Friday, June 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የደን ማስተር ፕላን ከ22 ሚሊዮን ሔክታር በላይ የተራቆተ መሬት ለማገገም የሚቻልበትን ተስፋ ሰንቋል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሦስት ዓመታት በፊት ይፋ በተደረገ ጥናት መሠረት፣ በኢትዮጵያ እያደገ ከመጣው የማገዶ ፍጆታ በመነሳት በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ 300 ሚሊዮን ዛፎች መተከል እንዳለባቸው ተጠቅሶ ነበር፡፡ በዚህ ሳይወሰን ደንና የደን ውጤቶችን የመጠቀም ፍላጎትም በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የደን መመንጠርን በማስፋፋት፣ የመሬት መራቆትን እያባባሰ መምጣቱም ለኢትዮጵያ የደን ዘርፍ ልማት የሚያገለግል የአሥር ዓመታት የደን ማስተር ፕላን ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡

ይህንኑ መነሻ በማደረግ በተባበሩት መንግሥትታት የልማት ፕሮግራም የሚታገዝ፣ በስዊድንና በኖርዌይ መንግሥታት የገንዘብ ድጋፍ በአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የሚተገበር የአሥር ዓመት የደን ማስተር ፕላን ዝግጅት ተጠናቆ ይፋ የተደረገው ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡

የአሥር ዓመት ብሔራዊ የደን ሀብት ልማት ዕቅድ የሚል መጠሪያ ያለው ይህ ዕቅድ፣ ከደን ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ፖሊሲዎችና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች የሚመራ እንደሚሆን ሲገለጽ፣ የአሥር ዓመታት የደን ልማትን የተመለከተ ማስተር ፕላን ማዘጋጀት ያስፈለገው፣ የአገሪቱ የደን ሽፋን በየጊዜው እያሽቆለቆለ በመምጣቱ እንደሆነ ይህም በሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ በማገዶ እንጨትና በግብርና መሬት መስፋፋት ላይ የታየው መጠነሰ ሰፊ ፍላጎት የደን ይዞታን በከፍተኛ መጠን እያመናመነው እንደመጣ ተጠቅሷል፡፡

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተካሄደውና የአሥር ዓመቱ ማስተር ፕላን ሰነድ ይፋ በተደረገበት ወቅት የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አገሪቱ ስትተገብረው የቆየችው ለአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ የደን ጭፍጨፋንና መመናመንን በመቀነስ የደን ልማት እንቅስቃሴዎች የሚደረጉበት ተግባራት መስፋፋት እንዳለባቸው ስትራቴጂው ማስፈሩን አስታውሰዋል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የደን ሽፋን አከራካሪነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ 15 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ሲጠቀስ፣ ይህ መጠን በቅርቡ ወደ 20 በመቶ እንደሚያደግ ይጠበቃል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2030፣ 22 ሚሊዮን ሔክታር የተራቆተ መሬት እንዲያገግምም ለማድረግ መታቀዱ ሲገለጽ፣ የደን ዘርፉ ለኢኮኖሚው (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) በአሁኑ ወቅት እያበረከተ የሚገኘው የአራት በመቶ አስተዋጽኦም፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ወደ ስምንት በመቶ እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡

በዚሁ መሠረት የአሥር ዓመታት መርሐ ግብሩ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚተገበሩ ሥራዎችን አካቷል፡፡ እስካሁንም የ133 ሺሕ ሔክታር የተራቆተ መሬት እንዲያገግምም መደረጉ ታውቋል፡፡ ዘጠኝ ሺህ ሔክታር መሬትም በደን እንዲሸፈን ሲደረግ፣ ለ4,873 አባወራዎችም የኑሮ መደጎሚያ እንደሚያስገኝ ተብራርቷል፡፡ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የሚያገኙ 7,667 ሰዎችም እስካሁን ሲተገበር በቆየው የፕሮግራሙ አካል ተጠቃሚ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ምንም እንኳ የደን መመናመንና የመሬት መራቆት አሳሳቢ እየሆነ ቢመጣም፣ በአገሪቱ ያለውን አነስተኛ የደን ሀብት ጠብቀው ያቆዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ከደን ዘርፉ ያላቸው ተጠቃሚነት አነስተኛ መሆን ለደን ጭፍጨፋ መባባስ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ በርካቶች የደን መሬቶችን ለእርሻ ሥራ በመመንጠር ደን መራቆትን ሲያስፋፉ ይታያል፡፡ በአንፃሩ ሚኒስቴሩን ጨምሮ በርካታ የደን ባለሙያዎች፣ ደንን በመንከባከብ ሊገኙ ስለሚችሉ አገራዊ ጥቅሞች ሲያብራሩ ይደመጣሉ፡፡ ሚኒስትሩን ገመዶ (ዶ/ር) ጨምሮ የደን ብሎም የሥነ ምኅዳር ጥበቃና ክብካቤ ተቆርቋሪዎች፣ የደን ይዞታን በማስፋፋት የሚገኙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች በርካታ ስለመሆናቸው ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡

በደን መስክ መሻሻል ብታሳይና የደን ዘርፉን እንደሚፈለገው መጠን ትኩረት ተሰጥቶት ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ እንደሚያበርክት ቢታመንበት፣ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ውኃ በመላክ ከሌሎች የወጪ ምርቶች ያልተናነሰ ገቢ ማስገኘት እንደሚችል ከሚያምኑት መካከል የደን ባለሙያውና ብሔራዊ የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት አስተባባሪው ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) ይጠቀሳሉ፡፡

እንደ ይተብቱ (ዶ/ር) የቆየ ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ የደን ሀብቷን ብታስፋፋ ከፍተኛ የውኃ ክምችት እንዲኖር ስለሚያስችላት የውኃ ሀብቷን እንደማንኛውም ሸቀጥ ምርት ወደ ውጭ ከመላክ ባሻገር፣ ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ብሎም ለግብርናውም ጭምር በመስኖ ለማረስ የሚያግዝ የውኃ ሀብት እንደ ልብ እንዲገኝ ለማስቻል ደን ቦታ ሊሰጠው የሚገባ የተፈጥሮ ሀብት ስለመሆኑ አብራርተው ነበር፡፡

በደን አስተዳደርና ክብካቤ ሥራዎች ምክንያት ከ12 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ከመጨፍጨፍ ተርፎ ለአገሪቱ የካርቦን ንግድ አስተዋጽኦ የሚያረክት የ5.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ክምችት መገኘቱን በተመለከተ ያብራሩት፣ ሙሉጌታ ልመንህ (ዶ/ር)፣ በፋርም አፍሪካ የምሥራቅ አፍሪካ የደንና የተፈጥሮ ሀብት ኃላፊ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት፣ የደን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በአግባቡ ሊታይና ሊታወቅ ባለመቻሉ ምክንያት፣ ኢትዮጵያ እንደ ቻይና፣ ፊንላንድና ስዊድን ካሉ አገሮች እኩል ከደን ማግኘት የሚገባትን ትልቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማግኘት እንዳልቻለች ገልጸው ነበር፡፡ ደን መጠበቅና መንከባከብ ውጤት የሚኖረው የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ እንደሆነ የሚያምኑት አቶ ሙሉጌታ፣ ኢትዮጵያ በደን ልማትና አጠቃቀም መስክ ልትከተል ስለሚገባት ስትራቴጂዎችም አብራርተው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች