Saturday, January 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበት የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አምራቾችን ይጠባበቃል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመጀመርያው ምዕራፍ የግንባታ ሒደት በ102 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የውጭ አምራቾችን እየተጠባበቁ የሚገኙ 19 የማምረቻ ሕንፃዎችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በ4.1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነቡበት ትልቅ ማምረቻ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕቅድ ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትርና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በአዳማ የተገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ አዲስ አበባን ከጂቡቲ፣ እንዲሁም አዲስ አበባን ከአሰብ ወደብ የሚያገናኝ በንግድ ኮሪደሯ አዳማ ከተማ የተገነባ የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ነው፡፡ ይህም ሆኖ እንደ ሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ቀድመው አልገቡበትም፡፡ እስካሁን ሊጠቀሱ የሚችሉት አንቴክስ ቴክስታይልና ቻርተር ቬንቸርስ አፓረል ኢትዮጵያ የተባሉ የስፔንና የሆንግ ኮንግ ሁለት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ዋይኬኬ የተባለ የጃፓን ኩባንያ በተጓዳኝ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ላይ እንደሚሰማራ ይጠበቃል፡፡ እሑድ መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ በተመረቀው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ይታያሉ፡፡ 

በአዳማ ግንባታው በከፊል የተጠናቀቀውና የመጀመሪያውን ምዕራፍ 19 የማምረቻ ሕንፃዎችን በማጠናቀቅ ለሥራ ያዘጋጀው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ከ147 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ወይም ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የጠየቀ ቢሆንም፣ እስካሁን በፓርኩ ለማምረት ዝግጅት መጀመራቸው የተገለጸው ሁለት የውጭ ኩባንያዎች ብቻ ናቸው፡፡

እሑድ መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ በአማራ ክልል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ በኢኮኖሚ ዕቅድ ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትርና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) እንዲሁም በሌሎችም ባለሥልጣናት የተመረቀው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ልክ እንደ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዘመናዊ የግንባታና የመሠረተ ልማት ዝርጋታን የተከተለ አሠራር እንደተተገበረበት አርከበ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የፓርኩ ጠቅላላ የመሬት ስፋት 2,000 ሔክታር መሬት የሚሸፍን ቢሆንም፣ መጀመሪያው ምዕራፍ ፓርኩ ግንባታ ከሚከናውንበት 365.5 ሔክታር ውስጥ በ102 ሔክታር ላይ የተገነቡ 19 የማምረቻ ሕንፃዎች ለሥራ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በሕንፃዎቹ ውስጥ ለማምረት ዝግጅት መጀመራቸው የተነገረላቸው የስፔኑ አንቴክስ ቴክስታይል፣ የሆንግ ኮንጉ ቻርተር ቬንቸርስ አፓረል ኢትዮጵያ እንዲሁም ዋይኬኬ ኮርፖሬሽን የተሠራው የጃፓን የአልበሳት ተጓዳኝ አካላት አምራች ኩባንያ ዝግጅት እያደረጉ ከሚገኙት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ ምንም እንኳ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ2,000 ሔክታር መሬት የሚያካልል ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ይሁን እንጂ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ፓርኮች በርካታ የውጭ አምራቾችን ለመሳብ የሚጠባበቅ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ መንግሥት ይፋ ያደረጋቸው ኩባንያዎች ከላይ የተጠቀሱት ቢሆኑም፣ በፓርኩ ክልል ውስጥ የራሳቸውን ማምረቻ ሕንፃዎች በመገንባት ሒደት ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች መኖራቸው አልቀረም፡፡

ጂያግሱ ሰንሻይን ውል ቴክ ስታይል የተሰኘውና የሱፍ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቹ የቻይና ኩባንያ የራሱን ፋብሪካ ለመገንባት 80 ሔክታር መሬት መረከቡንና ሥራ መጀመሩን ያስታወቀው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መግለጫ፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ ለሚያከናው ነው የምርት ተግባር ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ መመደቡንም አስታውቋል፡፡ ሰንሻይን ግሩፕ በቻይና ከሚታወቅባቸው የአልባሳት ምርቶቹ መካከል፣ ለቻይና ብሔራዊ የክብር ዘብ የሚያዘጋጃቸው ሦስት ዓይነት ወታደራዊ የደንብ አልባሳት በተቋሙ ለሕዝብ ዕይታ ቀርበው ከሚጎበኙት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ኪንግደም ሊነን ኢትዮጵያ በሚል መጠሪያ በቻይናው ኪንግደም ሆልዲንግስ ኩባንያ ሥር የሚተዳደረው ሌላኛው የቻይና ሆንግ ኮንግ ኩባንያም በ32 ሔክታር መሬት ላይ የማምረቻ ፋብሪካ፣ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እየገነባ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ኩባንያ በተለይ በኒለን ምርቶቹ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በክር አምራችነቱ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ዋይኬኬ ግሩፕ የተሰኘው የጃፓን ኩባንያ በአንፃሩ የተጓዳኝ ምርቶች ላይ የተሠማራ ኩባንያ ነው፡፡ በዚፕ አምራችነቱ ሰፊ ዕውቅና ቢያተርፍም፣ በሌሎችም የፕስቲክና የአርክቴክቸር ምርቶቹ ሰፊ ገበያ እንዳለው የኩባንያው ድረ ገጽ ላይ የሠፈሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እንዲህ ያሉ ኩባንያዎች መምጣታቸው ቢጠቀስም እነዚህ ግን በ2,000 ሔክታር መሬት ላይ ለሚንሰራፋው የኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚጠበቁት ኩባንያዎች አኳያ ግን በርካቶች ገና እንደሚመጡ አመላካች ነው፡፡

ይህም ሆኖ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ለ25 ሺሕ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንደሚያስገኝ የገለጹት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ሌሊሴ ነሜ ፓርኩ ዘመናዊ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት እንደተገነባለትም አስታውቀዋል፡፡ የተገነባው የፍሳሽ ማጣሪያ 11 ሺሕ ሜትሪክ ኩብ ፍሳሽ እንደሚያጣራ ጠቅሰዋል፡፡ በግንባታ ላይ የሚገኙ ስድስት ፓርኮች እንዳሉና እስካሁንም አምስት ፓርኮች ሥራ እንዲጀምሩ መደረጋቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቅሰዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የግንባታ ሒደት በተለይም በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ሒደት የተለየ የግንባታ ፍጥነት እንዲተገበር በማድረግና በአሥር ወራት ገደማ የፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ 37 የግንባታ ሕንፃዎች ዕውን የተደረጉበት ሒደት ይታወሳል፡፡ የቅርብ ክትትል በማድረግ ሥራውን የመሩት አርከበ (ዶ/ር) በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝና በሌሎችም ከፍተኛ ኃላፊዎች ዘንድ ከኢሕአዴግ ያልተመለደ ሙገሳ ተችሯቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምረቃ ሥነ ሥርዓትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ይህንኑ ደግመውታል፡፡ አርከበ (ዶ/ር) ለፖለቲካ አሻጥር ጊዜ የሌላቸው፣ በሳምንት ሰባት ቀናት ያለ ዕረፍት የሚሠሩ ምርጥ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በአደባባይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነግሮላቸዋል፡፡

አርከበ (ዶ/ር) በንግግራቸው ከሐዋሳው ባሻገር፣ የቦሌ  ለሚ ቁጥር 1፣ የመቀሌ፣ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ቀደም ብሎም የአይሲቲ ፓርክ የተሰኘውና በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን መስኮች በተለይም በሶፍትዌርና ሃርድዌር ምርቶች ለሚሠማሩ ወጣቶች ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ የሚታሰበው ፓርክ እስካሁን ከተገነቡት መካከል ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና አዳማን ጨምሮ በዚህ ዓመት ብቻ ሰባት ፓርኮች ማለትም የድሬዳዋ፣ የቂሊንጦ ፋርማሲውቲካል፣ የቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለት፣ የጅማ፣ የባህር ዳርና የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሥራ እንደሚገቡ አርከበ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ እንደ አርከበ (ዶ/ር) የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻውን አንድ ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ማስገኘት የሚችልና ከግዙፍ ፓርኮች ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ አርከበ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ በአዳማ የተገነባው ፓርክ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ለሚያልፈው ብቻም ሳይሆን ወደ አሰብ ወደብ ለሚያመራው የንግድ እንቅስቃሴ አዳማ ዋነኛዋ የንግድ ኮሪደር ስለመሆኗ ጠቅሰዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳም የፓርኩ ግንባታ በአቅራቢያው ለሚገኘው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የጥናት ማዕከል በመሆን ማገልገል እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች