Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበለውጥ ምዕራፍ ለአሳሳቢ ግጭቶች ተገቢው ትኩረት ይሰጥ!

በለውጥ ምዕራፍ ለአሳሳቢ ግጭቶች ተገቢው ትኩረት ይሰጥ!

ቀን:

በሸዋዬ ተስፋዬ

ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የመደመርና ይቅርታ ለውጥ ጎን ለጎን አሳሳቢ የሆኑ አካባቢያዊ ግጭቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ እነዚህ ግጭቶች የብዙ ዜጎች ሕይወት አካልና ሥነ ልቦና ላይ አስከፊ ጉዳቶችን ከማድረሳቸው በተጨማሪ፣ ዜጎች ያፈሩትን ንብረት ለዘረፋና ውድመት በማጋለጥና ረጅም ጊዜ ከሚኖሩበት አካባቢ በማፈናቀል ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ አስከትለዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ከጥልቅ ሐሳብ የመነጩና ግጭትን በመከላከል ረገድ ትኩረት የሚሹ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን በመሰንዘር አስተዋጽኦ ለማበርከት ያለመ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የለውጥ አመራሩ ሥልጣን ከተቆጣጠረ አንስቶ በወሰዳቸው ዕርምጃዎች መልካም ጅምሮችን አመላክቷል፡፡ ከእነዚህም መሀከል አያሌ የፖለቲካ መሪዎችንና ጋዜጠኞችን ከእስር መፍታት፣ የመገናኛ ብዙኃን በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ፣ ባለፉት ዓመታት በእስረኞች ላይ የደረሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በግልጽ ማሳወቅ፣ የታገዱ ድረ ገጾች የአገር ውስጥ ሥርጭትን መፍቀድ፣ በውጭ አገሮች እስር ቤቶች የታጎሩ ዜጎችን ከእስር ማስፈታት፣ የኢትዮ/ኤርትራ ድንበር ውዝግብን ለመፍታት የሰላም ስምምነት መጀመር፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት የፀረ ሽብር፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበራትን የሚመለከቱ ሕግጋት ማሻሻያ እንቅስቃሴ መጀመር፣ በአሜሪካ ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) ጋር በአገራዊ ጉዳዮችና በተያዘው ለውጥ ላይ ውይይት ማካሄድ፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስና በእስልምና ሃይማኖት መጅሊስ መሪዎች መሀል የነበረው ልዩነት በእርቅ እንዲፈታ፣ በአሸባሪነት የተፈረጁና የትጥቅ ትግል የሚያካሄዱትን ጨምሮ በውጭ አገሮች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ አክቲቪስቶች፣ በአገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል በመሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ጥሪ ማስተላለፍ ዋና ዋናዎች ናቸው፡፡

