ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመጡ ቁጥር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በሚፈጠርበት የአሠራር ክፍተቶች ከትችትና ወቀሳ አስመልጦት አያውቅም፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማክሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በብሔራዊ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግልጫ ለሪዮ ኦሊምፒክ በማራቶን የአገሪቱን ተወካዮች ይፋ ማድረጉን ተከትሎ አሁንም የተቃውሞ አስተያየቶች እየቀረቡበት ይገኛል፡፡
በቅርቡ ፊቱን ወደ ማራቶን ያዞረው የቀድሞው የረዥም ርቀት ኮከቡ ቀነኒሳ በቀለና የካናዳ ማራቶን ባለክብሩ የማነ ፀጋዬ ከሪዮ ኦሊምፒክ ምርጫ ውጪ መሆናቸውም ተረጋግጧል፡፡ ፌዴሬሽኑ ለምርጫ የተጠቀመበትን መሥፈርት በመግለጫው አሳውቋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይፋ ባደረገው መሥፈርት መሠረት በወንዶች 49 ነጥብ በማግኘት በተራ ቁጥር አንድ የተቀመጠው ለሚ ብርሃኑ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ የተመረጠው ፈይሳ ሌሊሳ በ46 ነጥብ፣ ሌሊሳ ዲሳሳ ደግሞ በተመሳሳይ 46 ነጥብ አራተኛ ተመራጭ በመሆን ተጠባባቂ ሆኗል፡፡ በተራ ቁጥር አምስት የተቀመጠው የማነ ፀጋዬ ደግሞ ሁለተኛው ተጠባባቂ በመሆን ተከታዩን ደረጃ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡
በሴቶች በተደረገው ምርጫ 49 ነጥብ በማግኘት የመጀመሪያ ተመራጭ ትዕግሥት ቱፋ ስትሆን፣ የዓለም ሻምፒዮናዋ ማሬ ዲባባ ደግሞ 46 ነጥብ ሁለተኛዋ ተመራጭ ሆናለች፡፡ በተራ ቁጥር ሦስት የተቀመጠችው ትርፊ ፀጋዬ በተመሳሳይ 46 ነጥብ፣ አበሩ ከበደ 45 ነጥብ በማግኘት ተጠባባቂ መሆኗ ተረጋግጧል፡፡
ከሪዮ ኦሊምፒክ ምርጫ ውጪ መሆኑን ያረጋገጠው ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ የምርጫው ውጤት በታወቀ በጥቂት ሰዓታት ልዩነት ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው አስተያየት አሁንም ምርጫው ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ ቅሬታውን አሰምቷል፡፡