እንደሚታወቀው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከዕድሜ ርዝመት እንዲሁም የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች በተለያየ ደረጃ የእርጅናና የስንጥቅ ጉዳት ይስተዋልባቸዋል፡፡ የጥገና ፍላጎትን መሠረት ተደርጎ ላለፉት ዓመታት የተለያዩ የጥገና ትግበራ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የተጠቀሱትና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከመንግሥት በጀት እንዲሁም የተለያዩ አጋር አካላትን (የአሜሪካን መንግሥት፣ ዩኔስኮ፣ የዓለም ቅርስ ፈንድ ወዘተ…) በማስተባበር ከጥገና ባሻገር በታሪክ 1960ዎቹ የጣሊያናዊው የኢንጂነር አንጀሊን የቀጥታ ጥገና ፕሮጀክት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ውጤታማ የቅርስ ጥገና ተግባር ከመንግሥትና የአሜሪካን ፈንድ በተገኘ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ከአብያተ ክርስቲያናቱ የአሜሪካን ፈንድ በተገኘ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አብያተ ክርስቲያናቱ እጅግ ተጎድተው በነበሩት የቤተ ገብርኤል ሩፋኤል አብያተ ክርስቲያናት አብነታዊና ውጤታማ የቅርስ ጥገና ተከናውኖ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ለማስመረቅ ተችሏል፡፡
ከጥገናው ፕሮጀክት የተገኘ ምርጥ ተሞክሮን በማስፋት የቀሪ አብያተ ክርስቲያናቱ አሳሳቢ የጥገና ፍላጎት ላይ የባህል ቱሪዝም ሚኒስቴርና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከባለድርሻ አካላት፣ የላሊበላ ደብር ሰበካ ጉባኤ አካላትና የሕዝብ ተወካዮች ጋር ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. እና ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጨምሮ ተደጋጋሚ ሰፊ ምክክር በላሊበላ ከተማና አዲስ አበባ ተደርጓል፡፡ በምክክሩም ተሞክሮውን ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በአስቸኳይ በማስፋት ከአሥር ዓመት በፊት በአውሮፓ ኅብረት ፕሮጀክት የተገነቡትን ጊዜያዊ መጠለያዎች ሊነሱ እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የተለያዩ ለጋሽ አካላትን ለማስተባበር በተደረገ ጥረትም የተጨማሪ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት (የቤተ ጎልጎታ ሚካኤል) ጥገና በተያዘው በጀት ዓመት ከአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ቅርስ ፈንድ በተገኘ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ ድጋፍ የዲዛይንና ጥገና ፕሮጀክቱ ሥራ ተጠናቆ በአዲሱ ዓመት መባቻ ለምረቃ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከለጋሽ አካላት ጋር በመቀናጀት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተወሰኑትን አብያተ ክርስቲያናት መታደግ ተችሏል፡፡ ለቀሪ አብያተ ክርስቲያናት የጥገና ፕሮጀክት በመጀመር ተጨማሪ ቅርሶችን ለመታደግ የተጀመረውን ተሞክሮ ማስፋት የሚቻል ስለመሆኑ በዩኔስኮ ግምገማ ተካሂዶ እ.ኤ.አ. መስከረም 5 ቀን 2018 የቀጠሉበት ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ጥገናውም በሁሉም ቀሪ ቅርሶች በማዳረስ ጊዜያዊ መጠለያዎቹን ለማንሳት ለተያዘው ግብ ተግባራዊነት ግን ከፍተኛ ፋይናንስ እጥረት አጋጥሟል፡፡
ፕሮጀክቱን በተያዘው ዓመት ለማስቀጠልም ለቤተ ገብርኤል ሩፋኤል እንዲሁም የጎልጎታ ሚካኤል ዓለም አቀፍ ጥገና ፕሮጀክቶች ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ማስፈለጉ ከግምት ውስጥ ገብቶ ጥገናውን ለሁሉም ቀሪ አብያተ ክርስቲያናት ለማከናወን እጅግ ውስብስብ የሆኑትን የብረት መጠለያዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ለማንሳት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚጠይቅ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ ባለሥልጣኑ ከአጠቃላይ አገር አቀፍ የ37 ሚሊዮን ብር የቅርስ ጥገና ዓመታዊ ካፒታል በጀት ጣሪያው 20 ሚሊዮን ብር ያክል የመደበ ቢሆንም የተጠቀሰውን ከፍተኛ በጀት የሁሉንም የባለድርሻ አካላት ተግባራዊ ትብብርን ይጠይቃል፡፡
የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የላሊበላ ነዋሪዎች የሰሞኑን ሰልፍ ጨምሮ በአስቸኳይ ፋይናንስ የማፈላለግና ፕሮጀክቶቹን የማስቀጠል ሥራ እንዲሠራ እያሳሰቡ የሚገኝ ሲሆን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ባለሥልጣኑ ክልልና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ቅርሶቹን ሙሉ በሙሉ ጠግኖ በማጠናቀቅ ጊዜያዊ መጠለያዎቹን የማንሳቱን ሥራ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ተግባሩ የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቅ እንደመሆኑ ሁሉም አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና ቅንጅት እንዲያረጋግጡ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