ለ2019 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ የኬንያ አቻውን (ሃራቤ ስታር) የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ በመጪው ቅዳሜም በኬንያ የመልስ ጨዋታውን እንደሚያካሂድ ይጠበቃል፡፡
የቶትንሃሙን አማካይ ቪክቶር ዋኒያማን ጨምሮ ሌሎችም ፕሮፌሽናሎችን ያካተተው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን፣ ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ተጠቃሎ ባሕር ዳር መግባቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የዋሊያዎቹን የዝግጅትና የሥልጠና ሒደት ሊያዘናጉ የሚችሉ ዜናዎች ከወደ ኬንያ ሲደመጡ ሰንብተዋል፡፡
የኬንያ መንግሥት የአገሪቱን እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በሙስና ሳቢያ መመርመር እንደጀመረ ማስታወቁን ተከትሎ፣ የዓለም እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በኬንያ ላይ ዕገዳ ጥሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ዕርምጃው ለኬንያ ተጨዋቾች ሥነ ልቦና ጥሩ እንደማይሆን በተለይ በኢትዮጵያ ስፖርት ሚዲያ ዘንድ በሰፊው ሲወራ ቢቆይም፣ ኬንያውያን ተጨዋቾች ግን ዋልያዎቹን አሸንፈው ሙሉ ሦስት ነጥብ በመያዝ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2012 በደቡብ አፍሪካ በተሰናዳው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት መነቃቃትን ፈጥሮ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንቅስቃሴ፣ ደረጃውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ነገሮች ሳይመቻቹለት ቆይተዋል፡፡ እግር ኳሱ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ የሕዝብ ድጋፍ ያለውና አንጡራ የአገር ሀብት ከሚፈስባቸው ዘርፎች አንዱ ሆኗል፡፡ የሰው ሀብትን ጨምሮ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚፈስበት ይህ የስፖርት ዘርፍ ግን ዘመኑ የሚጠይቀው የአደረጃጀትና የአሠራር ሥርዓት ስላልተዘረጋለት አጥጋቢ ውጤት ማስመዝገብ ተስኖት ይዋልላል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑም ሆነ ክለቦች በሚሳተፉባቸው ውድድሮች ሽንፈት በገጠማቸው ቁጥር፣ ከሁሉም አቅጣጫ ከሚደመጠው የአንድ ሰሞን ኡኡታና ትችት ወጣ ብሎ የስፖርቱን መሠረታዊ ችግሮች በመለየት መሥራት ለዚህም ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጀምሮ እስከታች ባለው መዋቅር ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥና ውጤት ተኮር አካል እንደሚያስፈልግ በርካቶች ያምናሉ፡፡
ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች አንዳንዶቹ ፊፋ በኬንያ ላይ ዕገዳ ሊጥል ይችላል በሚል በአገሪቱ የስፖርት ሚዲያ ሲነገር የሰነበተው ዘገባ፣ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ለሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አንዳች እንደማይፈይድለት ያስረዳሉ፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚያካሂደውን የዝግጅት ሒደት ላይ መዘናጋት እንዳያመጣ የሚሠጉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ለእግር ኳሱም ሆነ ለዋሊያዎቹ ውጤታማነት የሚጠቅመው በችግሩ ዙሪያ አድምቶ መነጋገርና ትክክለኛውን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የጠፋውን ውጤት ማምጣት የሚያስችል ሥራ ላይ ሲተኮር እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
የዋሊያዎቹ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ በያዙት ስብስብ አማካይነት ለአገሪቱ እግር ኳስ ትንሳዔ የሚሆን ነገር ለመሥራት ጥረት ላይ እንደሚገኙ ይታመናል፡፡ አሠልጣኙ ከሁለት ሳምንት በፊት ከሴራሊዮን አቻቸው ጋር በሐዋሳ ከተማ ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታቸው ሙሉ ሦስት ነጥብ ማስመዝገባቸው ጥሩ ጅምር ብቻም ሳይሆን፣ ለስብስባቸው መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው በባሕር ዳሩም ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡
በኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ በተፈጠረው የሙስና ጉዳይ ምክንያት፣ የኬንያ ተጨዋቾች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የካፍን መርሐ ግብር ለማሟላት ካልሆነ በቀር፣ በሙሉ አቅማቸው ላይጫወቱ ይችላሉ የሚሉ መላ ምቶች ሲስተጋቡ ሰንብተዋል፡፡ ይህንን መላምት የሚያጠናክረው ተጨዋቾቹ ከኬንያ ወደ አዲስ አበባ ከዚያም ወደ ባሕር ዳር የገቡት ተንጠባጥበው መሆኑ ነበር፡፡ ይሁንና ፊፋ በኬንያ ፌዴሬሽን ላይ የጣለውን ዕገዳ በጊዜያዊነት ማንሳቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አዲስ አበባ ተጠቃሎ የገባው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን አባል የሆነውና በእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ ለቶተንሃም የሚጫወተው ቪክቶር ዋኒያማ፣ ‹‹ዋሊያዎቹን አሸንፈን ሦስት ነጥብ ይዘን ለመሄድ መጥተናል፤›› በማለት ለዋልያዎቹ አጭር መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የዋሊያዎቹን ወቅታዊ ብቃት አስመልክቶ ለኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ቤተሰቦች ሌላም ሥጋትና ተስፋ ስለመሆኑ እየተነገረ የሚገኝ ጉዳይም አለ፡፡ እንደ ኬንያ ፌዴሬሽን ሁሉ የሴራሊዮን እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በተመሳሳይ የሙስና ቅሌት ከአገሪቱ መንግሥት ጋር በፈጠረው እሰጣ ገባ፣ ፊፋ ጣልቃ በመግባቱ ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ ተመሳሳይ ሁኔታ አዙሪት ውስጥ መሰንበቱ ታውቋል፡፡ ሆኖም ፊፋ አሁንም ሴራሊዮንን በጊዜያዊነትም ቢሆን፣ ከጋና ጋር የሚጠብቃትን መርሐ ግብር ማከናወን እንደምትችል ይፋ አድርጓል፡፡ ይህም ተስፋና ሥጋትን ያጫረ አጋጣሚ መሆኑ አልቀረም፡፡
ይሁን እንጂ የዋሊያዎቹን ወቅታዊ ብቃት መነሻ በማድረግ በሚዲያውም ሆነ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ቡድኑ ጠንካራ ዝግጅት እንዲያደርግ ካልሆነ በቀር፣ በእንዲህ ያሉ ዜናዎች እንዳይዘናጋ ማድረግ የሚጠበቅባቸው መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ‹‹ተጨዋቾቹ ሥራቸውን ብቻ ይሥሩ እንጂ ፊፋ እንዲህ አለ፣ የኬንያ ቡድን እንዲህና እንዲያ ተባለ፣›› ማለቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳት አለው በማለት አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች፣ ጉዳዩ የሚያስከትለው የሥነ ልቦና ጫናም ሊታሰብበት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡
መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በባሕር ዳር ስታዲዮም የሚደረገውን የኢትዮጵያና የኬንያ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ፣ ከቀኑ 10.00 ሰዓት ጀምሮ ዲኤስ ቲቪ በቀጥታ ሥርጭት እንደሚያስተላልፈው ይታወቃል፡፡ በርካታ የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች ከአዲስ አበባና ከሌሎችም ከተሞች ወደ ባሕር ዳር ከተማ ማምራታቸው ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀታቸውም እየተነገረ ነው፡፡ እንደ በርካቶቹ ደጋፊዎች እምነት፣ ብሔራዊ ቡድኑ ባሕር ዳር ላይ በሚያደርገው ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ በሜዳው አንድ ቀሪ ጨዋታ ስለሚኖረው ለ2019 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሰፊ ዕድል ይኖረዋል፡፡
አሠልጣኝ አብርሃምም ሆኑ ስብስባቸው እስካሁን ባለው የቡድናቸው አቋም ደስተኛ ስለመሆናቸው ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በተለይም ከሥልጠና ፍልስፍና ጋር ተያይዞ በአሠልጣኞችና በተጨዋቾች መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድም የሐሳብ አለመጣጣሞች ሲደመጡ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ችግሩ ሙሉ በሙሉም ባይሆን አሠልጣኙና ተጨዋቾቹ ተግባብተው እየሠሩ በመሆናቸው፣ የቡድኑ አባላት ደስተኛ ስለመሆናቸው የዋሊያዎቹ አምበል ጌታነህ ከበደ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት መናገሩ ይታወሳል፡፡