በኢትዮጵያ ስፖርትን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር የተፈጥሮ መስህቦችን ከማስጠበቅ አልፎ በስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ መወዳደር ብቻም ሳይሆን፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ላይ መሥራት ላይ ያተኮር ስፖርታዊ ክንውን መካሔድ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡
ስፖርትን ከቱሪዝም ጋር ያስተሳሰረው ይኸው የተራራ ላይ ሩጫ፣ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ ወንጪ ከተማ አካባቢ በሚገኘው የወንጪ ሐይቅ ስምጥ ሸለቆ ዙሪያ ለአምስተኛ ጊዜ ተካሂዷል፡፡
በሪያ ኢትዮጵያ ስፖርትስ በተባለው ተቋም አዘጋጅነት ቅዳሜ፣ መስከረም 26 ቀን 2011 ዓ.ም. የተካሄደው የወንጪ ስምጥ ሸለቆ ሐይቅ የተራራ ሩጫ ላይ፣ በጠቅላላው 300 ተሳታፊዎች መካፈላቸውን ዝግጅት ክፍሉ አስታውቋል፡፡ ከ30 በላይ የውጭ ዜጎች መሳተፋቸውንም የድርጅቱ መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበር አትሌት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም ተናግሯል፡፡
የዘንድሮ የወንጪ ሐይቅ የተራራ ላይ ሩጫ ካለፉት ዓመታት በላቀ ሁኔታ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ወደ 40 በመቶ ከፍ እንዳደረገ ያስታወቀው ዝግጅት ክፍሉ፣ ውድድሩ ግማሽ ማራቶን ወይም 21 ኪሎ ሜትር እና 10‚000 ሜትር ርቀቶችን እንደሸፈነ አትሌት ገብረ እግዚአብሔር ገልጿል፡፡
እንደ ዝግጅት ክፍሉ መግለጫ ከሆነም፣ ቦታው ከባህር ጠለል በላይ 3,380 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኘው ወንጪ ሐይቅ ዙሪያ የተካሄደ ውድድር ሲሆን፣ ውድድሩን ያስጀመሩት የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የወንጪ ኢኮ-ቱሪዝም ማኅበር አባላት ናቸው፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ወንጪ ሐይቅ የተራራ ሩጫን ጨምሮ ሌሎች የተራራ ላይ ሩጫዎችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ሪያ ኢትዮጵያ ስፖርትስ፣ በያዝነው ዓመትም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው መካከል፣ ‹‹ኢትዮ ትሬል›› የተሰኘውን የተራራ ሩጫ ለማከናወን ጥናት ላይ እንደሚገኝ በተለይም በአዲስ አበባ እንጦጦ ተራራ ላይ የተራራ ሩጫ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ 155 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ወንጪ ሐይቅ ዙሪያ የተካሄደው የተራራ ሩጫ፣ የአገሪቱን ልዩና ማራኪ የተፈጥሮ ፀጋ ለተሳታፊዎች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎችና በድርጅቱ ድረ ገጽ አማካይነት ለዓለም በማድረስ ወደፊት የተሻለ የቱሪዝም ፍሰት ለአካባቢውም ሆነ ለአገሪቱ ይዞ እንደሚመጣ ያስታወቀው ዝግጅት ክፍሉ፣ በሁለቱም ፆታ አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች ማበረታቻ ሽልማት ማበርከቱን አስታውቋል፡፡