Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱሪዝም ድርጅት የአገር ውስጥና የውጭ ሥራዎች ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጣቸው ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለወራት ሲያነጋግር የሰነበተውን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ድርጅት አመራር የተረከቡት አዲሷ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ በድርጅቱ ሲከናወኑ የቆዩና ክፍተት ታይቶባቸዋል የተባሉ፣ በአገር ውስጥና በውጭ ሲካሄዱ የቆዩ ተግባራት ከሰኞ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጣቸውን አስታወቁ፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ሌንሳ መኮንን ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ በድርጅቱ የገበያና የፕሮሞሽን ሥራዎችና በአዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ሥራዎች ላይ ክፍተቶች በመታየታቸው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በገበያና በአዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ልማት ላይ አተኩሮ እንዲሠራ በመንግሥት ኃላፊነት ቢሰጠውም፣ በተለይም በቀደመው አመራር ጊዜ፣ ክፍተት ታይቶባቸዋል ያላቸውንና ጥልቅና የማያዳግም ዕርማት ያስፈልጋቸዋል ብሎ ያመነባቸውን የሥራ ሒደቶች ወይም ክንውኖች፣ ማለትም ቱሪስት አመንጪ ተብለው ከሚታሰቡ አገሮች ጋር የሚደረጉ የቢዝነስ ለቢዝነስ ሥራዎች፣ የጉበኝት መርሐ ግብሮችን (ፋን ትሪፕ)፣ የዓውደ ርዕይ ተሳትፎዎችን፣ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ልማትና ነባር የፕሮሞሽን ኅትመት ሥራዎች እንዲቆሙ መደረጉ ተብራርቷል፡፡

‹‹በግብይት ሥራችን ላይ ክፍተት ያገኘንባቸውና መሻሻል ያለባቸው፣ በአዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ክፍተት ያገኘንባቸው ሁኔታዎች ስላሉ፣ አራት የማርኬቲንግ ሥራዎችንና አንድ የአዳዲስ የመዳረሻ ልማት ሥራ አስቁመናል፤›› ያሉት ወ/ሪት ሌንሳ ለቢዝነስ ልውውጥ፣ ልምድና ተሞክሮ ለማግኘት፣ በተለያዩ አገሮች የሚደረጉ ጉብኝቶች እንዲቆሙ መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማት በፊት ነባሮቹን ማስተካከል ስለሚያስፈልግ እንዲቆሙ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ዋነኛ የተቋሙ ሥራዎች ላልተወሰነ ጊዜ ይቋረጡ እንጂ፣ ከወዲሁ ጥናቶችና ትንተናዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ወጣቷ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉት ሥራዎች ለጊዜው ቆመው እንዲመረመሩ ያስፈለገው ክፍተት ስለተገኘባቸው ነው ይበሉ እንጂ፣ ጉድለቱ ምን እንደሆነ ግን በዝርዝር አልገለጹም፡፡ የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ጥላሁን፣ ከደመወዝና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እንዲነሱ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡ በቱሪዝም ድርጅት የቦርድ አመራርና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መካከል ንትርክ ያስነሳው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አመራር ጉዳይ፣ በተለይም በአቶ ዮሐንስ ላይ የቀረበው ያላግባብ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ ትልቅ መነጋሪያ ነበር፡፡

አቶ ዮሐንስ በድርጅቱ ከሚከፈላቸው ደመወዝና ከሚታሰብላቸው ጥቅማ ጥቅም ባሻገር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በኩል ይከፈላቸው የነበረው ተጨማሪ ደመወዝ ትልቅ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የሚመራው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድ፣ አቶ ዮሐንስ በሕግ ይጠየቁ እስከማለት ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ 

ለአሥር ወራት የቆየው ነባሩ የቱሪዝም ድርጅት አመራር በአዲስ እንዲተካ ከተደረገ ወዲህ፣ ላለፉት ሁለት ወራት ድርጅቱን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተሾሙት ወ/ሪት ሌንሳ ከዚህ ቀደም በግላቸው በአመራር መስክ፣ በሕዝብ ግንኙነትና በኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ አማካሪ ስለመሆናቸው የሚጠቅሱ ቁንጽል መረጃዎች አሉ፡፡

ከወ/ሪት ሌንሳ በተጨማሪም የሙዚቃ ባለሙያው አቶ ሰርፀ ፍሬ ስብኃት በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት መሾማቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ምክትል ዋና አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ሐጎስ አብርሃ (ዶ/ር)፣ የድርጅቱን የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት ሥራዎች እንደሚመሩ ታውቋል፡፡ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር፣ የቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ሥነ ጽሑፍና የብራና ጥናት ማዕከል አስተባባሪና የግዕዝ፣ የውጭ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ መምህር ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች