Sunday, June 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ግምገማዊ አስተያየት በተናፋቂ ትዝታዎቻችን

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የመጽሐፉ ርዕስ – ተናፋቂ ትዝታችን

የመጽሐፉ ደራሲ – ኮሎኔል መለሰ ተሰማ

የመጽሐፉ ገጽ – 232 ኤ5 መጠን

መጽሐፉ የክብር ዘበኛ አካዴሚ ሁለተኛ ኮርስ አባላትንና የኮሪያ ጦርነትን የሚያመለክቱ ፎቶግራፎችን ይዟል፡፡ የዘማቾች የስም ዝርዝርም ተካቶበታል፡፡

መንደርደሪያ

ባለፈው ነሐሴ መገባደጃ ‹‹ተናፋቂ ትዝታችን›› የሚል ርዕስ ያለው የክብር ዘበኛን፣ የኮሪያና የኮንጎ ዘመቻን የሚያስታውስ መጽሐፍ በልዑል ራስ  መንገሻ ሥዩም የክብር እንግድነት በሕይወት የሚገኙ ጥቂት የኮሪያ ዘማቾች፣ ልጆቻቸው፣ የልጅ ልጆቻቸው፣ የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ኤምባሲ ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል፡፡ ምንም እንኳን የኮሪያና የኮንጎ ዘመቻን የሚመለከቱ መጻሕፍት በውጪው ዓለም የታተሙ ቢሆንም አንድም ሰው ሳይማረክባትና አስከሬን እንኳን ሳታስነካ ከፍተኛ ጀብድ በፈጸመችው ኢትዮጵያ ግን የታተሙት ከሦስት አይበልጡም፡፡ አንደኛው ‹‹መታሰቢያ›› በሚል ርዕስ ስለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ክብር ዘበኛ ጦር አካዴሚ አንደኛ ኮርስ ሲሆን፣ እሱም በኮርሱ አባላት ታሪክ አሰባሳቢ ኮሚቴ አማካይነት ተጠናቅሮ በ1999 ዓ.ም. የታታመ ሲሆን ሁለተኛው ይኸው ኮሎኔል መለሰ ተሰማ ‹‹ተናፋቂ ትዝታችን›› በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቁት መጽሐፍ ነው፡፡

መጽሐፉን ሳነብ የተሰማኝ ቢኖር አንዳንድ ሰው፣ ገና ሲወለድ፣ ገና ነፍሱን ሲያውቅ ከዚያም ወጣት እየሆነ ሲሄድ፣ ሌላው ሰው የማይሰማው የኃላፊነት ስሜት፣ ወገንን የመርዳት ስሜት፣ አገርን የመርዳት ስሜት፣ ወገንን ከአደጋ የማዳን ስሜት፣ አገርን ከአደጋ የማዳን ስሜት የሚሰማው መሆኑን ነው፡፡ እኔ የምኖረው ሌሎች ስለኔ እየሞቱ ስለሆነ እኔም ሌሎች እንዲኖሩ ግንባር ቀደም ሆኜ መገኘት አለብኝ የሚል ስሜት ያድርበታል፡፡ አገሩንና ወገኑን በአፍ ሳይሆን በተግባር መውደድ ማለት ከጣፋጭ ነገሮች ሁሉ የሚጣፍጥ ሆኖ ወደ ልቦናው ረቂቅ ምንጭ ወደ ልቦናው ይፈሳል፡፡ የአገርና የወገን ፍቅር ቋያ በልቡ ውስጥ ይቀጣጠላል፣ ልቡም በነዚህ በሁለቱ ፍቅር ይግላል፡፡ የጋለው ልብ በደሙ የሌሎችን ሰላም፣ የሌሎችን ደኅንነት፣ የሌሎችን ህልውና ያግላል፡፡ የጀግንነት አርአያ የመሆን እምነት በልቦናው ያድራል፣ እናም የጀግንነት አርአያ ለመሆን ቆርጦ ይነሳል፡፡ የሰው ልጅ ለዘለዓለም ትቶት የሚያልፍ ክብር እንጂ ሕይወትማ እንደደመና ጥላ በፍጥነት የምታልፍ መሆኗን በዓይነ ልቦናው በግልጽ ያያል፡፡ ስለዚህም ዘለዓለማዊ የክብር ስሙን ጥሎ ለማለፍ ቆርጦ ይነሳል፡፡

ካለበለዚያማ ለሰው ብሎ ለምን ይሞታል? ለምን ውድ ሕይወቱን ለማያውቀው ሰው ጭምር በአጭር ወይም በተራዘመ ጊዜ በጽናት ታግሎ አሳልፎ ይሰጣል? በእርግጥስ ለምን ይሰጣል? ለምንስ ለሌሎች ብሎ መከራውን ያያል? ለምንስ ፍዳውን ይበላል? ጁሴፔ ማዚኒ ‹‹አገርህን አፍቅር፤ ወላጆችህ የሚተኙት በአገርህ ነው፡፡ ፍቅር የሚባለው ቃል በቋንቋህ ሲነገር የምትሰማባት፣ ፈጣሪ የሰጠህ፣ ለሕዝብና ለወገን ሠርተህ ወደ እሱ የምትሄድባት አገርህ ናት›› ሲል እንደተናገረው ይሆን? ወይስ በርትራንድ ራስል ‹‹አገሩን ከሁሉም የበለጠ የሚወድ ከሁሉም የበለጠ ይሠራል›› እንዳለው ነው? ወይስ ግሪካዊው ሴነከ ‹‹ሰዎች አገራቸውን የሚያፈቅሩት ታላቅ ስለሆነች ሳይሆን ስለሚያፈቅሯት ነው›› እንዳለው ይሆን?

የመጽሐፉ ደራሲ አጭር ታሪክ

‹‹ጀግና አርበኞች ለአገራቸው ይሞታሉ እንጂ አገራቸውን አይገድሉም›› ሲል በርትራንት ራስል እንደገለጠው ኮሎኔል መለሰ ተሰማ ያኔ ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት እየተባለ ይጠራ በነበረውና ዛሬ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ አስተዳደር ውስጥ በምትገኘው በአለታ ወንዶ ከተማ ውስጥ በ1920ዎቹ የመጀመርያ ዓመታት ዳንዴ አለታ ጊዮርጊስ ቀበሌ ተወለዱ፡፡

አለታ ወንዶ በቡና አብቃይነታቸው ከሚታወቁት ወረዳዎች ውስጥ አንዷ ከመሆኗም በላይ በድንጋይ ላይ በተቀረፁ ጥንታዊ ቅርሶቿ ትታወቃለች፡፡ አለታ ወንዶ የፍራፍሬና የእንሰት ምርት የሚገኝባት እንዲሁም ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላትና በደን የተሸፈነች ናት፡፡ የኮሎኔል መለሰ ተሰማ በአባታቸው የግራዝማች ተሰማ ደበላ የደጃዝማች አባነፍሶ ወታደር ሲሆኑ እናታው ወ/ሮ አዛለች የራስ ብሩ ወልደገብርኤል ወታደር የነበሩት የመንዝ ጌታ መሪጭ ወልደገብርኤል ልጅ ናቸው፡፡ ደጃዝማች ባልቻና ራስ ወልደ ገብርኤል እንደቅደም ተከተላቸው የሲዳሞ ጠቅላይ ገዥዎች ነበሩ፡፡

መለሰ ተሰማ በልጅነት ዕድሜያቸው ማለትም የጣሊያን ፋሺስት ወታደር በ1928 ዓ.ም.አዲስ አበባን ከመያዙ ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ አዲስ አበባ መጥተው አባ ዘውገ በሚባሉ መምህር የፊደል ገበታ የተቋደሱ ሲሆን፣ በወቅቱ ሰፍኖ በነበረው ሥጋት ምክንያት ወደ አርሲ ሄዱ፡፡ እዚያም በአባ ገብረሥላሴ መምህርነት የፊደል ቆጠራ ትምህርታቸውን በመቀጠል ዳዊት ለመድገም በቅተዋል፡፡ ያኔ ዳዊት የደገመ ትልቅ ሥፍራ ይሰጠው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ቀጥሎም በ1917 ዓ.ም.በተቋቋመው በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው መማር ጀመሩ፡፡ ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ለመግባት የአማርኛና የእንግሊዝኛ መሠረታዊ ዕውቀት ፈተና ማለፍ አስፈላጊ ስለነበር ፈተናውን ወስደው ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥም ከሁለተኛ ክፍል ተዛወሩ፡፡ ያኔ እሳቸው ሲማሩ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል የነበረ ሲሆን፣እሳቸው ሲገቡ ደረጃው ሁለት ክፍሎችን በመጨመር ከፍ አደረገና ሰባተኛ ክፍልንና ስምንተኛ ክፍል ከፈተ፡፡ ከስድስተኛ ክፍል ወደ ሰባተኛ ክፍል ሲያልፉ በመጀመርያ ወር ላይ የሚያምር የወታደር ልብስ የለበሱ ሰዎች ወደ ትምህርት የመጡት ተማሪዎች በስፖርት አስተማሪው፣ በጋሽ ግርማ ፊሽካ፣ ተጠርተው እንዲሰበሰቡ አደረጉ፡፡ ወቅቱ የፋሺስት ጣሊያን ሠራዊት ከወጣ ከሰባት ዓመታት በኋላ፣ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ባቆመ በአራትና አምስት ዓመቱ ስለነበር ወደ ተፈሪ መኮንን የመጡት የክብር ዘበኛ በመጀመርያ በሠልፍ ላይ ቀጥሎም በክፍል ወታደሮች ስለነ ጄኔራል ፊልድ ማርሻል ሮሜል፣ ‹‹የበረሃው ተኩላ›› እየተባሉ ስማቸው ገኖ ስለሚነገርላቸው ስለ ጀርመናዊው ከፍተኛ የጦር አዛዥ ስለፊልድ ማርሻል ሞንቶጎመሪ፣ ስለባለ አምስት ኮከቡ ዝነኛው አሜሪካዊ የጦር ጄኔራል ስለ ማርሻል ዳግላስ ማክ አርተር እያነሱ ወኔ የሚቀሰቅስ ገለጻ ሰጡ፡፡

ሆኖም ወታደር የመሆን ዝንባሌ ያሳየ ወጣት ስላልነበረ ከመካከላቸው 25 ያህል ብቃትና ንቃት አላቸው ብለው ያመኑባቸውን ወጣቶች እየጠሩ ያኔ ማክ ተብሎ ይጠራ በነበረው መኪና ላይ እንዲወጡና ዛሬ ቪላ ኃይለ ሥላሴ (ቤላ) እየተባለ በሚጠራውና በጣሊያንና በጀርመን ኤምባሲዎች መካከል በሚገኝ፣ የድሮ የጣሊያኑ የጦር አዛዥ የጀኔራል ግራዚያኒ ወታደሮች ይኖሩበት ወደነበረው፣ ለእነሱ ግን ክብር ዘበኛ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ወደ ሆነው ሥፍራ በአጀብ ወሰዷቸው፡፡ ከዚያም ከሌሎች ትምህርት ቤቶች ተመልምለው የመጡ 30 ወጣቶች ተቀላቀሏቸው፡፡ ሌሎችም ከልዩ ልዩ ትምህርት ቤቶች ተመርጠው መጡና ቁጥራቸው ወደ 150 ያህል ከፍ አለ፡፡ምልምል የክብር ዘበኛ ወጣቶች በማሠልጠኛ ጣቢያው ለወታደራዊ መኮንንነት የሚያበቃ የጽንሰ ሐሳብና የተግባር ትምህርት ለሦስት ዓመታት (ከ1941 – 43) ተከታትለው በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ ተመረቁ፡፡ ለዚህምየኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የክብር ዘበኛ የጦር አካዴሚ ዲፕሎም ሰጥቷቸዋል፡፡

ኮሎኔል መለሰ የክብር ዘበኝነት ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ ወደፊት በዚህ ጽሑፍ እንደምናገኘው በኮሪያና በኮንጎ ዘምተው ግዳጃቸውን ተወጥተውና የአገራቸውን ክብር አጉልተው የተመለሱ ሲሆን፣ በትምህርቱ መስክ በብዙ የሥልጠና መስኮች በማለፍ ከፍተኛ ዕውቀት አካብተዋል፡፡ በ1955 ዓ.ም.በአየር ወለድ የኮማንዶ ትምህርት ተከታትለው የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡ የምድር ጦር ተግባረ ዕድ ክፍል የተዋጊ መሐንዲስ ትምህርት ተከታትለው በመፈጸማቸው የትምህርት ቤቱን የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የምድር ጦር የጦር ትምህርት ቤት ዋና መምርያ ለአዛዥነትና ለመምርያ መኮንንነት የሰጠውን ትምህርት በመከታተል በ1956 ዓ.ም.በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡

የኮሪያ ዘመቻ

እነኮሎኔል መለሰ ተሰማ የተሳተፉበት የኮሪያ ጦርነት (1943 እስከ 1946) የተባበሩት መንግሥታት የኅብረቱ አባሎችን ጥቅም የሚነካ ኃይል ቢነሳ ለመደቆስ አቅም እንዳለው ያሳየበት የመጀመርያው ጦርነት ሲሆን፣ በዚህም ደቡብ ኮሪያን ለመርዳት በተዘጋጀ ጦርነት የኢትዮጵያን የክብር ዘብ ጨምሮ 41 አገሮች ተሳትፈውበታል፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ኮሪያ የዘመተው፣ በጀግንነት የተዋጋውና አንድም እንኳን በሰሜን ኮሪያ ሠራዊት ያልተማረከው ‹‹ቃኘው ሻለቃ›› እየተባለ ይጠራ የነበረው ኢትዮጵያዊ ሠራዊት ቁጥር እስከ ከ6,037 የሚደርስ ሠራዊት የተላከ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 3,500 ያህሉ በቀጥታ በጦርነቱ ተካፋይ የሆኑ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል 122 የሕይወት መስዋዕትነትን የከፈሉ ሲሆን 536 ያህል ደግሞ መቁሰላቸው ይታወቃል፡፡

የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የኮሪያ ዘማቾች አጽም ተሰባስቦ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር ያረፈ ሲሆን፣በየዓመቱም የሠሩት አኩሪ ተግባር እየተወሳ ይዘከራል፡፡ ይህም ሆኖ ኮሎኔል መለሰ ወደ ኮሪያ የዘመቱት ከሦስተኛው ዘማች ጋር ሲሆን፣ ከእሳቸው በፊት ሁለት የዘማች ቡድን መላኩ ይታወሳል፡፡ በዘመቻው መጨረሻም በሕይወት የተረፉትም ወደ አገራቸው በክብር ተመልሰው አገርንና ሕዝብን የሚያኮሩ ጀግኖች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የክብር ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡የቃኘው ሻለቃ ጦር ከ41 አገሮች መካከል የተማረከ ሠራዊት የሌለው ከመሆኑም በላይ በተሠለፈባቸው 238 ግንባሮችም ድል በማድረግ ይታወቃል፡፡

ዛሬ የኮሪያ ጦርነት ካበቃ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ሠራዊት አኩሪ ድል አስመዝግቦ ከተመለሰ 62 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ከነዚህ ዓመታት ውስጥ 17ቱ የደርግ ዓመታት የኮርያ ዘማቾች ማኅበር መንቀሳቀስ አልቻለም ነበር፡፡ ከ1984 ዓ.ም. ወዲህ ግን ተደራጅቶ የዘማቾችንና የልጆቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ከመሆኑም በላይ በኢትዮጵያና በኮሪያ መካከል ለሚካሄደው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት በማበርከት ላይ ሲሆን፣ የዘማች ልጆች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው፡፡ ኮሎኔል የኮሪያ ዘማቾች ማኅበር ፕሬዚዳት መለሰ ከተመረጡበት ጊዜ ለዘማቹና ለቤተሰቡ ክብካቤ እንዲደረግ ጥረት በማድረግ ላይ ከመሆናቸውም በላይ ማኅበሩ ብሔራዊና ዓለም አስተዋጽኦ እንዲኖረውም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

የኮንጎ ዘመቻ

 የኮንጎ ጦርነት (ሐምሌ 4 ቀን 1952 እስከ ጥር 9 ቀን 1958 ዓ.ም.) የተነሳው፣ ከቅኝ ገዥዋ ቤልጅየም በ1952 ዓ.ም.ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ሲሆን፣በዚህ ጊዜ ካታንጋ የተባለው የኮንጎ ግዛት መሪ የነበረው ሞይሲ ትሾምቤ በማዕድን የበለፀገችውን ግዛት እገነጥላለሁ ብሎ ጦርነት ያውጃል፡፡ በዚህ ጊዜ አሥር ሺሕ ያህል ሠራዊት የነበራት ቤልጅግ ሠራዊቴን አድናለሁ ብላ ጣልቃ ትገባለች፡፡ የኮንጎ ኪንሻሳ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካሳቩቡና ጠቅላይ ሚኒስትር ፓትሪስ ሉሙምባም አገራቸው እንዳትከፋፈል ለተባበሩት መንግሥታት ሐምሌ 4 ቀን 1954 ዓ.ም.ላይ የድረሱልኝ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ በማግሥቱም ጋና ወታደራዊ ዕርዳታ እንድታደርግላት ይጠይቃሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ምክር ቤትም ሐምሌ 6 ቀን 1954 ዓ.ም. በኮንጎ ሊደረግ ስለሚገባው ወታደራዊ እገዛ በማድረግ የቤልጅግ ሠራዊት ያለ ችግር ኮንጎ ኪንሻሳን ለቆ እንዲወጣ ለማድረግና የመንግሥቱን የድረሱልኝ ጥሪ በመመለስ ቅጥር ወታደሮች አገሪቱን ወደ ከፋ ጦርነት እንዳይወስዷት ለማድረግ ወታደራዊ እገዛ ለማድረግ ወሰነ፡፡ ቁጥሩ 20ሺሕ ያህል የጋና ሰላም አረጋጋጭ ሠራዊት የተባበሩት መንግሥታትን ዓርማና ትጥቅ ይዞ ሐምሌ 7 ቀን 1952 ዓ.ም.ደረሰ፡፡ በዚህም መሠረት የቤልጅየም ሠራዊት በነሐሴ 24 ቀን 1952 ዓ.ም.ዕቃውን ጠቅልሎ ወጣ፡፡ የእርስ በርሱ ጦርነት ቀጥሎ ጠቅላይ ፓትሪስ ሉሙምባ ካታንጋ ላይ የካቲት 13 ቀን 1953 ዓ.ም.ተገደሉ፡፡ ወዲያውም 11 ሺሕ የተባበሩት መንግሥታት ሠራዊት ካታንጋ ነሐሴ 20 ቀን 1953 ዓ.ም. ገባ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከ1952 እስከ 1956 ባለው ጊዜ 3,000 ያህል የክብር ዘበኞቹን ልኮ ሰላም ያስከበረ ሲሆን፣ በዚህም ዘመቻ ኮሎኔል መለሰ የመጀመርያው ዘማች ቡድን አባል በመሆን ተካፋይ ሆነዋል፡፡ ኮሎኔል መለሰ የመጀመርያው ቡድን አባል ቢሆኑም በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት ከሁለተኛው ዘማች ቡድን ጋር በመሆን ያኔ ሊፖልድቪል ዛሬ ኪንሻሳ ተብላ በምትጠራው ዋና ወታደራዊ ግዳጃቸውን ሰላም በማስከበር አበርክተዋል፡፡

ኮሎኔል መለሰ ያኔ ያገለግሉ የነበሩት በወታደራዊ ደኅንነት ዘርፍ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪን ዋና አዛዥ በመሆን ይመሩ የነበሩት ጄኔራል ከበደ ገብሬ ነበሩ፡፡ ጄኔራል ከበደ ወደ ኮንጎ የዘመቱት የመጀመርያው ቡድን መሪ ሆነው ሲሆን ያሳዩት ወታደራዊ ብቃት ታውቆ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ ሆነዋል፡፡በዚህ ጦርነት አራት የኢትዮጵያ አየር ኃይል F-86 የተባሉ ተዋጊ ጀቶች ተሳታፊ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በኮንጎ ዘመቻ በግንባር ቀደምነት የተሠለፈው የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ከአራቱ የመደበኛ ጦር መምሪያዎች አንደኛው ነው፡፡

መጽሐፉ ከሚያነሳቸው ዓበይት ቁምነገሮች በጥቂቱ

በመጽሐፉ ከዚህ ቀደም ስለነበረው ባህላዊና ዘመናዊ ወታደር፣ ባህላዊውና ዘመናዊው ወታደር ለአገር ነፃነት ላበረከተው አስተዋጽኦ የክቡር ዘበኛ ማቋቋም ለምን እንዳስፈለገ በሰፊው አቅርቧል፡፡ መግቢያውም መጽሐፉን መጻፍ የተፈለገበትና ዓላማው፣ በመጽሐፉ ውስጥ በየምዕራፉ የተካተቱት መሠረታዊ ሐሳቦች፣ የመጽሐፉ ወሰን፣ በመጽሐፉ ያልተጠቀሱ፣ በመጽሐፉ አዘገጃጀት የገጠሙ ችግሮች ጉዳዮችን ያካተተ ነው፡፡ በመጽሐፉ ክብር ዘበኞች እንደምን ወደ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ክብር ዘበኛ መኮንንነት አካዴሚ እንደመጡ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በዚህ ምዕራፍ የጦር አካዴሚው መቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት፣ ወደ አካዴሚው ለመግባት እንዴት እንደተመለመሉ፣ የጦር አካዴሚው የነበረበት ቦታና ታሪኩ፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ቀጥሎ ከጦር አካዴሚው መቋቋም ጋር ግንኙነት ያላቸው ከፍተኛ መኮንኖች፣ የጦር አካዴሚው አደረጃጀት (በመማሪያ ቁሳቁስና በመሣሪያ ወዘተ.)፣ የጦር አካዴሚው አደረጃጀት በሰው ኃይል፣ በአስተዳደር፣ በማሠልጠን፣ በጦር አካዳሚው የነበሩ የውጭ ዜጎች እነማን እንደሆኑና ከየት እንደመጡ)፣ የጦር አካዴሚው ለዕጩ መኮንንኖች የሚሰጣቸው ትምህርት በዝርዝር (ሥርዓተ ትምህርቱ) በማቅረብ የጦር አካዴሚው ታሪክ እስከዛሬ በየትኛው ጸሐፊ ባልቀረበ መንገድ ነገር ግን ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ባለው መልኩ አቅርቧል፡፡

መጽሐፉ ከዚህም በተጨማሪ በወቅቱ ይሰጥ የነበረውን የክብር ዘበኛ መኮንነትን የተግባርና የጽንሰ ሐሳብ ትምህርት የሚያካትት ሲሆን፣ የክብር ዘበኛው ይጠቀምበት የነበረ መሣሪያ (በነፍስ ወከፍ፣ በቡድን፣ ንጉሠ ነገሥቱን ወይም ከዚያ በመለስ ያለ ኃላፊ ሲጠብቅ፣)፣ የክብር ዘበኛው ሲሰማራ የሚያከናውነው (ከመሰማራቱ በፊት ዕቅድ ያወጣል? ስብሰባ ያካሂዳል? የዕለቱ ሥራ ምን እንደሆነ ይነገረዋል? ማን በምን ቦታ መጠበቅ እንዳለበት ያውቃል? በቤተ መንግሥት፣ በኃላፊ ቤት፣ በመንገድ፣ በሕዝብ በዓላት፣ በሥራ ጉብኝት ቀንና ቦታ፣ በእረፍት ቀንና ቦታ እንዴት ጥበቃ ይደረጋል? የጥበቃ ተርታ እንዴት ይወጣል? የክብር ዘበኛው ከውጭ ጋር ያለው ግንኙነት (ከሌሎች ወታደራዊ ክፍሎች፣ ከሕዝብ ጋር፣ ከሥውር ደኅንነት ጋር ወዘተ.) ምን ይመስል ነበር? የክብር ዘቡ አደጋ ናቸው ወይም ሊሆኑ ብሎ የሚያስባቸው ምንድን ነበሩ? (ፊውዳል መኳንንቶችና መሳፍንቶች፣ ህቡዕ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ተማሪዎች፣ የውጭ ጠላት. . . ስለእያንዳንዱ ማብራሪያ) የሚሉትን ጥያቄዎች ይመልሳል፡፡

