዋቸው፡፡ አራጣ አበዳሪዎች ከፍተኛ ወለድ ሳይሆን ሙሉ ንብረትህን ነው የሚፈልጉት፡፡ አንዳንዶቹ አራጣ የሚበደሩት  ጉምሩክ ዕቃ ለማውጫ አጥተው ነው፡፡ ስለዚህ ያመጣሁት ዕቃ በጣም ተፈላጊ ስለሆነ ዕቃዬን ገበያ ካወጣሁ በኋላ የተበደርኩትን እመልሳለሁ ይላል፡፡ የ15 ቀን ሥራ ሊሆን ይችላል፡፡ አራጣ አበዳሪው ለዚህ ዕቃ ማውጫ የሚሆን ብድር ከሰጠ በኋላ እርግጠኛ የሚሆነው ያንን ዕቃ መሸጥ እንዳይችል ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ዋስትና የሚይዘው ንብረት ነው፡፡ ቀደም ብሎ በደላሎቹ ዕቃህ ይቀየርብሃል፡፡ ዕቃውን እንዳታወጣ ያደርግና ቀኑ ያልፋል፡፡ አንተ ደግሞ ባዶ ቼክ ላይ ፈርመሃል፡፡ ካላመጣህ ንብረቱን ይወስዳል፡፡ ስለዚህ የአራጣ አበዳሪ ጉዳይ ጠቀም ያለ ወለድ ማግኘት አይደለም፡፡ ንብረትህንና አንተነትህን የመውሰድ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ምክንያታዊ ከሆንክ በብድር መነገድ ጥንቁቅ የሆነ ሰው ሥራ ነው፡፡ በተጨማሪ ቫት መክፈል የምትችል ከሆነ ማለት ነው፡፡ መክፈል ካልቻልክ ግን ያለህንም ታጣለህ፡፡ ስለዚህ ብድር ስትወስድ እንደምትከፍለው ማረጋገጥ አለብህ፡፡ ምክንያቱም የአንተ ህልውና በመክፈል ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ችግሩ የከፋ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሰሞኑን ዛምቢያ ውስጥ የተፈጠረውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብድሩ ባለመመሰሉ ኤርፖርታቸውን ወሰዱ፣ ዜስኮ የሚባለውን የኢነርጂ ኩባንያቸውን ወሰዱት፡፡ ቻይና ብድር ስትላቸው ይሰጡሃል፡፡ ቢዝነስህን ማወቅ አለብህ፡፡ ጀምረኸው ያደገ ቢመስልህም ክፍተቶች ይኖሩታል፡፡ ለምሳሌ እኛ ዘንድ ስኳር ኮርፖሬሽንን ውሰድ፡፡ እነዚህን የስኳር ፋብሪካዎች ዕቅድ ስታይ ይማርክሃል፡፡ እንደ ዕቅዱ ገንብተህ ጨርሰህ በተባለው ጊዜ ኤክስፖርት አድርገህ ቢሆን ኖሮ ራሱን በራሱ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ግንባታ የወሰድከውን ብድር ካልከፈልክ ችግር መጣ ማለት ነው፡፡ በዛምቢያ የሆነውን ስታይ ቻይናዎቹ በብድር ሰበብ ሀብቷን በሙሉ ነው የወሰደችው፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህ ዛምቢያ ላይ የታየው ነገር ከእኛ አንፃር ሲታይስ?

አቶ ጋሼ፡- የእኛ የቻይና ብድር 59 በመቶ አካባቢ ደርሶ ነበር መሰለኝ፡፡ አሁን ከዱባይና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተገኘው ዶላር መክፈል ባንችል ኖሮ ችግር ሊገጥመን ይችል ነበር፡፡ አንድ ሁለት ፋብሪካ ሳያልቅ አሥር ዓመት ስላለፈው ዕዳ መክፈል ጀምረናል፡፡ የግልህን አስተያየት ስጥ ካልከኝ አንዳንድ ጊዜ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለግል ዘርፉ ሸጫለሁ ሲል ፈልጎ ይመስልሃል? ግን አይደለም፡፡ ያለብህን ዕዳ መክፈል አለመቻል ነው፡፡ እንዲህ ባለው ተመሳሳይ ምክንያት ግሪክ መርኮቦቿ በጀርመን ተወስደዋል፡፡ አበዳሪ አገሮች ሀብትን ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ አገር ይወድቃል፡፡ አንድ ኩባንያ ብቻ አይደለም የሚጎዳው፡፡ ለዚህ ነው የመንግሥት የፋይናንሻል ኢንፎርሜሽን መታወቅ ያለበ፡፡  የዓለም አቀፍ ሙያተኞች የፋይናንስ ሪፖርት እንዲታወቅ ይደረጋል፡፡ እንዲተገብሩት ይደረጋል፡፡ መንግሥት ግን አይተገብርም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ጋሼ፡- ምክንያቱን አላቅም፡፡ ለዚህ ነገር ኦዲተር ጄኔራሉ ሲበሳጭ አስተውያለሁ፡፡ ለምንድነው መንግሥት ደረጃውን ጠብቆ የማይሠራው? ምክንያቱም መንግሥት የግብር ከፋዩን ገንዘብ የሚጠቀም በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ደረጃዎችን መጠቀም ግዴታ ነው፡፡ 200 ቢሊዮን ብር የሚሆን ገንዘብ እየሰበሰብክ ለምን አታደርግም የሚል ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡ ተጠያቂነትን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡  

አሁን ለምሳሌ መንግሥት ምን ያህል የጡረታ ዕዳ እንዳለበት የሚያውቅ የለም፡፡ ፋይናንሻል ስቴትመንት የለም፡፡ አሁን መተግበር የሚገባው አይኤፍአርኤስ (IFRS)  ሲስተም (ከ150 በላይ አገሮች የሚሠሩበት የፋይናንስ ሪፖርት ሲስተም) ተጠቅመህ የፋይናንስ ሪፖርትህን እንድስታስባ ያስገድዳል፡፡ እንዲህ ታውቆ አሁን እንኳን መክፈል የማትችል ከሆነ አሁን መክፈል ባይኖርብህ ከአሥርና ሃያ ዓመታት በኋላ የምትከፍል ከሆነ፣ ያ ዳታ መታየት አለበት፡፡ ይህ ግልጽነትና ተጠያቂነት ነው፡፡ የሌላን ሰው ሀብት የሚያስተዳደር አካል በአግባቡ ያን ኢንፎሜሽን መስጠት ያስፈልገዋል፡፡ ለሕዝብ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይኼን ፈልገህ የምታደርገው አይደለም፡፡ በእርግጥ የፋይናንስ መረጃ ከዴሞክራቲይዜሸን ጋር የሚሄድ ነው፡፡ በወሬ እንደሰማሁት ድሮ ሀብትና ንብረት የንጉሡ ነው ይባል ነበር፡፡ የፋይናንስ ሪፖርት የሚሠራ ባለሙያ ያስፈልጋል ሲባል፣ ምን ይሠራል ለእኔ አይደል እንዴ የሚመዘግበው ይባል ነበር፡፡ ስለዚህ የእኛም ስም ሒሳብ መዝጋቢ ሆኖ ቀረ፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ጤናማነት ለማስቀጠል ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ ያለው ኢኮኖሚ ማመንጨት የሚያስችለውን ታክስ መሰብሰብ እንዲቻል አስተማማኝ መረጃ ከቀረበ፣ አንተም መክፈል የሚገባህን የታክስ መጠን ታውቃለህ፡፡ ሰብሳቢው አካልም ያውቃል፡፡ ዝም ብሎ የሚጭንብህ የለም፡፡ ለሁሉም አንድ ዓይነት ከሆነ አሠራሩ ተቀርፆ በዚያ ደረጃ መሠራት አለበት፡፡ ይህንን ካደረግክ መክፈል የሚገባው ሰው ይከፍላል፡፡ መክፈል የማይገባውም አይከፍልም፡፡ በእኛ አገር ግን መክፈል የሚገባው ሁሉ ታክስ እየከፈለ ነው ወይ? አይደለም፡፡ ካልከፈለ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ  አንዱ መልካም አስተዳደርን ይነካል፡፡ የፋይናንስ ሪፖርት ከመልካም አስተዳደር ጋር ይሄዳል የሚባለው መክፈል ያለበት ስለሚከፍል፣ የታክስ ሥርዓቱ በአግባቡ ስለሚተገበርና ተገቢ የሆነ የሀብት ክፍፍልን ስለሚያመጣ ነው፡፡ ይህ ስለሌለ ነው ችግር ያለው፡፡ እኛ አገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ተናግረውታል፡፡ ታክስ በየትኛውም አገር 90 በመቶ ወይም 80 በመቶ የሚከፍለው 20 በመቶ የሚሆነው ነጋዴ ነው፡፡ የተቀረው ላይ 80 በመቶ ጥረት ብታደርግ የምታገኘው ትንሽ ነው፡፡ ስለዚህ ዒላማ ማድረግ ያለብህ ዋና ታክስ ከፋዮች ላይ ነው፡፡ ግን ታክስን ሊሰውሩ የሚችሉት ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ከፍተኛ ግብር ከፋይ  አልከፈለም ማለት፣ ግብር ለመሰብሰብ ያስቀመጥከውን ግብ ያዛባል፡፡ ይህንን ለመሙላት ዘመቻ ውስጥ ትገባለህ፡፡ በእኛ አገር ዘመቻ ውስጥ ሲገባ ጎረቤትህ ያላቸውን እንጀራ ጋጋሪ 40 ሺሕ ብር ክፈይ ማለት ነው፡፡ ይህ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንድ በኩል በየትኛውም አገር የኢኮኖሚው ሞተር የሚባለው አነስተኛና መካከለኛው ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት አነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ ያለውን ቢዝነስ ለማበረታታት ስትራቴጂ ቀርፆ ያበረታታል፡፡ ይህንን የሚያደርገው እነዚህን አነስተኛና መካከለኛ ቢዝነሶች ከፍ አድርጎ የተሻለ ግብር ለማግኘት ነው፡፡ ለዚህ ነው የሚያመቻቸው፡፡ ካልሆነ ታክስ እፎይታና የመሳሰሉትን እንደ አደጋ ታሳድጋለህ፡፡ ነገር ግን እዚህ አካባቢ በትክክል ስለማይሠራ፣ እነዚህ ማደግ ያለባቸውን አካላት በግምት ግብር እየተመንክ መልሰህ ከገበያ ታወጣቸዋለህ፡፡ በዚህ ምክንያት ፈቃድ የሚመልሱ ብዙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረቡና የኦዲት ሥራ እንዲህ ባለ ችግር ውስጥ ካለ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እናንተስ ምን አደረጋችሁ?

አቶ ጋሼ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የምንሠራቸው ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ ደረጃዎችን ማስተግበር፣ ባለሙያውን መቆጣጠር፣ የትምህርት ሥርዓቱ እንዲቃኝ ማድረግና የመሳሰሉትን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ አንፃር ምን አደረጋችሁ?

አቶ ጋሼ፡- ይህን ለማስተግበር መጀመርያ ስትራቴጂ ቀርፀናል፡፡ ከየት ተነስተን ወዴት ነው የምንሄደው ለሚለው አዋጁ የጊዜ ገደብ አስቀምጧል፡፡ በአዋጁ የተቀመጠው እጅግ ቢዘገይ አዋጁ ከወጣበት ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃዎች በአምስት ዓመት ውስጥ ይተገበራል፡፡ ይህ ማለት በ2012 ዓ.ም. ማለት ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የሚዘጋጅ የፋይናንሻል ኢንፎርሜሽን አስተማማኝ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ፋይናንሻል ኢንፎርሜሽን መተግበር ግን በጣም ውስብስብ ነው፡፡ የማይነካው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ፍኖተ ካርታ ነው የተዘጋጀው፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅታለች፡፡ እንዴት እንተግብረው? የሚለውን ለማምጣት ዓለም አቀፍ ተሞክሮውን አይተን የአይኤፍአርኤስ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ፡፡ ሪፖርት አቅራቢ አካላት ከታወቁ በኋላ በሦስት ከፈልናቸው፡፡ ምክንያቱም የባለሙያዎች ቁጥጥር አነስተኛ ስለሆነ ነው፡፡  ስለዚህ ፍኖተ ካርታው ተዘጋጅቶ ምዝገባ ተጀምሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ነጋዴው ወጥቶ ሪፖርት ያደርጋል? እየመዘገባችሁና አዋጁን እያስተገበራችሁ ነው?

አቶ ጋሼ፡- ይኼ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ሌሎች አገሮች አይኤፍአርኤስን የሚያስተዋውቁት የግሉ ሴክተሮች ናቸው፡፡ እውነት ለመነጋገር ባለፉት ሦስት ዓመታት ሕዝብና መንግሥት የጨለማና የብርሃን ያህል የተራራቁበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የታክስ አዋጅ ስላወጣህ አይከፈልም፡፡ ታክስ ለመክፈል አስቸጋሪ ነገር፡፡ ታክስ መንግሥትና ሕዝብ መተማመን ላይ አመኔታ ሲኖረው የሚጨምር ነገር ነው፡፡ ነጋዴው ለምን አይመጣም የሚለው ብዙ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፡፡ መንግሥት ይህ ሊተገበር ይገባል ተብሎ ተነስቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ነጋዴውን ቦርድ ውስጥ ያስገባነው፡፡ ይኼ ነገር ለራሱ እንደሚጠቅመው ማወቅ አለበት፡፡ በእኛ በኩል መንግሥት እጅግ ቢዘገይ የዓለም አቀፍ ደረጃዎች በአምስት ዓመት ውስጥ ይተገብራል፡፡ ይህ ማለት በ2012 ዓ.ም. ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት በ2012 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘጋጅ የፋይናንሻል ኢንፎርሜሽን አስተማማኝ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ፋይናንሻል ኢንፎሜሽን መተግበር ግን በጣም ውስብስብ ነው፡፡ የማይነካው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀው ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ገብታበታለች፡፡ እንዴት እንተግብረው የሚለውን ለማምጣት የዓለም አቀፍ ተሞክሮውን እየታየ እየሠራን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የሚጀምሩት ተቋማት የትኞቹ ናቸው?

አቶ ጋሼ፡- የፋይናንስ ተቋማትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከፋይናንስ ተቋማት ባንኮችና ኢንሹራንሶች ናቸው፡፡ ሁለተኛ ቡድን ውስጥ ያሉትና የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው የተባሉት ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ነው፡፡ ከፍተኛ የግብር ከፋዮች የተባሉት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በዓመት የሚያገላብጡ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ላይ የሚመዘገቡና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ያሉት አነስተኛና መካከለኛ ቢዝነሶች ናቸው፡፡ ዓመታዊ ገቢያቸው ከአንድ እስከ 50 ሚሊዮን ብር ያለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በመጀመርያው ቡድን ውስጥ ያለውን በሚፈለገው መንገድ ለማስኬድ ምን ተሠርቷል? አሁን ያለበት ደረጃስ?

አቶ ጋሼ፡- ደረጃውን ለማግኘት የሁለት ዓመት የጊዜ ዝግጅት ስለሚጠይቅ፣ በ2008 ዓ.ም. የመጀመርያው ቡድን የአይኤፍአርኤስ ደረጃ በ2010 ዓ.ም.፣ ሁለተኛው ቡድን በ2011 ዓ.ም. እና ሦስተኛው ደግሞ በ2010 ዓ.ም. ያዘጋጃል፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው ቡድን ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሚለቀው የሒሳብ ዓመት ማዘጋጀት ነበረበት፡፡ እዚህ ላይ ደረጃዎቹን የማስተዋወቅ የድጋፍ ሥልጠና ሰጥተን ነበር፡፡ ስለዚህ ውጤታማ ነው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የፋይናንስ ተቋማትና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በአይኤፍአርኤስ መሠረት የሒሳብ ሪፖርታቸው ተዘጋጅቷል ማለት ነው?

