Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስት ዐውደ ርዕዮች በአንድ የሚስተናገዱት መድረክ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘጠነኛ ጊዜ የሚሰናዳው አዲስ ቢውልድ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና ቴክኖሎጂ ‹‹ዐውደ ርዕይ›› ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ለማካሄድ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡

የኢትኤል አድቨርታይዚንግና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሃይማኖት ተስፋዬ እንደገለጹት፣ ዐውደ ርዕዩ በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ሁነኛ የንግድ ትስስር የሚፈጠርበት መድረክ ነው፡፡ ከ12 አገሮችና ከ91 በላይ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቻይና፣ ከጀርመን፣ ከግሪክ፣ ከጣሊያን፣ ከቱርክ፣ ከዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ከ80 በላይ ኩባንያዎች ይሳተፉበታል፡፡ 20 የግንባታ ግብዓትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤቶችም ለዕይታ ይቀርቡበታል፡፡

በዓለም ላይ ኢንዱስትሪው የደረሰበትን የምጥቀት ደረጃ በተመለከተም ከፍተኛ ተሞክሮ እንደሚቀሰምበት ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀው፣ በዘርፉ በአገር ደረጃ እያጋጠመ ያለውን የጥራት፣ የዋጋ፣ የጊዜ፣ እንዲሁም የደኅንነት ችግሮችን በተመለከተ ዐውደ ርዕዩ ሰፊ የመማማሪያ መድረክ ጭምር እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡  

በመግለጫው ወቅት በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ደርቤ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት የኮንስትራክሽን ዕቃዎች በብዛት ከውጭ እየገቡ በመሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ጉዞ ላይ በተለይም ከግብዓት አቅርቦት አንፃር የሚያጋጥሙ ፈተናዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ የሚያተኩር የውይይት መድረክም የዐውደ ርዕዩ አካል ይሆናል፡፡

ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዐውደ ርዕይ ጎን ለጎን ስድስተኛው የግብርናና የግብርና መሣሪያዎች፣ የምግብ ቴክኖሎጂዎችና የፓኬጂንግ ዐውደ ርዕይ እንደሚካሄድ፣ በዐውደ ርዕዩ ለሚሳተፉ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችም የኢትዮጵያ ምርትና የገበያ ዕድሎች የሚተዋወቁበት የንግድ ትስስርም የሚፈጥሩበት መድረክ መዘጋጀቱን አዘጋጆቹ አስታውቃዋል፡፡ አዲስ አግሮ ፉድስ ኤንድ ፓኬጂንግ፣ የግብርና መሣሪያዎች፣ የምግብ ማቀነባበሪያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ እንዲሁም የረቀቁና በዓለም የታወቁ የቡና፣ የፍራፍሬ፣ የጣፋጭ ምግቦችና የሌሎችም ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎች በዐውደ ርዕዩ ለኢትዮጵያ ገበያ ይተዋወቃሉ፡፡

በዘንድሮው የአግሮ ፉድስና ፓኬጂንግ ዐውደ ርዕይ ከ28 በላይ የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ሲጠበቅ፣ ከህንድ፣ ከቱርክና ከታንዛኒያ የሚመጡ በርካታ ኩባንያዎች ይካፈላሉ፡፡ በተጨማሪ የልምድ ልውውጥ፣ እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻዎች የምክክር መድረክ ያካሂዱበታል፡፡

 ሦስተኛው ዐውደ ርዕይ፣  ለመጀመርያ ጊዜ እንሚካሄድ የተጠቀሰው ‹‹አዲስ ፓወር ዐውደ ርዕይ›› የተሰኘው ሲሆን፣ መንግሥት ዕምቅ የኃይል አቅምን ቀስ በቀስ እያጎለበተ በመምጣቱ፣ በኢትዮጵያ 2.9 ሚሊዮን ደንበኞች የኃይል አቅርቦት ማግኘት እንደቻሉ ያስታወሰው የአዘጋጆቹ መግለጫ፣ የኃይል መሠረተ ልማቱም የኢትዮጵያን 60 በመቶ ቆዳ እንደሸፈነ፣ ሆኖም የተጠቃሚነቱ ሲታይ 25 በመቶ ብቻ በመሆኑ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከኃይል አቅርቦት ውጭ እንደሆኑ የሚያመላክት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ መረጃው ያሳያል፡፡ በመሆኑም ዓለም አቀፍ የኤሌክትሪክ፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ እንዲሁም ላይቲንግ መስኮች ላይ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች የሚሳፉበት ይህ ዐውደ ርዕይ፣ በኢትዮጵያ ኢነርጂ ዘርፍ ውስጥ ባለድርሻ የሆኑ አካላትን በማገናኘት የግብይትና የአቅርቦት መስኩን እንደሚያስተሳስር ይጠበቃል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች