Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበሕገወጥ መንገድ ሠራተኞችን በሚመለምሉ የውጭ ዜጎችና ኤምባሲዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

  በሕገወጥ መንገድ ሠራተኞችን በሚመለምሉ የውጭ ዜጎችና ኤምባሲዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

  ቀን:

  የውጭ ሥራ ሥምሪት መጀመር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ይደረጋል

  በ2006 ዓ.ም.  ዕግድ ተጥሎበት የነበረው የውጭ ሥራ ሥምሪት ከረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የሚጀመር ቢሆንም፣ በሕገወጥ መንገድ ሠራተኞችን በሚመለምሉ የውጭ አገር ዜጎችና ኤምባሲዎች ላይ መንግሥትና የሚመለከተው አካል ዕርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ተጠየቀ፡፡

  ላለፉት አምስት ዓመታት ሕግን ብቻ ተከትለው የሚሠሩ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች የመንግሥትን ውሳኔ እየተጠባበቁ ቢቆዩም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች በሆቴልና እንግዳ ማረፊያ ተቀምጠው የቤት ሠራተኞችን በቱሪስት ቪዛ ከአገር እንዲወጡ በማስደረግ፣ በየቀኑ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መንግሥት ዕግድ ጥሎባቸው ወደነበሩ የዓረብ አገሮች ሲልኩ እንደነበርና አሁንም እየላኩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች ማኅበር አባላት፣ ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ለግማሽ ቀን በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረጉት ስብሰባ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ መዝገቡ አሰፋ እንደተናገሩት፣ ከውጭ አገር ዜጎች በተጨማሪ የኮሚሽን ኤጀንትነት ፈቃድ ወስደውና ከኤምባሲዎች ጋር በመመሳጠር ፎርም እያስሞሉ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በርካታ ኢትዮጵያውያንን ሲልኩ ነበር፡፡ አሁንም እየላኩ ነው፡፡ ድርጊቱ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መሆኑ ቢታወቅም፣ በግልጽ የሚታወቁ የሕክምና መስጫ ተቋማትና የጉዞ ወኪሎችም ተባባሪ መሆናቸውንም የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጭምር እንደሚያውቁ አስረድተዋል፡፡

  ዘርፉ ከሚያመነጨው ኢኮኖሚ አገሪቱም ተጠቃሚ እንድትሆን፣ ለሥራ የሚሄዱትም ወገኖች ተመጣጣኝና የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙና መብታቸው እንዲከበር ለማድረግ መንግሥትና በተለይ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ሌሎቹም ተቋማት ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ እየመለመሉና እየላኩ የሚገኙት የውጭ ዜጎች፣ ለኮሚሽን ኤጀንትነት ፈቃድ ወስደው ከኤምባሲዎች ጋር በመመሳጠር የሚልኩ፣ ተባባሪ የሕክምና ተቋማትና የጉዞ ወኪሎች ላይም ዕርምጃ በመውሰድ አሠራሩ ሕግን የተከተለ እንዲሆን ማድረግ እንዳለባቸው አቶ መዝገቡ አሳስበዋል፡፡

  በስብሰባው ላይ የተገኙት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ  ምሥጋኑ አረጋ (አምባሳደር)፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ሴክተሩ ተዘግቶ ቢቆይም ሕጋዊ መንገድ ተከትለው የሚሠሩ ኤጀንሲዎች ወጪ ብቻ እያወጡ በጉዳት መጠበቃቸው፣ ምን ያህል ለሕግ ተገዥ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዘርፉ እንዲሻሻል ሕግ ሲወጣ፣ ደንብና መመርያ ሲዘጋጅ ጊዜ መውሰዱን ጠቁመው፣ የዜጎች ሕይወት ከመሆኑ አንፃር ከሌሎች የሥራ ዓይነት እንደሚለይና በጥንቃቄ ሲሠራ መቆየቱን አክለዋል፡፡ የዜጎች ጉዳይ የእያንዳንዱ ኤጀንሲ ባለቤትና የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፣ የተበላሸውን የሴክተሩን ገጽታ በመቀየር፣ ሕገወጦችን በማጋለጥና ሕግና ሕግን ብቻ ተከትሎ በመሥራት የሥራውን ዘርፍ በማብዛት፣ ወንድ ሠራተኞችም የሚሄዱበትን ሕጋዊ አሠራር ማመቻቸት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሴክተሩ ውስብስብና ሰውን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ ከሌላው የንግድ ሥራ የተለየ መሆኑን አምኖ ኃላፊነትን በአግባቡ በመወጣት መሥራት እንዳለባቸው የማኅበሩ አባላትን አሳስበዋል፡፡ መላክ የሚቻለው ሁለትዮሽ ስምምነት በተፈራረሙት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ጆርዳንና ኳታር ብቻ መሆኑንም አስታውዋል፡፡ ሁሉም ተጨፍልቆ ማለትም ሕጋዊውም ሆነ ሕገወጥ ሆኖ ሲሠራ የነበረው አንድ በመሆን፣ የጠፋውንና ‹‹ሕገወጦች›› የሚለውን ስም ማደስ እንደሚገባቸውም ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡  

  ሚኒስትር ዴኤታው በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለበርካታ ዓመታት አምባሳደር ሆነው በመሥራታቸው፣ በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረውን አስከፊ ድርጊት በቅርበት ያዩ በመሆናቸው በሚኒስትር ዴኤታነት መሾማቸው ተገቢና ለዘርፉ ትክክለኛ ሰው መገኘቱን የማኅበሩ አባላት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

  መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ቀደም ብሎ ወጥቶ የነበረውን የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 632/2001 በመተካት አዋጅ ቁጥር 923/2008 መውጣቱንና ቁጥጥሩን ማጥበቁን የጠቆሙት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ መዝገቡ፣ አዋጁን ለማስፈጸም የወጡ ደንብና መመርያን ከእነ ጉድለታቸውም ቢሆን ተቀብለው ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

  የውጭ አገር ሥራ ሥምሪትን በሚመለከት መንግሥት ዕግድ የጣለው ከአምስት ዓመታት በፊት ቢሆንም፣ በጉብኝነት ቪዛ በማሳበብ በየቀኑ በርካታ ሠራተኞች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ይወጡ እንደነበርና ፖሊስ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኤምግሬሽን ሠራተኞችና የአየር መንገድ ሠራተኞች እንደሚያውቁ፣ በመዳረሻ አገሮች ያሉ ኤምባሲዎች (ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች) የተቀባይ አገር አሠሪዎች በዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ግፍና በደል እያወቁ፣ ከማስቆም ይልቅ ተባባሪ ከመሆን የዘለለ ተግባር አለመፈጸማቸውን የስብሰባው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

  ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ የሚጀመረውን የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሸራተን አዲስ ይፋ እንደሚያደርጉም ተጠቁሟል፡፡        

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...