አቶ ጋሼ፡- አዎ፡፡ ይህንን ባንኮች ሠርተዋል፡፡ ኢንሹራንሶችና ባንኮች ውጤታማ ናቸው፡፡ ምሥጋና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ለነበሩት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም አቶ በየነ ገብረ መስቀል ይህ እንዲተገበር አድርገዋል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ ሒሳብ ዘግተው ሪፖርት ማቅረብ የማይችሉ ናቸው፡፡ ሒሳብ አለመዝጋት እንደ መብት የሚቆጠርበት ነበር፡፡ ይህ ተስተካክሎ 90 በመቶ የሚሆኑት ከስኳር ኮርፖሬሽንና ከመብራት ኃይል ሀብትና ንብረታቸው ምን ያህል እንደሆነ እንኳን የማያውቁ አሉ፡፡ ከእነሱ በስተቀር (አሁን አንድ ቦርድ ናቸው) አሁን ሒሳባቸውን ኦዲት እያስደረጉ ናቸው፡፡ ሰኔ 2010 ዓ.ም. ለሚያልቀው የሒሳብ ዓመት የሚያቀርቡ ሪፖርት ጥሩ ዕድገት አለው፡፡ የእኛ አገር ከሌሎች የሚለየው የጉምሩክ አዋጆችና የፋይናንሻል ስቴትመንት በአይኤፍአርኤስ እንዲዘጋጅ ተቀብላለች፡፡ ከዚህ ውጪ ከተዘጋጀ መቀበል የለባትም፡፡ ግን እዚያ ላይ የራሳቸውን ሥራ ሠርተዋል ወይ ብትል ችግር አለ፡፡ አሠራሩን መተግበር ካለብህ አይተህ የምትፈልገው አይደለም፡፡ ቴክኒካዊ ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ እዚህ ላይ መሠራት ቢኖርበትም ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ እንደ ትልቅ ክፍተት መታየት እንዳለበት የሚታመነው የሒሳብ መዝገብ ይዘው የሚሠሩ ነጋዴዎች እጅግ ጥቂት መሆናቸው ነው፡፡ አሁን ደግሞ በአዲሱ አሠራር መሠረት ያልተሠራ ሒሳብ ተቀባይነት የለውም ከተባለ የእናንተ ተቋምና የጉምሩክ አሠራር እንዴት ሊሆን ነው?

አቶ ጋሼ፡- ለዚህ መሥራት ነው፡፡ ጥራት ያለው ፋይናንሻል ኢንፎሜሽን ማምጣትና አቅም ግንባታውንም አብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አቅም መገንባት የግድ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተዋል፡፡ በትክክል ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡት ትራንዛክሽን ማሳለፍ ይችላሉ እንዴ? ያስቸግራል፡፡ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያሉ የአካውንቲንግ ተማሪዎች በአይኤፍአርኤስ እንዲሠለጥኑ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ አዘጋጅተን ኢንቨስተሮችን ኑ እንላለን፡፡ እዚህ ሲመጡ ሥራቸው ውስብስብ ነው፡፡ ስለሚሠሩት ሥራ ዕውቀቱ ሊኖረን ይገባል፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ አገሮች ኩባንያዎች ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ይከፍታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኩባንያ ሲቋቋም ታክስ የምትከፍለው 30 በመቶ ነው፡፡ ኢራን ውስጥ አሥር በመቶ ነው፡፡ ስለዚህ ታክስ መክፈል የምትፈልገው አነስ ያለው ቦታ ነው፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ የሚከናወኑ የተለያዩ ሥራዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን የሚያዩ ባለሙያዎች አሉ ወይ? ኢንቨስትመንት ከመጣ ማስከፈል አለበት፡፡ አለበለዚያ ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል ማለት ነው፡፡ ቻይናዎች ባለሁለት አኃዝ በሚያድጉበት ጊዜ ጥናት ሠሩ፡፡ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት እየመጣ ነው፡፡ ነገር ግን አገር ውስጥ ነው የሚሠራው፡፡ በወቅቱ ኢኮኖሚው ይፈልግ የነበረው 235 ሺሕ ብቃት ያላቸው አካውንታቶች ነው፡፡ የነበረው ግን 130 ሺሕ፡፡ ስለዚህ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ይህንን ክፍተት ካልዘጋነው የኢኮኖሚ ዕድገቱ ይቆማል የሚል ድምዳሜ የያዘ ጥናት አወጡ፡፡ ስለዚህ ስትራቴጂ ነድፈው ትልቅ ኢንስቲትዩት አቋቁመው ባለሙያቸውን ውጭ ልከው አስተማሩ፡፡ የአይኤፍአርኤስ ስታንዳርዶች ሲወጡ አስተያየት የሚሰጡና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሆነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ኢኮኖሚው የሚመጥን ባለሙያ እንዲፈጠር ምን መደረግ አለበት? አሁን እናንተ የሠራችሁትስ ምንድነው?

አቶ ጋሼ፡- ይህንን በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል አሠራር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ፕሮፌሽናል መስፈርት የወጣው፡፡ ቦርዱን ጠንካራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ጉምሩክ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ደመወዝ ከፍ ይደረግ ተባለና ተተገበረ፡፡ ያደረግነው ግን የመደራደር አቅም ከፍ ማድረግ ነው፡፡ እዚህ ያለው ሊሆን አይችልም፡፡ ግን መፍትሔው ከመጀመርያውኑ የሚቀርበው ኢንፎርሜሽን አስተማማኝ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ አስተማማኝ መረጃ እንዲቀርብ ማድረግ ነው፡፡ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች የታክስ ጂዲፒ ከሁሉም አገሮች ያነሰ ነው ይባላል፡፡ ልክ ነው ደረጃ የለም፡፡ የምትከታተልበትን አሠራር ካልፈጠርክ እንዴት ሊመጣ ይችላል? ባለሙያ የለም፡፡ ይህ ነው መስተካከል ያለበት፡፡ አሁን በሚሠራበት ነጋዴው የሒሳብ ሪፖርት ይዞ ሲቀርብ ሌባ ነው ትላለህ፡፡ ምክንያቱም አስተማማኝ ነገር የለም፡፡ እዚያ የተቀመጠውም ምን እንደሚፈልግ አታውቀውም፡፡ ለኦዲትና ለሒሳብ ደረጃ ግልጽ ነገር ቢቀመጥ ችግር አይኖርም፡፡ ስለዚህ በሒሳብ ሪፖርት ላይ መተማመን የሚኖረው ትክክለኛ የሆነ የፋይናንስ ሪፖርት ሲኖር ነው፡፡ አሁን እኛ ትግል ነው የያዝነው፡፡ የሰለቻቸው ጥለውን ሄደዋል፡፡ እንደ ዜጋና እንደ ባለሙያ የምለው አገርን ለማሳደግ እዚህ ላይ መሥራት ነው፡፡ ፋይናንስ ላይ በአግባቡ ካልሠራንና ሀብት አመዳደብ ላይ በትክክል ካልሠራህ ለጥፋት ትዳረጋለህ፡፡ ስለህዳሴ ግድብ ምንም ሪከርድ የለም ነው የተባለው፡፡ በሕዝብ መዋጮ እየሠራህ የተሰበሰበውን ገንዘብ ለዚህ ነው የዋለው የሚል መረጃ የለም ማለት  ነው፡፡ የሰጠኸኝን ገንዘብ በዚህ በዚህ አውለዋሁ፣ ስትጨምርልኝ ደግሞ እንዲህ አሳካዋለሁ ማለት አለብህ፡፡ አምጣ ብቻ አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- ግን እዚህ ላይ የህዳሴ ግድብ የሒሳብ ሪፖርት እርስዎ መሥሪያ ቤት መቅረብ ነበረበት?

አቶ ጋሼ፡- ማንኛውም ሪፖርት አቅራቢ አካል ሒሳቡን ኦዲት ማስደረግ አለበት፡፡ ቦርዱ ሥልጣን አለው ስልህ የራሱ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ያቋቁማል፡፡ ለምሳሌ አንድ  የተሳሳተ የሒሳብ ሪፖርት ቢቀርብ ባለቤትና የፋይናንስ ኃላፊው ይጠየቃሉ፡፡ የኦዲተሩን ነፃነት ማስጠበቅ አንዱ ኃላፊነታችን ነው፡፡ ለምሳሌ ነጋዴዎች የሒሳብ ባለሙያ ማኅተም ነው የሚመቱት፡፡ አንድ ሺሕ ደንበኛ ያላቸው ባለሙያዎች አሉ፡፡ መርካቶ ውስጥ ትርፍ ስንት እንዲሆንልህ ነው የምትፈልገው ብለው የሚጠይቁ አሉ፡፡ እነዚህን ባለሙያዎች ጭምር ነው የምትቆጣጠረው፡፡ እንዲህ ያለውን የሒሳብ  ባለሙያ ማንም የሚጠይቀው የለም፣ አሁን ግን ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው እያንዳንዱ ባለሙያ ፕሮፌሽናል ኢንሹራንስ መግባት ያለበት፡፡ ምክንያቱም ከነጋዴው መጠበቅ አለበት፡፡ ይህ ቦርድ የተቋቋመው የሕዝብ ጥቅምን ለማስጠበቅ ነው፡፡ የሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቀው አቅም ያለው ባለሙያ ሥራውን በአግባቡ ያለ ተፅዕኖ መሥራት መቻል አለበት፡፡ ይህንን ሊያስፈጽሙ የሚችሉ ሥራዎችን ሁሉ ቦርዱ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ሙያ ውስጥ ያሉ ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ አለባቸው? ከእናንተስ ጋር እንዴት ይሠራሉ?

አቶ ጋሼ፡- የሙያ መሠረት ወይም የሙያው ህልውና የተመሠረተው የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው፡፡ በኃላፊነት የምንሠራው ሥራ ቀጣሪና ተቀጣሪ መሆን ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ የምንሰጠው ምስክርነት በማኅበረሰቡ ላይ ምን ያመጣል ለሚለው ግዴታ አለብን፡፡ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለደንበኞች የምንሰጠው የራስን አቅም ከዘመናዊ አሠራሮች ጋር በማዳበር ነው፡፡ ኃላፊነቱን ጠብቆ በሥነ ምግባር መሥራት ነው፡፡ ቦርዱን የባለሙያዎቹን አቅም ለመገንባት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ አንዱ አገር አቀፍ የሙያ ማኅበር እንዲመሠረትና ባለሙያውን እንዲቆጣጠር፣ ከዓለም አቀፍ አካውንቲንግ አሶሴሽን ጋር እየተሠራ ያለ ሥራ አለ፡፡ ይህ እስኪተገበር ባለሙያው ባለው የሥነ ምግባር ደንብ መሥራት አለበት፡፡ ይህንን የሥነ ምግባር ደንብ ተከትለው የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ፣ ቁጥራቸው የበዛ ሥነ ምግባርን ያልተከተሉ ገንዘብ ለመልቀም ብቻ የሚሠሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በእነዚህ ባለሙያዎች ላይ ክትትል ጀምረናል፡፡ በርካታ ባለሙያዎች ፈቃዳቸው እየተሰረዘ ነው፡፡ ማስጠንቀቂያም የተሰጣቸው አሉ፡፡ ባለሙያው የሕዝብን ጥቅም ካላስጠበቀ ተጠቃሚው አካል በሙያው ላይ ያለው አመኔታ ይወርዳል፡፡ አሁንም በአገራችን በሚፈለገው ደረጃ አይደለም፡፡ ቦርዱ የተቋቋመው ይህንን አመኔታ ለመጨመር ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ካልሠራን አገርም ይወድቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍተኛ የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው ለምሳሌ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ሪፖርቶችን አምጡ የምትሉበት ዕድል የለም?

አቶ ጋሼ፡- አለን፡፡ የህዳሴ ግድብን ግን አላየንም፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዘንድ እየሄድን ነው በሙሉ ተመዝግበዋል፡፡ ችግሩ ያለው የቦርዱ ቁጥር ትንሽ መሆንና የነጋዴው ቁጥር መጨመሩ ነው፡፡ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ 230 ሺሕ ነጋዴ ወይም ሪፖርት አቅራቢ አካል አለ፡፡ ይህ ሪፖርት አቅራቢ ቦርዱ ዘንድ መመዝገብ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በገቢዎችና ጉምሩክ ሕግ መሠረት ሒሳብ መያዝ ኖሮበት የሚይዝ አለ? ዝም ብሎ ግብር የሚከፍል አለ?

አቶ ጋሼ፡- ይህንን ለመለየት የምንችለው ስናውቀው ነው፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በእያንዳንዱ ግብር የሚከፈልበት ቦታ ላይ ባነሮች አስቀምጠን መመዝገብ ጠቀሜታውን እንነግራለን፡፡ ብዙ ግን ትኩረት አይሰጠውም፡፡ ጥረት አድርገናል፡፡ የፖለቲካው ሁኔታ ብዙ ትኩረት እንዳይስብ አድርጎት ይሆናል እንጂ ጥረት አድርገናል፡፡ እኛ ግን ባለፈው ዓመት ውስጥ ሁሉንም እንመዘግባለን ብለን ተነስተን የተመዘገበው ግን ስድስት ሺሕ አይሞላም፡፡ እዚህ አስመዝግቡ ስለሚሏቸው አሁን ቁጥሩ እየጨመረ ነው፡፡ ከእነሱ ጋር በቅንጅት ስለሠራን ይዘው የሚቀርቡት የሒሳብ ሪፖርት አይቀበሉም፡፡ ምክንያቱም ገቢዎች ሄጄ በምን የፋይናንሻል ስቴትመንት ሠራህ? የውሸት እንዳልቀረበልህ በምን ታውቃለህ? አዋጁ ወጥቷል፡፡ ለአንተ የቀረበው መረጃ ለቦርዱ የቀረበ ኦርጂናል ቅጂ መሆኑን ማረጋገጥ አለብህ ይላል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የሒሳብ ሪፖርት ሲቀርብ ለቦርዱ የሚቀርበውም ሆነ ለገቢዎች የሚቀርበው አንድ ዓይነት መሆን አለበት ማለት ነው?

አቶ ጋሼ፡- በግዴታ!

ሪፖርተር፡- በዚህ መሠረት እየተሠራ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ጋሼ፡- እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ክፍተት የለም?

አቶ ጋሼ፡- ፍላጎት ይኖራል፡፡ ለምሳሌ አሁን አዲሱ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር  ሲመጡ ውጤታማ እየሆነ እየመጣ ነው፡፡ ከዚያ በፊት እኮ ብዙ ደብዳቤዎች ጽፈናል፡፡ ባለሥልጣኑ (ገቢዎችና ጉምሩክ) ዘንድ ስትሄድ ባለሙያዎቹ ለማሠራት ገቢዎች ውስጥ ማንን ታውቃለህ? ነው ይህ ችግር ነው፡፡ ይህንን ማስቀረት የሚቻለው እንዲህ ያለውን አሠራር ስታስቀምጥ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረ አንድ የገቢዎች ዳይሬክተር ይህ አዋጅ ወጥቷል ብለን ስናሳየው፣ ደብዳቤ ይዛችሁ ካልመጣችሁ አላናግራችሁም ነበር ያለን፡፡ ስለዚህ ፍላጎት አለ፡፡ ግልጽነት ሲመጣ ብዙ ነገሮች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ከባንክ የሚበደሩት እነማን ናቸው? እነዚህ የኢንዶውመንት ፈንድ የሚባሉት በባንክ ብድር ነው እኮ የሚሠሩት፡፡ የእነሱ የሒሳብ ሪፖርት ኦዲት ተደርጎ መታወቅ አለበት፡፡ ቁጥጥር መደረግ አለበት፡፡ ሕዝብ ማወቅ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ግን እናንተ በተቋቋማችሁበት አዋጅ መሠረት ከኢንዶውመንት መጥተው የተመዘገቡ አሉ?

አቶ ጋሼ፡- አልመጡም፡፡ ጥረት ግን መጥቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጭቅጭቅ አለ፡፡ አዋጁን ለማስፈጸም በክልል ደረጃ ነው የሚታየው ሁሉ ተብለናል፡፡ አያገባችሁም ተብለናል፡፡ የፋይናንስ ጉዳይ እንደ ከባቢው ነው፡፡ ይኼ የእኔ አየር ስለሆነ እንደፈለግኩ እበክለዋለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አየር ይንቀሳቀሳል፡፡ ፋይናንስ እንደዚያ ነው፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት፡፡ አንድ አካባቢ ያለ ባንክ የተለየ አይሆንም፡፡ በመላ አገሪቱ ውስጥ ነው የሚሠራው፡፡ ፋይናንስን በአገር ደረጃ መገደብ አይችልም፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ይህንን ነገር በሚገባ ተረድተውት ነበር፡፡ ሲሠራበት ነበር፡፡ አሁን መፍረክረክ እየመጣ ነው፡፡ ስለኢኮኖሚ እያወራህ ይህንን አለመፈጸም ተገቢ አይደለም፡፡ ማንኛውም ተቋም የፋይናንስ ሪፖርቱን በግልጽ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ለባንክና ለገቢዎች የተለየ ሪፖርት ማቅረብ አይቻልም፡፡ ለሁሉም ተቋማት የሚቀርበው የፋይናንስ ሪፖርት ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ ይህም መረጋገጥ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ቦርዱ እየሠራ ነው፡፡ ቦርዱ አንድ ወጥ የሆነ የፋይናንስ ሪፖርት እንዲቀርብ፣ ሁሉም በእኩልነት የሚሠራበት አሠራር እንዲዘረጋ እየሠራ ነው፡፡ ሁሉም በዚህ መንገድ ካልሄደ ተጠያቂነት ይኖራል፡፡ አዋጁን ለማስፈጸም እየተሠራ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...

ኢትዮጵያ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት ማበጀት እንደሚገባት ማሳሰቢያ ተሰጠ

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀበት ጊዜ አንስቶ ለተለያዩ ጥያቄዎችና ሐሳቦች...