የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ለእረፍት ከሄዱ በኋላ፣ የአዲስ ዓመት የሥራ ዘመናቸውን የሚጀምሩት በጋራ በሚያካሂዱት የመክፈቻ ጉባዔ ነው፡፡
የሁለቱም ምክር ቤቶች የተናጠል የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንቦች፣ ሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመናቸውን በይፋ የሚጀምሩበት የጋራ ጉባዔ በመስከረም ወር የመጨረሻ ሰኞ ቀን እንደሚሆን ደንግገዋል፡፡ የሥራ ዘመን መክፈቻው የጋራ ጉባዔም የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር በአዲሱ የሥራ ዘመን መንግሥት ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የአስተዳደር ጉዳዮችን በተመለከተ የሚያደርጉትን ንግግር በማዳመጥ ነው፡፡
በዚሁ መሠረት ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ የሁለቱ ምክር ቤቶች አምስተኛ የመርጫ ዘመን ተወካዮች አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመናቸውን በጋራ የመክፈቻ ጉባዔ ለመጀመር፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ታድመዋል፡፡
ተወካዮቹ የተሰበሰቡበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ላለፉት በርካታ ዓመታት የነበረው ገጽታው ተቀይሯል፡፡ ከአፈ ጉባዔው ሰገነት ጀርባ የነበረው ቀይ መጋረጃ ተነስቷል፣ የግድግዳዎቹ ቀለሞች ተቀይረዋል፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት የአፈ ጉባዔውን ሰገነት ተደግፎ የቆመው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግዙፍ ፎቶ ተነስቷል፣ የእግር ምንጣፎች ሳይቀሩ ተቀይረዋል፡፡
በአዳራሹ የተገኙት ተወካዮች አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ የተለያዩ የባህል አልባሳት ተላብሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ የሆኑ የፓርላማና የፌዴሬሽን ምርክ ቤት አባላትም ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መከፈትን ካበሰሩ በኋላ፣ ለዕለቱ የተዘጋጀውን ንግግር አሰምተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የሚያቀርቡት ንግግር የመንግሥትን ዕቅዶች የሚገልጽ በመሆኑ፣ የንግግሩ ይዘት የሚረቀቀውም በመንግሥት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንቱም እንደ ርዕሰ ብሔርነታቸው በንግግሩ ላይ ሐሳባቸውን የማካተት መብት አላቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀውን ንግግር ማሰማት ሲጀምሩ ቀዳሚ ያደረጉት ያለፈውን ዓመት የአገሪቱን ሁኔታ በመቃኘት ነበር፡፡
‹‹ያለፈው ዓመት በዓይነቱ የተለየ እንደነበርና አገሪቱም በከፍተኛ የለውጥ መዘውር ውስጥ ገብታ የነበረችበት እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን፤›› በማለት የጀመሩት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ በዓመቱ ታላላቅ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕቅዶችን ለመፈጸም ታስቦ የነበረ ቢሆንም በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በታቀደው ልክ ሳይፈጸም መቅረቱን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ለበርካታ ዓመታት የሕዝቡን መሠረታዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ የተከተለው ዘገምተኛ አካሄድ፣ አገሪቱን በአሳሳቢ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትገኝ አድርጓት መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
ብዝኃነትን የምታስተናግድ ጠንካራ አገር ለመገንባት ትጋት ሲደረግ ቢቆይም፣ በዚሁ ልክና መጠን ኢ ፍትሐዊና ኢ ዴሞክራሲያዊ አሠራሮች መንሰራፋት የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ፈተና ውስጥ እንዳስገቡት፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋትና ቁልፍ የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር የአሠራር ነፃነታቸውን ከማስጠበቅ አንፃር መንግሥት ያልተሟላ አካሄድ በመከተሉ፣ ኅብረተሰቡ አማራጭ የትግል መድረኮች እንዳይኖሩት ትርጉም ያለው የሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
‹‹በአጠቃላይ ከወሳኝ ባለድርሻ አካላት ጋር አገራዊ መግባባትን ባልፈጠረ የፖለቲካ ምኅዳር ብቻችንን ስንዳክር ቆይተናል፡፡ ዜጎቻችን በፍትሕና በአስተዳደር በደሎች ሲሰቃዩ፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ሲጣበቡና ሲጣሱ እያየን በዕለት ተዕለት የአጭር ጊዜ ዕይታዎች ተውጠን ችግሮቹን ከምንጫቸው የሚያደርቁ ዘመን ተሻጋሪ ስትራቴጂዎችንና ዕርምጃዎችን ሳንወስድ ለረዥም ጊዜ ቆይተናል፤›› ሲሉ ያለፈውን ዓመት ብቻ ሳይሆን፣ ለዓመታት የተደራረቡ ችግሮችንና የመንግሥት ስህተቶችን ነቅሰው አመላክተዋል፡፡
በስተመጨረሻም ቢሆን ችግሮቹን የገመገመው ገዥው ፓርቲና ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ አመራር ነባራዊ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በፅሞና ገምግሞ ለሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት በመገዛት በሁሉም ዘርፎች አዲስ ታሪክ ለመጻፍ መንደርደር መጀመሩን፣ ይህ ደግሞ የተስፋ ጎህ እንዲቀድ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ብሎም አገራዊ ፖለቲዊ ምኅዳሩን ለማስፋት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉ፣ የነፍጥ ትግልን መርጠው በስደት ላይ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ጭምር በሰላማዊ መንገድ በአገር ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ሰላማዊና የሠለጠነ የፖለቲካ ውይይት እንዲጠናከር መሠረታዊ የለውጥ ዕርምጃዎች መወሰዳቸው፣ በውጭ ጉዳይ ግንኙነት የኢትዮጵያና የኤርትራን ሕዝቦች ጥቅም መሠረት በማድረግ አዲስና ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ለመመሥረት የሚያስችል ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱን ለአብነት አንስተዋል፡፡
የተጀመረው ሰፊ የዴሞክራታይዜሽን ሥራ ከማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስና ዘላቂ ሰላምና የሕግ የበላይነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በ2011 ዓ.ም. ትኩረት አድርጎ መንግሥት ሊሠራባቸው ይገባል ያሉዋቸውን ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችም ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው አቅርበዋል፡፡
ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች
በመልካምም ሆነ በፈታኝ የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የአገሪቱ ሕዝቦች ለዘመናት በአብሮነትና በመቻቻል እሴታቸው ሆነው ቢቆዩም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ነፃነትንና ሥርዓተ አልበኝነትን ባለመለየት ሕግና ሥርዓትን የሚያከብር እንቅስቃሴና ድርጊት መስፋፋት፣ በአገሪቱ የተጋረጠ ፈተና ሆኖ መታየት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ዜጎች ክቡር ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለዘመናት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ትተው መሰደዳቸውንና በጥቅሉም የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ መውደቁን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
በሕገ የበላይነት የማይመራ አገር ዕጣ ፈንታ ጥፋትና መበታተን ብቻ እንደሆነ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ለዘንድሮው ዓመት ልዩ ትኩረት በመስጠት የእያንዳንዱን ዜጋ ደኅንነትና ነፃነት ለማስከበር አስፈላጊውን ዕርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡
የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ እንዲጎለብት የተጀመሩ መልካም የሪፎርም ሥራዎች ተቋማዊ ቅርፅ ይዘው እንዲቀጥሉ የሕግ ማዕቀፎችን የማሻሻልና ተቋማትን ማጠናከር ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ፣ ይኼንኑ ለመምራት ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመው የሕግና ፍትሕ አማካሪ ጉባዔ የጀመራቸው ተግባራት በዚህ ዓመት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ጉባዔና በሥሩ በተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ በመታገዝ የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የሲቪክና የበጎ አድራጎት ማኅበራት አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ የማሻሻል ሥራ ዘንድሮ እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል፡፡ የምርጫ ሕጉ ሥልጣን በኃይል ከሚያዝበት አዙሪት ተወጥቶ በሐሳብ ክርክርና ልዕልና በሕዝብ ምርጫ ብቻ ሥልጣን ወደሚያዝበት ሰላማዊና የሠለጠነ ሥርዓት የሚያሸጋግር የጨዋታ ሕግ ስለሆነ፣ መንግሥት በልዩ ትኩረት እንደሚመለከተውና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመመካከር የምርጫ ሕጉ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንዲሆን የተጀመሩ የማሻሻያ ሥራዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም የምርጫ አስፈጻሚ ተቋማትም በገለልተኝነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችሉ ተገቢ ዕርምጃዎች በዚህ ዓመት እንደሚወሰዱ ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ተቋማት ከተደራራቢ ተልዕኮና ተግባር እንዲወጡና የሀብት ብክነት እንዲቀንስ፣ እንዲሁም ቀልጣፋ ቢሮክራሲ ለማስፈን የሚያስችል የመንግሥት አወቃቀር ለውጥ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለምክር ቤቱ እንደሚቀርብም አስታውቀዋል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በተከሰተው አለመረጋጋት፣ እንዲሁም በኢኮኖሚው ውስጥ ሥር እየሰደዱ በመጡት የውጭ ምንዛሪና የኃይል አቅርቦት እጥረት፣ የሎጂስቲክስ፣ የታክስና የመንግሥት አገልግሎቶች ቅልጥፍና ችግሮች ምክንያት የኢኮኖሚ ዕድገቱ ትርጉም ባለው ደረጃ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡ በግብርና ላይ የተመሠረተው የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈለገው ፍጥነት ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ወደ ተመሠረተ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ካለመሸጋገሩ በተጨማሪ፣ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገትም ቢሆን በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የሕዝቡ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የወጣቶች ሥራ አጥነት ጋር ሳይጣጣም መቆየቱንም አውስተዋል፡፡
በአገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መጥፋትና አለመረጋጋትና እያደገ የመጣው ሥር የሰደደ ኢኮኖሚያዊ ችግር ባለሀብቶችን ተስፋ ማስቆረጡንና ዘገምተኛ የንግድ ሥራ ውጤትን ማስከተሉን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ይሁንና እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማሽቆልቆል እንዲገታ በአጭር ጊዜ ወደ መደበኛው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለመመለስ የማገገሚያ ፖሊሲ መተግበር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የአገሪቱ አጠቃላይ ብድርም ሆነ የመንግሥት ብድር ከተቀመጠለት ጣራ በላይ እንዳያልፍ በጥብቅ የማረጋገጥ ሥራ ከዘንድሮ ጀምሮ በልዩ ትኩረት እንደሚከናወን፣ የመንግሥት ኢንቨስትመንት አስተዳደርና ቅልጥፍናን የማሻሻል ሥራ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠውና የመንግሥት ፋይናንስ ከመንግሥት ሴክተር ውጪ (ከግል ባለሀብቶች) የሆኑ ኢንቨስትመንቶችን ለማሳደግ በሚያስችል መንገድ አሠራሩ እንደሚሻሻልም ገልጸዋል፡፡
የፋይናንስ ገበያውን አወቃቀር የማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን በገንዘብ ገበያ፣ በካፒታል ገበያና በኢንሹራንስ ገበያ መካከል ተገቢ መስተጋብር እንዲኖር ለማድረግ መንግሥት ዘንድሮ ልዩ ትኩረት እንደሰጠው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለምታመርታቸው ምርቶች አስተማማኝ ገበያ ለመፍጠርና አገሪቱ ከአካባቢው አገሮች ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስር አካል ለማድረግና ንቁ ተሳታፊም እንድትሆን፣ የንግድ ድርድሮች በአዲስ መንፈስና ጥረት እንደሚከናወኑና የተጀመሩ ድርድሮችም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ዘመን እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ረገድ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አገሮች መካከል ልዩ የንግድና የልማት ትስስር እንዲፈጠር፣ በአፍሪካም ደረጃም ቢሆን የአቡጃ ስምምነትን መሠረት በማድረግ አኅጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት እየተደረገ ባለው ድርድር መንግሥት ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካ አኅጉር ነፃ የሕዝቦች እንቅስቃሴ እንዲጎለብት የአፍሪካ መሪዎች በተስማሙት መሠረት፣ ለአፍሪካ አገሮች ዜጎች ነፃ የመዳረሻ ቪዛ መስጠት ይጀመራል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር መንግሥት ዘንድሮ ትኩረት ያደርግባቸዋል በማለት ያነሷቸውን አመላካቾች በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ የውጭ መንግሥት ተቋም አማካሪ የሆኑ ባለሙያ፣ አብዛኞቹ በፕሬዚዳንቱ የተነሱት ጉዳዮች የሚያሳዩት መንግሥት ወደ ሊበራል ዴሞክራሲ እያደላ መሆኑን ያመለክታል፣ አልያም የዚህ አዝማሚያ ይታይበታል ብለዋል፡፡
የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ፕሮግራምን ለማስፈጸም በዴሞክራሲና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርሆዎች መካከል መጣጣምን ሳይሆን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ውስን ዴሞክራሲን በመፍቀድ ተልዕኮውን በማረጋገጥ ላይ የሚያደላ መሆኑን፣ በፕሬዚዳንቱ ዘንድሮ መንግሥት ትኩረት ያደርግባቸዋል የተባሉት በሙሉ ከተፈጸሙ ግን ዴሞክራሲን የመክፈትና የማስቀደም ፍላጎት መኖሩን ያሳያል ብለዋል፡፡ የሲቪል ማኅበራትና የበጎ አድራጎት አዋጅ፣ የፀረ ሽብር አዋጁ፣ የሚዲያ ነፃነትና የመረጃ ነፃነት፣ እንዲሁም የምርጫ ሥርዓቱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ተልዕኮ ለማረጋገጥና ይኼንንም ዕውን ለማድረግ የአውራ ፓርቲ ልዕልናን ለማስፈን ኢሕአዴግ የተጠቀመባቸው ናቸው የሚሉት ባለሙያው፣ ከንግግሩ መረዳት የሚቻለው ይህ ጊዜ እያበቃ መሆኑን መረዳታቸውን ይገልጻሉ፡፡
መንግሥት ወደ ሊበራል ዴሞክራሲ እያደላ መሆኑን ወይም የዚህ መገለጫ ባህሪያት እየታዩበት መሆኑን ከሚጠቁሙት መካከል ከዴሞክራሲ ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንቱ ያመለከቷቸው፣ ዘንድሮ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች በተጨማሪ መንግሥት በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትኩረት ያደርግባቸዋል የተባሉት ለዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የተጀመረውን ድርድር በአዲስ መንፈስና ጥረት ለማፋጠን፣ እንዲሁም በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ንቁ ተሳታፊ ለመሆን ልዩ ትኩረት እንደሚደረግ መግለጻቸውም ይኼንኑ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ አገሮች የንግድ ትስስርና በአካባቢያዊ ነፃ የንግድ ሥርዓት ውስጥ በንቃት መሳተፍ የኢትዮጵያን ገበያም ክፍት ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ዝግ እንዲሆን ለተደረገው የኢትዮጵያ ገበያ አዲስና የሊበራል ኢኮኖሚ ባህሪያትን መላበስ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ልማትን ውስን የሚያደርገውን ተሳትፎ በመቀነስ የመንግሥትን ፋይናንስ ለግሉ ዘርፍ ለማካፈል እንደሚሠራ ፕሬዚዳንቱ መናገራቸው፣ የአዝማሚያዎቹ መገለጫዎች መሆናቸውን በመግለጽ ትግበራው ብልህነትንና ጥንቃቄን እንደሚፈልግ አማካሪው አሳስበዋል፡፡