Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርማጠንጠኛ

ማጠንጠኛ

ቀን:

‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል……››

በአስፋው ትሁኔ

መኖርን የመሰለ ነገር የለም ሲባል እንዲያው ዘበት ይመስላል፡፡ መኖር ደግ ነው፡፡ ደጉንም ክፉውንም፣ ወጪውንም ወራጁንም በየፈርቁ ያሳያል፡፡ መኖር የእውነትም የቀጠሮና ጊዜ መጠበቂያ ነው፡፡ ‹እውነትና ንጋት እያደር ይገለጣል› እንዲሉ፡፡ አዋቂ፣ ደንቆሮ፣ ቅን፣ ተንኮለኛ፣ ሀቀኛ፣ ሸፍጠኛ፣ እውነተኛ፣ ዓባይ ሆኖ በጊዜውና በባለ ጊዜው እየተደቆሰ ይኖርና ጊዜው በሌላኛው የግዱን ቦታ ሲለቅለት የተገላቢጦሹ እንደ ነበር ይታወቅለታል፡፡ ይኼንን ለማየት ዕድሜ የሰጠው ባለ እውነት የታደለ ነው፡፡ ‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል ድሃ ሞኝ ነው ሞቱን ይመኛል፤›› የሚሉት፡፡

አንድ አምስት ዓመታት ያህል ወደ ኋላ ልመልሳችሁና ኦሮሚያን በጋራ እንመልከት፡፡ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ቀስ በቀስ እየበቀሉና እየረዘሙ ደግሞም እየበዙ እንደሚሄዱ የኦክቶፐስ ቅርንጫፎች ሙስናና አድርባይነት፣ ክህደትና ፀረ ኦሮሞ ተላላኪነት እየተበራከተ የሚሄዱበት ነበር፡፡ ከዚያን ወዲህ አድርባዩና ፀረ ኦሮሞ ተላላኪው ቡድን የመጨረሻ ድል የተጎናጸፈ የመሰለበትም ወቅት ነበር፡፡

በተለያዩ ጊዚያት በግልጽም በሥውርም እያመለጡ ይወጡ የጀመሩት የሕዝብ ብሶቶች ከላይ እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅሮች ዘንድ የማላገጥ ያህል ተደመጡ እንጂ፣ ውክልና የሰጣቸው የሥልጣኑ ባለቤት ሕዝብ የምሩን ተቸግሮ ነው ብሎ ትኩረት ቢጤ የሰጠው አልነበረም፡፡ የመብት ጥያቄውን እየጠነከረ በሄደ መጠን እንደ ድፍረት ተወስዶ እልህ መያያዝና ልክ ወደ ማስገባት የጉልበት አቅጣጫ በመዞር ሕዝቡን ወደ ማሰር፣ መደብደብና መፍጀት ተገባ፡፡ ሰላምን በኃይል በመመንዘር የጀገነ ትዕቢትና ንቀት ተተገበረ፡፡

ሕዝባዊ ንቅናቄው በኋላም የነጠረ ሕዝባዊ አመፅ እንጂ ቀልድ አለመሆኑ ታውቆ ጉዳዩ እየመረረ ሲሄድ ጀግኖች ተርበተበቱ፣ በፍርኃት ተንዘፈዘፉ፣ ራዱ፡፡ አንደበተ ርቱዓን ተጎላደፉ፣ ተንተባተቡ፣ ፈጣኖች ቀዘዙ፣ ሠነፉ፡፡ ትግሉ አይቀሬ ሆኖ ለውጥ መምጣቱ ሲረጋገጥ ተባች ልሂቃን ሁሉም ነገር ተምታታባቸው፡፡ ዕውቀታቸው ትንሳዔ በመሆኑ ውሸት አዋረዳቸው፡፡ የቅጥፈት ብዕራቸው ነጠበባቸው፡፡ ዘመንም ከዳቸው፡፡ ዕውቀታቸው አለማወቅ፣ ብርታታቸው ርዕድና ቁመናቸው ፍርክርክ ሆኖ ቀን መሸባቸው፡፡

መኖር ደግ ነው፡፡ ‹ንገረው ንገረው…› የተባለው እውነት ሆነ ፡፡ ተነገረ ተነገረ እምቢ ተባለ፡፡ ተመከረ ተዘከረ ሰሚ ሲጠፋ ቄሮ መጣ የሚያጣፋ፡፡ ይኼንን ሁሉ ሒደት ዋ!  እተባለ ሲነገረው የነበረ መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ እያለ በአመፃ በመኖሩ እየመረረው በሰፍነግ ሞልቶ ውርደትን ጨለጠ፡፡ የግዱን!

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንዴት አድርጎ ነበር በመንግሥት ላይ የመጣውን አደጋ ያስጠነቀቀው? በነፃ ግን አይደለም፡፡ መስዋዕትነት ከፍሎበት፣ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ በሆነ የሰቆቃ ኑሮ ለመኖር ተገዶ፣ የዜግነት መብትና ክብሩን ገብሮ፣ ከመኖሪያ ቤቱ በፖለቲካ ጫናና በፀጥታ ኃይል ተባርሮና ከከተማ ወደ ባላገር ተሰዶ እየኖረም ያለመታከት፡፡ ወንጀል ሳይሠራ ተወንጅሎ ፍትሕ ተነፍጎ እየታሰረና እየተፈታ የኖረው ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› ብሎ፡፡ እልፍን ማየት ላይ መድረስ መታደል ነው፡፡ የሞራል ካሳ፣ የኅሊና ቁስል ማስታገሻ ነው፡፡

 

እና የያኔው ማውገዣ ዛሬ የትግል አቅጣጫ ማስያዣና መሞገሻ፣ ያኔ እኩይ ሐሳብ የተባለው ዛሬ የመድኅን ጥሪ፣ ያኔ ኩሸት ተብሎ ለመሰደድ ምክንያት የተደረገው ዛሬ ከወርቅ የነጠረ እውነትና የዕውቀት ድልብ ሆኖ ሲደሰኮር ቀልብ ሲስብ፣ አልፎ ተርፎ ጠላት ሲለበልብ ደርሶ ማየት ምንኛ መታደል ነው! ትዝብቱ ግን የትናንቱ አውጋዥ አሳዳጅ ዛሬ ደግሞ የለውጡ አዛዥ አራማጅ፡፡ ሌላ ‹እልፍ ቢሉ እልፍ ይገኛል› ሊያስፈልገን ይሆን?

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙትን ሕግ አልባ ድርጊቶች ለመከላከል ያስችል ዘንድ በተለያዩ ጊዚያት የሰላ ሂስ በማቅረብ ይታወቃል፡፡ ለአብነትም ያህል ‹‹የጎምቱ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ስላቅ!!!›› በሚል ርዕስ ዲሪርሳ ኢላላ ዱጋሳ በሚል የብዕር ስም መጋቢት 7 ቀን 2008 ዓ.ም.  በሪፖርተር ጋዜጣ የአማርኛው ዕትም ላይ ‹‹….  ዘመናትን ያልተሻገረ፣ የትውልድ መተካካትን ያላስተናገደና ውጤቶቹ በሙሉም ሆነ ከሞላ ጎደል በአሁኑ ሕይወታችንና ….  ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ የሚችሉ እስከሆኑ ድረስ ታሪክ ከሚለው ተርታ ሊሠለፉ አይችሉም፡፡ በአንድ የተወሰነ ዘመን እየተመላለሱ የተፈጸሙ፣….ክንውኖችና ‹‹የሞኝ ለቅሶ—-›› ዓይነት እንጂ …..በተለይም የፖለቲካ ክስተቶችና ተመሳሳይ ክንውኖች ከሆኑ ስላቅ ዓይነት ዝባዝንኬ ድርጊቶች ይሆናሉ፡፡

‹‹ምክንያቱም እንደ ሰው ልጆች፣…………አምናና ካቻምና ያሳለፍናቸውን….  ዛሬም የምንነከርባቸው ከሆነ፣ ፈጽመን ባሳለፍናቸው ስህተቶች ውስጥ አሁንም የምንዘፈዘፍባቸው ከሆነ መማርም ማስተማርም ያልቻልን እንትኖች ሆነናልና ማለት ነው፤”  በማለት ግብዝነትን ተጠይፎባቸዋል፡፡

እንደ መሪዎች ያለባቸው ኃላፊነት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ሲኖርባቸው፣ በተለይ ዕውቀትንና የሰው ኃይልን ከፖለቲካ አመለካከት ጋር በማያያዝ ማምከናቸውን በተመለከተ ‹‹የእኛዎቹ ፖለቲከኞች›› የፖለቲካ አመለካከት (ቅኝት) ልዩነትን እንደ ፀጋ የሚመለከቱ ሆነው ለመገኘት አልታደሉም፡፡ ይልቁንም ከያኔው ከወርቃማው የለጋነት የትግል ዘመናቸው ጀምረው እንኳንስ የአመለካከት ልዩነትን በአግባቡና በሠለጠነ አኳኋን ማስተናገድ፣ በቃላት አጠቃቀም ሳይቀር በመለያየት (ወዛደር፣ ላብ አደር የመሳሰሉትን ያስታውሷል) ጦር የመሞሻለቅንና አፈሙዝ የመደጋገንን የመሰለ ጎታታ ተሞክሮ ተግተው ያደጉ ነበሩ፤” ብሏቸዋል፡፡

የትምክህትና የእኔ ብቻ ዕብሪተኝነታቸውን በተመለከተ የፖለቲካ ክርክሩ ፖለቲካ ‹‹በሞተ ፈረስ መጋለብ!›› በሚል ርዕስ አባ መጋል በሚል የብዕር ስም በዚሁ ጋዜጣ ቅጽ15 ቁ.27/1037 መጋቢት 29 ቀን 2002 ዓ.ም. ሲጽፍ፣

‹‹የምርጫ 2002 ሒደት እየቀጠለ ነው፡፡ አንደኛው መገለጫው ተፎካካሪዎች (ተቃዋሚዎች የሚለውን አጠራር መጠቀም ስላልተፈለገ ነው) ……በዛሬው ዳሰሳውም ላይ በአራተኛው ዙር ተፎካካሪዎች የተመላለሱበትን ሳይሆን፣ በመጀመርያው ክፍል ያላቸውን የትምህርት ፖሊሲ ለሕዝብ እንዲገልጹ የተደረገበትን ብቻ ለመዳሰስ ይሞክራል …. የጽሑፉ አቅራቢ ግን ካሁን ወዲያ ተፎካካሪዎች ሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ እየደገፉ የሚሄዱበት…. …የመጀመርያው ክፍል ተፎካካሪዎች ዕድል የተሰጣቸው በዙሩ የመከራከሪያ ርዕስ ላይ ያላቸውን አማራጭ ፖሊሲ እንዲያቀርቡ ነበር….  ተፎካካሪዎቹ በእርግጥ የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ሳይሆን ያቀረቡት አንዳንድ የአፈጻጸም ለውጦችን እናደርጋለን የሚል ሐሳብ ነው፤›› ብሎ ነበር፡፡ ጸሐፊው የዛሬ አሥርት ግድም እነሱ ተቃዋሚ ሲሉ እሱ ተፎካካሪ ብሎ በጠላትነት ተፈርጆ፣ ውግዘት ምሱ ሆኖ የቅጣት ዓይነቶች ከመኖሪያ ቤት እስከ ማስለቀቅ ድረስ ሲፈጸምበት ከርሞ ዛሬ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተፎካካሪዎች ብለው ባደባባይ መጥራት ችለዋል፡፡ ድንቅም ተብሏል፡፡ ለካንስ ቀድሞ ማወቅ ወንጀል ነበር እነሱ ቀድመው ካላወቁ?

 

እነኚህ ሰዎች በተለይም ‹‹ቁልፍ ቁልፎቹ የዛሬና የትናንት ፖለቲከኞች ሳይሆኑ የዚያ የወርቃማው የፖለቲካ ዘመንና ትውልድ ፈርጦች ነበሩ፡፡ ……የፖለቲካ መግቢያ መውጫ ሽንቁር ጠንቅቆ የገባቸው ስለሆኑ የተጨቆነ የተገፋ ሕዝብ ምን ስሜት እንደሚሰማው፣ ያመረረ የተከፋ ሕዝብ ምንም ከማድረግ እንደማይመለስ ለእነሱ መንገር ለቀባሪው ከማርዳት ይቆጠራል፤›› ይልና የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከፍተኞቹ የወቅቱ የፖለቲካ መሪዎች በትዕቢትና በሕዝብ ንቀት መወጠራቸውን “እነኚህኞቹ የእኛዎቹ ጎምቱ ፖለቲከኞች …… ያኔ ክቡር ዓላማ ያስጨበጣቸው ብሩህ አዕምሯቸው፣ የበረሃ ንዳድ ረሃብና መስዋዕትነትን ያስመረጣቸው ንፁህ ኅሊናቸው በዕድሜ ብዛት አሊያም በተመቻቸ ኑሮ ተለውጧል ማለት የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ከሆነ በወርቃማ ቀለም የጻፉትን ታሪክ፣ በሕይወት ቤዛነትና በደም ቀለም ያሳመሩትን ግብረ ሰብዕነታቸውን በጥላሸት ሲለቀለቁት ማየትን ያህል አሳፋሪ ክስተትም አይኖርም፤” ብሎ የዘነጉትን ሰብዕናቸውን መኮርኮር ሞክሮ ነበር፡፡ ‹‹ያን የሚያክል የሕዝብ የድጋፍ ማዕበል በሁለት አሥርታት ውስጥ ብቻ በብርሃን ፍጥነት እየመነመነ ከዓይናቸው ሥር ሲሸሽ፣ የዓላማቸው ዓምድ እንደ ዘበት እየተናደ ሲሄድና ፍርስራሽ ብቻ የመሆን ምልክት ሲያሳያቸው፣ እየሌሉ አለን አለን ማለት ስላቅ ከመሆን ውጪ ሌላ ምን ሊሆን? ቢሆንም……እንዴትስ? ለምንስ? ቢባል አጭሩ መልስ የተፉትን መልሰው ስለዋጡ፣ ለስግብግብነት አጎብድደው የሕዝብ ተዓማኒነት ስለከዳቸው፣ አገርን አሳንሰውና ሕዝብን ንቀው ራሳቸውን አልቀው ስለተገኙ ይሆናል፤›› ሲል ገልጿቸዋል፡፡

የፖለቲካ ባህሪያቸውን እንደሚከተለው አስፍሯል “እነኚህ ባዮች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመገንባትን ኃላፊነት የመሸከም አቅም፣ ፍላጎትና ዓላማ አላቸው ወይ?  የሚለው ነው፡፡ ምላሹ አሉታዊ ነው፡፡ ጎምቱዎቻችን ከሁሉም በላይ አቅምና ፍላጎቱ የላቸውም፡፡ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንድ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መለኪያው የሦስቱ የመንግሥት ተቋማት ዓምዶች (ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ አካላት) በየራሳቸው መቆም ራሳቸውን ችለው የመንቀሳቀስና አንዱ ሌላኛውን የመቆጣጠር አግባብ መኖር ነው፡፡ ይህ እውነታ ከሌለ የሕግ የበላይነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚባሉ የዴሞክራሲ እሴቶች ስማቸውን እንኳ ማንሳት ለስላቅ እንጂ ለእርምት አይደለም፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ ሁሉም የመንግሥት መዋቅር ኢሕአዴግ ሆኖ ‘አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ’ ዓይነት ነገር ነው፡፡ ለሥርዓቱ ጭራሽ መበስበስ ዓይነተኛው ሰበብ ይህ ሲሆን ውጤቱ የቁልቁል መወርወር ጉዞ ነው፡፡”

የአመፁ መነሻ በኦሮሚያ ውስጥ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተሳቦ ሕገ መንግሥትን የተንተራሰ የፊንፊኔ ጥያቄን በተመለከተ፣ ‹‹ተወደደም ተጠላ  ‘የእኛ የእኛ ነው የእናንተም የእኛ ነው’ ማለት ካልሆነ በስተቀር ‘አዲስ አበባ’ የኦሮሞ ሕዝብ (የኦሮሚያ ሕዝብ ማለት አይደለም) መሬት ነው፡፡ ……ልዩ ጥቅም ሲባል………   በ’አዲስ አበባ’ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ዘርፍ (ምክር ቤት) ውስጥ በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩትን የኦሮሞ ተወላጆች ሳይሆኑ የኦሮሚያ ነዋሪ ኦሮሞዎች ቀጥተኛ ወኪሎች ስንት መቀመጫ በቋሚነት ይዘዋል? ‘አዲስ አበባ’ በየዓመቱ ከምታገኘው የተለያዩ ገቢዎች ምን ያህሉን ለኦሮሚያ ታስገባለች? ………የክልልና የአገሪቱ መዲና፣ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ ሆና ተጠሪነተቷ ለኦሮሚያ ክልል ቢሆን ምን ተዓምርነት አለው? ‘የእኛ የእኛ ነው የእናንተም የእኛ ነው’ ማለት ካልሆነ በሰተቀር፡፡ ስላቁ ባልኖረና በፊንፊኔ ሰበብ ተቀጣጥሎ የማይጠፋው እሳት ሁላችንንም ባልፈጀን፤”  የማስጠንቀቂያ ደወል ደውሎ ነበር አሁንም ድረስ የሚያቃጭል፡፡

የካቲት 23 ቀን 2002 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በስቱዲዮው የቀረፀውን ፌዴራሊዝምና ያልተማከለ ሥርዓት በሚል ርዕስ ላይ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካሄዱትን ክርክር ሲገመግም፣ እጅግ አደገኛ ግን ሰላማዊ በሆነ ዘይቤ ኢትዮጵያዊነትን እያራመደ ያለው ኢሕአዴግ ነው በማለት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በሪፖርተር ቅ15፣ ቁ 25/1030 መጋቢት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. አባ መጋል አሰፋው በሚል ስም ‹‹የፖለቲካ ክርክሩ ፖለቲካ አልሸሹም ዞር አሉ›› በሚል ርዕስ ኢሕአዴግን ወንጅሎታል፡፡ ሚሊኒየሙ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ተብሎ ነው የሚታወቀው …ታዲያን ይኼ የዘመን አቆጣጠር ለኦሮሞው፣ ለሱማሌው፣ ለሲዳማው፣ ለሐዲያው፣ ለኩሎው፣ ለደራሳው፣ ለመዠንገሩ፣ ወዘተ ለሙስሊሙ፣ ለዋቄፋታው፣ ወዘተ ምኑም አይደለም…..

……ሕገ መንግሥቱ በፈቀደው አግባብ ዜጎች በነቂስ ወጥተው በምን ዓይነት የአስተዳደር ዘይቤ እንተዳደር፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መስተጋብራችን በምን ላይ የተመሠረተ ይሁን ብለው ዕጣ ፈንታቸውን ከወሰኑ የሚያከራክር፣ የሚያታግልና የሚያናቁር ጉዳይ  በዚህ ዙሪያ አይኖርም፡፡ የሕዝብን ፍላጎትና ውሳኔ ከመቀበል በስተቀር፡፡ በአገር መበታተንና መፈራረስ ሥጋት እንቅልፍ ለራቃቸው ወገኖችም ሆነ የመገንጠል ፍቅር ለሚያኳትናቸው ክፍሎች እረፍት የሚሰጥ መፍትሔ ይህና ይኼው ብቻ ነው፡፡ ኢሕአዴግንም ከመወንጀልና ከመብጠልተል የሚያሽረው መፍትሔ ይህና ይኼው ብቻ ነው፡፡ ‹‹Nagaatti!!››

ይኼው ጽሑፍ አቅራቢ ‹‹ጉልበቴ በርታ በርታ›› በሚል ርዕስ                              አስፋው በሚል ስም ሰኔ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ …….ከ1987 ዓ.ም. ወዲህ ኦሕዴድ በፈታኝ ሰላማዊ ትግል ውስጥ ሲዳክር….. ሰው በፈጣን ዕርምጃ መጓዝ ሳይሆን፣ ሲያስነክሰው…….ኦሕዴድ በሕዝብ ውስጥ የተከለው የዴሞክራሲ ዓምድ ሕዝቡ ለመብቱ ተሟጋች እንዲሆን አስችሎት… መንግሥት ደግሞ የሥልጣኑ ምንጭና ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ምላሽ ሰጪ መሆኑን ዛሬ ድረስ ቆይቶ ከማየት የበለጠ መታደል አይኖርም፤›› ይላል፡፡ ቀጥሎም…“የኦሮሚያ መንግሥት ሲመሠረት የተፈለገው የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ቱታ ከኒሳ ባንድ ላይ ተምሞ በአንድ አፍ በአንድ ልብ መብቱን ማስከበር መቻሉ ላይ ተደርሶ፣ ………ደግሞም የዚህን ሕዝብ ውክልና የተቀበለው መንግሥት የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ወደ ተግባራዊ ምላሽ መስጠቱ ዘመን ላይ በሕይወት ደርሼ ማየቴ መንግሥቱን በመመሥረት……. የግንባር አጥንት መሆኔን ወደድኩት፡፡ የያኔ ሥራዬ በሕዝብና በታሪክ ፊት እንዳላስኮነነኝ ተገነዘብኩ፡፡ የኦሮሚያን መንግሥት ለማቋቋም መዳከሬን እሰየሁ አልኩት፡፡ ይኼንን ሳያዩ የተሰውትን የትግል ጓዶች አከበርኩ፤” በማለት መንግሥት እያሳየ ያለውን የተስፋ ጭላንጭል ያወድሳል፡፡

በዚሁ ይቀጥልና “የኦሮሚያ መንግሥት መመሥረታችንን ስናውጅ ያኔ እኛ በቁም ነገር ነበር ያደረግነው …..የታቹን ከፍ የላዩን ዝቅ አድርጎ የጎንዮሽ የሚያስቀምጥ፣ ጌታና ምንዝር ሕዝብ አለመኖሩን የሚያረጋግጥ፣ ባለአገርና አገር አልባ አለመኖሩን፣…. አበሰርን አረዳን የዛሬ ሁለት አሥርት ግድም….

“…  የአዲስ አበባን የክርስትና ስም ፊንፊኔን ከታሪክ መዘክር ውስጥ አውጥተን ጉልህ ስም ስናደርግ ያኔ ለዋዛ ፈዛዛ አልነበረም ለቁም ነገር እንጂ…..የአዲሱ መንግሥት መዲናነትን ስናጎናጽፋት እንዲሁ በእመ አልቦ ሳይሆን፣… የሕዝብን መብት ተንተርሰን ሀቅን አክብረን በቁም ነገር ነበር…..  የኦሮሞ ዘመንኛ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ሆኖ ጽሑፉ በቁቤ ይደረጋል ስንል ለፌዝ አልነበረም፡፡ …የዚህ መንግሥት ትንሳዔ ሰንደቅ ዓላማ ሲቀረፅ እንዲሁ በምናብ ለጉራና ለይሁን ማለት ያደረግነው ሳይሆን፣…. የአርሲ ኦሮሞ ታጋዮች ‹‹የጋ*›› ባንዲራ ይዛችሁ ተገኛችሁ ተብለው በጢቾ……. አምስት ዓመት ፅኑ እስራት የታደቡበትን….. ባህላዊ እሴቶችን ከትግል መስዋዕነቱና ከድል ራዕዩ ጋር አናበን በቁም ነገር ነበር፡፡ የትግል ቀልድ የድል ከንቱ ታይቶም ተሰምቶም ስለማይታወቅ፣ ሁሉንም ስናደርግ ለይስሙላ ለከማን አንሼ ብለን አንዳችም የሠራነው አልነበረም፤” በማለት ወደ ኋላ አጠንጥኖ የኦሮሚያ መንግሥት ምሥረታና በወቅቱ የተወሰዱ ዕርምጃዎችን ይዘከራል፡፡ የዚህ መንግሥት ምሥረታ ፋይዳ ምን እንደሆነ ሲያመላክት “…….ሕዝባችንን መታገያ አስታጥቀን ተቀጣጣይ ችቦ ነበር የለኮስነው፡፡ የትግል አቅጣጫ የድል ፋና ነበር የቀደድነው፡፡ የማይፈርስ ዓምድ የማይናድ ሀውልት ነበር የገነባነው፡፡ የእኩልነት ማሳ አርሰን የነፃነት ዘር ነው የዘራነው፡፡ የአብሮ መኖርና የመቻቻል ቦይ የመከባበር መንገድ ቀድደን የልማትና የብልፅግና ዘዴ ነበር የዘየድነው…  በአራት ወራት ዕድሜ ውስጥ ብቻ.. በታሪክ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የኦሮሞን ዘመናዊና ሁሉን ኦሮሞ አቀፍ መንግሥት መሥርተን፣ የኦሮሚያን የመንግሥት ቢሮክራሲ….አዋቅረን… ተንቀሳቀስን… ለቀልድም ለይስሙላም ደግሞም አይሆን ይሆን በሚል ጥርጣሬም አልነበረም፤” በሚል ቆፍጠን ያለ ደግሞም በውል የታሰበበት መሆኑን በሚያሳውቅ አነጋገር ነበር፡፡

ይኼንን ታላቅ ገድል የፈጸሙ የመንፈስ ኩራት እንጂ ማቴሪያላዊ ትሩፋትን ያልጠበቁና ያልነገዱበትን እነዚያን በሕይወት የሌሉና በሕይወት ኖረው የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የማይታወቁትን መንግሥት ሠሪዎችን “… በቁርጠኝነትና በልበ ሙሉነት ሕዝባቸውን ባለ ራዕይ ያደረጉትን… መንግሥት መሥራቾች ቁም ነገረኞችና አገር ሠሪዎች …..አሞገስኳቸው ተዘከርኳቸው፡፡ ክብር ለእነሱ ሞገስ ለእነሱ… ምርጥ አርቆ አስተዋይ የኦሮሞ ልጆች፡፡ ድካማቸው ራዕያቸው እያስተጋባ ለዝንተ ዓለም እየደመቀ እየጎላ የሚሄድ ብፁዓን!!  ..ለምን ቢባል………  ዘመን የማይሽረውን፣ አልፋና ኦሜጋ የማይቀረውን …..ዘመናት የነፈጉትን መንግሥታት የቀሙትን መንግሥቱን አቆሙለት፡፡ እንደ ዘበት አሳልፎ ለማንም የማይሰጠውን መብቱንና የመብቱ ትግል የሆነውን ማንነቱን ደግሞም ለመብቱና ለማንነቱ መከበሪያ የሆነውን ግዙፍ መሣሪያ መንግሥቱን አገሩንና በከፊል ሀብቱን አስታጠቁት ..የፊንፊኔን ልዩ ጥቅም  የሙግታችን አንዱ አካል ሊሆን የቻለው .. የእኛ መሆኗ ስለተረጋገጠ እንጂ … ስለየኛነቷ በሆነ ነበር ዛሬ ትግሉ ይሆን የነበረው፡፡ ትግል የሚወሰነው በወቅት፣ በቦታና በሁኔታዎች ውስጥ ነው፡፡ እነዚህን አመቻችቶ የተወሰደ ዕርምጃ ይሰምራል፡፡ እነዚያ ድንቅዬዎች ይኼን ተገንዝበው ሌላው ሳይባንን እነርሱ ነቅተው መጥቀው የወሰዱት ዕርምጃ ዛሬ ማንነታችንን አላቀው፡፡ ከንቱ ውዳሴ አይደለም፤” ብሎ ያልቃቸዋል፣ ያሞግሳቸዋል፡፡

ጸሐፊው አሁንም ያስጠነቅቃል እንዲህ ሲል፣ “የኦሮሚያ ጉዳይ እስከ መጨረሻውና ለሁሌም በውል ካልተመለሰ፣ የኦሮሞ ሕዝብ እስከ ወዲያኛው በአገሪቱ ውስጥ በልኩ የሚመጥን መብት ካላገኘ ትግሉም ሞቷል ታጋዮቹ በሕይወት ኖሩ አልኖሩ ሞተዋል::”

ፊንፊኔ …….ከሁሉም በላይ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች መከበራቸው የግድ ነው፡፡ …… ምክር ቤት ውስጥ የከተማይቱ ነዋሪ ኦሮሞ ተመራጮችን ሳይጨምር በቀጥታ ከኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች የሚወከሉ አባላት ቁጥር… ከንቲባዎች፣ አፈ ጉባዔዎችና ካቢኔዎች ሹመትና ሥርጭት…… ቋንቋና ሰንደቅ ዓላማ ጥምር፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ቅጥር ተመጣጣኝ……የከተማይቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ውሳኔ ላይ የኦሮሚያ ሕዝብና መንግሥት ይሁንታ፣ የኦሮሚያ አካል እንደሆነች በሕግ መንደንገጉ…..

……በኢኮኖሚውም አንፃር በጥቅሉ ፊንፊኔ ከምታገኘው ገቢ ሩቡን በቀጥታ ለኦሮሚያ ፈሰስ ማድረግ ይኖርባታል… ምክንያቱም ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ነገር አንዳችም ከኦሮሚያ ውጪ አሊያም የኦሮሚያን ምድር ሳይነካ ፊንፊኔ የሚደርስ ነገር የለም፡፡ በመጨረሻ ሀብት እየከሰመ የሚሄደው የኦሮሚያ ስለሆነ ታክስ ኤክስፖርት በማድረግ የቀውስ ተሸካሚ መሆን ስለሚመጣ፣ የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ጉዳይ በቂ ትኩረት ማግኘት ኖርበታል፡፡

ቢሆንም ግን የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት ጉዳይ አሁንም ምኑ ተይዞ ጉዞ ዓይነት ነው……….ለነገሩማ እንጂ አያሌ አይነኬዎች አሉ፡፡ አንዳንድ በክልል ደረጃ ላይ ሰፊ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት የተሸከሙ የፌዴራል መንግሥቱ ተጠያቂ መሥሪያ ቤቶች በተለይም መብራት ኃይል፣ ቴሌና የውኃ አገልግሎት አካላት የሕዝብን ብሶት በመቀስቀስ በኩል ሸጋ ሰበብ ሊሆኑ የሚችሉ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ክልሎችን አያደምጡ፣ ባለቤታቸው ፌዴራል አያውቃቸው፣ ለአሥር አሥራ ምናምን ቀን የውኃ፣ የመብራትና የቴሌፎን ግንኙነት አገልግሎት በተከታታይ ያጣ ሕዝብ …..  እነዚህ በክልሎች ውስጥ የሚሠሩትን መሥሪያ ቤቶች አስተዳደር ክልሎች ቢረከቡ ሰማይ አይደፋብን……

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...