የተያዘው የመደመርና የይቅርታ ለውጥ በአብዛኛው ኅብረተሰብ (ዳያስፖራውን ጨምሮ) ከፍተኛ ድጋፍ የተቸረውና በአገሪቱ መፃኢ ዕድል አዎንታዊ ተስፋ ያሳደረ ከመሆን አልፎ በጎረቤትና በልማት አጋር አገሮች እንዲሁም፣ በዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅቶች ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይኼም የለውጡ እንቅስቃሴ በአገራችን የፖለቲካ መረጋጋት እንዲሠፍን፣ እንዲሁም የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ልማት ዕውን እንዲሆን ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ ከመገንዘብ የመነጨ ነው፡፡ ከእዚህ በተቃራኒ ለውጡን በሕዝበኝነት የሚነዳና ፋይዳ ቢስ እንደሆነ በመፈረጅ በጥርጣሬ የሚመለከቱና የሚቃወሙ ጥቂት አካላት መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ሆኖም ምንም እንኳ የማይፈለግ ቢሆንም፣ በማንኛውም ለውጥ እንቅስቃሴ ጥርጣሬና ተቃውሞ የሚጠበቅና ሊያጋጥም የሚችል በመሆኑ፣ በለውጡ ትግበራ የተቃዋሚዎችን ሥጋትና ጥርጣሬ ለመቅረፍና በአጋርነት እንዲሠለፉ ለማስቻል በለውጥ አመራሩ በኩል ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ይኼ በእንዲህ እያለ ከለውጡ ዋዜማ አንስቶ በአንዳንድ አካባቢዎች ልዩ ልዩ ግጭቶች በመከሰታቸው ምክንያት፣ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ከፍተኛ ሥጋት ላይ ወድቋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አብዛኛው ሕዝብ በአስከፊ ድህነት በሚጎሳቆልባቸውና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በጎደለባቸው ታዳጊ አገሮች በልዩ ልዩ ምክንያቶች ግጭቶች መከሰታቸው የተለመደ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ በአገራችን ልዩ ልዩ የሕዝብ ፍላጎቶችን ለማስተናገድ የሚያግዝ የዴሞክራሲ ሥርዓት ያለመዳበር ምክንያት በኅብረተሰብ አካላት በኩል ፍላጎትን በአመፅ ለማስፈጸም መንቀሳቀስ እየተዘወተረ መጥቷል፡፡ ከዚህ ሌላ በተያዘው ለውጥ ላይ አብዛኛው ሕዝብ ያሳደረው ተስፋ እንዲመናመን ተቃዋሚዎች ብሶትን በማራገብ በእየ አካባቢው ግጭት እንዲነሳ በፅናት እንደሚንቀሳቀሱ መገመት ይቻላል፡፡ ከለውጡ ዋዜማ አንስቶ በመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ከተሰጣቸው የአካባቢ ግጭቶች መካከል የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች በሚኖር ሕዝብ መሀል በወሰን ምክንያት በተደጋጋሚ የተከሰቱ ግጭቶች፣ በሲዳማ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል (ጨምበላላ) አከባበር በሐዋሳ ከተማ ከሚኖሩ የወላይታ ብሔረሰብ ተወላጆች ጋር የተነሳ ግጭት ያስከተለው ጥቃት፣ በወልቂጤ ከተማ አጎራባች ከሚኖሩ የቀቤና ብሔረሰብ ተወላጆች ጋር የተነሳ ግጭት ያስከተለው ጥቃት፣ በ1976 ዓ.ም. በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በመንግሥት የሠፈራ ፕሮግራም ረዥም ጊዜ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚኖሩ የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች ጋር የተነሳ ግጭት ያደረሰው ጥቃት፣ በኦሮሚያ ክልል በጉጂና በደቡብ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች ክልል በጌዴኦ ብሔረሰቦች አጎራባች አካባቢ በወሰን ምክንያት የተከሰተ ግጭት ያስከተለው ጉዳት፣ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ደገሃቡርና ሌሎች ከተሞች በሚኖሩ የሌሎች ብሔረሰቦች ተወላጆች ላይ የተሰነዘረ ጥቃት፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች ክልል በመስቃንና ማረቆ ቤተ/ጉራጌ ብሔረሰቦች ማኅበረሰብ መካከል በወረዳ ምክር ቤቶች ምርጫ ምክንያት የተከሰተ ግጭት የደረሰው ጥቃት፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ በአሸዋ ሜዳ በተለይ በቡራዩ ከተማ ከጋሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ጋር በተነሳ ግጭት የደረሰ ጥቃት፣ ይኼን ግጭት ተከትሎ በአዲስ አበባና በአርባ ምንጭ ከተሞች የተካሄደ የተቃውሞ ሠልፍን ለመቆጣጠር በሕግ አስከባሪዎች አማካይነት በተወሰደ ዕርምጃ የደረሰ ጉዳት፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ምክንያት በተከሰተ ግጭት በዜጎች ላይ የደረሰ ጥቃት፣ በጋምቤላ ከተማ ወጣቶች የተቃውሞ ሠልፍ ለማካሄድ ሲንቀሳቀሱ በሕግ አስከባሪዎች በተወሰደ ዕርምጃ በዜጎች ላይ የደረሰ ጉዳት፣ እንዲሁም በቅርቡ በድሬዳዋና በሐዋሳ ከተሞች ዓላማውና ማንነታቸው ባልታወቀ አካላት አማካይነት በመኖሪያ ቤቶች ላይ የተደረገ ምልክት በነዋሪዎች ላይ ያሳደረው ሥጋትና ያለመረጋጋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በእነዚህ ግጭቶች መነሻ በተሰነዘረ ጥቃት ምክንያት የብዙ ዜጎች ሕይወት ሕልፈት፣ የአካል ጉዳትና የሥነ ልቡና ቀውስ፣ እንዲሁም ጥረውና ግረው ያፈሩት ንብረት ውድመት ደርሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬአቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ለመኖር ተገደዋል፡፡ ይኼ ሁኔታ ከወዲሁም ዜጎች በነፃነት ለመዘዋወር ንብረት ለማፍራትና በእኩልነት አብሮ ለመኖር እምነትና ዋስትና እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡

የግጭቶች አጠቃላይ ባህሪ

      የግጭቶችን ባህሪ ለመግለጽ በቅድሚያ የእያንዳንዱን ግጭት መንስዔ፣ እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችን በጥልቅ መመርመር የሚሻ በመሆኑ ጽሑፉ ከአጠቃላይ ግንዛቤ በመነሳት በደምሳሳው ለመቃኘት ይሞክራል፡፡ ለግጭቶች መነሻ ማንኛውም ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ቢሆንም፣ በቅድሚያ ፍላጎትን በአመፅና በኃይል ማስተጋባት ሕገወጥ የወንጀል ድርጊት በመሆኑ የሚወገዝ ነው፡፡ ከእዚህ በኋላ ግጭቶች በዜጎች ሕይወት አካልና ሥነ ልቦና ጉዳት ማድረስም ይሁን ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ለውድመት ማጋለጥ አይኖርባቸውም፡፡ በተጨማሪ ግጭቶች አያሌ ንፁኃን ዜጎቻችን ለረዥም ጊዜ ከሚኖሩበት እንዲፈናቀሉ በማድረግ፣ በአገራቸው ውስጥ በነፃነት ለመዘዋወርና አብሮ ለመኖር እምነት እንዳይኖራቸው ማድረስ አይገባቸውም፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች መንስዔዎችን በውል መገንዘብ፣ ውጤታማ ለሆነ የግጭት አፈታት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የተከሰቱ የአካባቢ ግጭቶች መንስዔዎች ፈርጀ ብዙና ውስብስብ በመሆናቸው፣ ከዚህ በታች ለምሳሌ የቀረበውን ማንሳት ይቻላል፡፡ በቅድሚያ በብሔርና በቋንቋ ላይ የተመሠረተው የክልል አደረጃጀት ዜጎች በሕገ መንግሥት የተረጋገጠላቸውና በማንኛውም የአገራችን አካባቢ በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመሥራትና አብሮ የመኖር መብት በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችል የሕግ ጥበቃ ያለመኖር፣ በተለያዩ አካባቢዎች ለደረሰው የዜጎች መጠቃትና መፈናቀል ምክንያት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ድርቅ ያስከተለውን ችግር ለመቋቋም በተነደፈው የሠፈራ መርሐ ግብር አማካይነት ለረጅም ጊዜ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መፈናቀልን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በመቀጠል በተግባር የዋለው የክልል አደረጃጀት የአካባቢው ብሔረሰብን ጥቅምና ፍላጎት ለማረጋገጥ አልቻለም በማለት፣ የሚፈልጉትን የአስተዳደር ዕርከን (ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ) በመጠየቅ በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚከሰቱ ግጭቶች እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ለምሳሌ ያህል በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል የሲዳማ፣ የጉራጌና የሌሎች ብሔረሰቦችን ፍላጎት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በክልል አስተዳደር በኩል እነዚህ ጥያቄዎችን በሕግ አግባብ ማስተናገድና ምላሽ መስጠት አለመቻሉ፣ ኅብረተሰቡ በሕጋዊ አሠራር እምነት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው በከተሞች መስፋፋትና በኢንቨስትመንት ቦታ ፍላጎት ምክንያት ብዙ አርሶ አደሮችን ከእርሻ መሬታቸው በማፈናቀል የሚመነጭ ቅሬታ ነው፡፡ ይኼ በመንግሥታት የካሳ አከፋፈል ሕግና መመርያ የሚፈጸም ቢሆንም፣ የክፍያው መጠን አርሶ አደሩ ኑሮውን በዘላቂ መልክ እንዲመራ የማያስችል ከመሆኑ በላይ ለባሰ ድህነት አጋልጦታል፡፡ ከዚህ በመያያዝ በአገራችን ሊታረስ የሚችል መሬት የነፍስ ወከፍ ድርሻ በየጊዜው እየቀነሰ በአሁኑ ጊዜ 0.15 ሔክታር ያህል ደርሷል፡፡ በእዚህም ምክንያት አብዛኛው አርሶ አደር በአካባቢው የሚካሄድ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በበጎ ስሜት እንዳይመለከት አድርጎታል፡፡ በአራተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የአካባቢ ግጭቶች መንስዔ ከላይ ከተጠቀሱት የተለየ ነው፡፡ እንደ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት መግለጫ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ለውጡን በሚቃወሙ ኃይሎች የተደራጁና የሚመሩ ሲሆን፣ መሠረታዊ ዓላማቸውም የለውጡን እንቅስቃሴ ማደናቀፍ ነው፡፡ በመጨረሻም መንስዔው በውል የታወቀ ባይሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልዩ ልዩ ከፖለቲካ ነፃ በሆኑና ሕዝብ በሚሰበስብባቸው ኩነቶች (የእግር ኳስ ስፖርት ውድድርን ጨምሮ) በሚከሰት ግጭት ምክንያት የዜጎች ሕይወት፣ አካልና ሥነ ልቦና ጉዳት መድረስ አዘውትሮ ይታያል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት መንስዔዎች የሚንፀባረቅ የሕዝብ ፍላጎትንና ቅሬታን በማቀጣጠልና በማባባስ ወደ ግጭት እንዲያመራ ከሚያግዙ ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህም፣

 • የዴሞክራሲ ሥርዓት አለመዳበርና የመልካም አስተዳደር ችግር ቅድሚያ ይይዛል፡፡ ይኼን በመረጃ ለማሳየት፣
 • ዘ ኢኮኖሚስት በሚያጠናቅረው የዴሞክራሲ ቀመር ኢትዮጵያ 129ኛ ደረጃ ከ167 አገሮች የያዘች ሲሆን፣ ይህ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች አማካይ ደረጃ (30ኛ) ጋር ሲነፃፀር እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣
 • የሞኢብራሂም ፋውንዴሽን በሚያዘጋጀው የአፍሪካ መልካም አስተዳደር ቀመር ኢትዮጵያ 36ኛ ደረጃ ከ54 የአፍሪካ አገሮች የያዘች ሲሆን፣ ይኼም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች አማካይ ደረጃ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑ፣
 • በዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በሚዘጋጀው የአገሮች የሙስና ዕይታ ዘገባ መሠረት ኢትዮጵያ 108ኛ ደረጃ ከ176 አገሮች የያዘች መሆኑ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ያሳያል፡፡
 • አመፅና ግጭትን ለመቀስቀስና ለማባባስ የሚያግዙ እንደ ድህነት፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል መጓደል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ዝቅተኛ ደረጃ መሆን ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን በመረጃ ለማሳየት፣
 • በአሁኑ ጊዜ 105 ሚሊዮን ከሚያህለው የአገራችን ሕዝብ መሀል በቀን ከ1.90 ዶላር በታች በሚሆን ገቢ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የሕዝብ መጠን 26.7 በመቶ መሆን፣
 • ከጠቅላላ ሕዝብ 28.8 በመቶ የሚያህለው በከፍተኛ ደረጃ ለተመጣጠነ ምግብ ዕጦት የተጋለጠ መሆን፣
 • ከጠቅላላ ሕዝብ 56 በመቶ የሚያህለው በሥራ ዕድሜ (ከ15-64) የሚገኝ ቢሆንም የወጣቶች (ከ15-24 ዕድሜ) ሥራ አጥነት ምጣኔ 25.2 በመቶ መሆን፣
 • ከጠቅላላ ሕዝብ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘው 10% ከጠቅላላ ገቢ ያለው ድርሻ 2.6 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘው 10 በመቶ ከጠቅላላ ገቢ ያለው ድርሻ 31.4 በመቶ መሆን የችግሩን አስከፊነት ያመለክታሉ፡፡
 • የአካባቢ አስተዳደር ተቋማት ኃላፊነታቸውን በብቃት ስለመወጣታቸው በሕዝብ ያለው መተማመን በየጊዜው መሸርሸር፣
 • በአካባቢ አስተዳደር በኩል ለግጭትና ለቀውስ መንስዔ የሆኑ ፍላጎቶችን በቅድሚያ በመለየት (ቅድመ ዝግጅት) ያለመኖር፣ ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ረገድ ቸልተኝነት ማሳየትና የተቋማዊ አቅም ዝቅተኛ መሆን፣
 • ቀደም ሲል የፖለቲካ ለውጥ ለማስቻል የሕዝብ ተቃውሞን በማደራጀትና በመምራት አስተዋጽኦ ያበረከቱ የወጣቶች ስብስቦች (ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ . . . ) አሁንም ልዩ ልዩ ፍላጎትን በአመፅ ለመምራት መንቀሳቀስ፣
 • አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አክቲቪስቶች ኃላፊነት በጎደለው ስሜት ሕዝብን ወደ አመፅና ግጭት የሚያመራ ቅስቀሳ ማካሄድ፣
 • በመጨረሻም የማኅበረሰብ (የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች) ግጭት እንዳይከሰት፣ እንዳይባባስና ጉዳት እንዳያስከትል የሚያግዝ የሞራል እሴትና ሥነ ምግባር በማስፈን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መሆን የመሳሰሉ ናቸው፡፡

እዚህ ላይ ግጭቶችም ሆኑ ከላይ የተጠቀሱ መንስዔዎች ቀደም ሲል በአገራችን መኖራቸው አይካድም፡፡ ሆኖም ከለውጡ ማግሥት አንስቶ የተከሰቱ ግጭቶች በባህሪና በድግግሞሽ ከቀድሞው የተለዩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእዚህ ረገድ ሁኔታዎችን ይበልጥ ካባባሱ ምክንያቶች መሀከል ቀደም ሲል ተቃውሞን በኃይል ዕርምጃ ለመቆጣጠር የተፈጸመ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የግጭት ዑደትን ይበልጥ ማጠናከሩ፣ በለውጡ በተከፈተው የነፃነት ዕድል በመንቀሳቀስ በኩል በማኅበረሰብ ውስጥ መብትና ግዴታዎችን አስመልክቶ ያለው የግንዛቤ ጉድለት፣ በየጊዜው እያደገ የመጣው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ወጣቶች ሥራ አጥነት፣ እንዲሁም በመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአገራችን ከ51 ሚሊዮን በላይ በሚገመተው የሞባይል ቴሌፎን ደንበኛ አማካይነት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ያሳደረው ተፅዕኖ ዋና ዋናዎች ናቸው፡፡

በግጭት ወቅት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች

ከላይ እንደተመለከትነው የአካባቢ አስተዳደር ተቋማት ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ስለመቻላቸው በኅብረተሰብ ዘንድ ያለው እምነት ዝቅተኛ ደረጃ ደርሷል፡፡ በተለይ ደግሞ ለግጭትና ማኅበራዊ ቀውስ መንስዔ የሆኑ ፍላጎቶችን በመለየት ቅድመ ዝግጅት ያለመኖር፣ ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በኩል ቸልተኝነት ማሳየት፣ እንዲሁም የተቋማዊ አቅም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆን አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ወደ ፊት ለሚከሰቱ ግጭቶች ውጤታማ ምላሽ መስጠት የለውጡን እንቅስቃሴ በተረጋጋ ሒደት በመምራትና የአገራችን መፃኢ ዕድል ከፍተኛ ፋይዳ የሚኖረው በመሆኑ፣ እስካሁን ድረስ በግጭት ወቅት የተወሰዱ ዕርምጃዎችን አስመልክቶ ጽሑፉ ከዚህ በታች በአጭር ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡ የመጀመሪያው ከተለመደው በተለየ ግጭቶች በሚከሰቱ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን በይፋ ማሳወቅ ነው፡፡ ይህ ግልጽነት በቅድሚያ ሕገወጥ ድርጊትንና ፈጻሚ አካላትን ለማውገዝ፣ በመቀጠል ደግሞ በሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም የግጭቱን መንስዔና ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን፣ ያስከተለውን ጉዳትና የተወሰዱ ዕርምጃዎችን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፍ ዘገባና መግለጫ ትክክለኛና ሚዛናዊ መሆን፣ እንዲሁም ሁኔታውን ይበልጥ ከማባባስ በመቆጠብ በግጭት ወቅት የሙያ ሥነ ምግባር በመመራት መከናወን አለበት፡፡ በድኅረ ግጭት ወቅት መግለጫን ተከትሎ በመንግሥት ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በኩል ድርጊቱንና ያስከተለውን ጉዳት ማውገዝ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ በማያያዝ “ግጭቱና በዜጎች ላይ ያስከተለው ጥቃት በፍፁም ይኼንን ማኅበረሰብን አይወክልም”    የሚሰኝ መግለጫ ይደመጣል፡፡ በእርግጥ ይህ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ሆኖም በብዙ አካባቢዎች የደረሰውን ግጭትና በንፁኃን ዜጎች ላይ ያስከተለውን አስከፊ ጉዳት ማኅበረሰቡ ፍፁም ማስወገድ ባይችል እንኳ፣ በተወሰነ ደረጃ በመቀነስ በኩል የነበረው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መሆኑ በማኅበረሰባችን ላይ የተንሰራፋ የሞራል እሴትና ሥነ ምግባር መቀጨጭ ዓይነተኛ መገለጫ ከመሆን አልፎ የተጎዱ ዜጎችን የሚያፅናና አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደ የተቃውሞ ሠልፍ በስሜት ተገፋፍተው ጉዳት ለማድረስ የቃጡ ወጣቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎች በአካባቢው ባህል መሠረት በመማፀን መቆጣጠር በአርዓያነት የሚታይ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግጭቱንና ያስከተለውን ጉዳት አስመልክቶ አስቸኳይ ምርመራ እንደሚካሄድና በተጠያቂዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በመንግሥት ኃላፊዎች የሚተላለፍ መግለጫ የተለመደ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከሕዝብ ኃላፊነት የሞራል ልዕልና አንፃር የአካባቢ አመራሮችን ከኃላፊነት ማሰናበት፣ የወንጀል ድርጊትን በመከላከል ቸልተኝነት ያሳዩትንና ኃላፊነታቸው ያልተወጡትን ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ እንዲሁም በተፈጸመው ወንጀል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች ላይ ክስ መመሥረት እንደ መልካም ዕርምጃ ይቆጠራል፡፡

በድኅረ ግጭት ወቅት የሚወሰድ ሌላ ዕርምጃ በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በመንግሥት፣ በግል ድርጅቶችና በኅብረተሰቡ ትብብር የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማሰባሰብና ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ በግጭቱ ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረግ ጥረት ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ረገድ በቅድሚያ በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ፈቃደኝነት የሚሻ ቢሆንም ሕጋዊነትን ለማረጋገጥ፣ በንፅፅር ሲታይ በዝቅተኛ ወጪና በአጭር ጊዜ ለማከናወንና የተጎዱ ዜጎች ላይ እምብዛም ማኅበራዊ ቀውስ ሳይደርስ በዘላቂነት ለማቋቋም እንዲቻል፣ የመልሶ ማቋቋም ተግባር በሚኖሩበት አካባቢ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ በቅድሚያ በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የዕለት ተዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ዕርዳታ በማቅረብ ሕይወታቸውን በመታደግ፣ በመቀጠል ደግሞ በዚህ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ዘላቂ ኑሮ እንዲመሩ በሚሰጥ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ ጉዳዩ የሚመለከተው የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን የተቀናጀ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት፡፡

በግጭት ማስወገድና አፈታት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች

አስከፊ ድህነት በተንሰራፋባቸውና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባልተጎናፀፉ ታዳጊ አገሮች እንደሚታየው ሁሉ፣ በኢትዮጵያም በልዩ ልዩ መንስዔዎች የአካባቢ ግጭቶች መከሰት የሚያስገርም አይደለም፡፡ ግጭቶች በማኅበረሰብ ውስጥ በወቅቱ ከሚንፀባረቅና በየጊዜው ከሚፈጠር ፍላጎት የሚመነጩ በመሆናቸው እነዚህን ለማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት፣ የሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ በአመፅና ግጭት እንዳይስተጋባና በዜጎች ላይ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳያስከትል የሚያግዝ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥልት መንደፍ፣ ከዚህ አልፎ ግጭት በሚከሰትበት ጊዜ በዜጎች ሕይወት፣ አካልና ሥነ ልቦና ላይ ጉዳትና ማኅበራዊ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት በአካባቢ አስተዳደር በኩል በፍጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ዕርምጃ በመውሰድ፣ አገራችን ለተያያዘችው የለውጥ እንቅስቃሴ ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡

ከላይ ከቀረበው ማብራሪያ በመነሳት ከዚህ በታች የተመለከቱ አሥራ ሁለት የመፍትሔ ዕርጃዎች በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆኑ የጽሑፉ አዘጋጅ አበክሮ ያሳስባል፡፡ እነዚህም፣

 1. የለውጡ እንቅስቃሴ ወደ ነፃና ፍትሐዊ የፖለቲካ ምርጫ እንዲሸጋገር በመንግሥት፣ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በፖለቲካ አክቲቪስቶችና በመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች መካከል አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የጋራ መግባባት መኖር፣
 2. በግጭት ወቅት በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፍ መግለጫና መረጃ ትክክለኛ፣ ሚዛናዊና ሁኔታው እንዳይባባስ በጥንቃቄና በኃላፊነት መንፈስ የሙያ ሥነ ምግባርን በመከተል መከናወን፣
 3. የችግር ትንተና መደበኛ ዘዴ በመከተል ከማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ግልጽ ውይይት በማካሄድ ለግጭት መንስዔ የሆኑና የሚያባብሱ ፍላጎቶችን (ጥያቄዎችን) በቅደም ተከተል በመለየት የመፍትሔ ዕርምጃ መውሰድ፣
 4. በአገራችን ከተተገበረው ቋንቋ (ብሔር) ላይ ያተኮረ የክልል አስተዳደር አደረጃጀት ከማኅበረሰብ የሚቀርብ የአስተዳደር አደረጃጀት ዕርከን (ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ) እንዲሁም በአጎራባች አካባቢዎች መሀከል የሚነሳ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ሐሳብ መሠረት በገለልተኛ ኮሚሽን ጥናትና ምክረ ሐሳብ በመመርኮዝ ዘላቂ የመፍትሔ ዕርምጃ መተግበር፣
 5. በከተሞች መስፋፋትና ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከአርሶ አደሮች ለሚወሰድ የእርሻ ቦታ ተመጣጣኝ ካሳ መክፈል የሚያስችል የእርሻ መሬት ካሳ አከፋፈል ሕግ ማሻሻል፣ እንዲሁም ከእርሻ መሬታቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ዘላቂ ኑሮ መምራት እንዲችሉ አስፈላጊ ድጋፍ መስጠት፣
 6. የአካባቢ አመራር ኃላፊዎችን ምደባ የሙያ ብቃትና የአመራር ክህሎት መመዘኛ በመከተል ማካሄድ፣
 7. በአካባቢ አስተዳደር ዕርከን ግጭትን ለማስወገድና ለመፍታት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት ማመቻቸትና የተቀናጀ (ተቋም፣ የአሠራር ዘዴ፣ የሰው ኃይል) የአቅም ግንባታ ድጋፍ መስጠት፡፡ የእዚህ ተቋማዊ አቅም ግንባታ ትኩረት ጉዳዮች፣
 • የቅድመ ማስጠንቀቂያ በአካባቢ ማኅበረሰብ የግጭት መንስዔ የሆኑ ችግሮችን በመተንተን በአሳሳቢነት ደረጃ በቅደም ተከተል መለየት፣
 • የግጭት መንስዔዎችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት መግባባት ላይ መድረስ፣
 • ግጭትን በመቆጣጠርና ሕግን በማስከበር በዜጎች ሕይወት፣ አካል፣ ሥነ ልቦናና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በፍጥነት መንቀሳቀስ፣
 1. ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን እንቅስቃሴ ከአካባቢ አስተዳደር ጎን ለጎን ኅብረተሰቡን ንቁና የተደራጀ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
 2. በማኅበረሰብ ተቀባይነት ያለውና ተደራሽ የሆነ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ለመጠቀም የሚያስችል አሠራር ማመቻቸት፣
 3. የማኅበረሰብ መሪዎች (የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች) መልካም የሞራል እሴትንና በጎ ሥነ ምግባርን በማጎልበትና ግጭትን በማስወገድ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
 4. የወጣቶች ስብስቦች (ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ . . . ) በመደበኛ አደረጃጀት በመካተት በነፃነት የአባላትንና የአካባቢ ፍላጎቶችን በሕጋዊ መንገድ ለማስተጋባት እንዲችሉ ድጋፍ መስጠትና፣
 5. እንደ አስፈላጊነቱ በድህረ ግጭት ወቅት በገለልተኛ አካል የመመርመር አሠራር መከተል በዚህ ረገድ፣
 • የሚሰየመው የምርመራ ቡድን ከፖለቲካ ተፅዕኖ በነፃነት የሚንቀሳቀስና አስፈላጊ የሙያ ስብጥር ያላቸው አባላትን ያካተተ መሆን፣
 • ዓላማው በምርመራው ግኝት ላይ በመመርኮዝ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ፣ ተግባር ላይ የዋሉ ፖሊሲዎችንና መመርያዎችን ለማሻሻል፣ የአቅም ግንባታ ዕቅድ ለመንደፍና ለማስፈጸም፣ እንዲሁም ጠቃሚ ልምድና ተሞክሮ ለመቀመርና ለማስፋፋት የሚያግዝ ግብረ መልስ በማጠናቀር አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፡፡

የጽሑፉን መልዕክት ለማጠቃለል ከረጅም ጊዜ ወዲህ በአገራችን የተጀመረው ለውጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባትና መልካም አስተዳደር በማስፈን ረገድ ብሩህ ተስፋ ያሳደረና ከፍተኛ ድጋፍ የተቸረው ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ከለውጡ ዋዜማ አንስቶ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች በመከሰታቸው በዜጎች ሕይወት፣ አካልና ሥነ ልቦና እንዲሁም ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተላቸው በተጨማሪ ከሚኖሩበት አካባቢ በማፈናቀል ማኅበራዊ ቀውስ አድርሰዋል፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ የለውጥ አመራር ኃላፊዎችን ትኩረት ከመረበሽ ባሻገር፣ አብዛኛው ሕዝብ በተያዘው ለውጥ እንቅስቃሴ የሰነቀውን ተስፋ በመሸርሸር አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ የሚስተዋለውን ሥጋት ለመቅረፍ እንዲቻል፣ ከእዚህ በላይ የቀረቡ የመፍትሔ ዕርምጃዎች በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆኑ የጽሑፉ አዘጋጅ አበክሮ ያስገነዝባል፡፡

      ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...