Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፒቪኤች ኩባንያ በኢትዮጵያ ላበረከተው አስተዋጽኦ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተሸለመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሠራተኛ ማኅበራት እንዳይደራጁ በመከልከልና በደመወዝ ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ ‹‹አዋርድስ ፎር ኮርፖሬት ኤክሰለንስ›› በሚል መጠሪያ በተለያየ ዘርፍ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አሜሪካውያን ኩባንያዎች የሚሰጠውን ሽልማት፣ በአፍሪካ ፒቪኤችን ጨምሮ ለሁለት ኩባንያዎች መስጠቱን ይፋ አደረገ፡፡

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትሯ ማኒሻ ሲንግ እንዳስታወቁት ኩባንያዎቹ ላበረከቱት መልካም አስተዋጽኦ ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ዘንድሮ ለሁለት ኩባንያዎች የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሽልማት እንዲያገኙ ተወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፕሮጀክትን ከማማከር ጀምሮ አምራች ኩባንያዎቹን በማምጣት ጨርቃ ጨርቅና አልባሳትን እያስመረተ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው ፒቪኤች ኮርፖሬሽን፣ ላከናወነው ‹ዘላቂ እንቅስቃሴ› በሚል መነሻ ለሽልማት መብቃቱን ምክትል ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያው በምርት ሒደት ወቅት የአካባቢ ብክለት እንዳይከሰት፣ ብሎም ምንም ዓይነት ዝቃጭ ወደ አካባቢ እንዳይለቀቅ የሚያስችል የፍሳሽ ሥርዓት እንዲተገበር ላበረከተው አስተዋጽኦ ሽልማት እንደተሰጠው አብራርተዋል፡፡

ይሁንና ፒቪኤችን ጨምሮ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ 18 ያህል ትልልቅ የውጭ ኩባንያዎች ሠራተኞች በማኅበር እንዳይደራጁ መከልከላቸውንና የሚከፍሉት ደመወዝም እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ቅሬታ ሲቀርብባቸው ቆይቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች የሚነሱበትን ኩባንያ የአሜሪካ መንግሥት መሸለሙ እንዴት ይታያል የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው ምክትል ሚኒስትሯ፣ በምላሻቸው የጠቀሱት ኩባንያው የተሸለመበት ዘርፍ ለዘላቂ ኦፕሬሽን ባበረከተው አስተዋጽኦ እንደሆነ፣ ሆኖም ኩባንያዎች ከሠራተኞቻቸው ጋር በመደራደርና የጋራ ጥቅማቸውን በሚያስጠብቅ ስምምነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ሁሉም ኩባንያዎች ከሠራተኞቻቸው ጋር የሚያስማሙ የጋራ ድርድር ውጤቶች ላይ እንዲደርሱ እናበረታታለን፡፡ መልካም የቅጥር ሁኔታ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሽልማት የሚያገኙ ኩባንያዎቻችንም ችግሮቻቸውን እንዲገመግሙና እንዲፈቱ ድጋፍ እንደግፋቸዋለን፤›› ያሉት ምክትል ሚኒስትሯ፣ ፒቪኤች በታዳሽ ኃይል አጠቃቀምና ለአካባቢ ተስማሚነት ባላቸው የሥራ ትግበራዎች ዘርፍ ተመዝኖ ለሽልማት መብቃቱን ጠቅሰዋል፡፡

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሚኒስትር ረዳት የሆኑት አምባሳደር ማቲው ሐሪንግተን በበኩላቸው የአሜሪካ ሸማቾች በሌሎች አገሮች ውስጥ የሚያመርቱ የአሜሪካ ኩባንያዎች የሥነ ምግባር ሕጎችን ተከትለው እንደሚያመርቱ በማመን ምርቶቻቸውን ይገዛሉ ብለዋል፡፡ ይህንን አሜሪካውያን ሸማቾችን መሠረታዊ ፍላጎት የማያሟሉ ኩባንያዎች የገበያ ችግር እንደሚገጥማቸው ስለሚገነዘቡ፣ በአመራረት ሒደታቸው ወቅት ተገቢውን ሥነ ምግባር የመከተል ግዴታ ይጠብቃቸዋል በማለት ቁጥብ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሆኖም በጥር ወር በአዲስ አበባ በተስተናገደውና የአፍሪካን ዝቅተኛ የደመወዝ መነሻ ለመወሰን በዓለም ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን አማካይነት በተካሄደው ስብሰባ ወቅት የዓለም ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ዋና ጸሐፊ ሻሮን ባሮው፣ በኢትዮጵያ ለሠራተኞች በወር 600 ብር ብቻ የሚከፍሉ አምራች ኩባንያዎች፣ እንዲህ ያለውን ከኑሮ በታች የሆነ የደመወዝ ሥርዓት ሊያሻሽሉ እንደሚገባቸው አስጠንቅቀው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የመደራጀት መብታቸው መገፈፉን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ሠራተኞች መብታቸውን ለማስጠበቅና ጥቅማ ጥቅማቸውን ለማስከበር በማኅበራት ሕገ መንግሥታዊ የመደራጀት መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ ሲገልጹ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ ሠራተኞችን ለማደራጀት ሲሞከር የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች ፈቃደኞች ሆነው ባለመገኘታቸው፣ ሠራተኞች ከፓርኩ ውጭ እንዲደራጁ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱንም ኮንፌደሬሽኑ አስታውቆ ነበር፡፡ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በሌሎችም ፓርኮች ለሠራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ ከሚታሰበውም በታች ዝቅተኛ በመሆኑ፣ በርካታ ሠራተኞች ሌላ ሥራ ፍለጋ ጥለው እንደሚሄዱ በተለይም በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይህ የሠራተኞች ፍልሰት ከፍተኛ እንደነበር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊዎች ሲገልጹ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህም ይባል እንጂ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች ከ18 ሺሕ በላይ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሽልማት ከተበረከተለት ፒቪኤች ኮርፖሬሽን በተጨማሪ፣ በቶጎ የሚንቀሳቀሰውና ለ700 ሴቶች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል የፈጠረውና ለ14 ሺሕ አቅራቢዎችም የገቢ ምንጭ እንዳስገኘ የተነገረለት የመዋቢያና የግል ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች አምራች የሆነው አላፊያም ‹‹ሴቶችን ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማብቃት›› በሚለው ዘርፍ ሽልማት አግኝቷል፡፡

ፒቪኤች ኮርፖሬሽን ባለፈው ዓመት ከዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሽያጭ በማስመዝገብ በአልባሳት ብራንድ ምርቶች የሚታወቁ እንደ ካልቪን ክሌን፣ ቶሚ ሔልፊገር፣ ቫን ሔውስ፣ አይዞድ፣ አሮው፣ ስፒዶ፣ ዋርነርስ፣ ኦልጋና ሌሎችም ብራንዶችን በማቅረብ በ40 አገሮች ውስጥ ምርቶቹ የሚሸጡለት ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች