Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ልማት ባንክ ያላመው ሀብት

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመንግሥት የልማት ፖሊሲ አስፈጻሚነት የሚጠቀስ ባንክ ሆኖ የሚያገልግልና ይኼንኑ ተግባሩን እየተወጣ እንደሚገኝ ይታመናል፡፡

መንግሥት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና ሊያጫውቱለት እንደሚችሉ ላመነባቸው የኢንቨስትመንቶች መስኮች ብድር የማቅረብ ኃላፊነቱን እስከ ቅርብ ጊዜ ድርስ የሰጠው ለዚሁ ባንክ ነበር፡፡ በዚሁ መነሻነትም ዝቅተኛ በሚባል የወለድ ምጣኔ ብድር ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ባንኩ በአብዛኛው ቅድሚያውን በመስጠት ብድር ከሚሰጥባቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውስጥ የግብርና ሥራዎች፣ የማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችና መሰል ዘርፎች ይጠቀሳሉ፡፡

ባንኩ እንዲያስፈጽም ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንፃር ሲፈተሽ፣ ዓላማውን ማሳካት ያልቻለባቸው በርካታ ምክንያቶች ይታያሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሰሞኑ እንደሰማነው የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን 40 በመቶ ገደማ መድረሱ፣ ባንኩ ከሚጠበቅበትና ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ ሚናውን በአግባቡ ተወጥቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህም ይባል እንጂ የተበላሸ ብድር መጠኑ መብዛቱ ግን እንደ ንግድ ባንኮች በሚታይ መለኪያ አያስገምተውም፡፡ የልማት ባንክ ተልዕኮ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ማስቻል በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች ያስቀመጠውን የአምስት በመቶ የተበላሸ ብድር ጣሪያ አልፈሃል ተብሎ ባይወነጀልም 40 በመቶ ሲደርስ ግን ቀይ መስመር ማለፉን ይጠቁማል፡፡

ይሁንና የአንድ ባንክ የተበላሸ ብድር መጠን 40 በመቶ ሲደርስ፣ ከሰጠው ብድር ውስጥ እኩሌታውን የሚጠጋጋ ገንዘብ ወደማይመለስበት ደረጃ ደርሷል፣ ተበዳሪው ዕዳውን ለመወጣት የማይችልበት አጠራጣሪ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ያመለክታል፡፡ የባንኮች የተበላሸ ብድር መጠን ከአምስት በመቶ በላይ በሚሆንበት ወቅት፣ ለዚሁ በተቀመጠ ድንጋጌ መሠረት፣ ለእያንዳንዱ አጠራጣሪ ብድር በመቶኛ እየተሰላ ተመጣጣኝ መጠባበቂያ በብሔራዊ ባንክ ቋት ውስጥ እንዲያስቀምጡ ባንኮቹ ይገደዳሉ፡፡

ስለተበላሸ ብድር የአገሪቱ መመርያ ይኼንን ቢልም፣ ልማት ባንክ ለተበላሸው ብድር ክምችቱ ምን ያህል ገንዘብ ተቀማጭ አድርጎ ይሆን? የሚለው መታየት አለበት፡፡ የልማት ባንክ ያስመዘገበው አጠራጣሪና ተመላሽነቱ የሚያሠጋው የ40 በመቶ የብድር መጠን የአገር ሀብት ለፕሮጀክት ማስተግበሪያነት የተበተነው ይህን ያህል ገንዘብ በምን አግባብ ይመለስ ይሆን የሚል ሐሳብ ቢያዋልለን አይገርምም፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ለባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን ልጓም ባለመበጀቱና በየወቅቱም ማስተካከያ ባለመደረጉ፣ በየዓመቱ መጠኑ እየጨመረ መጥቶ ዛሬ ላይ 40 በመቶ የተበላሸ ብድር ለመታቀፍ በቅቷል፡፡ ባንኩ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ ከአምስት ዓመት በፊት ዘጠኝ በመቶ የነበረው የተበላሸ የብድር መጠን አሥር በመቶ፣ 12 በመቶ፣ 20 በመቶ፣ እያለ በ2009 ዓ.ም. ላይ 25 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ ይህ አካሄድ ጤናማ አለመሆኑ ይታወቅ ነበርና መላ ሊበጅለት ይገባል በሚባልበት ወቅት እየባሰበት ሄዶ በ2010 ዓ.ም. ወደ 40 በመቶ አሻቀበ፡፡

እዚህ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ምን እየተጠበቀ እንደነበር በግልጽ ባይታወቅም፣ ባንኩ የፖሊሲ ባንክ ነው በሚል ሰበብ አዋጭነቱ ለተረጋገጠውም እንዲሁ መሬት በጨበጣ እየያዘ ለብድር ለቀረበው ጥያቄ ሲረጭ የከረመው የሕዝብ ገንዘብ፣ በአግባቡ ጥቅም ላይ ውሎ ተመላሽ የሚደረግበትን አሠራር ደንግጎና ተቆጣጥሮ የሚሠራ ተቆርቋሪ ኃላፊና ባለሙያ አልነበረውም ወይ? የሚለውን ጥያቄ ደጋግመን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡

ባንኩ የሚሰጠው ብድሮች የመመለሳቸው አዝማሚያ ከአጠራጣሪነት በላይ የሚያሠጋ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱ ቢታወቅም፣ አዳዲስ ብድሮችን ከማቅረብ ግን አልገደበውም፡፡ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአገር ሀብት ያላግባብ ጥቂቶች እየተቀራመቱት፣ ኢንቨስተር ተብዬዎቹ የአገር ውስጥም የውጭ ቁማርተኞችም በየጊዜው እየዘገኑ ወደየመጡበት ሽው የሚሉበትን ገንዘብ በገፍ የሚያገኙት ከልማት ባንክ እንደነበር ማሳያው የባንኩን የሐራጅ ማስታወቂዎች የሚከታተል ሁሉ ልብ የሚለው ነው፡፡ የዜና አውታሮች የዘገቧቸውን መለስ ብሎ መመልከቱም ይኼንኑ እውነታ ያረጋግጣል፡፡

ባንኩ ብድር የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች በሰበብ አስባቡ ፍሬ ሳያፈሩ መቅረታቸው ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ትኩረት የተሰጣቸውና በየዓመቱ ብድር ሲለቀቅላቸው የቆዩ ፕሮጀክቶች ውጤት አልባ መሆናቸውም ድርብ ኪሳራ ነበር፡፡

ለዚህም የባንኩ መሪዎች የብቃትና የተጠያቂነት ጉዳይ መፈተሽ አለበት፡፡ የብድር አሰጣጡ ችግር ያለበት በመሆኑ፣ የማይመለሱ ዕዳዎችን የተሸከመው ልማት ባንክ፣ ብድሩ ባይመለስለት ምን ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ሲታይም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በጥንቃቄ እንዳልሠራ ብንገምት ከዕውነታው ያወጣናል ብለን አናስብም፡፡

ለሰፋፊ እርሻዎች የተሰጡ ብድሮች እዚህ ይጠቀሳሉ፡፡ በዘመናዊ መንገድ አርሰውና አምርተው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ይተርፋሉ የተባሉ የእርሻ ፕሮጀክቶች፣ ስንትና ስንት ሕዝብ አፈናቅለው በወሰዱት መሬት ላይ አንድ ኩንታል እህል ሳያመርቱ ለዓመታት አጥረው ያለ ሥራ መቆየታቸው የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ፍሬ አልባዎቹ መሬቶች የወሰዱትን ሳይመልሱ ሌላ ብድር እንዲለቀቅላቸው ተደርጓል መባሉም ባንኩ ለገባበት ቀውስ ትልቅ አበርክቶ አላቸው፡፡

ብድር የተወሰደባቸው የእርሻ መሬቶች አብዛኞቹ ጾም ያደሩ፣ የሜካኒካል እርሻ ያላያቸው መሬቶች ሆነው መገናኘታቸው ሆድ ያስብሳል፡፡ ባንኩ በሰጠው ብድር ለእርሻ ኢንቨስትመንቱ የሚሆኑና በብድር ተገዝተዋል የተባሉ የግብርና መሣሪያዎችም የውኃ ሽታ መሆናቸው ባንኩ ሥራውን እየመዘነ ብድሩን እንደማይለቅ የሚያሳብቅበት ክፍተት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በባንኩ ኃላፊዎች የተጠቀሰው አንድ አጋጣሚ ችግሩን ያሳያል፡፡ ስንትና ስንት ሚሊዮን ብሮች የተወሰደበት የእርሻ ፕሮጀክት ዕዳውን በወቅቱ ባለመመለሱ ባንኩ የፕሮጀክቱን ንብረት ለመሸጥና ብድሩን ለማስመለስ ሲነሳ ያገኘው የተበላሸ ትራክተር ብቻ እንደነበር ኃላፊዎቹ መጥቀሳቸው የችግሩን ጥልቀት ያሳያል፡፡

ባንኩ እንዲህ ባለው የተበላሸ ብድር ውስጥ ሰጥሞ በሚገኝበት ወቅት፣ አዳዲሶቹ የባንኩ ኃላፊዎች፣ ነገሮች ከተስተካከሉ የተበላሹ ብድሩን መጠን መቀነስ እንደሚቻልና  ተጨማሪ ብድር በመስጠት ሕይወት እንደሚዘራ ተናግረዋል፡፡ የኃላፊዎቹ ተነሳሽነት መልካም ቢሆንም፣ የባንኩ ተግባር አሁንም የሕዝብ ገንዘብ መና ማስቀረት እንዳይሆን ያሠጋናል፡፡ እያበደረ ያለው የሕዝብ ገንዘብ በመሆኑ፣ ባንኩ የሚሰጠው ብድር እንደ ከዚህ ቀደሙ ውስጥ ለውጥ በስምምነት እንዳይመለስ ተደርጎ የሚበተን ሳይሆን፣  ግልጽና የቁጥጥር ሥርዓቱና የብድር ዕዳው የሚያስከትለውን ኃላፊነት በሚገባ የሚያስፈጽም አካል ባንኩን ሊመራው እንደሚገባ ማሳሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለተመረጡ ፕሮጀክቶች የሚሰጠው ገንዘብ ለተገቢው ፕሮጀክት ስለመሰጠቱ ለማወቅ ከባንኩ ኃላፊዎች ባሻገር በዘርፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ይሁንታን እንዲያገኝ ማድረግ፣ ሕዝብም አስተያየት እንዲሰጥባቸው ቢደረግ ይመረጣል፡፡

በስመ የፖሊሲ ባንክነት የሕዝብ ገንዘብ ለማይገባውና ባለሀብት ነኝ ለሚለው ሁሉ መዘራት የለበትም፡፡ የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን እንዲህ እያደገ መምጣቱ፣ መንግሥትም ፖሊሲውን ማሳካት እንዳልቻለ ያሳያልና፣ የልማት ባንክ ሪፎርም እየተደረገ ነው ከሚባለው በላይ ያለፈውንና የወደፊቱን በጥልቀት በመፈተሽ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባዋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት