Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመኢአድ አዲስ ፕሬዚዳንት መረጠ

መኢአድ አዲስ ፕሬዚዳንት መረጠ

ቀን:

ግንቦት 20 እና 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ ዶ/ር በዛብህ ደምሴን ፕሬዚዳንት አድርጐ መምረጡን አስታወቀ፡፡

ፓርቲው ይህን ያስታወቀው ማክሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ መግለጫውን የሰጡት ደግሞ አዲስ የተመረጡት የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ሌሎች የፓርቲው አመራር አባላት ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ዶ/ር በዛብህ ደምሴን ፕሬዚዳንት፣ አቶ አሰፋ ሀብተ ወልድን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ሙሉጌታ አበበን ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም አቶ አዳነ ጥላሁንን ደግሞ ዋና ጸሐፊ አድርጐ መምረጡን አስታውቋል፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ ከአሁን በኋላ በፓርቲው ውስጥ የሚኖራቸውን ሥራና ተሳትፎ አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ፣ ‹‹አቶ አበባው በካቢኔ አባልነት ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ይህም በመሆኑ አዲሱ አመራር በሥራ አስፈጻሚ አባልነት ይዟቸዋል፤›› በማለት አቶ ሙሉጌታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው ምን ያህል አባላት ተገኝተው ነው ምርጫ የተከናወነው ለሚለው ጥያቄ ደግሞ፣ ‹‹የመኢአድ መሥራች ጉባዔ 600 አባላት ያሉት ሲሆን፣ የጠቅላላ ጉባዔው ምልአተ ጉባዔ ደግሞ 301 እና ከዚያ በላይ አባላት ሲገኙ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ባለፈው ቅዳሜና እሑድ ባካሄድነው የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ 320 የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ተገኝተዋል፡፡ ይህንንም የምርጫ ቦርድ ተወካዮች ታዝበዋል፤›› በማለት አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡

በአዲሱ አመራር በኩል የሚታዩት በርካታ አዛውንቶች ከመሆናቸው አኳያ ፓርቲው ውስጥ ያለው የወጣቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል? ተብለው የተጠየቁት የፓርቲው አመራሮች፣ ‹‹ብዙ ወጣት አባላት አሉን፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ግን ፖለቲካ በዕድሜ አይለካም፡፡ መለካት ያለበት በተግባራዊ አስተዋጽኦ ነው፡፡ አንድ ሰው ወጣት ስለሆነ አገር ይመራል ማለት አይደለም፡፡ ፖለቲካ ልምድ፣ ዕውቀትና ተያያዥ ጉዳዮች ይጠይቃል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው አዲስ አመራር ከመምረጥ ባለፈ ከፓርቲው ጋር ከወራት በፊት እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው የነበሩትን የፓርቲው ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ እንድርያስ ኤሮ እና ሌሎች አባላትን ማገዱንም እንዲሁ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ አቶ እንድርያስ ኤሮ፣ አቶ ወርቁ ከበደ፣ አቶ ሙሉጌታ መንገሻ፣ አቶ ብሩ ደሲስ፣ አቶ ፀጋዬ እሸቴና አቶ ይርዳው ሽፈራውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከፓርቲው እንዲወገዱ መወሰኑን አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል፡፡

አዲስ የተመረጡት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ የ72 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ፣ ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በታሪክና በኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡

በፓለቲካው ዓለም ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በተቆጣጠረበት የሽግግር ወቅት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ቡድን የተባለ ድርጅት በማቋቋም ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም የምርጫ 97 ክስተት በነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) እንደተመሠረተ የላዕላይ ምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...