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሁሉ የኮሪያ ዘመቻና ለምን ወደ ኮሪያ እንደተዘመተ፣ ወደ ኮሪያ የተደረገ ጉዞ፣ የኮሪያ አጭር ታሪክ፣ የኮሪያውያን ባህል፣ የኮሪያ የአየር ንብረት፣ በኮሪያ ዘመቻ የተካፈሉ አገሮች፣ የኮሪያ ዘመቻ (ጦርነት) ፍጻሜና ከዘመቻ መልስ፣ ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት፣ የኮንጎ ዘመቻና ለምን ወደ ኮንጎ እንደተዘመተ፣ ወደ ኮንጎ የተደረገ ጉዞ፣ የኮንጎ አጭር ታሪክ፣ የኮንጎውያን ባህል፣ የኮንጎየአየር ንብረት፣ በኮንጎ ዘመቻ የተካፈሉ አገሮች፣ የኮሪያ ዘመቻ (ጦርነት) ፍጻሜና ከዘመቻ መልስ፣ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት፣ በሶማሊያ የተደረገ ጦርነት፣ ለምን ወደ ሶማሊያ እንደተዘመተ፣ መቼ እንደተዘመተ፣ ምን ውጤት እንደተገኘ፣ በአገር ውስጥ ያገለገሉባቸው የጦር ክፍሎች፣ በኃላፊነት ያከናወኗቸው፣ በሥራ ሒደት የገጠማቸው ችግር ለክብር ዘበኛ ታሪክ መዳበር በሚረዳ መልኩ ቀርቧል፡፡

ወደ መገባደጃ ላይም የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ መበተን በሚመለከት ሲሆን፣ ከዚህም ጋር የክብር ዘበኛና መፈንቅለ መንግሥት፣ የክብር ዘበኛ አባላት ወደ ልዩ ልዩ የጦር ክፍሎች መበተን፣ የክቡር ዘበኛን ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ማደራጀትና ሥራው፣ ክብር ዘበኛ ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በኅብረተሰቡ ዘንድ የነበረው ተቀባይነት፣ የክብር ዘበኛ መበተን ያስከተለው ቀውስ፣ የክብር ዘበኛ መኮንኖች በደርግ ዘመን፣ የክብር ዘበኛ መኮንኖች በኢሕአዴግ ዘመን የሚሉት ስፋትና ጥልቀት ባለው መልኩ ሰፍሯል፡፡

በአጭሩ በመጽሐፉ በሌሎች የታሪክ ጸሐፊዎች ያልተዳሰሱ ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡ ከሚያውቋቸው ታላላቅ ሰዎች መካከልም ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ፣ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጄኔራል ታፈሰ ተሰማ፣ ጄኔራል ወርቅነህ ገበየሁ፣ ሌተናል ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ ጄኔራል ወልደማርያም ኃይሌ፣ ኮሎኔል ታምሩ ዘገዬ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ወልደማሪያም ኃይሌ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ዳዊት አብዲ፣ ሪቻርድ ኒልሰን፣ ካፒቴን ሆርን፣ ካፒቴን አፍሲለን፣ ሻምበል አሥራት ደፈረሱ፣ ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ጀኔራል መኮንን ደነቀ፣ አበበ ቢቂላና እውነተኛው አሠልጣኝ፣ የሁለተኛው ኮርስ ተካፋይ ለመሆን ተመልምለው የነበሩት ገብረክርስቶስ ደስታን የሚመለከቱ አዳዲስ መረጃዎች ያቀርባሉ፡፡

ከኮሎኔልመለሰተሰማ መጽሐፍ የምንማረው

የዛሬ 33 ዓመት ለንባብ ያበቁት ራልፍ ኔደር መሠረታዊ መልዕክታቸው «አርበኞች አባቶቻችን ከጠላቶች ጋር በመፋለም ነፃነታችንን፣ ሰላማችንና ዳር ድንበራችንን አስከብረውልናል፤ ዛሬ ወጣቱን ትውልድ አርበኛ ለማድረግ ምን ማድረግ አለብን?» ከሚል የሚነሳ ነው፡፡

ልክ እንደ አሜሪካዊው ጋዜጠኛ እኛም «አርበኞች አባቶቻችን ከጠላቶች ጋር በመፋለም ነፃነታችንን፣ ሰላማችንና ዳር ድንበራችንን አስከብረውልናል፤ ዛሬ ወጣቱን ትውልድ አርበኛ በተለይም የልማት/የህዳሴ አርበኛ ለማድረግ ምን ማድረግ አለብን?» ብለን እንጠይቅ፡፡ መልሱን በትክክል ለመገንዘብ የአገራችንን ወጣት በዓይነ ህሊናችን እንመልከት፡፡ ከግማሽ በላዩ ወጣት ነው፡፡ «ይህ ወጣት ትውልድ ዓለምን ለመጨበጥና እንደምትመቸው አድርጎ ለመግራት ብርቱ ፍላጎት ያለው ትውልድ ነው፤» ብለን እንውሰደው፡፡ በባህሪያቸው ቦዘኔነት ለሚያጠቃቸውም ቢሆን ትንሽ ቦታ እንተውላቸው፡፡ በመጀመርያ ግን «አርበኝነት ምንድነው?» አርበኝነትን ለጊዜው «የጦር መሣሪያ ትግል» እና «የልማት አርበኝነት» ብለን በሁለት እንክፈለው፡፡

የጦር መሣሪያ ትግል የተደረገበት አርበኝነት

በአማርኛችን «አርበኛ» የሚለው ቃል «አርነት/ነፃነት በእኛ ዕውን ይሆናል» እንደማለት ነው፡፡ ከጣሊያን ጋር አምስት ዓመት የተዋጉ ኢትዮጵያውያን «አርበኞች» ተብለው ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ አርበኞች ቅኝ አገዛዝን አንቀበልም፣ ጭቆናን አንሻም፣ ፍትሕ የሌለው ሥርዓትን እንቃወማለን በማለት ጣሊያንን ለመውጋት፣ በመውጋትም ድል ለማድረግ ቆርጠው ጫካ የገቡ  ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ «የጦር ሜዳ አርበኛ» «የውስጥ አርበኛ» አለ፡፡ የጦር ሜዳው አርበኛ ጣሊያን ከገባበት ጊዜ ጫካ ገብቶ የጦር መሣሪያ ትግል የጀመረ ሲሆን፣ አገልግሎቱም ከአንድ ቀን እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ ይችላል፡፡ የውስጥ አርበኛው ደግሞ የጦር መሣሪያ ትግል ባያደርግም የጣሊያን ደጋፊ መስሎ ወይም ሳይመስል አርበኞቹን በልዩ ልዩ መንገዶች የሚረዳና ለመርዳቱ በምስክር የተረጋገጠለት ነው፡፡ ከነዚህም የውስጥ አርበኞች መካከል የታወቁ የጣሊያን ባንዳዎች የነበሩ፣ ነገር ግን ውስጥ ለውስጥ ይረዱ ነበር ተብለው የሚታሰቡ ናቸው፡፡ ዕርዳታውም፣ አርበኛውን በጨለማ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ልብስ መላክ፣ ኬላ አልፎ እንዲሄድ መፍቀድ፣ ቢታሰር መፍታት፣ ቤተሰብ መርዳትና መረጃ ማስተላለፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ «የጣሊያን ወታደሮች ዛሬ በዚህ በኩል ስለሚያልፉ ዘወር በሉ» ወይም «ይህን ያህል ጦር ይዞ ስለተንቀሳቀሰ ጠብቃችሁ ግጠሙት» የሚል ሊሆን ይችላል፡፡

የልማት አርበኞች

የልማት አርበኞች ስንል ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት እንችል እንደሆን አንዳንድ ሊሄዱ የሚችሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን እናንሳ፡፡ በመግቢያው ላይ አርበኛ ማለት «አርነት/ነፃነት በእኛ ዕውን ይሆናል» የሚል አንድምታ እንዳለው ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከነፃነት በኋላ በተቀዳሚ መሥራት የጀመሩት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋምና በማስፋፋት ላይ ነበር፡፡ ያኔ ለመመማር የነበረው ፍላጎት ዝቅተኛ ስለነበር እስከ 1953 ዓ.ም. ድረስ ልብስ እየተሰጠ፣ ደብተርና እርሳስ እየተሰጠ ሁለተኛ ደረጃ ሲሆኑም አዳሪ ትምህርት ቤት እየገቡ ነው፡፡ ከስድስተኛ ክፍል «የተማረ ያስተምር» በሚል መፈክር ለአስተማሪነት ሥራ መቀጠር ይቻል ነበር፡፡ ከ1953 ዓ.ም. ወዲህ ማለትም 25 ዓመት ያህል የትምህርት አርበኝነት ዘመቻ ከተካሄደ በኋላ ዩኒቨርሲቲ ለመቋቋም በቃ፡፡ ስለዚህ ለ25 የተካሄደው የአርበኝነት ዘመቻ የአሁኑን ትውልድ ከሞላ ጎደል ካለማወቅ ነፃ አወጣ፡፡

የአገር ፍቅር አርበኝነት

አገርን አርበኛ ሆኖ ለማልማት ከሁሉ አስቀድሞ የሚያስፈልገው ጥልቅ የአገር ፍቅር ነው፡፡ ወጣቱን ትውልድ በአሁኑ ጊዜ በግንባር ቀደምትነት ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ የአገር ፍቅር ስሜትና የአገር ፍቅር ወኔ ነው፡፡ የአገር ፍቅር ስሜትና የአገር ፍቅር ወኔ ከራስ ወዳድነት ስሜት ተላቆ እኔ ለአገሬ ዕድገት እሠራለሁ፤ ወገኖቼን ከረሃብ ከእርዛት ነፃ ለማውጣት ቆርጬ ተነስቻለሁ፤ ይህም ብርቱ ዓላማዬ ግብ እስኪደርስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እከፍላለሁ ከሚል የሚመነጭ ነው፡፡ አገሬ በድህነቷ ምክንያት ተዋርዳለች፣ ዝቅ ብላ ታይታለችና ከወደቀችበት አነሳታለሁ የሚል ቁርጠኛ ውሳኔ በራስ ላይ ማስተላለፍንም ይጨምራል፡፡ በተወለድንባት፣ እየተጫወትን ባደግንባት፣ በተማርንባት ከጓደኞቻችን ጋር በጨፈርንባት አገራችን ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲለመልም ተግቼ እሠራለሁ ብሎ መነሳትን ይጠይቃል፡፡

በአካባቢው ሕዝብ ከልማት ጎዳና እንዲወጣ፣ እርስ በርስ እንዲናቆር፣ በጎ ነገር ሁሉ እንዳያይ፣ የሚያደርጉ እነማን እንደሆኑ ለይቶ በማወቅ ከነዚህ ኃይሎች ጋር ያለ ምሕረት ይታገላል፡፡ እየታገለም የእነሱን ጥልቅ የአገር ፍቅር እምነትምን እንደሆነ ያሳውቃል፡፡ አገር ከግል ፍላጎት ጀምሮ የሁሉም ነገር የበላይ እንደሆነ ያስተምራል፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት ከልብ መንጭቶ ሲንቦገቦግ የወዳጅን ልብ የበለጠ ሲያበራ የጠላትን ልብ እንደሚያርድ በተግባር ያሳያል፡፡ ጥሪውን እንዲሰሙ ሰምተውም እንዲቀበሉ በፍፁም ቅንነት ይሠራል፡፡

የልማት አርበኝነት

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ከፍተኛ የልማት ሥራዎች እየታዩ ነው፡፡ እነዚህን የልማት ሥራዎች ለማፋጠን የፖለቲካ አመለካከት፣ የሃይማኖት፣ የዘር፣ የጎሳ ወይም የሌላ ልዩነት አያግደንም፡፡ በተጠቀሱትና ባልተጠቀሱት ጉዳዮች ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ አገራችንን ማልማት ያለብንም በአንድ ላይ ሆነን መሆን ይኖርበታል፡፡ በአሜሪካ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሃይማኖቶች እንዲሁም ዘሮች አሉ፡፡ ቅራኔያቸው ግን ሥርዓቱን እኔ የተሻለ አንቀሳቅሰዋለሁ ከሚል ነው፡፡ ያም ቢሆን በሕዝብ ድምፅ አሸናፊዎች ሲሆኑ ነው፡፡ አብርሃም ሊንከን የተባሉ ፕሬዚዳንት አገራቸው በእርስ በርስ ጦርነት ስትናጥ በነበረበት ጊዜ የተናገሩት አንድ ትልቅ ቁም ነገር «የመርከቧን መሪ ጨብጠን ወደ ፈለግነው አቅጣጫ ልንመራት የምንችለው ከሁሉ አስቀድሞ መርከቧ ስትኖርነው፤» በማለት ሕዝብ የእርስ በርሱን ጦርነት አቁሟል ለልማት እንዲተጋ ማሰባቸው ለሁላችንም ምክር ሊሆን ይችላል፡፡ አገራችን ዘላለማዊት ስትሆን ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ግን ተለዋዋጭ ነው፡፡ ዘርም፣ ቋንቋም ተለዋዋጭ ነው፡፡ ትውልድ አልፎም ትውልድ ይተካል፡፡ ስለሆነም የጥላቻን መርዝ አስወግደን የተጀመረውን የልማት ለውጥ ማካሄድ ተቃውሞ ቢኖረንም በአግባቡ እያቀረብን ለማስተካከል የበኩላችንን አወንታዊ ሚና መጫወት ይጠበቅብናል፡፡

ለሁሉም የዕውቀት መስኮች ማለትም አርቆ አስተዋይነት፣ በጥበበኛነት፣ በባህል፣ በመንፈሳዊ ዕውቀት፣ በወኔያቸው፣ በመንፈሳዊ ቅዱስነት ሙላታቸውና ብልፅግናቸው፣ የሚያክሙን መንፈሳዊ ሐኪሞች ያስፈልጉናል፡፡ እንደዚህ ወይም እንደዚያ ያለ የተለየ ዓይነት ወይም ችሎታ ያለው ብለን የምንመርጠው ሳይሆን አጠቃላይ ግንዛቤ ያለውን ነው፡፡

አንጎል በቅርቡም ሆነ ከእርሱ ርቀው፣ ከጥቃቅኖቹም ሆነ ከትላልቁ ከሚገኙ የሰውነታችን መላ ሴሎች ጋር በነርቭ ፀጉሮች አማካይነት እንደሚገናኘው ሁሉ፣ እንደዚህ ያሉት የአንጎል ካድሬዎች ከመላው የአካላችን ግዛት ውስጥ ከሚገኙ አቶሞች፣ ሞለኪውሎች፣ ቅንጣቶች ጋር እንደሚገናኙት፣ እንደሚያገናኙትና አንዱን ከሌላው ጋር እንደሚያስተሳስሩት ሁሉ የመንፈስና የአስፈላጊው እውነት ሐኪሞችም ሁሉንም ኅብረተሰብ አካል ይደርሳሉ፡፡ እጆቻቸው በዋናዎቹ ተቋማት ላይና ውስጥ ያርፋሉ፡፡ በጨዋነት ሰሜትም፣ ካለፈው ጊዜ የመጣና በአሁኑ ጊዜ ጥልቀት ያገኘ እንዲሁም ወደፊት ሊዘረጋ የሚችል ከመንፈስና ከእውነት አንዳች ነገር በሕይወት ላለው ፍጡር ሁሉ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡

አስተሳሰባችንን፣ ስሜታችንን፣ መንገዳችንን፣ ፍልስፍናችንን እንደገና ህያው እስካደረግን ድረስ የራሳችንን ሰማያዊና የማይሞት ሥልታችንን አሰባስበን ማምጣት የሚያስችሉን ናቸው፡፡ ለዚህም ነው፣ እንደምመለከተው፣ የምንጓዝባቸውን ጎዳናዎች በሙሉ ከሁሉ አስቀድመን መፈተሽ፣ መመርመር፣ እንደገናም አጠናክረን መሥራት ያለብን፡፡ ለዳግማዊ ህዳሴያችን አርአያ፣ ምሳሌ፣ መነሻና፣ መለኪያ የሚሆኑን ወኔችን፣ ቆራጥነታችን፣ የሚያነሳሳ መንፈሳችን፣ በሃይማኖት ረገድ ፍሬያማ መሆናችንነት፣ (ያለፈውን ታሪካችንን) ለማረጋገጥ የሚያስችል ከባቢ ሁኔታ፣ ጽናታችን፣ በመካከላችን ውስጥ የሚገኘው ስበታችን፣ ኮስታራንታችን፣ ምክንያት በማቅረብና በነገረ ጥበብ ችሎታችን፣ የማንናወጽ መሆናችን፣ ለራሳችን ነፃነት የሚያጎናጽፈን ሰብዓዊ ሩህሩህነታችን ናቸው፡፡ የፍልስፍና ጥልቀት፣ የማጣራት፣ የማሻሻል፣ ወደፊት የማራመድ፣ በኪነ ጥበብና በፍልስፍናችን ውስጥ የሚገኝ በጥልቅ እሳቤ የተሞላ አመለካከታችን፣ ይህም ሁሉ ከዋናው ማዕከል ጥራት ያለውና በአሠራር ሊያስኬድ በሚችል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተና በራዕይ የተነሳሳ ሊሆን ይገባል፡፡

የትምህርት አርበኝነት

በጥቂት አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃና በአንድ ዩኒቨርሲቲ ከ30 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ ቆይተናል፡፡ ዛሬ ግን የተፈለገውን ያህል ባይስፋፋም በርካታ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል፡፡ ከ30 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ከተቋቋሙ ገና አሥር ዓመታት አልሞሉም፡፡ በነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩና የሚሠሩም ለብለብ ባለ ሥልጠናና ዕውቀትም ቢሆን ተሞልተዋል፡፡ እውነቱን ለመካድ ካልፈለግን በስተቀር በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የትምህርት አርበኝነት ዘመቻ አስተማሪዎችና ተማሪዎች እኩል የስድስተኛና የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ይወስዱ ነበር፡፡ አብረውም የሚያጠኑ ነበሩ፡፡ ነገሩ ጠንከር ሲልም ተማሪዎቻቸው የሚያስጠኗቸው አስተማሪዎች ነበሩ፡፡ «የዛሬ ተማሪ. . .?» በማለት ከማጥላላት ጀምሮ ሌሎች አስጸያፊ ነገሮች የምንናገረውም እኛና የኛ ልጆች፤ ደግሞም ለኛ ልጆችና የልጅ ልጆች ሆኖ ሲገኝ ነገሩ በእጅጉ ያሳፍራል፡፡

እርግጥ ነው የአሁኑ ትምህርቱ ጥራት እንደተፈለገው ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግንከዳር ሆነን የምንነቅፈውን ጨምሮ ሁላችንም በትምህርቱ ጥራት የምንረባረብ የትምህርት አርበኞች ብንሆን በቀላሉ የማይገመት ለውጥ ልናመጣ እንችላለን፡፡ ለመሆኑ ዛሬ ምንም ዓይነት ልዩነት ይኑረን ምን ይህ ጊዜያዊ ልዩነት ሳይገድበን ተቻችለን፣ ተከባብረን፣ ተፋቅረን የትምህርት አርበኞች ሆነን ካልሠራን የኛንም ጨምሮ የነገረውና የከነገ ወዲያው ትውልድ እንደሚጎዳ ማሰብ ይሳነናል? ወይስ ይህ ሥርዓት ይውደቅ እንጂ ወደ ምዕራብ አገሮች የተሰደዱትና ከኢትዮጵያዊ ባህል ጋር የተራራቁት ወገኖቻችንን አምጥተን ክፍቱን ቦታ እንሞላበታለን ብለን እናስባለን? እንዲያው ለመሆኑ የአሁኑን ትምህርት ለመንቀፍ የሚያስችለን የኛ ሀቅ ምንድነው?

አባ ቤኒዲክት 16 «የሀቅ ግንዛቤ ጥርጣሬ ላይ መውደቁ እርግጥ ነው፡፡ በእርግጥም ሀቅ ከሚገባው በላይ ተወግዟል፡፡ በምትኩም አለመቻቻልና ጭካኔ በሀቅ ስም ቀርበው ሲተገበሩ ኖረዋል፡፡ ስለዚህም ሰዎች «ይህ ሀቅ ነው» የሚለውን ዓረፍተ ነገር ሲሰሙ ወይም «እኔ ሀቅአ ለኝ» በማለት ሲናገሩ በሚሰሙበት ጊዜ ሥጋት ያድርባቸዋል፡፡ ሀቅ ብትይዘን እንጂ እኛ ይዘናት አናውቅም፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው እውነት አለኝ ብሎ ሲናገር መጠንቀቅ እንዳለበት የማያጠያይቀውም ለዚህ ነው፡፡ ሀቅን ልንደርስበት አንችልም ብሎ መተው ደግሞ አፍራሽ ነገር ነው፡፡ «አዎን ሰው ሀቅን መሻት አለበት፤ ሀቅን ማግኘትም ይችላል ብሎ በድፍረት ለመናገር ወኔው ሊኖረው ይገባል፡፡ ሀቅን ለማብራራትም ሆነ ሀቅ አለመሆኑን ለማሳየት መለካት የሚያስችል መለኪያ እንደሚያስፈልገው ሳይናገሩት የሚሄድ ነገር ነው፡፡ በመቻቻልም መደገፍ ይኖርበታል፡፡ የሰውን ልጅ ታላቅ ያደረገው ዝልቅና ያገኙ እሴቶችም በሀቅ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ለዚህም ነው ሰብዕና ሀቅን መገንዘብ ያለባትና የሕይወት መመርያ አድርጋ በመውሰድ እንደገና መረዳትና መተግበር የሚገባትም ለዚህ ነው፡፡ ሀቅ በአመጽ ሳይሆን በራሷ ኃይል ዳግም ትገዛለች፡፡ የዮሐንስ ወንጌል ዋነኛ መልዕክት የሚያጠነጥነውም ኢየሱስ ከጲላጦስ ፊት ሲቀርብ ሀቅ መሆኑንና የሀቅ ምስክር እንደሆነ በፍቅር ስሜት ነበር፤» ይሉናል፡፡

ከጥንት ጀምሮ ሲያብሰለስለን የነበረው የዓባይ አለመገደብ ጉዳይ ብቻ አልነበረም፡፡ ለኛ ለአክሱም ጥበብ፣ ለላሊበላ ጥበብ፣ ለአዳዲ ማርያም ጥበብ ባለቤቶች፣ ለኛ ለዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና ባለቤቶች፣ ለኛ ለይሃ፣ ለጎንደር፣ ለእንፍራንዝ፣ ለደንቀዝ ጥበብ ባለቤቶች ብዙ ሥልጣኔያችን፣ ብዙ ዕውቀታችን፣ ብዙ ጥበባችን፣ ብዙ ፍልስፍናችን ዛሬም ከተቀበረበት ጉድጓድ ሆኖ እንድናወጣው የጥሪጩኸት እያሰማን ነው፡፡ የልማት አርበኝነትን በሚመለከት በርካታ ምሁራን ትተውልን ያለፉት አስተምህሮ በእጅጉ ብዙ ነው «በዚች ዓለም ላይ ልዩነት የሌለበትን አንድነት ለማምጣት የሙጥኝ ከማለት ይልቅ ልዩነት ቢኖርም አንድ ለመሆን በመፈልግ አንድነት ሊመጣ ይችላል፡፡ ልዩነትን ለማጥፋት መሞከር ፍፁም የማይቻል ነገር ነው፡፡ በሕይወት ስንኖር ሰላም የማስፈን ምስጢርም ሰላም የሚያደፈርሱ ነገሮችን በመቻል ነው፤»  ከሚሉን መውላና ዋሕዱዲን ኻን የምንማረው አንዱ መሠረታዊ ቁም ነገር የአመለካከት ልዩነት ቢኖረንም ልዩነቶቻችን የልማት አርበኝነታችንን ማስፋፋት እንጂ እኛ ከልጆቻችን የበለጥን መሆናችንን ለማሳየት ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረግ ከቶ አይገባንም፡፡

የትምህርት አርበኝነትን ማስፋፋት ማለት የማኅበራዊ ኑሮ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የባህል፣ የሃይማኖት ተመራማሪ አርበኞችን፣ ማለትም በልዩ ልዩ ምክንያቶች አገሪቱን ሊገጥሟት የሚችሉ አርበኞችን ዝግጁ ማድረግ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles