የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) አራት መሥሪያ ቤቶችን በማጠፍ የክልሉን የአስፈጻሚ አካላት ብዛት ከ42 ወደ 38 ዝቅ እንዲል፣ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጠራው የምክር ቤቱ አራተኛ ዓመት አምስተኛ የሥራ ዘመን ሦስተኛ አስቸኳይ ጉባዔ ወሰነ፡፡
በዚህም መሠረት በክልሉ አስፈጻሚ አካላት ውስጥ የተጨመሩ አዳዲስ አካላት ሲኖሩ፣ የተቀነሱና የተጣመሩም አሉ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት የክልሉን መንግሥት አስፈጻሚ አካላት እንደገና ለማደራጀትና ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን ያወጣውን አዋጅ 199/2008 አሻሽሎ ነው እነዚህን ለውጦች ሊያመጣ የቻለው፡፡
ምክር ቤቱ ከኤጀንሲነት ወደ ቢሮነት ከለወጣቸው አንዱ የኢንዱስትሪ ልማትና ማስፋፊያ ኤጀንሲ ሲሆን፣ የኢንተርፕራይዝና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሆኖ እንዲደራጅ፣ የኮንስትራክሽን ቢሮ የነበረው ደግሞ ባለሥልጣን ሆኖ እንዲደራጅ አድርጓል፡፡
የውኃ፣ ኢነርጂና ማዕድን ልማት ቢሮ ለሁለት ተከፍሎ የማዕድን ልማት ለብቻው የሆነ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ለሁለት ተከፍሎ የንግድ ቢሮና የገበያ ልማት ኮሚሽን በመባል እንደገና ተዋቅረዋል፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከነበረው ስፖርት ለብቻው ኮሚሽን እንዲሆን ሲደረግ፣ ወጣቶች ከሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ጋር ተቀላቅሏል፡፡
የእንስሳት ሀብት ልማት ኮሚሽንና የግብርና ግብዓቶች ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክር ቤቱ ያቋቋማቸው ተቋማት ናቸው፡፡
የመሬት አስተዳደርን የሚመለከት አዲስ ተቋም እንዲቋቋም ያደረገው ምክር ቤቱ፣ የመሬትን ሥራ የሚያከናውኑ ሦስት መሥሪያ ቤቶችንም በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ሥር እንዲታቀፉ አድርጓል፡፡ በዚህ ቢሮ ሥር የሚታቀፉት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲና የከተማ መሬት ይዞታና መረጃ ምዝገባ ኤጀንሲ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ የመስኖ ልማት ባለሥልጣንና የቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን እንዲታጠፉ ተደርጓል፡፡
ምንም እንኳን ክልሉ ቀደም ሲል የነበረው ፍትሕ ቢሮ በ38 ዝርዝር ውስጥ ባይካተትም፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሹመትን ጨፌ ኦሮሚያ ሰጥቷል፡፡
ምክር ቤቱ በክልሉ ለሚገኙ የአስፈጻሚው አካል መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ ሹመቶችን የሰጠ ሲሆን፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ሦስት ሹመቶችንም አፅድቋል፡፡ በዚህም መሠረት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ፣ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ዘርፍ ኃላፊና አቶ አህመድ ቱሳ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ በመሆን ተሾመዋል፡፡
የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ በነበሩት ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ምትክ አቶ አድማሱ ዳምጠው የተሾሙ ሲሆን፣ አቶ መሐመድ አደሞ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ዋና ዳይሬክተር በመሆን ተሹመዋል፡፡ አቶ መሐመድ በአልጀዚራና ኦፕራይድ በተሰኘው ድረገጽ ላይ ይሠሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የኦቢኤን ቦርድ ዳይሬክተር እንዲሆኑ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተሾሙ ሲሆን፣ ደረጀ ገረፋን (ዶ/ር) ጨምሮ ስድስት የቦርድ አባላትም ተሰይመዋል፡፡