Sunday, May 26, 2024

መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲያስጠብቅ ኢሶዴፓ ጠየቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከማንኛውም ጉዳይ በፊት መንግሥት ለሕዝቦች ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ ቅድሚያና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) አሳሰበ፡፡

ፓርቲው ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹በሰላማዊ ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸሙ ያሉት አሰቃቂ ጥቃቶች በአስቸኳይ ሊገቱ ይገባል›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

‹‹ባለፉት የኢሕአዴግ አገዛዝ ዓመታት ዜጎቻችን በብሔር ማንነታቸው ምክንያት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የተለያዩ ጥቃቶች እየደረሰባቸው ከመኖሪያቸውና ከሥራ ገበታቸው እየተፈናቀሉ፣ በገዛ አገራቸው ለስደትና እንግልት ሲዳረጉ ቆይተዋል፤›› የሚለው የፓርቲው መግለጫ፣ ሁኔታው ከመሻሻልና መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባስ በአሁኑ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በመላ አገሪቱ የዚህ ዓይነት ጥቃት  ሰለባዎች እየሆኑ ነው በማለት፣ ጉዳዩ ከመሻሻል ይልቅ በመጠን እየጨመረና እየሰፋ መሄዱ እንደሚያሳስበው አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት ለአብነት ያህል ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነዋሪ በነበሩት የኦሮሞ ብሔር አባላትና በሌሎች የተለያዩ ብሔረሰቦች አባላት ላይ ግድያዎችና ማፈናቀል መከሰቱ፣ በደቡብ ክልል ነዋሪ በሆኑና ለዘመናት አብረው በሰላም ሲኖሩ በነበሩት የመስቃንና የማረቆ ብሔረሰቦች መካከል በወሰን አከላለል ምክንያት በመስቃን ወረዳ በኢንሳም ከተማ የተነሳው ግጭት የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈ መሆኑን፣ በርካቶች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት እንደሆነ፣ በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ፓርቲው በመግለጽ፣ መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ በመውሰድ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲያስከብር በፅኑ ጠይቋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ከዚህ በላይ የተጠቀሱትና የመሳሰሉ ጥቃቶች በአገራችን በርካታ አካባቢዎች እየተለመዱ መምጣታቸውና በዜጎቻችን ላይ ከፍተኛ ጉዳቶች እያስከተሉ መሆናቸው፣ እንዲሁም በመንግሥት በኩል ችግሮቹ እየታወቁ እነዚህን ዘግናኝ የወንጀል ድርጊቶች ለማስቆም የሚያስችሉ ወቅታዊና ተመጣጣኝ ዕርምጃዎች አለመወሰዳቸው፣ የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት አሥጊ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባና የሕገ የበላይነት የሌለበት ሁኔታ በአገራችን መፈጠሩ፣ የኢሕአዴግ አገዛዝ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን አመላካች ናቸው፤›› ሲል መንግሥትን ወቅሷል፡፡

‹‹መንግሥት በዜጎች ላይ በፀረ ሰላም ኃይሎች እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን በአስቸኳይ በማስቆምና ዜጎች ዘላቂ ሰላም የሚያገኙበትና ደኅንነታቸው የሚረጋገጥበትን ተጨባጭ ዕርምጃ እንዲወስድ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ የሚገኙት ወንጀለኞች በሕግ ተጠያቂዎች እንዲደረጉ፣ እንዲሁም ለግጭቶች ምክንያት እየሆኑ ያሉት መሠረታዊ ችግሮች በአግባቡ ተጠንተው ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው፤›› ሲል ፓርቲው አጥብቆ ጠይቋል፡፡

ኢሶዴፓ ከአራቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ስብስቦች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በስብስቡ ውስጥ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (አረና)፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ይገኛሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -